Saturday, 31 August 2019 12:56

“የነገዋን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ አቅጣጫ የሚያመራት ጠንካራ ትምህርት ነው” ፍሬአለም ሺባባው፤ የልማት ባለሙያ)

Written by 
Rate this item
(2 votes)

እስከማስታውሰው ድረስ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄዎች አሉ፤ በመሆኑም ያደግሁት ችግርን አሜን ብለን መቀበል የለብንም የሚል እምነት ይዤ ነው። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ የተሻለ ትምህርት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ የተገነዘብኩት፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ የሚያስችል አንድ ሀሳብ አፈለቅሁ:: ያ ሀሳብ የሕይወቴን አቅጣጫ ወደ መምህርነት፤ የማህበራዊ ስራ ፈጣሪነትና በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ ወደ መቀስቀስ አመጣው፡፡ ሁሉም ነገር የተጀመረው በሀሳብ ችግርን ለመጋፈጥ በመዘጋጀትና ለሀሳቡ ተፈጻሚነት በመንቀሳቀስ ነው፡፡
የተወለድኩት በአዲስ አበባ ሲሆን ያደግሁትም በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ከስምንት እህቶችና ከሦስት ወንድሞቼ ጋር ነበር፡፡ ልጅ ሳለሁ ቤተሰቦቼ ወደ አማራ ክልል ስለተዛወሩ፣ እኔም ከቤተሰቡ ጋር ወደዚያው በማምራት፣ የልጅነት ህይወቴን ባህር ዳር አካባቢ አሳለፍኩ፡፡
አባቴ ስራ ፈጣሪ ነበር፤ እናቴ ደግሞ እኔንና ሌሎች ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለባት የቤት እመቤት ነበረች፡፡ በቤተሰባችን ውስጥ የሴቶች ቁጥር የሚበልጥ ቢሆንም፣ የጾታ ሚናና የወንዶችን አስፈላጊነት በተመለከተ ግንዛቤ መያዝ የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነበር፡፡ አባቴ ወንድ ልጆች ሲወለዱ አብዝቶ ይደሰት ስለነበር፣ ሴት መሆን ጥሩ እንዳልሆነ እየተሰማኝ አደግሁ፡፡ ልጅ ሳለሁ አይናፋርና ቁጥብ ነበርኩ። ‹‹በሰዎች ፊት መናገር ነውር ነው›› ተብሎ ይነገረን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ነበር፣ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ውስጥ በሚገኘው ሜሪት ኮሌጅ የመግባት እድል አገኘሁ፡፡ እንደ አባቴ ሥራ ፈጣሪ የመሆን ፍላጎት ስለነበረኝ፣ የአነስተኛ ንግድ አስተዳደር ለማጥናት ወሰንኩ፡፡
በትምህርት አቀባበል ፈጣን ስለነበርኩና እንግሊዝኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቻሌ፣ አሜሪካ ካለው ሁኔታ ጋር ራሴን ለማላመድ ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ በእርግጥ ያረፍኩባቸው ቤተሰቦቼም ብዙ ድጋፍ አድርገውልኛል። በዚህ ወቅት ነው ስለ ራሴ ብዙ ነገሮችን ማሰላሰልና ማወቅ የጀመርኩት፡፡ በልጅነቴ ወደ ውስጤ ሰርጾ ስለገባው የተዛባ የጾታ አመለካከት ጥያቄዎችን ማንሳት ያዝኩ። በሞግዚትነት የተቀበለችኝ አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ በድፍረት እንድናገርና ሀሳቤን በነጻነት እንድገልጽ ታበረታታኝ ነበር፡፡ በመሆኑም ብዙም ሳልቆይ በሰዎች ፊት ለመናገር ያግደኝ የነበረው አይነጥላ ተገፈፈልኝ፡፡ እሳት የላስኩ ተናጋሪ ወጣኝ። በወቅቱ ይህ ለውጥ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶችና ሴቶች በማስተማሪያነት የማጋራው መልካም ተሞክሮ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡
በኮሌጁ የጀመርኩትን ትምህርት ለሦስት ዓመታት እንደተከታተልኩ ለማቋረጥና ወደ አገሬ ለመመለስ የሚያስገድድ ሁኔታ ገጠመኝ። በወቅቱ ወላጆቼ በፍቺ ትዳራቸውን አፍርሰው ተለያይተው ስለነበር፣ ወደ አገር ቤት ተመልሼ፣ ታናናሽ እህትና ወንድሞቼን የመንከባከብ ኃላፊነት ወደቀብኝ፡፡ ይህ በሕይወቴ ካጋጠሙኝ ፈታኝ ሁኔታዎች አንዱ ነበር፡፡ በቀጣይ ወዴት አቅጣጫ መሄድ እንዳለብኝ ለማሰብ አቅም አልነበረኝም፡፡ በዚህ ወቅት ነው ከባለቤቴ ጋር ተገናኝተን፣ ወደ አሜሪካ ተመልሼ ትምህርቴን የመከታተል ዕቅዴን በመሰረዝ፣ ባህርዳር ለመቆየት የወሰንኩት፡፡
በሪልእስቴት ኢንቨስትመንት መስክ የመሰማራት ሀሳብ ነበረኝ፡፡ ይሄን ሀሳቤን የቀየርኩት ግን በአጋጣሚ ነው፡፡ የሦስት አመት እድሜ ለነበረው ልጄ አጸደ ሕጻናት ሳፈላልግ በፍጹም ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በከተማዋ የነበሩት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከአንደኛ ክፍል ጀምረው ነበር የሚያስተምሩት:: የተለያዩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ተዟዙሬ ስጎበኝ፣ ያየሁትን ነገር ለማመን ተቸግሬ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቶቹ  ያስተዋልኩት የጥራት መጓደል በጣም አስደነገጠኝ፡፡ አንድ ነገር መሥራት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ‹‹ለምን ትምህርት ቤት አላቋቁምም?›› የሚል ሀሳብ በውስጤ ተፈጠረ፡፡ ሃሳቤን እውን ማድረግ የምችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ጀመርኩ:: በዚህ ወቅት ነው መንግስት፣ ትምህርት ቤት መገንባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች፣ መሬት በነጻ እንደሚሰጥ መግለጫ ያወጣው። ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ህልሜን እውን ለማድረግ ቆርጬ ተነሳሁ፡፡
ከአጸደ ሕጻናት እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ለመክፈት የሚያስችል የፕሮጀክት ንድፍ ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ ከባለቤቴ ጋር በመሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የመክፈል አቅም አጠናን፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በብቁ መምህራን በኮምፒውተር ቤተ ሙከራ፣ በመጫዎች ቦታ፣ በበቂ መጻሕፍትና በሌሎች የመማር ማስተማር ቁሳቁስ ለተደራጀ ትምህርት ቤት፣ ምን ያህል ገንዘብ መክፈል እንደሚችሉ ለማወቅ ነበር ጥናቱን የሰራነው። ማህበረሰቡ የመክፈል አቅም ካለው ትምህርት ቤቱ መቋቋምና በዘላቂነት መቀጠል እንደሚችል፣ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ እምነት ነበረን። ለጥናታችን በተጠቀምንበት መጠይቅ ውስጥ ሦስት አይነት የክፍያ አማራጮችን ነበር ያቀረብነው፡፡ በጣም የሚገርመው መጠይቁን ከሞሉ ሰዎች አብላጫ ቁጥር ያላቸው፣ ከፍተኛ የተባለውን የክፍያ አማራጭ ነበር የመረጡት። ከዚያም በመነሳት እቅዳችን ተግባራዊና የሚያዋጣ ሊሆን እንደሚችል ተረዳን። እናም የባህር ዳር አካዳሚ ግንባታ ተጀመረ፡፡  
ግንባታውን የጀመርነው በተለያዩ ምዕራፎች በመከፋፈል በአነስተኛ ጅምር ነበር፤ እናም የአጸደ ሕጻናት፣ የአንደኛ ደረጃ፣ የመካከለኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶች የሚሰጡባቸውን አራት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ገንብተን ጨረስን። ሃምሳ ተማሪዎችን ብቻ ይዞ በ2001 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የባህር ዳር አካዳሚ፣ በአሁኑ ጊዜ 2700 ተማሪዎች አሉት፡፡ ሌሎች በርካቶችም ተቀባይነት አግኝተው ወደ አካዳሚው ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የባህር ዳር አካዳሚ ተማሪዎች የብቃት ደረጃ እጅግ ጥሩ የሚባል ሲሆን አብዛኛዎን ጊዜ በክልሉ ከሚገኙ ተማሪዎች ከፍተኛውን ውጤት የሚያስመዘግቡትም የዚሁ አካዳሚ ተማሪዎች ናቸው፡። በተማሪዎቻችንና በአካዳሚያችን መምህራን ብቃት ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ትምህርት ቤታችን ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ለተማሪዎች አጠቃላይ የትምህርት እድገት ድጋፍ የምናደርግበት የክትትል ፕሮግራም ነው። ለወላጆች የምናዘጋጃቸው አውደ ጥናቶችና ሥልጠናዎችም በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከጾታ ጋር የተያያዙ የተዛቡ አመለካከቶችን ለማስቀረት ተግተን እንሰራለን። ለወንድ ተማሪዎች የምግብ ዝግጅት፣ ለልጃገረዶች ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትን የሚፈጥሩ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሥራ መደቦች ተቀጥረው በመሥራት ላይ ከሚገኙ 216 የአካዳሚው የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤታችን የሚጠቀስበት ሌላው ትልቅ ነገር ደግሞ የትምህርት ቤቱ ሰራተኞች፣ ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ራሱን የቻለ የሕጻናት እንክብካቤ ክፍል በግቢው ውስጥ መኖሩ ነው:: በሥራ ቦታዎች ላይ መሰል የሕጻናት እንክብካቤ አሰራሮች መስፋፋት እንዳለባቸው በአጽንኦት እናገራለሁ፡፡ ትምህርት ቤታችንም በዚህ መልካም ተመክሮው በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ሊሰጠው ይገባል እላለሁ፡፡
ትምህርት ቤቱን በማቋቋሙ ሂደት ከገጠሙን ዋነኛ ችግሮች መካከል ብቃት ያላቸው መምህራንን ለማግኘት አለመቻል አንዱ ነው፡፡ ለትምህርት ቤቱ ያስቀመጥኳቸው ደረጃዎች ከፍተኛ እንደመሆናቸው፣ የምንቀጥራቸውን መምህራን እንደገና በራሳችን በማሰልጠንና በማብቃት፣ ምርጥ መምህራን የሚሆኑበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንዳለብን ተስማምተናል፡፡ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመጋፈጥ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም። ልናከናውነው አንችልም የምንለው ምንም አይነት ነገር መኖር የለበትም ብለን ስለተነሳን፣ ይሄን አቋማችንን አስጠብቆ ማስቀጠልም ሌለው የገጠመኝ ፈተና ነበር፡፡
ለሚገጥሟችሁ ማናቸውም ችግሮች መፍትሄዎችን ለመፈለግ በራስ መተማመንና ቁርጠኝነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች፣ በእለት ተዕለት ሕይወታቸው ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች፣ መልካም አጋጣሚዎችን መፍጠር እንዲሁም ችግሮችን ለመፍታት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በአጽንኦት ማሰብ እንደሚገባቸው እንዲገነዘቡ እፈልጋለሁ:: የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች ወደ ገንዘብ አመንጪ ዕድሎች በመቀየር እንደ ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪ፣ ለውጦችን አስመዝግቡ፡፡ የተሻለች ኢትዮጵያንም ሆነ የተሻለች አለምን መፍጠር የምንችለው በዚህ መልኩ ነው፡፡
ከሌሎች አጋሮቼ ጋር በመሆን የአማራ ሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች ማህበርን በ2004 ዓ.ም ባህር ዳር ውስጥ ለማቋቋም የገፋፋኝ፣ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ የንግዱን ማህበረሰብ እንዲቀላቀሉ ለማበረታታት ያለኝ ጥልቅ ፍላጎት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ ሦስት ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን በአገሪቱ ከሚገኙት የሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች ማህበራት በትልቅነቱ የሁለተኛነት ደረጃ ለመያዝ በቅቷል፡፡ የማህበሩ የመጀመሪያዋ ፕሬዚዳንት ሆኜ ባገለገልኩባቸው አራት አመታት፣ በንግዱ ዘርፍ ያሉ ሴቶች እንዲነቃቁና ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎችን አከናውኛለሁ፡፡
በተጨማሪም ሴቶች በክልሉ ልማት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ሀሳቦቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ ለማበረታታት በትጋት ሰርቻለሁ፡፡ ያ ወቅት በሕይወቴ ግሩም ከምላቸው ጊዜያት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የሴቶችና የማህበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች አፈ ጉባኤ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በቅርቡ የአፍሪካ ሴት ሥራ ፈጠራ ፕሮግራም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኛለሁ፡፡ በቦርዱ የሚጠበቅብኝን ሥራም በደስተኝነት መተግበሬን ቀጥያለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአገራችን ከተቋቋሙት የግል ባንኮች በአንደኛው፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
እንደነ ማህታማ ጋንዲና እማሆይ ቴሬዛ ያሉ ታላላቅ ግለሰቦች፣ የሰሯቸውን ሥራዎች፣ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ሳደንቅ ነው የኖርኩት፡፡ ለማህበረሰባቸው ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች፣ በእያንዳንዷ ቀን መነቃቃትን ይፈጥሩልኛል፡፡ የትምህርት መስፋፋት ተቆርቋሪ እንደመሆኔ፣ ከትምህርት ገበታ ራሴን አርቄ አላውቅም። በልማት ጥናቶች ላይ በማተኮር በሰብዓዊና ማህበራዊ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ተቀብያለሁ፡፡ አሁንም በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ በልማት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቴን በመከታተል ላይ እገኛለሁ፡፡
ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ ከመቅረባቸው በፊት ተገቢ ምግብ መመገብ እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥቼ በመሥራት ላይ የምገኘውም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ቤት ምሳ ፕሮግራሞች እንዲካተቱ በማድረግ ላይ ነው:: በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቼ ማሰብ የጀመርኩት ከአንድ የአካዳሚያችን ሰራተኛ በደረሰኝ መረጃ ላይ ተመስርቼ ነበር፡፡ በዕለቱ ካገኘሁት መረጃ ለመረዳት እንደቻልኩት፣ በአካዳሚያችን ተማሪ የሆነ አንድ ህጻን፣ ሁሌም ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ ነበር ወደ ትምህርት ቤት የሚመጣው፡፡ ተማሪው ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ በመምጣት፣ የተመገበ አስመስሎ፣ ጾሙን ውሎ ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር፡፡ የመረጃውንም እውነትነት ካረጋገጥኩ በኋላ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቼ ለመሥራት ወሰንኩ፡፡ በሌሎች አገራት የትምህርት ቤት የምሳ ፕሮግራሞች እንዴት እንደተጀመሩ ጥናት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ የመንግስትና የሕዝብ አጋርነት ለመፍጠር በአልሚ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ምግቦችን እያዘጋጁ ለትምህርት ቤቶች የሚያቀርቡ አነስተኛ የንግድ ተቋማትን ለማቋቋም ነው የፈለግሁት:: በአሁኑ ሰዓት ከመላ አገሪቱ ሴቶችን እየተቀበለ በምግብ ይዘት፣ በምግብ ደህንነትና ንጽህና አጠባበቅ በማሰልጠን፣ የራሳቸውን ንግድ ፈጥረው ለትምህርት ቤቶች ምግብ ማቅረብ እንዲችሉ እድል የሚፈጥር፣ የትምህርት ቤት ምግብ ማሰልጠኛ በአዲስ አበባ በማቋቋም ላይ እገኛለሁ፡፡ መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የትምህርት ቤት የምሳ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ የሚያደርግ ብሄራዊ ቦርድ በማቋቋም፣ እኔ የጀመርኩትን እንቅስቃሴ፣ ከ2012 ጀምሮ በመረከብ፣ አገር አቀፍ የትምህርት ቤት የምሳ ፕሮግራም እንደሚጀምር ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡
ትምህርት ቤቶች ወደፊትም የምተጋላቸው ዋነኛ ትኩረቴ ሆነው እንደሚቀጥሉ አውቃለሁ፡፡ አንድ አገር የሚለወጠው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው:: የለውጡ ዋነኛ ቁልፍም ትምህርት ነው፡፡ ጠንካራ ትምህርት ቤቶች የጠንካራ መጪ ዘመን መሰረቶች ናቸውና፡፡ የነገዋን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ አቅጣጫ የሚያመራት ጠንካራ ትምህርት ነው፡፡
(“ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች”፤ 2007 ዓ.ም)


Read 1741 times