Saturday, 16 June 2012 08:59

ሉሲዎቹ እና ዋልያዎቹ ‹ታሪክ ሰሪ› ሆነዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ዛሬ እና ነገ ከሜዳቸው ውጭ በዳሬሰላምና በፖርቶኖቮ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያዎች ወሳኝ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡ በ2013 እኤአ በኢኳቶርያል ጊኒ በሚዘጋጀው 8ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ሉሲዎች የመጨረሻውን ወሳኝ ግጥሚያ  ከታንዛኒያ ጋር ሲያደርጉ ዋልያዎቹ በበኩላቸው ደቡብ አፍሪካ በምታዘጋጀው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ የመልስ ጨዋታቸው ቤኒን ለመግጠም ይሰለፋሉ፡፡ ሉሲዎች  ወደ ዳሬሰላም የተጓዙት ሐሙስ ረፋድ ላይ  ሲሆን ዋልያዎቹ ደግሞ ትናንት  ወደ ቤኒን በረርዋል፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገቡት ተስፋ ሰጭ ውጤት በእግር ኳሱ ላይ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል፡፡

ባለፈው ሳምንት በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ሴንተራል አፍሪካ ፤ደቡብ አፍሪካና ቦትስዋና የሚገኙበትን ምድብ 1 በሳምንት ልዩነት ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች 4 ነጥብና ሁለት የግብ ክፍያ አስመዝግቦ መሪ የሆነው ዋልያዎቹ የተሰኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ስኬት በእግር ኳሱ ለተፈጠረው  መነቃቃት መገለጫ ይሆናል፡፡ በተያያዘ ሉሲዎች ዛሬ በዳሬሰላም የታንዛኒያ አቻቸውን በመግጠም በታሪክ ለ3ኛ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ከቻሉ የተፈጠረው መነቃቃት በከፍተኛ ደረጃ መናሩ የማይቀር ይሆናል፡፡ ከወራት በፊት ለለንደን ኦሎምፒክ ለማለፍ ከመጨረሻው ምእራፍ መድረስ የቻሉት ሉሲዎች አሁን ደግሞ በአፍሪካ ዋንጫ ደጃፍ ላይ በመድረስ ያሳዩት ብርታት ለወንዶች ብሄራዊ ቡድንም መነሳሳት እንደፈጠረ ይታመናል፡፡የብሄራዊ ቡድኖቹ ማበረታቻና ቀጣይ  ስራዎችበእግር ኳሱ በሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች የተፈጠረው መነቃቃት ሌሎች አካላትንም በስፖርቱ እድገት እንዲንቀሳቀሱ ምክንያት ሊሆን የበቃ ሲሆን የቡድኖቹ አባላት ሰሞኑን በፌዴራል የስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ለሁለቱም ቡድኖች አባላት በነፍስ ወከፍ የአራት  ሺ ብር ማበረታቻ ሲሰጥ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ  ደግሞ ለዋልያዎቹ ቋሚ ተሰላፊዎች ሰባት  ሺ ብር፤ ለተቀያሪዎች  አምስት ሺ ብር  እንዲሁም ለቀሪዎቹ የቡድኑ ተጨዋቾች  ሁለት ሺ ብር ሸልሟል፡፡ በሸራተን አዲስ በተካሄደው  ስነስርዓት ሉሲዎች በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ቀደም ብሎ በተሰጣቸው የማበረታቻ ሽልማት  በአሁኑ ባይካትታቸውም ከታንዛኒያ ጨዋታ መልስ ለቡድኑ ጠቀም ያለ ሽልማት ለመስጠት

በመሰራት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ አስታውቀዋል፡፡ የአዲስ ብሄራዊ ስቴዲየም ዲዛይን  የኢትዮጵያን ሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ለማበረታት ከሰሞኑ በሸራተን አዲስ ከተከናወነው ስነስርአት ጋር በተያያዘ የፌዴራል መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ ሊያስገነባ ያቀደው የብሄራዊ ስቴዲየም ዲዛይን  አሸናፊም ታውቋል፡፡በስራና ከተማልማት ሚኒስቴር በተከናወነው የዲዛይን ጥናትና የመረጣ ስራ ያሸነፈውን የብሄራዊ ስታድዬም ዲዛይን የሰራው ጄዳው አማካሪ አርክቴክቶችና መሐንዲሶች የተባለ ድርጅት ነው፡፡ አሸናፊ የሆነው የብሄራዊ ስታድዬም ዲዛይን 60ሺ ተመልካቾች መያዝ የሚችልና 10ሺ መኪናዎችን ማቆም የሚያስችል መሆኑ ሲገለፅ ዲዛይኑ ፊፋ ያወጣውን መስፈርት የሚያሟላና የኢትዮጵያን ባህላዊ ሴቶች ላይ ተመስርቶ በቡና ቅርፅ መሰራቱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ በእለቱ ተናግረዋል፡፡ዲዛይኑ ሙሉ ለሙሉ በቀጣይ ዓመት ይገባደዳል የተባለው ብሄራዊ ስታድዬም ግንባታው ከ2 ዓመት በኋላ ግንባታው የሚጀመር ሲሆን ወጭው እስከ 1.6 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ብሔራዊ ቡድኖቻችን እያስመዘገቡ ያሉት ውጤት ላለፉት 30 ዓመታት ተዳክሞ የቆየውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማነሳሳቱ በመንግስት አካላት የሽልማት ማበረታቻዎችና በስታድዬም ግንባታ እቅድ የሚገለፅ ብቻ ሳይሆን በስፖርት አፍቃሪው ህዝብም ከፍተኛ ተስፋ እንዲፈጠር መንስኤ መሆኑ ተስተውሏል፡፡ ይሁንና ለሁለቱም ቡድኖች ከወዲሁ ቀጣይ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው በርካታስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ሁለቱም ቡድኖች ኢትዮጵያን በመወከል በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ ውድደሮች ለሚኖራቸው ተሳትፎ እና ውጤታማናት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመርያው ተግባር በብሄራዊ ቡድኖቹ ተጨዋቾች ውጤታማነት መሰረት በተለያዩ አካላት የሚሰጡ የማበረታቻ ሽልማቶች መጠናከራቸው ነው፡፡ ሰሞኑን የፌደራል ስፖርት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ለዋልያዎቹ እና ለሉሲዎቹ የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት እና ልዩ ብሄራዊ ስታድዬም ለመገንባት

ቃል በመግባት ያሳዩት ተነሳሽነት በሌሎች አካላትም መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል ሁለቱም ብሄራዊ ቡድኖች በኢንተርናሽናል ውድድሮች በሚኖራቸው ተሳትፎ ለሚያደርጉት ዝግጅት በሁሉም ረገድ በቂ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት፡፡ ኢትዮጵያን የሚወክሉት እነዚህ ቡድኖች በዝግጅታቸው ወቅት በቂ  የልምምድ ፕሮግራም እንዲኖራቸው፤ ዝግጅታቸው በአቋም መፈተሻ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች እንዲጠናከር እንዲሁም በትጥቅ አቅርቦት እና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በቂ እገዛ እንዲደረግላቸው ሰፊ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ያሉት የረጅም ጊዜ አስተዳደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም በፕሮፌሽናል አደረጃጀትና የባለሙያዎች እጥረት ያሉ  ችግሮች ከመሰረቱ መፍትሄ እንዲያገኙ በተፈጠረው መነቃቃት መነሻነት በስፋት መስራት ግድ ይሆናል፡፡ ደጋፊዎች ስሜትየኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብራዚል በ2014 ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ በሚደረገው የምድብ ማጣሪያ መሪነቱን መያዙ ሰሞኑን በእግር ኳሱ ዓለም አነጋጋሪ ሊሆኑ ከበቁ ውጤቶች አንዱ ሆኖ በተለይ በአፍሪካ ደረጃ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሐናት በዋልያዎቹ የተመዘገበው ውጤት ያልተጠበቀ መሆኑን በሚገልፁ ዘገባዎቻቸው በአፍሪካ እግር ኳስ ፈር ቀዳጅነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ ከ3 አስርት ዓመታት የውጤት ማጣት በኋላ በታላቅ ተስፋ መነቃቃት መጀመሯን አውስተዋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የሚሠሩ ኢትዮ ስፖርት እና ኢትዮ ፉትቦል የተባሉ ሁለት ድረገፆች በዋልያዎቹ አስናቂ ታሪክ ላይ ባጠናከሩት ዘገባ ላይ ከአገር ውስጥና ከተለያዩ ዓለም ክፍሎች የደረሱ አስተያየቶችም የተፈጠረውን መነቃቃት አጉልተው ያሳያሉ፡፡ በሁለቱ ድረገፆች ዘገባዎች ላይ የተሰጡ አስተያየቶች በ2014 ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የኢትዮጵያን ተሳትፎ ተስፋ በማድረግ፣ በሳላዲን አድናቆቶችና ቀጣይ የፕሮፌሽናል ጉዞ ያሉ ምኞቶችን በማንፀባረቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅጽል መጠሪያ ላይ በተደረጉ ክርክሮች ያመዘኑ ናቸው፡፡ ከአስተያየቶቹ አንዱ ብሔራዊ ቡድኑ የሺ ዘመናት ታሪካችን፣ የኩራታችንና የክብራችን መገለጫ ሆኗል በሚል ሃሳቡ በአንድ ላይ ተባብረን ከሰራን ለውጥ እናመጣለን ብሎ ሲናገር፣ አንድ እንግሊዛዊ አስተያየት ሰጭ በበኩሉ ኢትዮጵያን በ2014 እ.ኤ.አ በብራዚሉ ዓለም ዋንጫ እንጠብቃታለን ብሎ ተስፋውን ገልጿል፡፡ በተለያዩ የማድነቂያ ቃላቶች የኢትዮጵያን ምርጥ አጥቂ ሳላዲን ሰኢድ ያወደሱ አስተያየቶች ደግሞ ተጨዋቹ በአውሮፓ እግር ኳስ በፕሮፌሽናልነት ሲጫወት ለማየት ያላቸውን ምኞት ገልፀዋል፡፡ በአስተያየቶቹ የተንፀባረቀው አስገራሚ የሃሳብ ልውውጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅጽልመጠሪያ በሆነው ዋልያዎቹ ላይ የተደረገው ክርክር ነው፡፡ በርካታ አስተያየት ሰጭዎች ቅጽል ስሙ የብሔራዊ ቡድኑን ማንነት አይገልፅም በሚል መከራከሪያቸው ሃሳባቸውን ሲገልፁ፣ አንዳንዶች ደግሞ ኦል አፍካን ዶት ኮም፣ እና ቢቢሲ ስፖርት በዘገባዎቻቸው ብሔራዊ ቡድኑን ጥቋቁር አናብስት ማለታቸውን በመጥቀስ ዋልያዎቹ የሚለው ስያሜ እንዲቀየር ጠይቀዋል፡፡ ሉሲዎችና የዳሬሰላሙ ፍጥጫበታንዛኒያ ዋና ከተማ ዳሬሰላም የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ብሄራዊ ቡድን ከ2 ሳምንት በፊት 2ለ1 በሜዳው ያሸነፈውን የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ዛሬ ሲገጥም ሁለት እድሎችን ይዞ ነው፡፡ በጨዋታው ሉሲዎች የአቻ እና የማሸነፍ ውጤት ካገኙ  ወደ 8ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቀጥታ ይገባሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለወሳኙ ጨዋታ በልምምድ እና በስነልቦና ካደረገው ዝግጅት ባሻገር  አቋሙን ለመለካት ባለፈው ቅዳሜ ከጋና አቻው ጋር በአዲስ አበባ ተጫውቶ 0ለ0

ተለያይቷል፡፡ የሉሲዎቹ እና የትዊጋ ኮከቦች የሚባሉትን የታንዛኒያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን  ግጥሚያ የማላዊ ዳኞች እንደሚመሩ ካፍ ያስታወቀ ሲሆን ጨዋታው ከ48ሺ በላይ ተመልካች በሚያስተናግደው የታንዛኒያ ብሄራዊ ስታድዮም መካሄዱን አመልክቷል፡፡ የትዊጋ ኮከቦች በቱርክ ለሚገኝ ክለብ የምትጫወት ሶፊያ ሙዋሲኪሊ የተባለች ተጨዋቻቸውን ለዛሬው ጨዋታ ማሰለፋቸው የተከላካይ መስመራቸውን እንደሚያጠናክር የገለፀው የታንዛኒያው ዴይሊ ኒውስ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሉን በሜዳቸው ለመወሰን እንዲችሉ ከፍተኛ ድጋፍ ከህዝብ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡ዋልያዎቹና የቤኒኑ የመልስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ ከወር በፊት ከቤኒን ጋር እዚህ አዲስ አበባ ላይ 0ለ0 መለያየቱ ይታወሳል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ሽኮኮዎች በሚል ስሙ የሚታወቀውን የቤኒን ብሄራዊ ቡድን ሲገጥም ወደ ሁለተኛው ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር  ብቸኛው አማራጩ ማሸነፍ  ብቻ ነው፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ከቤኒን ጋር ለሚኖረው የመልስ ጨዋታ ወደ ስፍራው ሲጓዝ በጉዳት ላይ የሚገኘው  ሳላዲን ሙሉ ለሙሉ ባለማገገሙ ለ15 ቀን እረፍት ተሰጥቶት መቅረቱ ሲታወቅ መሱድ መሀመድ እና ታፈሰ ተስፋዬ በጤና ችግር ከቡድኑ ጋር የማይሄዱ ሌሎች ተጨዋቾች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በነገው ጨዋታ ሲገናኙ በ2 ሳምንት ውስጥ የሚያደርጉት 3ኛ የማጣርያ ግጥሚያቸው በመሆኑ የውድድሮች መደራረብ ፉክክራቸውን ሊቀንሰው እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በጐል ዶት ኮም አንባቢዎች በቤኒን ኢትዮጵያ ጨዋታ ላይ በተሰጡ 3 ከፍተኛ የውጤት ትንበያዎች ውጤታማነቱ ለኢትዮጵያ ያጋደለ ሆኗል፡፡ በጐል ዶት ኮም አንባቢዎች ከሰጡት ትንበያዎች 29.41% ያህሉ ቤኒን በሜዳዋ በኢትዮጵያ 1ለ0 እንደምትሸነፍ፣ 25.53% የሚሆኑት አሁንም በድጋሚ ቤኒን በሜዳዋ በኢትዮጵያ 2ለ1 እንደምትረታ ገምተዋል፡፡ 11.77% ያህሉ ደግሞ የጨዋታውን ውጤት 2ለ2  ገምተዋል፡፡ በቤኒን እና በኢትዮጵያ ጨዋታ ላይ ስኮርዌይ የተባለ ድረገጽ በሰራው አሃዛዊ ትንተና መሠረትም የኢትዮጵያ ውጤታማነት አመዝኗል፡፡  እንደ ሶከርዌይ ግምገማ በዛሬው ጨዋታ የኢትዮጵያ የማሸነፍ ዕድል 33.3% ግምት ሲያገኝ ለቤኒን 16.67% ተሰጥቷታል፡፡ በ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 8 ከአልጀሪያ፣ ከማሊ እና ከሩዋንዳ ጋር የተደለደለችው ቤኒን እንደ ኢትዮጵያ ምድቧን በ4 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ እየመራች ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ለቤኒን ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ግምት ካገኙ ተጨዋቾች  በትልልቅየእንግሊዝ ክለቦችና በአውሮፓ የተለያዩ ክለቦች መፈለግ የጀመረው ስቴቨን ሴሲጎን ግንባር ቀደሙ ተጠቃሽ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከፓሪስ ሴንተዠርመን ወደ እንግሊዙ ክለብ ሰንደርላንድ በ6 ማሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ የገባው ስቴፈን በዘንድሮው የውድድር ዘመን የሰንደርላንድ ኮከብ ተጨዋች በመሆን ተመርጧል፡፡ ከስቴፈን ሴሲጐን ፈላጊዎች ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል

ይጠቀሳሉ፡፡

 

 

Read 4327 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 09:13