Print this page
Saturday, 31 August 2019 13:12

‹‹ጥቁር ሽታ!›› - የመሐመድ ነስሩ ሰማይ!

Written by  ደረጃ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 ኢትዮጵያ ውስጥ የአጫጭር ልቦለዶች ንባብ በብዛት የተለመደው በዘመነ ደርግ ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡ እንደ ማንኛውም ሶሻሊስት አገር፣ በአዲሱ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፕሮግራም የምትመራው ኢትዮጵያም፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለሕዝብ ንቃተ ህሊና ማሳደጊያና ለአብዮት እመርታ ልትጠቀምበት ሞክራለች፡፡ በሚያስተላልፈው ጭብጥ እንጂ በውበቱ ላይ ያን ያህል የሚያተኩሩ አብዮታውያን እምብዛም ቢሆኑ፣ በኛ አገር ግን በአጋጣሚም ሆነ በሌላ ምክንያት፣ በወቅቱ የነበሩት አሳታሚ ድርጅቶች፣ ይዘቱን ብቻ ሳይሆን ቅርፁንም አብጠርጥረው ይፈትሹ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ  በወቅቱ የታተሙትን ሥራዎች ዘወር ብሎ ማየት ብቻ ይበቃል፡፡
ሥነ ጽሑፍ በየዘመኑ በሚነሱ የፍልስፍና፣ የእምነትና በነባር ባህላዊ ቀለሞች መቃኘታቸው ግድ የመሆኑን ያህል ቅርፆችም በየዘመኑ ሲለዋወጡ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ በመላው ዓለም ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የሚታይ መልክ ነው፡፡ አሁን ወዳለንበት ዘመን ስንመጣ፣ በሕትመት አደባባይ እንደ አሸን የፈሉት ግጥሞች ናቸው፡፡ የጥራታቸውን ጉዳይ በተመለከተ፣ በሕዝቡ ልብ ውስጥ ተቀባይነት የማግኘት ዝንባሌ የፈጠሩትን ያህል የተሰለቹበትም ሁኔታ አለ፡፡
አጫጭር ልቦለዶች ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ይታያሉ፡፡ ባብዛኛው በጋዜጦች ይታተማሉ። ከዚያ በተረፈ በመጽሐፍት የመጠረዛቸው ጉዳይ ያን ያህል የተጋነነ አይደለም፡፡ በጋዜጣ ላይ ልቦለዳቸው ከሚታተምላቸው ደራስያን አንዱ ደግሞ መሀመድ ነስሩ ነው፡፡ የመሐመድ ልቦዶች ትንሽ የሚያፈነግጡ፣ ትረካቸው ፈጣን፣ ሀሳባቸውም ቀለል ያለ ሆኖ፣ ልቡ ግን ትልቅ ከበሮ የሚደቃ አይነት ነው፡፡
መሐመድ በቅርቡ ያሳተመው ‹‹ጥቁር ሽታ›› የተሰኘ መጽሐፉም የዚሁ ቀለም ንክር ነው፡፡ 203 ገጾች ያለው ይህ መጽሐፍ፤ ሃያ አምስት አጫጭር ልቦለዶችን ይዟል፡፡ ከሃያ አምስቱ ውስጥ ከጥቂቱ በቀር አብዛኛዎቹ በጣም አጫጭር ናቸው፡፡ ትረካው ግን ዘና ብሎ ሳይጨነቅ የሚፈስስ አይነት ነው፡፡ ምናልባትም ኤድጋር አንላፖ እንደሚለው፤ በአጭር ልቦለዱ ውስጥ ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ጠመንጃ፣ ታሪኩ እስኪያልቅ ድረስ ካልተተኮሰ፣ መግባት የለበትም የሚለው ዐይነት አጥር ግድ ላይለው ይችላል፡፡
ይሁንና ብዙዎቹ ሀሳቦቹ ሕይወትን በግርድፉ ሳይሆን በደቃቁ የሚያዩ አይነት ናቸው፡፡ ሀሳብ ውስጥ ገብተው ብዙ ይፈትላሉ፣ ብዙ ይጠይቃሉ:: የተፈጥሮን እንቆቅልሾች፣ የማህበራዊ ሕግጋትን ዳስ ሳይቀር ይነቀንቃሉ፡፡ ለምን?... እንዴት?... ወዘተ አይነት ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡ ሕይወትን አክብዶ ሳይሆን አቅልሎ የማየት ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ አንዳንዴም ከለመድናቸው ቃላትና ሀሳቦች በመነሳት ያላየናቸውን ጥቃቅን ጉዳዮች ይበረብራሉ። ለምሳሌ ሦስቱ ‹‹መ›› ዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ በተለያዩ ንዑስ ርዕሶች የከፋፈላቸው ይህ አጭር ልቦለድ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
የሰው ልጅ ታሪክ የሦስት ‹‹መ››ዎች ታሪክ ነው፡፡
መወለድ!
መኖር!
መሞት!
ሲወለድ እያለቀሰ ነው፡፡ ሲኖር እያለቀሰና እየሳቀ ነው፡፡ ሲሞትስ?... እሱ የሌሎች ድርሻ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ነግ በኔ ብለው ወይ ያለቅሳሉ ወይ…
በዚህ ልቦለድ፣ ገና ከመወለዱ በፊት ካለው ምጥ ይጀምራል፡፡ ከዚያም እልልልል ይባላል፡፡ ወንድ ነው ሴት ነውም አለ፡፡ በአጋጣሚ የመሐመድ ገፀ ባህሪ ወንድ ልጅ ሆነና ‹‹ወንድዬ›› ተባለ፡፡  ወንድዬ አደገና ቀበሌ መታወቂያ ሊያወጣ ሄደ፡፡ ቀበሌና እኛ መች ተለያይተን እናውቃለን? እውነቱን ነው፡፡ ለሠልፍ ለጨው፣ ለስኳር፣ ለሳሙና---ደርግ የጀመረው ሰልፍ፣ ይኸው እስከ ዳቦው ዘልቋል፡፡
ወንድዬ ግን መታወቂያ ሊያወጣ ሄዶ፣ ቀልቡ ከንፈር፣ አንገትና ጡት ላይ ወደቀ፡፡ የወደደው ግን ፀጉሯን ነው፡፡ አጭር ነገር ይወዳል፡፡ አጭር ንግግር፤ አጭር ፂም፣ አጭር ቀሚስ፣ አጭር ፀጉር…
ይህ ደግሞ የሆነው እናቱ አጭር ስለሆነች ነው፡፡
ያው ወደዳት፣ ጥቂት አጫወታት፤ ቀጠራት፣ ተገናኙ፡፡ ተፋቀሩ፡፡ ሄለንም እንደርሱ ተረግዛ ነው የተወለደችው፡፡ ዕድሜ ትበልጠዋለች፡፡ ቢሆንም በሰበብና በምሳሌ አሳምኖ ነው በእጁ ያደረጋት:: የነቢዩ መሐመድንና የከድጃን የትዳር ህይወት ጠቅሶ፡፡
ጸሃፊው ገጽ 25 ላይ እንዲህ ይለናል፡-
“ከድጃ አርባ ዓመት፣ ነቢዩ መሐመድ ደግሞ ገና ሃያ ዓመት፡፡ ፍቅር የማይሰራው ተዓምር የለም አየሽ!” ገባት፡፡ ደስ አላት፡፡
ሊጋቡም ወሰኑ፡፡
አንድ ቀን ተቀጣጥረው ሲጠባበቁ አረፈደች፤ ጠበቃት፡፡
ሔለን ምን ያህል እንደዘገየች ለማወቅ ሰዓቷን እየተመለከተች፣ በሱ አንፃር ለመሆን መንገዱን ስታቋርጥ፣ ጉዞዋም ሃሳቧም ድንገት ተቋረጠ፡፡
ኡኡኡኡኡኡ --
ወንድዬ ትዕይንቱን እስከ መጨረሻው መከታተል አልቻለም፡፡ መውደቋን አየ፡፡ ወደቀች፡፡ አንድ ጥንታዊ ፈላስፋ “ሞትና ሕይወት አንድ ናቸው” አለ:: ወዳጆቹም “ሞትና ሕይወት አንድ ከሆኑ ታዲያ ለምን አትሞትም” ብለው ጠየቁ፡፡ ፈላስፋው መለሰ፤ “ሞትና ሕይወት አንድ ስለሆነ ነው፡፡ “
የመሐመድ ነስሩ ታሪኮች እንደዚህ ናቸው:: የሃሳብ ክብሪት ይጭራሉ፣ ይነድዳሉ፣ ያበራሉ:: ከዚያ ከሰሉን ይጥሉታል፡፡ ከሰሉ ትዝታ ነው፣ ብርሃኑም ተስፋ፡፡
ለመጽሐፉ በርዕስነት የተመረጠው “ጥቁር ሽታ” በጣም ልብ ያንጠለጥላል፡፡ በጣም ልብን ይንጣል፤ ከአንዳች ምክንያት ኋላ ኋላ እያስሮጠ፣ በፍለጋ ያባትታል፡፡ ተራኪው የሚተርከው በአንደኛ መደብ አንፃር ነው፡፡ ግራ የተጋባ ገፀ ባህሪ ነው፡፡ “ቆንጆ ነኝ” እያለ ከንፈሩን፣ ዐይኑን፣ አፍንጫውን ሁሉ ይነግረናል፡፡ በሴቶች የተከበበ ጽጌረዳ መሆኑ ነው:: ይሁንና ያገኘሁትን ሁሉ አላፍስም፤ የማፈቅራት አንድ ፍቅረኛ ግን አለችኝ ይላል፡፡
ፍቅረኛው ረድኤት ናት፡፡ ረድኤት ቀይ ናት፣ ፀጉርዋ እንደ ቄጠማ ነው፡፡ ብቻ ቆንጆ ናት፤ ግን ከእኔ አትበልጥም ይለናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን በእጅጉ እንደሚወዳት ይናገራል፡፡ ቢሆንም ግንኙነቱን የሚያደፈርስበት ነገር አለ፡፡ ይህን ችግሩን እንዲህ ይገልፀዋል፡-
“ቤተሰቦቼም ሆኑ ጓደኞቼ አይረዱኝም:: ከጥቂት ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ በቀር ለማንም ነግሬው የማላውቀውን ምስጢሬን ልነግራችሁ ነው:: ከአርባ ምንጭ ወደ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝኩ ነበር:: አውቶቡሱ አዕምሮ በሚበጠብጥና አፍንጫ በሚበጥስ ሽታ ተበክሏል፡፡ ሁሉም አፍንጫውን ይዟል፡፡ ገሚሱ ያስነጥሳል፤ ሌላው ያስላል፤ የቀረው አፍንጫውን ይዳብሳል፡፡ ሽታው በጠበጠኝ፡፡ ጐንበስ ብዬ ጫማዬን አየሁ፡፡ አዲስና ንፁህ ነው፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ ሽታው የሚፈልቀው ከእግሬ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኜያለሁ፡፡
ጨነቀኝ፡፡
ያንን ሁሉ ኪሎ ሜትር ከመሸማቀቅ ብዛት ስኒ አክዬ፣ ከማፈር ብዛት ስኒ አክዬ፣ የጥፍሬ ቆሻሻን ቦታ ለመያዝ እየተመኘሁ፣ ጉዞዬን ቀጠልኩ፡፡ አፈርኩ:: አንገቴን ደፋሁ፡፡ ተጨነቅሁ፡፡ ሰውነቴ ላብ ማመንጭት ጀመረ፡፡ ላብ በላብ ሆንኩ፡፡ ከጭንቀት ብዛት አዕምሮዬ ተበጠበጠ፡፡ ጩህ ጩህ አለኝ፡፡ የተጫማሁት አዲስ ጫማ ነው፡፡ የለበስኩት አዲስ ካልሲ ነው፡፡ ታዲያ ይሄ ሽታ የሚመጣው ከየት ነው?... ግራ ገባኝ፡፡ ዛሬ ብቻ አይደለም፣ ሁሌም ግራ እንደገባኝ ነው፡፡--”
እንግዲህ ህይወቱ ይህ ነው፡፡ ፍቅረኛው ረድኤትንም ቀጥሯት ይሸሻል፡፡ ጫማዬ ይሸታል ብሎ ይሳቀቃል፡፡ ምክንያቱን ስለማይናገር ረድኤት ዕብድ ትሆናለች፡፡ ትናደዳለች፡፡ ተቀጣጥረው ሲገናኙ ብዙም ሳይቆይ ‹‹እንሂድ!›› ይላታል፡፡ ፊቷ በርበሬ ይመስላል፡፡
ቢሮም ውስጥ ቁጭ ብሎ በዚሁ ስሜት ይረበሻል::
“ቢሮ ቁጭ ብዬ የጫማዬ ሽታ ይረብሸኛል፣ የስራ ባልደረቦቼ ትኩረታቸው እኔ ላይ ነው፡፡ ወይም ይመስለኛል፡፡ ጫማዬንና ፊቴን እያፈራረቁ ያዩኛል:: ወይም ይመስለኛል፡፡ ሲንሾካሾኩ የሚንሾካሾኩት ስለ እኔ ነው፡፡ ወይም ይመስለኛል፡፡ ሲስቁ የሚስቁት በኔ ነው፡፡ ወይም ይመስለኛል፡፡--”
እንዲህ ግራ የሚጋባውና የሚሸማቀቀው ገጸ ባህሪ ጉዳይ ያሸማቅቃል፤ በተለይ ከረድኤት ጋር በዚህ የተነሳ የሚፈጥሩት ግጭት መጨረሻው ምን ይሆን? ያሰኛል፡፡ ጉዞው የት ያደርሰናል? የሚለው ምጥ፣ እስከ ታሪኩ መቋጫ ድረስ ይዘልቃል፡፡ ባንዲት ነጠላ ርዕሰ ጉዳይ ያባትለናል፡፡
የትኛውም የፈጠራ ሥነ ጽሑፍ አንዱ ግብ፣ ሰዎችን በሐዘንም መሀል ቢሆን ማዝናናት ስለሆነ፣ እያዘንን እንረካለን፣ እያማጥን ደስ ይለናል፡፡ በተለይ የረድኤት ጉዳይ ተስፋ እያስቆረጠ ሲመጣ፣ ነፋስ ቀልባችንን ይወስደዋል፤ የት እንደሚያደርሰንም አናውቅ!
አንድ ቀን፤
‹‹ምን መሰለሽ ረዲዬ…›› ሲላት
‹‹ተወኝ ባክህ!››
‹‹አንዴ አድምጭኝ ልንገርሽ››
‹‹ምንም የምትነግረኝ ነገር የለም››
ታክሲ አስቆመች፡፡
‹‹አለ---ብዙ የምነግርሽ ነገር አለ››
እያወራሁ ትታኝ ወደ ታክሲው ሆድ ገባች፡፡ በትካዜ እንደተዋጥኩ በእግሬ ማዝገም ጀመርኩ፡፡ እያዘገምኩ ደወልኩላት፡፡ አነሳችውና፡-
‹‹ምን ቀረህ ደግሞ!›› አለችኝ፡፡
‹‹በቃ በኔ ጨክነሽ ሄድሽ ረዲ… በኔ ጨከንሽ?››
‹‹አዎ›› ብላ ስልኩን ዘጋችው፡፡
ብዙዎቹ አጫጭር ታሪኮች፤ የህሊና ጥያቄ፣ የፍልስፍና ሀሳቦች፣ የሰው ልጅ ሕይወት መስመሮች ላይ የሚፈስሱ ናቸው፡፡ ትናንሽና  የሳሱ በሚመስሉ ነገሮች፣ ትልልቅ የሕይወት ግንዶች ተጠፍረው ያቃስታሉ፡፡ እንባ ውስጥ የተነከሩ ሳቆች ከንፈራቸውን ሲገልጡ፣ ሺህ የተስፋ ፍሬዎች ይበተናሉ፡፡ ደራሲው ጥሩ አይን፣ የበቃ ምናብ አለው፡፡ ከቆርፋዳ ህልም፣ የደነደነ ቡቃያ ያወጣል፡፡ ሜዳና ፈረሱን በሚገባ የተጠቀመበት ይመስለኛል፡፡ ቀለል ባለ፣ የሚያዝናና ትረካ መፍሰሱም፣ አንባቢን እንዳይሰለችና ከችክታ ማዶ ለማዶ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡       


Read 1115 times