Saturday, 31 August 2019 12:46

ያሬዳዊ ሶፊስትሪ በዋሽንግተን ዲሲ

Written by  ዳኛቸው አሰፋ (ከአዲስ አበባ)
Rate this item
(7 votes)

  ያሬድ ጥበቡ፣ “የመንግሥት ፈላስፋ ወይስ የሞራሊቲ ጠበቃ” በሚል ርእስ፣ በእኔ ላይ ያቀረበውን ትችት በጥሞና አነበብኹት፡፡ ከኹሉ አስቀድሞ በጽሑፉ ላይ፣ “ፈላስፋ” የሚል ቃል በመጠቀሙ ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ ይኸውም፣ አንድን ሰው ፈላስፋ ብለን እስከጠራነው ድረስ፣ የመንግሥትም ኾነ የሌላ በማለት ቅጽል ብንጨምርበት ፈላስፋነቱ አይሻርምና፡፡
የያሬድ ትችት በኢንተርኔት እና በጋዜጣ (በረራ) ከመቅረቡም በላይ፣ በ`ዶምቦስኮ` (ህወሓቶች ከትውልዳቸው ምርጥ ልሂቃን ለማውጣት የከፈቱት ት/ቤት) ምሩቅ ቴዎድሮስ ፀጋይ፣ የራዲዮ ፕሮግራም ላይ ጸሐፊው በራሱ አንደበት አንብቦታል፡፡
የእኔ ጽሑፍ በዋናነት ለያሬድ ጥበቡ ትች ምላሽ የሚሰጥ ቢኾንም፣ ስለ ቴዎድሮስ ፀጋይ፣ አዲስ አበባ የሚኖር አንድ ወዳጄ ከዚህ ቀደም ካጫወተኝ ገጠመኝ ጋራ አያይዤ ለማለት የምፈልገው አለኝ፡፡
ትርክቱም፡- “ጊዜው የዛሬ ኀምሳ ዓመት ገደማ ሲኾን፣ አንድ ግእዝ የሚያውቅ ጀርመናዊ ወዳጃችን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር፡፡ እኔ እና ጓደኛዬ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያን እንዲጎበኝ ይዘነው ሔድን፡፡ በምንጎበኝበት ወቅትም፣ አንድ የደብሩ አገልጋይ ጥግ ላይ ቆመው በከፍታ ድምፅ የዕለቱን ስንክሳር ያሰሙ ነበር፡፡ አብሮኝ የሔደው ኢትዮጵያዊው ጓደኛዬ አንባቢውን፣ እባክዎን አባቴ ወደ አማርኛ ቢተረጉሙልን ብሎ ሲጠይቃቸው፣ ቀና ብለው አዩትና በቁጣ ቃል፣ አይቻልም! ብለው ንባባቸውን ቀጠሉ፡፡ በመካከላችን ፈረንጁ ቆሞ ስለ ነበር፣ አንድ ጊዜ ለእኔ አንድ ጊዜ ለጓደኛዬ የካህኑን የግእዝ ንባብ እየተከተለ ወደ አማርኛ ይመልስልን ጀመር፡፡ ካህኑም፣ አልፎ አልፎ ዐይናቸውን ወደ እኛ ጣል እያደረጉና በጥርጣሬ እየተመለከቱ እያሉ ንባብ ገደፉ፡፡ በዚህ ወቅት ፈረንጁ ጮኽ ብሎ ግድፈቱን ለማቃናት ሞከረ፡፡ ይህን ጊዜ ንባባቸውን ገታ አድርገውና እጃቸውን አጣምረው ፈረንጁን በትክታ እያዩ፣ ወቸው ጉድ! ሰይጣን ተመስሎ የማይመጣበት መንገድ የለም፤ አሉ፡፡
እኔም፣ የቴዎድሮስ ፀጋይን የፖለቲካ ዲስኩር በምሰማበት ጊዜ፣ “አይ ህወሓት ተመስላ የማትመጣበት መንገድ የለም!” እላለኹ፡፡  
ወደ ያሬድ ጥበቡ በምንመለስበት ጊዜ፣ ትቹ የተመሠረተበትን አስተሳሰብ፣ “ሶፊስታዊ” ብለን በርእሱ የጠቆምነውን ግሪካዊ ቃል ትርጓሜ፣ በመጠኑ አብራርቼ መጀመር ይኖርብኛል፡፡
ስለ ሶፍስትሪ ከተጻፉት በርከት ያሉ ድርሳናት መካከል፣ ሠረቀ ብርሃን ገብረ እግዚእ፣ ሕግ እና ሥርዐት፣ ግዳጅ እና ግዴታ መከበር እንዳለባቸው፣ “ክራይቶን” ከተሰኘው የፕሌቶ ዲያሎግ ውስጥ ወደ አማርኛ ከመለሱት ሥራቸው የሚከተለውን ገለጻ እናገኛለን፡፡
በብዙ ወርቅ እየተቀጠሩ እና ከከተማ ከተማ እየተዘዋወሩ ወጣቶችን ሲያስተምሩ፣ በአእምሮ ምርመራ ያልተጠመዱበት አንድም ሐሳብ አይገኝም:: … የትምህርታቸው ግብ ሰውን፣ አእምሮውን በሐሳብ ፍልስፍና እና በአእምሮ ምርመራ ትጉህ እና ብልህ ማድረግ፤ … አንደበቱን በሥርዓተ ሰዋስው፣ በቅኔ አገባብ፣ ሬቶሪክ ሕዝብን ለማስተዳደር እና ለመሥራት ይችላል ማሰኘት፤ … በምድር ዓለም በተድላ ለመኖር የሚችል እንዲኾን ማዘጋጀት ነበር፡፡
በእነርሱ ዘንድ አስተያየት እንጂ ፍጹም እውነት የለም፡፡ ለማንኛውም ሐሳብ እና ነገር፣ ኹኔታም ሚዛኑ እያንዳንዱ ሰው ነው፡፡ አስተያየቱም እንደ አስረጅነት፣ እንደ ክርክር ችሎታው የሚረጋ ወይም የማይረጋ ሊኾን ይችላል፤ እያሉ ያስተምሩ ነበር፡፡ በመጨረሻም፣ ማንኛውንም ሐሳብ እና የማኅበራዊ ትዳርን ሕገጋት በንቀት በማቃለል፣ በትዕቢት የሚመለከቱ፣ ሰውነታቸውን እጅግ አዋቂ አድርገው የሚያስቡ ነበሩ፡፡
ከላይ ከቀረበው፣ የፈላስፋው ሠረቀ ብርሃን ክፍለ እግዚእ የትርጉም ሐተታ እንደምንረዳው፣ ሶፊስታዊ አስተምህሮ፣ በተከታዮቹ አራት የአመለካከት ዕርከኖች ላይ የቆመ ነው፡፡ እነርሱም፤ 1ኛ. በዚህ ምድር ላይ በምቾት እና በተድላ ሊያኖረኝ የሚችል ስኬት እንዴት ማዳበር እችላለሁ? 2ኛ. የቋንቋ እና የክርክር ብልሃቴን በማሳደግ እንዴት ተቀናቃኜን ማሸነፍ እችላለሁ? 3ኛ. የአንድ ነገር እውነት የሚመረኮዘው፣ በግለሰቡ አተያይ እንጂ በእውነታው በራሱ አይደለም፡፡ ኹሉም ነገር አንጻራዊ ስለኾነ፣ ከሰው እይታ በላይ እና ውጪ እውነት የሚባል ነገር የለም፡፡ 4ኛ. ጸጋ፣ በጎነት፣ ግብረ ገብነት፣ እውነት፣ ፍትሕ ወዘተ. እንደየባህሉ ከሚተረጎሙ በቀር በራሳቸው የሚቆም ባሕርያዊ ትርጓሜ የላቸውም፡፡
ከላይ ከቀረበው የሶፍስታዊ አስተምህሮ የአመለካከት ዕርከኖች ጋራ፣ ያሬድ ጥበቡ በእጅጉ የተቆራኘ ግለሰብ ነው፤ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህንም በተከታዮቹ ሦስት አርእስተ ጉዳዮች ለይቼ አስረዳለሁ፡፡ 1ኛ. ያሬድ፣ በሞራሊቲ እና በባህል መካከል፤ 2ኛ. ያሬድ፣ በእውነታው እና በግቡ መካከል፤ 3ኛ. ያሬድ፣ በመውጣት እና ባለመውጣት መካከል፡፡  
በሞራሊቲ እና በባህል መካከል
ያሬድ ጥበቡ፣ ሞራሊቲን በሚመለከት እንደሚከተለው ጽፏል፡፡
በዘመናችን፣ ከዶ/ር ዳኛቸው የሚለዩ ብዙ ተመራማሪዎች እና ፈላስፎች፣ ሞራሊቲ አንጻራዊ ነው፤ ብለው ያምናሉ፡፡… ሞራሊቲ አንጻራዊ ነው ብለው የሚያምኑት ተብሎም ከተደረጉ ዘመናዊ ጥናቶች እንደምንረዳው፣ ብዙን ጊዜ ነገሮችን ከተለያዩ ጎናቸው መመርመር የሚያዘወትሩ ሰዎች፣ በሞራል ረገድ አንጻራዊ ናቸው፡፡… ዶ/ር ዳኛቸው ግን፣ በፕሌቶ እና አሪስቶትል ዘመን ላይ ቆመው ሞራል (ግብረ ገብነት) አንጻራዊ አይደለም፤ ምሉዕ ነው፤ አይጠየቅ ነው፤ ባህሎችንና መልክአ ምድሮችን ተሻጋሪ ነው ብለው ሊያሳምኑን ይሞክራሉ፡፡
ይህን አስተምህሮ ወደ መሬት በማውረድ፣ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተፈጸመ ወንጀልን እንደ ምሳሌ አንሥቶ አመለካከቱን ያብራራል:: ይኸውም፣ በዘመኑ አንድ ወጣት በሚኖርበት ማኅበረሰብ ባህል እና ወግ መሠረት፣ ለአቅመ አዳም ሲደርስ ሰው ይሰልብና የሰው ሕይወት ይጠፋል፡፡ ይህን ተከትሎም፣ በመደበኛው ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ ይፈረድበታል፡፡ የገዳዩ እናት ግን እንደምንም ብላ፣ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ፊት ቀርባ፣ “ልጄ ይህን የፈጸመው በባህል አስገዳጅነት እንጂ ከግል ወንጀለኝነት የተነሳ አይደለም፡፡ ዋናው ወንጀለኛ፣ ወደ ጎልማሳነት ለመግባት ሰውን መስለብ የሚፈቅደው ብቻ ሳይኾን፣ የሚያስገድደው ባህል ነው፡፡ ልጄ የማኅበረሰባችን ባህል ተጠቂ እንጂ ወንጀለኛ አይደለም፤” ብላ ተከራክራ በንጉሠ ነገሥቱ ፊት የልጇን የሞት ፍርድ አሻረች፡፡
ያሬድ ጥበቡ እንዳለው፣ በዘመናችን ሞራሊቲ አንጻራዊ ነው፤ ብለው የሚያምኑ ልሂቃን አሉ፡፡ ይኹን እንጂ፣ ይህ አይነቱ የሞራል እሳቤ ከጥንቱም ቢኾን፣ በሶፊስቶቹ ዘንድ የሚታመንበት ነበር:: ከኻያኛው መቶ ክ/ዘመን ወዲህ ደግሞ፣ የባህል አንጻራዊነት (Cultural Relativisim) የሚባለው አንዱ የሞራል ፍልስፍና ፈርጅ ነው፡፡ ከላይ የጠቀስነው የያሬድ አቀራረብ፣ ከባህል አንጻራዊነት አስተምህሮ ጋራ በእጅጉ የተቀራረበ ነው፡፡ በመኾኑም፣ ስለዚህ የባህል አንጻራዊነት የሞራል አዝማሚያ እና ፍልስፍና የተወሰነ ነገር ማለት ተገቢ ይኾናል፡፡
“ሞራሊቲ፣ እንደ ማኅበረሰብ ይለያያል፤ እንዲያውም ሞራሊቲ ማለት ተቀባይነት ላለው ልማድ የተሰጠ ስም ነው፡፡” (ሩስ ቤኔዲክት፣ 1934)
እንደ እዚህች የኻያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዕውቅ አንትሮፖሎጂስት አስተምህሮ፣ ልዩ ልዩ ባህሎች የተለያየ የሞራል መርሕ ተሸካሚዎች ናቸው፡፡ ኹለ-አድማሳዊ ሞራሊቲ አለ ብሎ ማመን ሥነ ተረት እንደ መቀበል ነው፡፡ በመኾኑም፣ ኹለንተናዊ የሞራል እውነት የለም፤ ካለም ተረታዊ ነው፡፡ እንዲያውም በርግጠኝነት ልንናገር የምንችለው፣ የልማድን እንጂ የሞራሊቲን መኖር አይደለም፡፡
እንደ ባህል አንጻራዊነት እሳቤ፣ አንድን ድርጊት በቋሚነት የምንመዝንበት ነፃ መስፈርት የለንም:: ይመዝንልናል የምንለው የትኛውም መስፈርት፣ ከባህል አሻራና ማኅተም ያልጸዳ ነው፡፡ በጥቅሉ፣ የባህል አንጻራዊነት የሚከተሉትን ነጥቦች በዋናነት የያዘ ነው፡፡ እኒህም፤ 1ኛ. የተለያዩ ማኅበረሰቦች ልዩ ልዩ ሞራላዊ ልማዶች አሏቸው፡፡ 2ኛ. ማንኛውም ድርጊት ከማኅበረሰቡ የሞራል መለዮ ከተነሣ ስሑት አይኾንም፡፡ 3ኛ. በሞራሊቲ፣ የማይነቃነቅ ወይም የማይዛነፍ የእውነት እና የምግባር ሚዛን የለም፤ ፍጹማዊ ሐቅ የሚባል ነገር የለምና፡፡
ለትችቱ ትች፤
በመጀመሪያ፣ የባህል አንጻራዊነት ዋናው የክርክር ምሶሶ የቆመው፣ ከተወሰነ የባህል ድርጊት እየተነሡ የሞራልን ባሕርይ የመወሰንና ሞራላዊ ምልከታን ማስቀመጥ ነው፡፡ ይኸውም፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ባህሉ የሚፈቅደው ድርጊት ካለ፣ ከዚያ ውስን ክዋኔ እየተነሡ ስለ ሞራሊቲ አጠቃላይ ብያኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ለምሳሌ፥ ኤስኪሞዎቹ እንደሚያደርጉት፣ የሴትን ልጅ ቁጥር ለመቀነስ ሲሉ ሴቶች ልጆችን ሲወለዱ እያለፉ ይገድሉ ነበር፡፡ እንደ ባህል አንጻራዊነት እሳቤ፣ ባህላቸው እስከ ፈቀደ ድረስ ለፈጸሙት ግድያ፣ ቤተሰቦች የሞራል ተጠያቂነት የለባቸውም፡፡ በመሠረቱ ግን ሞራሊቲ በዚህ ድርጊት ላይ የሚያነሣው ጥያቄ፣ የባህልን አንጻራዊነት የተሻገረ ነው፡፡ ይኸውም፣ ሰው በሕይወት ያለውን ተፈጥሯዊ ክብር እና በሕገ ልቡናውም ሕይወት የማጥፋትን በደል የሚለይ በመኾኑ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ሞራሊቲ ሴትን ልጅ መግደል ትክክል ነው ወይስ ትክክል አይደለም፤ ብሎ ማጠየቅን ሳይሻ፣ የእስኪሞዎቹን ድርጊት በሕይወት አጥፊነት ያወግዛል፡፡
በመቀጠል፡- እንደ ባህል አንጻራዊነት እሳቤ፣ የአንዱ ባህል ከአንዱ ባህል አይበልጥም፡፡ ጎጂ ባህል እና ጠቃሚ ባህል የሚባል ነገር የለም፡፡ ባህል እስከ ኾነ ድረስ በምንም መልኩ ጎጅ ሊኾን አይችልም፡፡ ከዚህ በመነሣት፣ በሞራል ሚዛን፣ ከፍተኛ ወይም ዝቅተኛ የሚባል ባህል የለም፡፡ ከዚህ አስተምህሮ አኳያ፣ ለአብነት ያህል፥ በባርነት፣ በፀረ ሴማዊነት፣ በተባዕታዊ ትምክህት እና በመሳሰሉት እኵያን ላይ አቋም ለመውሰድም ኾነ ትች ለመሰንዘር አንችልም፡፡
ይህም የሚኾንበት ምክንያት፣ የአንድ ድርጊት ትክክለኛነት አልያም ስሕተት የሚመሠረተው፣ ከሀገሬው ልማድ ጋራ የተስማማ ነው ወይስ አይደለም በሚል ስሌት ነው፡፡ ለማጠቃለል፣ የባህል አንጻራዊነት ዘይቤ፣ የሌላውን ባህል ብቻ ሳይኾን፣ የራሳችንንም ባህል በአገባቡ እየተቸን እንዳናበለጸግ ይገድበናል፡፡
በመጨረሻም፡- በባህል አንጻራዊነት፣ የባህል ዕድገት የሚባል ነገር የለም፡፡ የባህል ዕድገት ስንል፣ የባህል ልምምድ፣ ከዘመኑ ጋራ በአገባቡ እየተስማማ የሚጠናከርበት እና ለትውልድ የሚዘልቅበት ፍቱን ዐውድ ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም፣ የባህል አንጻራዊነት፣ የተሻለ እና ያልተሻለ የሚለውን መስፈርት ስለማይቀበል፣ በባህሎች መካከል ንጽጽር በመፍጠር የተሻለውን የማየት እና የመቀበልን በጎ ልምድ የሚከለክል ነው፡፡
መቋጫ፡- ሞራሊቲ፣ በምክንያታዊነት የሚመራ ሰው ኹሉ ሊቀበለው የሚችል ሕግ እና ደንብ ነው:: ይህ ሕግ እና ደንብ፣ በሰው ድርጊት ላይ ጫና የሚያሳርፍ ሳይኾን፣ ከማናቸውም ተፋላሚዎች ነፃ እና የማንንም ጥቅም ነጥሎ በግል የሚያስከብር አይደለም፡፡
የሞራል ግምገማ ወይም ምዘና በሚደረግበት ጊዜ፣ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ግምት በእኩልነት ላይ የተመሠረተ እንጂ፣ አንዱን ከሌላው በማበላለጥ አይደለም:: ከየትኛውም ባህል እና ወገን ብንኾን፣ ያለማዛነፍ ልንቀበላቸው የሚገቡ የሞራል እሴቶች አሉ፡፡ እነኚህ የሞራል እሴቶች፣ በራሳቸው በጎነት ቢኖራቸውም፣ ማኅበረሰባዊ ህላዌአችንን ለማስቀጠል ከፈለግን እነርሱን በተግባር አንብረን መጓዝ ግድ ይለናል፡፡ ለምሳሌ፥ አንድ ማኅበረሰብ፣ መግደልን፣ ስርቆትንና ሐሰትን ከፈቀደ፣ ማኅበረሰቡ እንደ ማኅበራዊ ህላዌውን ጠብቆ ለመዝለቅ ይቸገራል፡፡
ወደ ያሬድ ልመለስና፣ ስለ ሞራሊቲ በሰጠው ትች ላይ ተጨማሪ ትችት አክዬ፣ ወደ ሌላ ርእሰ ጉዳይ እሻገራለኹ፡፡
… ዶክተሩ ያላገናዘቡት ነገር፣ እንደ ሕንድ ያሉ የጥንት ሥልጣኔዎች እና በውስጣቸውም ያበቡት መጠነ ሰፊ የወግ አስተምህሮዎች በሞራሊቲ አስፈላጊነት አያምኑም:: በእነርሱ እምነት፣ ራስህን የዓለሙ አንድ አካል አድርገህ ካየህ እና የሰውም ብቻ ሳይኾን እንስሳትንና ዕፀዋትን እንደ ራስህ ካየህ፣ “አትግደል” የሚለው የሞራል ሕግ አስፈላጊነት ከየት ይመጣል ብለው ይከራከራሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች፣ ለተጻፉት ዐሥርቱ ትእዛዛት ሳይኾን፣ ለሕገ ልቡና ራሳቸውን ተገዥ አድርገው ታላቅ ሥልጣኔ ፈጥረዋል:: ይህ የሕገ ልቡና ጉዳይ ደግሞ፣ ኢትዮጵያውያንም ከምዕራባውያኑ ጋራ በከፊል የምንካፈለው እሴት ይመስለኛል፡፡…
በጥቅሱ የተቀመጠውን ሐሳብ በምፈትሽበት ጊዜ፣ በእጅጉ የሚያስገርምና በፍልስፍናው ዓለም፣ “ካታጎሪ ሚስቴክ” የሚባል ግድፈት እናገኛለን፡፡ ይኸውም ሕንዶቹ፣ ሞራሊቲ የሚባለውን ግሪካዊ ቃል ስላልተጠቀሙ፣ “በሞራሊቲ አያምኑም” የሚለው ፍረጃ ትክክል አይኾንም:: “ራስህን የዓለሙ አንድ አካል አድርገህ ካየህ፣ ለሰውም ብቻ ሳይኾን፣ እንስሳትንና ዕፀዋትን ጭምር እንደ ራስህ” ካየህ ማለቱ፣ ይኼ ምልከታ በራሱ የራሳቸው የሕንዶቹ የሞራል ፍልስፍና አይኾንም ወይ?
ኹለተኛ፣ ያሬድ በጽሑፉ ላይ እንደ ምሳሌ ያቀረበው ነፍስ ያጠፋው ወጣት፣ የባህል ጫና አሸንፎት፣ ያለማወቅ የሰው ሕይወት ጠፋበት እንጂ፣ እንደ ወንጀል መቆጠር የለበትም፤ ብሎ ሲያበቃ፣ ምሥራቃዊውም ኾነ ኢትዮጵያዊው የሞራሊቲ አስተምህሮ፣ ዐሥርቱ ሕገጋትን ባይቀበሉም፣ ከልቡናቸው ሕግ ተነሥተው መግደል ወንጀል እንደ ኾነ ሊረዱ ይችላሉ፤ ይለናል፡፡ ለሕንዶቹ የለገሰውን ከሕገ ልቡና የሚመነጭ ዕውቀት፣ ዐፄ ኀይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት እስካልከፈቱ ድረስ ኢትዮጵያዊው ወጣት ነፍስ ቢያጠፋ፣ የባህል ተጠቂ ስለኾነና ባለማወቅ ነው ብሎ ብቻ መደምደም አዳጋች አይኾንም ወይ?
ያሬድ፣ በእውነታው እና በግቡ መካከል
ከላይ በጥቂቱ ስለ ሶፊስታዊ አስተምህሮ ለማለት እንደሞከርኹት፣ የሶፊስቶች መቅድማዊ ዓላማ፣ እውነታ ላይ መድረስ ሳይኾን፣ የተለያየ ዘዴ በመጠቀም ተቀናቃኛቸውን ለማሸነፍ መሞከር ነው:: ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች መካከል፦ ሐሰተኛ ማስረጃ ማቅረብ፣ ነገሮች ግልጽነት እንዳይኖራቸው ማወሳሰብ፣ ማስፈራራት፣ ግለ ሰብእናን ማንኳሰስ፣ አጀንዳ ማስቀየስ፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ በእኔ አተያይ፣ እነኚህ አሉታዊ አካሔዶች፣ የያሬድ ኹነኛ መገለጫዎች ኾነው አግኝቻቸዋለኹ፡፡
በዚህ ንኡስ ርእስ ሥር፣ ይህንኑ ትዝብቴን በተጨባጭ የሚያስረዱልኝን ማሳያዎች እንደሚከተለው አቀርባለኹ፡፡
ማሳያ አንድ፤
“የአማራ ምሁራንና የኢንተርኔት፣ ፌስቡክ ምናምን እብዶች፣ ጀነራል አሳምነው ገዳይ ባይኾንስ፣ የመንግሥት እጅ ቢኖርበትስ ብለው መጠራጠራቸውን ፈላስፋው አልወደዱትም፡፡”
አሳዛኙ ድርጊት በተፈጸመ ማግሥት፣ ዐሥራ አንድ ያህል የክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዝዳንቶች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ዲኖች እና ዳይሬክተሮች፣ እንዲሁም መምህራን የተሳተፉበት የአማራ ምሁራን ጉባዔ በባሕር ዳር ተካሒዶ ነበር፡፡ ከኻያ አራት ገደማ የጉባኤው ተሳታፊ ምሁራን መካከል፣ ያሬድ እንደሚለው፣ ጀነራል አሳምነው ገዳይ ባይኾንስ ብሎ የተጠራጠረ አልነበረም፡፡ የብዙዎችን ንግግር ካደመጥሁ በኋላ፣ እኔ በተራዬ ስናገር፣ “ዛሬ በመካከላችሁ በመገኘቴና በጉዳዩ ያሳያችኹት ቁጭት ለእኔ ትልቅ ሕክምና ኾኖኛል፤” ካልኹ በኋላ፣ ድርጊቱን የሚያወግዝና አገር የሚያረጋጋ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡ ይኹን እንጂ፣ እኔ እና አንድ ፕሮፌሰር ቃላት የተለዋወጥነው፣ በጀነራል አሳምነው መግደል አለመግደል ላይ ሳይኾን፣ “አራት ሰዎች ዐጣን” በማለቱ ላይ ነው፡፡
እኔ፣ የማይኾን የሤራ እና የሸፍጥ ፖለቲካ አራመዱ፤ ያልኹት የፌስቡክ ጸሐፊዎችን እንጂ፣ የአማራ ምሁራን ጉባዔ ተሳታፊዎችን አልነበረም:: ከእነርሱ ጋራ ጉባዔውን በመግባባት አጠናቅቀን ነው የተለያየነው፡፡ ያሬድ ግን፣ ሙግቱን የግድ ማሸነፍ አለብኝ ብሎ ስለ ተነሣ፣  በሶፊስቶች ዘይቤ፣ ንግግሬን በማጣመም በሐሰተኛ ማስረጃ ለማጠናከር ተደፋፍሯል፡፡
ማሳያ ኹለት፤
ሀ. በኹለቱ ተማሪዎችዎ፣ በበሪሁን አዳነ እና በሽመልስ አብዲሳ ልዩነት አድርገው በሪሁንን ጥለው ከሽመልስ ለመወገን ምን ምክንያት አለዎት? በሪሁን፣ የአማራ ብሔርተኛ እና የሚድያ ታጋይ ሲኾን፣ ሽመልስ የኦሮሞ ብሔርተኛ እና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ነው፡፡ ግፍ እየተፈጸመበት ካለው በሪሁን ይልቅ በሪፐብሊካን ጋርድ ታጅቦ ከሚፈላሰሰው ሽመልስ ጋራ ያቆመዎት የሞራል ልዕልና ወይስ የሞራል ክሽፈት… ሳይመሽ ወደ ኅሊናዎ እና ወደ ሕዝብዎ ይመለሱ፡፡…
አሁንም እንደተለመደው፣ ያሬድ ማስረጃ ባነሰው ቁጥር ሶፊስታዊ ልምዱን ተጠቅሞ የሐሰት ማስረጃ በመፈብረክ ክርክሩን ለማሸነፍ ይሞክራል:: እንደርሱ አቀራረብ፣ ከበሪሁን ይልቅ ሽመልስን መረጥኽ፤ ሲለኝ፣ ነገሮችን አቃሎ ኹለቱ በፊቴ ለውድድር ቀርበው ሽመልስ ይሻለኛል፤ እንዳልሁ አድርጎ አቅርቦታል፡፡
በሪሁን፤
ከበሪሁን ጋራ የተዋወቅነው፣ በድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር የፍልስፍና ተማሪ ኾኖ ከገባ በኋላ ነው:: በሪሁን፣ ማንበብ የሚወድ እና ታታሪ ተማሪ ነው፤ በጋዜጠኝነት ሞያም የተሰማራ ነው፡፡ አንድ ቀን፣ “ዶ/ር፣ የቤት ኪራይ ችግር አለብኝ፤ የተወሰነ ወራት ከአንተ ጋራ ብቀመጥ ምን ይመስልሃል?” አለኝ:: እኔም፣ ዩኒቨርሲቲው ከሰጠኝ ቤት ውስጥ ኹለት ትርፍ ክፍል ስለነበረኝ አንዱን መጠቀም ትችላለኽ ብዬ አብሮኝ እንዲኖር ፈቀድኹ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው እስከ ምባረርበት ጊዜ ድረስ ለተወሰኑ ወራት በጋራ ኖርን፤ ስባረርም አብረን ጓዛችንን ሸክፈን ወጣን፡፡
እኔ እና በሪሁን፣ በየፊናችን ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴያችንን ስናደርግ ቆየን፡፡  ወደ መጨረሻ የትግሉ ምዕራፍ ላይ፣ እኔ ከተወሰኑ ሰዎች ጋራ፣ ኦሮ-አማራ የሚል ኮሚቴ አቋቁመን መንቀሳቀስ ጀመርን:: በዚህን ጊዜ፣ ከሽመልስ አብዲሳ ጋራ እንደገና ከፊቱ ይበልጥ መቀራረብ ጀመርን፡፡ ያሬድ እንዳለው፣ ከበሪሁን ይልቅ ሽመልስን የመምረጥ ጉዳይ ሳይኾን፣ የትግል አካሔዳችን ስላቀራረበን ነው፡፡
ከዚህ ላይ መናገር ባይገባኝም፣ በሪሁን በታሰረ ጊዜ፣ ከቅርብ ጓደኞቹ ወደ አንዱ ስልክ ደውዬ፣ የበሪሁን መታሰር ያሳሰበኝ እንደኾነ ገልጬ፣ በምን በኩል ለመተባበር እንደምችል ጠይቄዋለሁ፡፡ እርሱም ከአመሰገነኝ በኋላ፣ “የአንተ አስፈላጊነት በሚመጣ ጊዜ እናገኝሃለን፤” አለኝ:: ከዚህ በኋላ የኾነውንና እየኾነም ያለውን ነገር አሁን ለመግለጽ አልፈልግም፡፡
እንደተለመደው፣ ሶፊስታዊው ያሬድ ግን ለውንጀላ ቸኩሎ፣ እስረኛውን በሪሁንን ጥለህ ባለሥልጣኑን ሽመልስን መረጥኽ፤ አለኝ፡፡ እኔ ሽመልስን የማውቀው፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ከመኾኑ ከዐሥራ ኹለት ዓመት በፊት መኾኑ ቀርቶ፣ አሁን ከፍተኛ ሹመት ካገኘ በኋላ እንዳወቅኹት አድርጎ ማቅረብ፣ ለክሥ እና ውንጀላ ከሚቸኩል አእምሮ እንጂ፣ ከእውነት ፈላጊ ሰው የሚመነጭ አይደለም፡፡
ለ. ማስፈራራትን በሚመለከት፤ ያሬድ ማስፈራራትን ከሶፊስታዊነት ጠባዕዩ ብቻ ሳይኾን፣ ካደገበት የግራ ዘመም የፖለቲካ ባህልም የወሰደው ነው፡፡ “ሳይመሽብህ” የሚለውን የማስፈራሪያ ቃል የሰነዘረክብኝ የመጀመሪያው ሰው አይደለህም፡፡ አብረሃቸው በረሓ ከነበሩት ጓዶችህም በተደጋጋሚ ደርሶኛል፡፡
ማሳያ ሦስት፤
ሶፊስታዊ አስተምህሮ ነገሮችን ለማምታታት እንጂ ግልጽ ለማድረግ ስላልኾነ፣ ስለ ጀነራል አሳምነው ጽጌ ግድያ፣ ያሬድ ጥበቡ ሦስት ተጣራሽ ነገሮችን ይለናል፡፡
አንደኛ፡- “ዶ/ር ዳኛቸው፣ በሀገር ቤትም ኾነ በውጭ ካለነው የተለዬ መረጃ አላቸው ወይስ እስከ አሁን በሕዝብ ዐደባባይ በተጠመደው መረጃ ላይ ተመሥርተው ነው፡፡”
ኹለተኛ፡- “እኔ እስከማውቀው ድረስ ጀነራል አሳምነው እነአምባቸውን አልገደለም ብለው በርግጠኝነት የሚናገሩ እንኳንስ ፕሮፌሰሮች፣ እርስዎ የፌስቡክ ወረኞች ብለው የሚሰድቧቸው የማኅበራዊ ሚዲያ አሰናሳዮች ወይም ፊታውራሪዎች እስካሁን አላየሁም፡፡”
ሦስተኛ፡- “በእነዚህ አስገዳጅ ኹኔታዎች በቅጽበታዊ እብደት ውስጥ ሊገባ ይችል ይኾናል:: ለእነዚህ ዓይነት ዜጋ ደግሞ ይታዘናል እንጅ አያወግዙትም፡፡”
እነኚህ ጥቅሶች በግልጽ እንደሚያሳዩት፣ ያሬድ የተምታታ እና እርስ በርስ የሚጣረስ አመለካከት በማቅረብ፣ ኹኔታው ግልጽነት እንዳያገኝና እውነቱ ተደፍቆ እንዲቀር ሙከራ ማድረጉን ነው፡፡ ከኹሉ አስቀድሞ፣ ለእርሱ ትች መሠረት በኾነው ንግግሬ ላይ፣ ገዳይ እና ተገዳይ በአንድ የሞራል ገበታ አይቀርቡም አልኹኝ እንጅ፣ ያሬድ ጥበቡ ለጉዳዩ እንዳውገረገረው፣ አንድም ቦታ ላይ፣ ጀነራል አሳምነው ጽጌን አላወገዝኹም፡፡
ሌላው የሶፊስቶች አቀራረብ፣ በያሬድ የትች መንፈስ ላይ ጎልቶ እንደታየው፣ በኹሉም የዕውቀት ዘርፎች ላይ ዐዋቂ መስለው መታየታቸው ነው:: ከዚህ ላይ፣ የያሬድን የ“ቅጽበታዊ እብደት” ገለጻ በጥቂቱ እንመልከት፡፡ ያሬድ የሚንቀው ታላቁ ፕሌቶ፣ ዐዋቂ ማለት “ለኹሉም ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ሳይኾን፣ መልስ የሚገኝበትን መንገድ የሚያውቅ ነው::” እኔም በዚህ ፕላቶናዊ መርሕ ተነሥቼ፣ ያሬድ፣ “ቅጽበታዊ እብደት” ስላለው ሐረግ በቅጡ ለመረዳት ሳይኮሎጅስቱ ወዳጄ ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኘሁን ማብራሪያ ጠይቄ ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥቶኛል፤
ቅጽበታዊ እብደት ከወንጀል ሓላፊነት አያስጥልም:: የአእምሮ ሕመምተኛ ወይም በሽተኛ ሲባል፣ ሁል ጊዜ እብድ ነው ማለት አይደለም:: ለምሳሌ፥ እገሌ የስኳር ሕሙም ነው ሲባል ሁል ጊዜም ስኳሩ ከፍ ያለ ነው፤ ማለት አይደለም:: እንዲሁም የሰው ልጅ አበደ ሲባል፣ የአእምሮ ኹኔታው ወይም እብደቱ የማይለዋወጥ ነው ማለት አይደለም፡፡ አልፎ አልፎም ቢኾን፣ አእምሮው ጤናማነትን ያሳያልና፡፡
ወንጀል በሚፈጸምበት ጊዜ አንድ ሰው የነበረበት የአእምሮ ኹኔታ ወይም መንፈስ በተቀዳሚ መታየት አለበት፡፡ እንዲያውም ተቀዳሚ ጥያቄ ኾኖ የሚነሣው፣ ግለሰቡ በሕግ ተጠያቂ ሊኾን ይችላል ወይስ አይችልም ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ይነሣል እንጂ ቅጽበታዊ የሚባል የሳይኮሎጅ ካታጎሪ የለም፡፡
በወንጀል ድርጊት መፈጸም የሰውዬውን የአእምሮ ኹኔታ ማወቅና የሕግ ተጠያቂነት መወሰን የምንችለው፡- ሀ. የሰውዬውን የአእምሮ ታሪክ፤ ለ. ሰውዬውን ወደ አእምሯዊ ቀውስ (ሳይኮሲስ) የሚያደርስ ነገር መኖር አለመኖሩ፤ ሐ. ወንጀሉን ምናልባት ቅጽበታዊ የሚያደርገው፣ ድንገት ሽጉጥ መዝዞ ተኩሶ ቢኾን ነበር:: ይኹን እንጂ፣ የድርጊቱ አፈጻጸም ሒደት የሚያሳየው ፕሪሚዲቴሽን ያዘለ በመኾኑ፣ በቅጽበታዊ እብደት ውስጥ የሚካተት አይደለም፡፡
ያሬድ፣ በመውጣት እና ባለመውጣት መካከል፤
“የቀድሞው ዘመን ሶፊስቶች ያቀረቡት የጥቅም አገልጋይ አሳሳች ትምህርት፣ በጊዜያችንም ዘመናዊ ዳባ ለብሶ ወደ እልፍኝ አዳራሹ ለመግባት ይጠይቃል:: ዳባ እና ቆዳ ከለየን ቆየን፡፡” (እጓለ ገብረ ዮሐንስ፤ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ)
ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ በክፍሉ ዋና አዛዥ በጀነራል አሰፋ አየነ አቅራቢነት የሻምበልነት ማዕርግ ሲቀበል፣ ለአገሬ ለኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እና ለንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ በመታመን ደሜን አፈሳለሁ ብሎ በወንጌል ላይ እጁን በማድረግ ምሎ ነበር፡፡ ግን አያሌ ጊዜ ሳይዘገይ፣ ደርግ የተባለው መርእይ (Band) የዐፄን መንግሥት ሲገለብጥ፣ እንደ መሓላው ስለ ዘውዱ ክብር ደሙን ሊያፈስ ይቅርና ከሽፍቶቹ ጋራ በመተባበር ለማርክስሲት ሬጅም ታማኝ ነኝ፤ ሲል የመሓላ ቃሉን ሰጠ፡፡ አሁን ደግሞ ደርግን ከድቶ ለአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ እና ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ ነኝ፤ ብሎ ለመማል እየተሰናዳ አለ፡፡ ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ሌላ የሚምልበት አዲስ እምነት ያገኝና ምን እንደሚያደርግ አይታወቅም፡፡ (ብርሃኑ ድንቄ፤ አልቦ ዘመድ)
“ወጥቼ አልወጣኹም” በሚል ያሬድ ጥበቡ ራሱ ከጻፈው ስብስብ መጽሐፍ ተነሥቼ፣ የግለሰቡ ዋና መንፈስ፡- 1ኛ. ራሱ ካመነው ከመጀመሪያ የፖለቲካ ፍቅሩ ኢሕዴን ብሎም ብአዴን እና አሁን ደግሞ አዴፓ ጋራ መለያየት አቅቶታል፡፡ 2ኛ. እኔ፣ “ወጥቼ አልወጣኹም” ከሚለው የመጽሐፉ ርእስ የምወስደው ግንዛቤ፣ አንድ ግለሰብ፣ በተወሰነ የሞራል መልሕቅ ላይ ለመቆም፥ ከእኔነት፣ ከራስ ወዳድነት፣ ለራስ ትልቅ ግምት ከመስጠት፣ ከራስ በላይና ባሻገር ከአንድ ትልቅ በጎ ነገር ጋራ ተዋሕዶ የከበረ ማንነትን መንሣትንና መላበስን ይጠይቃል:: ያሬድ ግን፣ ይህን ማድረግ ስላልቻለ፣ የቀነጨረ ሞራላዊ እኔነት እንደያዘ አለ፡፡
የእልፍኝ አዳራሽ ማመልከቻ፤
የያሬድን ፖለቲካዊ ዜና ሕይወት በጥቂቱ ስንመለከት፥ የመግባት እና የመውጣት፣ እንደገና አሸነፈ ብሎ ላመነው ኀይል ማመልከቻ እያስገቡ በየጊዜው ደጅ መጥናትን በተደጋጋሚ አይተናል፡፡
ያሬድ ጥበቡ በወጣትነት ዘመኑ ወደ ኢሕአፓ ገባ፡፡ ከዚያም ከኢሕአፓ ከወጡት ውስጥ ኢሕዴንን መሠረተ:: በዚህ ድርጅት ውስጥ ጥቂት እንደቆየ፣ ለሥራ ወደ አሜሪካ ተልኮ ሳለ፣ ከድቶ እንደቀረ የድርጅቱ ኦፊሴልያዊ ታሪክ መጽሐፍ (የኢሕዴን/ብአዴን ታሪክ ከ1973-2008) ይገልጻል፡፡
ያሬድ ከክሕደቱ ባሻገር፣ በረሓ ያሉ ጓዶቹን በጣም ያስቀየማቸው፣ በራድዮ ቀርቦ፣ “ደርግን ለመጣል መሞከር ራስ ዳሽን ተራራን በመጫኛ ስቦ እንደ መጣል ይቆጠራል፤” በማለት ትልቅ የሞራል ስብራት እንዲደርስባቸው ለማድረግ መሞከሩ ነው፡፡ እነርሱ ግን የያሬድን ትንበያ ከቁም ነገር ባለመቁጠር፣ እንዲያውም “እንዳያልፉት የለም” ለሚለው መዝሙራቸው መነሣሣት ኾኖላቸዋል፡፡
በመቀጠል፣ በምርጫ 97 ወቅት ከቅንጅት ጋራ ኾኖ በዋሺንግተን ዋናው የፖለቲካው አጋፋሪ ኾነ፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ፣ “እነበረከት ስምዖን እና እነአዲሱ ለገሰ ጨዋታቸው፣ ፈገግታቸው ናፈቀኝ” ብሎ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አገኛቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምም፣ እንዴት መብት የሚረግጡ ሰዎች ይናፍቁሃል፤ ቢሉት፣ ወደ አሜሪካ ከተመለሰ በኋላ ሐሳቡን ቀየረ፡፡ ሐሳቡን የቀየረበት ዋና ምክንያት ግን የፕሮፌሰር መስፍን ትችት ሳይኾን፣ ወደ ድርጅቱ መልሱኝ ብሎ ለእነ በረከት ስምዖን ያስገባው ማመልከቻ ተቀባይነት ስላላገኘ ነው፡፡
በቅርብ ጊዜ፣ በኢሕአዴግ ውስጥ የተካሔደውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፣ በተደጋጋሚ ሲያደርግ እንደቆየው፣ የብአዴን መሪዎችን ለተወሰኑ ወራት ከውጭ ኾኖ ሲያወድስ ከቆየ በኋላ ተመልሶ ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ በመጀመሪያ ላይ፣ ከድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኰንን ጋራ ለብቻው ተገናኘ፡፡
ከዚያም ወደ ባሕር ዳር ሔዶ፣ የክብር አቀባበል ከተደረገለት በኋላ፣ የአገር እና ሌሎች የአፍሪካ መሪዎች በሚያርፉበት አቫንቲ በተባለው ሆቴል እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ መጽሐፉን ካስተዋወቀና ከሸጠ በኋላ፣ መኪና ከነሹፌሩ ተሰጥቶት ወደ ጎንደር አቀና፤ በዚያም በአዴፓ ፈቃድ በመንግሥት አዳራሽ መጽሐፉን አሻሽጧል፡፡
ይህ ሁሉ እየኾነ ባለበት ወቅት፣ ወደ አሜሪካ ከመመለሱ በፊት በተካሔደው የአዴፓ ጠቅላላ ጉባኤ ለመሳተፍ ማመልከቻ አስገባ፡፡ ኾኖም፣ ድርጅቱ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀረ፡፡ በዚህም ሳቢያ፣ ያሬድ ጥበቡ በእጅጉ ተቆጥቶ ወደ መጣበት አሜሪካ ተመለሰ፡፡
እንግዲህ የዚህ መጣጥፍ አንባብያን ልብ እንድትሉልኝ የምሻው፣ በተደጋጋሚ መንግሥትን አስገቡኝ እያለ ማመልከቻ የሚያቀርብ ግለሰብ፣ እኔን፣ “ከባለ ጊዜዎች ጋራ መቆም ምንም ዐይነት የሞራል ማማ ላይ መቆምን አይጠይቅም፤ ሥልጣንን መጠየቅ በተለይ መቆጣጠሪያ ልጓም የሌለውን ሥልጣን መጠየቅ ግን ከባድ ነው፤ ያስከፍላል፤ አገር ያሳጣል፤ የስደተኝነት ዕድሜን ያራዝማል፤ ወኅኒ ያስወረውራል፤ ቀዝቃዛ ስሚንቶ ላይ ያስተኛል፤” ብሎ የሚመክርበት ሞራላዊ ቁመና ሊኖረው ከቶ አይችልም፡፡  
እኔነትን የመሻገር ፈተና፤
ሞራሊቲን ለመጨበጥ የሚገዳደር ዋነኛ ፈተና ካለ የእኔነት ጥያቄ ነው፡፡ የተለያዩ የሞራል አስተምህሮዎች እንደሚነግሩን፣ ምንጊዜም ተቀዳሚ ውጥረት የሚነሳው፣ በራስ ወዳድነት እና በሞራሊቲ ጥሪ መካከል በሚፈጠር ተፃርሮ ነው:: በምናደርጋቸው ነገሮች ራሳችንን ዋና አድርገን ከተመለከትን፣ ከሞራል ከፍታ ላይ ልንደርስ አንችልም፡፡ በእኔ እምነት፣ የያሬድ ቀንደኛ ፍትወቱ፣ ይህ ነው ብዬ አምናለኹ፡፡
የያሬድ የእኔነት ፈቲው፣ ክርክሮች ኹሉ፣ አሸናፊ እና ተደናቂ ያደርጉኛል፤ የሚል የቀደመ ስሌቱ ነው፡፡ ታዋቂ ናቸው ብሎ የሚያምናቸውን ሰዎች ስም በመጥቀስ እና ቅቡልነታቸውን ወደ ራሱ ለማስተላለፍ መጣሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጠቀሳቸው የተወሰኑ ስሞች መካከል፦ እስክንድር ነጋ፣ በሪሁን አዳነ፣ ጀነራል አሳምነው ጽጌ፣ ኤርሚያስ አመልጋ፣ ወዘተ. አብነት ይኾኑናል፡፡
ትችቴን ለማጠቃለል ያህል፣ ያሬድ ጥበቡ፣ ባልተማረውና በአግባቡ ባልተገነዘበው ጉዳይ ላይ የድፍረት ፍረጃ እና ድምዳሜ እየሰጠ ከስሕተት ዳጥ ሲወድቅ የኖረ ሰው ነው፡፡ የማያውቀውን ግሪካዊ ባህል፣ የሩቅ ምሥራቅ ፍልስፍናዊ እይታ፣ የአማራው ቱባ ባህል ራሱን በሊቅነት ሠይሞ፣ ሌላውን “ተማር ልጄ” እያለ ለመምከር የሚቃጣው ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡   

Read 3083 times