Print this page
Saturday, 31 August 2019 12:43

የአረና ሊቀ መንበርና አመራር ድብደባ ተፈጸመባቸው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 ‹‹የዶ/ር ደብረጽዮንን ቤት አጠያይቃችኋል›› በሚል ነው ተብሏል

          የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር፣ የዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን መኖሪያ ቤት አጠያይቃችኋል በሚል የአረና ሊቀ መንበር አቶ አብርሃ ደስታና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አምዶም ገ/ስላሴ፣ ለሰዓታት ታስረው፣ ደብደባ እንደተፈጸመባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ነሐሴ 20 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ፣ ሁለቱ የአረና ከፍተኛ አመራሮች ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው፣ በእግራቸው እየተጓዙ ሳለ፣ በድንገት ሲቪል በለበሱ ሁለት የልዩ ፖሊስ ሀይሎች ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ “የዶ/ር ደብረጽዮንን ቤት እያጠያየቁ ሳለ ነው የያዝናቸው” በማለት ፖሊሶቹ ለጣቢያው አዛዥ መግለጻቸውንና ይህን ተከትሎም፣ የጣቢያው አዛዥ “ለምንድን ነው የምታጠያይቁት?” በሚል በዋናነት በኔ ላይ ድብደባ ፈጽመውብኛል ሲሉ አቶ አምዶም ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
ከ11 ሰአት እስከ ምሽቱ 3፡30 በፖሊስ ጣቢያ “ለምን የዶ/ር ደብረ ጽዮንን ቤት አጠያየቃችሁ?” በሚል እየተጠየቁ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና “እኛ አላጠያየቅንም” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን የገለጹት አቶ አምዶም፤ በመጨረሻ  ፖሊስ ቃላቸውን ተቀብሎ፣ መለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡  
በአጠቃላይ ፓርቲያቸው በትግራይ በሚያደርገው እንቅስቃሴ፣ በአመራሩና አባላቱ ላይ ወከባና እስራት እየተፈጸመባቸው መሆኑን የጠቆሙት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፤ መንግስት ከዚህ የአፈና ድርጊቱ እንዲታቀብ የሚጠይቅ መግለጫ በትላንትናው ዕለት ማውጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡  አራት የፓርቲውን አመራሮች ጨምሮ “አረናን ትደግፋላችሁ” በሚል በርካቶች ለእስር መዳረጋቸውን የሚናገሩት አቶ አምዶም፤ የአባላቶቻችንን ንብረት መንጠቅና ማዋከቦች እየተፈፀመብን ነው ብለዋል፡፡ የፓርቲው የአቢ አዲ ጽ/ቤት አስተባባሪ አቶ ዜናዊ አስመላሽ፤ 13 ፍየሎቻቸው በሃይል እንደተወሰዱባቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡  
 “ትግራይ ሰላም ነው እየተባለ፣ አባላቶቼ እየታሰሩና የፖለቲካ ምህዳሩ እየተዘጋ ነው” ያለው አረና፤”በዚህ አይነት ሁኔታ ቀጣዩን ምርጫ ማካሄድ የሚቻልበት እድል ጠባብ ነው” በማለት መንግስት ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲያበጅለት ጠይቋል፡፡    

Read 7435 times