Saturday, 31 August 2019 13:07

ሁለቱ ሙሴዎች - የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

ኢትዮጵያዊ የማህበራዊ ትስስር አውታር በሙከራ ላይ ነው
                             
             ሁለቱ ወጣቶች ትውውቃቸው ከልጅነታቸው ይጀምራል፡፡ ሁለቱም ለቴክኖሎጂና ሶፍትዌር ፈጠራ  ዝንባሌ እንደነበራቸው ይናገራሉ፡፡ ጓደኛሞቹ ሙሴ ዘለቀና ሙሴ ሙላቱ ይባላሉ:: ሁለቱ ሙሴዎች ብለናቸዋል፡፡ ሙሴ ዘለቀ በአሁኑ ወቅት፣ በቻይና ጀንዋሲቲ ጄጃኖማል ዩኒቨርስቲ፣ የ3ኛ ዓመት ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው:: ሙሴ ሙላቱ ደግሞ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ይማራል፡፡ የዓለማችን ታላላቅ የቴክኖሎጂ  ፈጣሪዎችን እንደ አርአያ እየተመለከቱ ማደጋቸውን ወጣቶቹ  ይናገራሉ፡፡ “ለኔ የፌስቡክ መሥራቹ ማርክ ዙከርበርግና የአፕል ኩባንያ ፈጣሪው ስቲቭ ጆብስ አርአያዎቼ ናቸው” የሚለው ሙሴ ዘለቀ፤ ከልጅነቱ ጀምሮ የእነዚህን ታላላቅ የፈጠራ ባለቤቶች የህይወት ተመክሮ እያጠና ማደጉን ያስታውሳል፡፡   
ከልጅነታቸው ጀምሮ ስማቸውን የሚያስጠራ አንዳች ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለሃገራቸው ማበርከት ያልሙ እንደነበረ የሚናገሩት ወጣቶቹ፤ በዩኒቨርሲቲ የምናጠናውን የትምህርት መስክ የመረጥነውም ተመካክረን ነው ይላሉ፡፡ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ቢገቡም፣ ህልማቸውን ግን በልባቸው ይዘው እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ የሙሴ ዘለቀ ወላጅ አባት አንጋፋው ፖለቲከኛ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፤ “ልጄን ወደ ቻይና ልኬ ከፍተኛ ወጪ አውጥቼ ሳስተምር፣ ብሩህ አዕምሮውን ተጠቅሞ አንዳች ፈጠራ ለሀገሩ እንደሚያበረክት ተማምኜ ነበር” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡  
ወጣቶቹ ዝንባሌያቸውን በትምህርት በማጐልበት፣ ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ቋንቋ መልዕክቶችና መረጃዎች የሚለዋወጡበት፣ የሚማማሩበትና የሚተዋወቁበትን የኢንተርኔት ማህበራዊ የትስስር ሚዲያ አውታር ለመፍጠር  ችለዋል፡፡ ለዚህ ፈጠራቸውም ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ  ንብረትና ፈጠራ ጥበቃ ኤጀንሲ የማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ ሁለቱን ወጣቶች በፈጠራ ሥራቸው  ዙሪያ አነጋግሯቸዋል:: እነሆ፡-


        እስቲ ስለ ፈጠራ ሥራችሁ አብራሩልኝ?
ሙሴ ዘለቀ፡- ፈጠራችን የማህበራዊ ትስስርና ሚዲያ አውታር ነው፡፡ ማንኛውም የማህበራዊ ሚዲያ የሚያደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ያካተተ ነው፡፡ ለምሣሌ ቻት ማድረግ፣ ፎቶዎችና ጽሑፎች በራሳችን ገጽ ላይ መለጠፍ፣ ማጋራት፣ ኮሜንት ማድረግ፣ የራስን ተከታይ ማፍራት፣ የራስን ገጽ መፍጠር የመሳሰሉት ሁሉ ያሉት ነው፡፡ ፌስቡክ የተሰኘው የማህበራዊ ትስስር አውታር የሚያደርጋቸውን በሙሉ መተግበር የሚያስችል ነው፡፡
አንድ ሰው የእናንተን የማህበራዊ ትስስርና ሚዲያ አውታር ለመጠቀም ምንድን ነው ማድረግ ያለበት?
ሙሴ ሙላቱ፡- ልክ ሌሎች ማህበራዊ አውታሮችን እንደሚጠቀመው ነው፡፡ ወደ ገጽታ ዶት ኮም ይገባል ወይም አፕሊኬሽን (መተግበሪያ) ካለ፣ እሱን ተጠቅሞ ወደ ገፁ በመግባት፣ የራሱን አካውንት ይከፍታል፡፡ ጓደኛ ያፈላልጋል፤ የጓደኞችን ጥያቄ ይቀበላል፤ ተከታዮች ይጋብዛል፡፡ በዚህ መንገድ የመገናኛ አውታሩ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው አካውንት የሚከፍተው በስልኩ ነው፡፡ ይህ መሆኑ ያልተገቡ ነገሮችን ከመለጠፍ እንዲቆጠብ ያደርገዋል፡፡ ተጠያቂነት እንዳለበትም ያስገነዝባል፡፡ ያልተጣራ ወሬ ለማውራት የተመቸ አይደለም፡፡
ከፌስቡክና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር አውታሮች የናንተን የተለየ ወይም የተሻለ የሚያደርገው ምንድን ነው?
ሙሴ ሙላቱ፡- አንደኛ ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላል፡፡ የጥላቻ መልዕክቶችን ማስቀረት ያስችላል፡፡ በአውታሩ መጥፎ መልዕክቶች ከተላለፉና ኩባንያችን እነዚያን መልዕክቶች አስወግድ ከተባለ ፈጥኖ ያስወግዳል፡፡ አሁን ፌስቡክ እንዲያስወግድ ሲፈለግ፣ ሂደቱ አስቸጋሪ ነው፡፡ የኛ ግን በእጃችን ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የማህበራዊ ትስስር አውታርን ለበጐ ዓላማና ለመማሪያ መጠቀም የሚል ነው፤ መርሃችንም፡፡
የሌሎች አገራትን  ልምድና ተመክሮ ለማጥናት ሞክራችኋል?
ሙሴ ዘለቀ፡- አዎ! እኔ በምማርበት ቻይና፣ ትልቁ ልክ እንደ ፌስቡክ የሚጠቀሙበት ዌቦ ይባላል:: ሌሎች የቻት ቲክ ቶክ የመሳሰሉ አሉ:: በዊቻት ከመገናኛነት ባሻገር  ገንዘብ ሁሉ ይላላኩበታል:: በጣም የዘመነ የማህበራዊ ትስስር አውታር ነው ያላቸው፡፡ ሩስያም በተመሳሳይ የራሷ አላት:: ኢትዮጵያውያንም ይሄን የኛን ፈጠራ የሆነ የማህበራዊ ትስስር አውታር በመጠቀም፣ የራሳችንን የመገናኛ መድረክ እንድናበለጽግ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ይሄን የቴክኖሎጂ ፈጠራ ለመስራት ምን አነሳሳችሁ?
ሙሴ ዘለቀ፡- ከድሮ ጀምሮ ለሶፍትዌርና ቴክኖሎጂዎች  ዝንባሌ ነበረን፡፡ ቻይና ስሄድ ደግሞ እነሱ ፌስቡክ እንደማይጠቀሙ ተረዳሁ፡፡ ዌቦ የሚባል የማህበራዊ ሚዲያ አማራጭ አላቸው:: ፌስቡክ ታግዷል፤ነገር ግን አሁን ሁሉም ዌቦን ስለሚጠቀም ፌስቡክ ቢለቀቅ እንኳ የሚጠቀመው እምብዛም አይኖርም፡፡ ቻይናውያን በራሳቸው ቋንቋ እርስ በእርስ የተሳሰሩበት ግዙፍ ማህበራዊ ሚዲያ ነው ያላቸው፡፡ እሱን በማየት ነው እኛስ ለምን የራሳችን ማህበራዊ ሚዲያ አይኖረንም፣ ብለን ያሰብነው፡፡ ይሄን ካሰብን በኋላም ማህበራዊ ሚዲያውን ወደ መፍጠሩ ሂደት ነው የገባነው፡፡
ይህን ማህበራዊ ሚዲያ ለመፍጠር ስትነሱ ምን ጥቅም አለው ብላችሁ ነው?
ብዙ ጥቅም አለው፡፡ ለምሣሌ በኛ ሀገር ትልቁ የማህበራዊ ሚዲያ አውታር ፌስቡክ ነው፤ ትዊተርም፣ ኢንስታግራምም አለ፡፡ ነገር ግን ፌስቡክ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ፌስ ቡክ ካለው የበላይነት የተነሳም መልካም ነገሮች ያሉትን ያህል፣ መንግስት ቁጥጥር ማድረግ በማይችልበት ሁኔታ በርካታ የጥላቻ መልዕክቶች ይተላለፉበታል፡፡ መንግስት ያንን ለመከላከል አንዳንዴ ኢንተርኔት ይዘጋል:: ይሄን ማድረጉ ብዙ ነገር ይጐዳል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት፣ በዚያው ልክ ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ሶፍትዌር  መፈጠሩ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡
ለኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ፈጠራችሁን አሳይታችሁ ከሆነ፣ ምን ዓይነት ምላሽ አገኛችሁ?
አሁን በቅርቡ አፍሪካውያን ብቻ የሚወዳደሩበት የፈጠራ ውድድር እንዳለ ተነግሮናል፡፡ እዚያ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ፍላጐት እንዳለን ነግረናቸዋል፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በውድድሩ እንድንሳተፍ  ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ ፈጠራችንንም በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎናል፡፡
ይህን ፈጠራችሁን የበለጠ በማበልፀግና በማስፋፋት በኩል ወደፊት ምን አስባችኋል?
ሙሴ ሙላቱ፡- ርዕያችን ሰፊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የኛ ፈጠራ ነው፣ ጥቅም ላይ ውሎ ማየት የምንፈልገው፡፡ ከዚያም ባሻገር በምስራቅ አፍሪካና በአጠቃላይ በአፍሪካ፣ አፍሪካውያን ስለ አህጉራቸው የሚወያዩበት፣ እርስበርስ የሚገናኙበትና የሚቀራረቡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጭምር ነው እቅዳችን፡፡ ከዚያም ሲያልፍ ወደ አለማቀፍ ደረጃ ለማሳደግ እንፈልጋለን፡፡ እቅዳችን ግዙፍ ኩባንያ አቋቁሞ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሀገራችንን ለማስጠራት ነው፡፡
ይሄን ፈጠራ ስትሰሩ ትልቁ ተግዳሮታችሁ  ምን ነበር?
ሙሴ ዘለቀ፡- ትልቁ ተግዳሮት የገጠመን በፋይናንስ በኩል ነበር፡፡ የስራውን ውጤታማነት ለመሞከር ሰርቨሮችን መግዛት ነበረብን፡፡ እሱ ደግሞ ውድ ነው፡፡ ያ ፈትኖናል፡፡ ነገር ግን በቤተሰቦቻችን ድጋፍ ተወጥተነዋል፡፡
ስራው ብዙ ወጪ ይጠይቃል ማለት ነው?
ሙሴ ዘለቀ፡- አዎ ብዙ ወጪ ይጠይቃል:: ለምሳሌ ለምንገዛው ዶሜይን ኔም፣ ‹‹ገጽታ›› (getsita) የሚለውን ስም ለማስያዝ፣ አሊባባ ወይም አማዞንን ማነጋገር፣ ከእነሱ ላይ ሰርቨር መግዛት አለብን፡፡ ከእነሱ ላይ ሰርቨር ገዝተን ነው ይሄን የማህበራዊ ትስስርና ሚዲያ አውታር መስራት የምንችለው፡፡ አሁን ገና ተጠቃሚዎቻችን ትንሽ ስለሆኑ ነው እንጂ ወደፊት ሲበዙ በየወሩ ለሰርቨር አቅራቢዎቻችን የምንከፍለው ይኖራል፡።
የሚዲያ አውታሩ በምን ያህል ጊዜ ወደ ሥራ ይገባል?
ሙሴ ዘለቀ፡- የማህበራዊ ትስስሮሽ ገጹ ተከፍቷል፤ ተሞክሯል፡፡ እስከ ማክሰኞ 100 ያህል ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ ለሙከራ ያህል እየተጠቀምንበት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ደግሞ መተግበሪያውን አዘጋጅተን ይፋ እናደርጋለን:: ሁሉም ሰው መተግበሪያውን (Application) በስልኩ በላፕቶፑ፣ ኮምፒውተሩና ታብሌቱ ላይ ጭኖ፣ ልክ ፌስቡክ እንደሚጠቀመው፣ የራሱን አካውንት ከፍቶ እንዲጠቀም እናደርጋለን፡፡ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ “ገጽታ (ገ)” የሚል ሎጎ ያለው መተግበሪያ ይፋ እናደርጋለን፡፡
ቤተሰቦቻችሁ ምን ያህል ድጋፍ ያደርጉላችኋል?
ሙሴ ዘለቀ፡- ቤተሰቦቻችን ምንም ሳይሰስቱ ባላቸው አቅም ሁሉ ድጋፍ እያደረጉልን ነው፡፡ ከድጋፍ ባለፈ እንደ ትልቅ ሃላፊነት ተደርጎ፣ “ከዚህ አገር ወጥተህ ስትማር አንድ ነገር ይዘህ እንድትመጣ ነው” ተብሎ ሁልጊዜ ይነገረኝ ነበር፡፡ እንደ አርአያ አድርጌ የምሰራውም እነ ማርክ ዙከርበርግን፣ እነ ስቲቭ ጆብስን ነው፡፡ ሁሌም ዝንባሌዬ የሶፍትዌር ቴክኖሎጂ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡
ሙሴ በላይ፡- እኔም ዝንባሌዬ የሶፍትዌር ጉዳይ ነበር። ኦን ላይን ጉዳዮች ላይ ለመሳተፍ እሞክር ነበር:: ለምሳሌ በኤሌክትሮኒክስ መገበያየት የመሳሰሉትን ነገሮች ለመስራት በሚል ነው ሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ መማር እንዳለብኝ ወስኜ አዳማ ዩኒቨርሲቲ የገባሁት፡፡ ቤተሰቦቼም ይህ ህልሜ እውን እንዲሆን ማንኛውንም ድጋፍ እያደረጉልኝ ነው፡፡ አዳማ ሄጄ እንድማር ያደረጉትም እነሱ ናቸው፡፡ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ተወዳድረው የሚገቡበት ዩኒቨርሲቲ ነው:: እኔም በዚህ መንገድ ነው የገባሁት፡፡
ይሄን የማህበራዊ ትስስሮሽ አውታር ተግባር ላይ እንዲውል ከማድረግ አንጻር ሊገጥመን ይችላል የምትሉት ተግዳሮት ምንድን ነው?
ሙሴ ሙላቱ፡- እኛ በሌላ አገር የተፈጠሩ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሰፊ መሰረት ያላቸውን ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኢንስታግራም የመሳሰሉትን ለመገዳደር የመጣን እንደመሆናችን፣ ከእነዚህ ኩባንያዎች መጠነኛ ተግዳሮት ሊገጥመን ይችላል። ነገር ግን እኛ ማህበረሰባችንን አሳምነን፣ የኢትዮጵያውያን የሆነው የማህበራዊ ትስስር አውታር ገናና እንዲሆን እንጥራለን፡፡
በቀጣይ ከዚህ የማህበራዊ ትስስሮሽ አውታር ፈጠራችሁ ባለፈ ምን መስራት ታስባላችሁ?
ሙሴ ዘለቀ፡- በተለይ በቴክኖሎጂ ዙሪያ እስካሁን ምንም አልተሰራም ብለን እናስባለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ባዶ ሜዳ ላይ ብዙ ስራ እንሰራለን፡፡ መፍጠር ባንችል እንኳ ከሌሎች አገሮች ተምረን ወደ ራሳችን አምጥተን የምንሰራቸው ቴክኖሎጂዎች ይኖራሉ፡፡

Read 8985 times