Saturday, 31 August 2019 13:18

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)

 “የትኛውንም አገር ለማጥፋት የአቶሚክ ቦንድ ወይም ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አያስፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው የትምህርት ጥራትን ማውረድና ተማሪዎች ፈተና እንዲያጭበረብሩ መፍቀድ ብቻ ነው”
             
         “ሞት አልፈራም” ያለ አንድ ጆቢራ ተራራ ጫፍ ላይ ቆሞ፤ “ሞት የት ነው ያለኸው? ወንድ ከሆንክ ናና ሞክረኝ“ እያለ መጣራት ጀመረ፡፡ አያ ሞትም ፉከራውን እየሰማ ከልቡ ሲስቅና ሲዝናና ድንገት ትን አለው፡፡ ለሰከንድ ዓይኑ ተጨፍኖ ሲከፈት የጆቢራው ድምጽ የለም፡፡ ወደ ታች ሲመለከት ጆቢራው የሰንበሌጥ ዝንጣፊ መስሎ ታየው፡፡ ሞት አዘነ፡፡ አንድም በራሱ ዕድል፣ ሁለትም በደፋሩ ሰው መጨረሻ፣ ሶስትም በእግዜር ጣልቃ ገብነት፡፡ … ለምን?
***
ወዳጄ፡- “ዕውቀት ሃይል ነው” ስንል የማሰብ ጉልበታችንን ለራሳችን፣ ለአካባቢ ማህበረሰባችንና ለአገር በሚጠቅም ስራ ላይ ከዋለ ፍሬ ያፈራል፣ የስልጣኔ ግብዐት ይሆናል፣ ምድራችን ለነዋሪዎቿ ሁሉ የተሻለ ቦታ እንድትሆን ተፈጥሮን ያግዛል ማለታችን ነው፡፡ ዕውቀት ትምህርት ለመማር ዕድል ላላገኙት ወገኖቻችን ብርሃን ሊሰጥ፣ መንገድ ሊመራ፣ ኑሯቸውን ሊያሻሽል፣ ከተተበተቡበት አጓጉል ባህል፣ ዕምነትና ልማድ እያላቀቀ ራሳቸውን እንዲችሉና ከተራመደው የዓለም ህዝብ ወይም በሌሎች ቦታዎች ከሚኖሩት ወንድሞቻቸው ተራ እንዲቆሙ ካላደረጋቸው ወይም ለጦርነት፣ ለሌብነት፣ ለውሸትና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ከዋለ ወይም ግላዊና ማህበራዊ ባህሪያችንን በማረቅ “ሙሉ ሰው” ሊያደርገን ካልቻለ ችግር አለው፡፡ እኔ እንደሚመስለኝ የመጣንበት መንገድ ትክክለኛው መስመር (Path) አይደለም፤ የትምህርት ስርዓታችን ተሳስቷል፤ አገራችን ህልውናዋ ተሽመድምዷል፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ባለፈው እሁድ ዕትሙ፣ ርዕሰ አንቀፁን የጀመረው፣ አንድ የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ በር ላይ የተፃፈውን መቅድም ወይም ጥቅስ መግቢያ በማድረግ ነው፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
“የትኛውንም አገር ለማጥፋት የአቶሚክ ቦንድ ወይም ረዥም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አያስፈልግም፡፡ የሚያስፈልገው የትምህርት ጥራትን ማውረድና ተማሪዎች ፈተና እንዲያጭበረብሩ መፍቀድ ብቻ ነው” ይላል፡፡
ጥቅሱ መጻፍ የነበረበት ወይም ትክክለኛ ቦታው እዚህ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የትምህርት ጥራት መውረድ ሳይሆን “ድባቅ” የገባው፣ ፈተና መጭበርበር ብቻ ሳይሆን የሃሰት ማስረጃ አገሩን የሞላው፣ አዋቂ እንዳላዋቂ የተቆጠረው፣ አላዋቂ ሊቅ የሆነው እዚህ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በማወቅም ሆነ አለማወቅ፣ ሆን ተብሎም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች፣ አገራችን ውስጥ ውስጡን እንድትፈርስ፣ በተቋም ደረጃ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ የነበረው የትምህርት ስርዓት ዋነኛው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥፋትና በደል በትውልድ ላይ ሲፈፀም፣ “አገሬን አጣኋት” ይላሉ ሊቃውንት፡፡
የትምህርት ፖሊሲው የወጣቶቻችንን ዕድሜ ሰርቋል፣ አቅማቸውን አሳንሷል፣ የአገር አለኝታ የሚሆኑ ሳይንቲስቶች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ቴክኒዮሎጂስቶች፣ ኢንዳስትሪያሊስቶች እንዳይፈጠሩ ዕንቅፋት ሆኗል፡፡ በራሱ ጥረት ማንነቱን ያሳወቀው የ11ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው፣ የወልቂጤው “ኢዘዲን”ን ዓይነት የማሰብ ጉልበት ወይም ብሩህ አእምሮ ያላቸው ወጣቶችን ከተደበቁበት ፈልፍሎ እያወጣ፣ ራሳቸውን realized እንዲያደርጉ አላገዛቸውም፡፡ ብዙ ዕምቅ አቅም ባክኗል፡፡
ወዳጄ፡- የፖሊሲው ባለቤቶች ልጆቻቸውን የት እንደሚያስተምሩ ላንተ አልነግርህም፡፡ አሁንም “ዕጣ ፈንታህን የምንወስነው “እኛ” ነን፣ ተማር የምንልህን ተማር፣ አትማር የምንልህን አትማር” እያሉህ ነው:: …”ማሰብ” መቻልና አለመቻልህ ፈተና ላይ ነው፤ እናም በትክክል አስብ!!
ወዳጄ፡- ህዝብ እንደ ህዝብ የሚጋለጠው፣ አገርን እንደ ባለ አበባ ዳንቴል የሚያስውበው ወይም እንደ አይሁድ፣ የክርስትናና የሙስሊም አባቶች አናታቸው ላይ እንደሚደፉት ባለ ጌጥ የኪሮሽ ቆብ ዕውቀት የሚስፋፋውና የሚዳብረው፣ አንድ ሁለት ብሎ ጀምሮ፣ በጊዜ ሂደት፣ ህብር በፈጠረባቸው የሃሳብ ጥልፎች ነው፡፡ ጥልፉ የተቋጨበት የመጨረሻው ክር በደንብ ካልተቋጠረ ወይም ከመሃል ከተመዘዘ በቶሎ “mend” ማድረግ ግድ ይሆናል፡፡ አለበለዚያ አንዱ ሌላውን እየተከተለ በመጣበት መንገድ ወደ ኋላ ይተረተራል፡፡ ብዙ ጊዜ፣ ብዙ ድካምና ዕውቀት የፈሰሰበት ጥበብ፣ በጥቂት ደቂቃዎች ይበተናል፡፡
ወዳጄ፡- ብዙ የአገራችን ሊቃውንት እድሜያቸውን የገበሩባቸው ታላላቅና አስገራሚ የድርሰት፣ የታሪክና የጥበብ ስራዎች ከየቤተ መጻሕፍት፣ ከገደማትና ከመስጊዶች እየተለቀሙ ተቃጥለዋል፤ በወራሪዎች ተዘርፈዋል፡፡ የተረፉትም በውስጥ አዋቂዎች ተሰርቀው ለቅርስ ነጋዴዎች ተሸጠዋል፡፡ በጥንትም ዘመን አሲሮ ባቢሎኒያንስ፣ ቱርኮች፣ ባይዛንታይን ክርስቲያኖች፣ ሞንጐላውያንና የመሳሰሉት ጦረኞች እርስበርሳቸው በሚዋጉበትና በሌሎች ህዝቦች ላይ በዘመቱበት ወቅት የመጀመሪያ ተግባራቸው መጻሕፍትንና የጥበብ ቅርሶችን ማውደም ነበር፡፡ በአገራችንም እስከ ጣሊያን ወረራ ድረስ ተመሳሳይ ውንብድና ተፈጽሟል፡፡ አገራችንን አደናቁረዋታል፡፡ ወዳጄ፡- ዕውቀት የሌለው ህዝብ ባሪያ ነው፡፡ የሌሎች አስተሳሰብ ጥገኛ!!
የመንግስትና የህዝብ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች፣ ተፈጥሯዊ ችሎታቸውን እንዲያወጡ በማበረታታት ወደሚያዘነብሉበት የአካዳሚክስ ወይም የቴክኒክ ሙያ እንዲሰማሩ ከማድረግ ይልቅ በፕሮፓጋንዳ አለባብሰው ከአንዱ ዲሲፕሊን ወደ ሌላው በማዘዋወር፣ ስልጣን የያዘው ቡድን ወይም የፖለቲካ ፓርቲ በመረጠው መንገድ እንዲጓዙ ይገፋፏቸዋል፡፡ ሰባ ሰላሳ እንደሚባለው ዓይነት:: ምናልባት ለአንዳንዶች ይህን ማድረግ “በውጤት ላይ እስካተኮረ ድረስ ለአገር ጠቃሚ ነው” ብለው እንዲያስቡ ምክንያት የሚሆነው የጆን ዴዊ ዓይነት ፕራግማቲክ አስተሳሰብ ሊሆን ይችላል፡፡ በኛ አገር ሁኔታ  ውስጡ ሲፈተሽ ግን “ነገ” ላይ ያነጣጠረ ጉዳት ነበረው፡፡ ነገ ዛሬ ሆኖ አየነው፡፡
ለምሳለ፡- አንድ እውነተኛ (Original) ስዕል ተሰርቆ ወይም ተደብቆ በምትኩ ፍፁም ተመሳሳይ የሆነ “ኮፒ” በቦታው ይቀመጣል እንበል፡፡ ባለቤቱ ወይም በረቀቀ መሳሪያ ካልተመረመረ በስተቀር ማንም ሰው ዋናውንና ተመሳሳይ ወይም ፎርጅዱን አይለይም፡፡ በዓለም የስዕል ገበያ ይህን ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ የጥበቡን ምስጢር የሚያውቁ ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ኦሪጂናል ዕውቀት የፈሰሰበት፣ በብዙ ድካም የተሰራ ቅርስ አይገኝም!! እናም ወዳጄ፡- የአገርና የህዝብ ማንነትም በረቀቀ መንገድ ማለትም በሆነ ፍልስፍና ወይም “ሌላ” ነገር ሽፋን ሊደበቅ ይችላልና አስብ፡፡
ጥያቄው፡- “ዜጐች ናቸው ወይስ ማንዴት የሌላቸው ፖለቲከኞች የአገራችንን መፃኢ ዕድል የሚወስኑት? የሚል ነው፡፡ ወዳጄ፡- የሽግግር ጊዜ መሆኑን ልብ ማለት የሚያስፈልግ ይመስለኛል:: ትምህርት ሚኒስቴር እኮ ዘመኑ የሚጠይቀውን፣ አለም ያለችበትን ሁኔታ ያገናዘበ ጠቃሚ ግብዓት “ካለ” አልቀበልም አላለም፡፡ በሚጠቅመንና በማይጠቅመን ነገር ሁሉ እየተነታረክን፣ የሽግግሩ ዕንቅፋት መሆን በራሱ የዕውቀት ድህነት እንዳይሆንብን እናስብ፡፡ “ብልጥ ልጅ፤ በጁ የገባውን ይዞ ሲያለቅስ፣ የሞኝ ራት ግን ለቁርስ ይሆናል” ይባላል፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሞት ሲያዝናናውና ሲያስቀው የነበረው ጆቢራ በመውደቁ አዘነ ብለን ነበር፡፡ ሞት፤ ከስንትና ስንት ጊዜ በኋላ አንዴ ብስቅ እግዜር ተመቀኘኝ በማለት ነበር ዕድሉን ያማረረው፡፡ ለነገሩ ጆቢራው ከተራራው ላይ ሲወድቅ ስር ከነበረ ትልቅ ዋርካ ላይ ተንጠልጥሎ ህይወቱ ተርፏል፡፡ ጆቢራው ያላወቀው ነገር ግን ቆሞ የነበረበት ተራራ ሞት ራሱ እንደነበረ ነው፡፡ ለዚህ ነው ሞት እየተገረመ ሲስቅ የነበረው፡፡ ትን ብሎት ትከሻው ሲነቃነቅ ነበር አጅሬ የተንከባለለው፡፡ ከሞትም ዐዋቂና ደንቆሮ አለ እንዴ?
 በነገራችን ላይ “knowledge has its seats in the head;.. and can become the pilot of the soul” በማለት የፃፈልን ማን ነበር? ፕሌቶ እንዳትለኝና ደስ እንዳይለኝ፡፡
ሠላም!!

Read 647 times