Saturday, 31 August 2019 13:21

ከህትመት ዶሴ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  የፍቅርን ልክና ሚዛን የሚያውቀው ማነው?


          መጻሕፍትን መርምሮ ሀገርን ዞሮ ካላዩትና ከአልተገነዘቡት ምን ይሆናል፡፡ የመጻሕፍትን ጥቅም ሀገርን በማየት ያገኘው ሁሉ አለፍቅር መጻሕፍት ከንቱ ሆነው ይኖራሉ፡፡ ሀገሩንም ባዕድ እንደሚወስደውና ጥቅም እንደማይገኝበት የታወቀ ነገር ነው፡፡
በምሥራቅ መጨረሻ አገሮች ያሉት ሕዝቦች ወደ ሥልጣኔ ደረጃ እንድረስ፣ አውቀን እንደማናውቅ መስለን ለምን እንቀመጣለን ብለው፣ ወደ ውጭ አገር ሄደው፣ በየመሥሪያ ቤቱ ገብተው፣ የእውቀት ሥራ ተምረው ተመልሰው፣ ወደ ሀገራቸው ገብተው፣ ለሀገራቸው መጠበቂያና መክበሪያ፣ ለንጉሣቸው ማስኰሪያ ልዩ ልዩ የሆነ ዓይነት የንግድ ዕቃ ሠርተው አትርፈው ስለተገኙ፣ የውጭ አገር የሠለጠኑ ሕዝቦች ሁሉ እርስ በርሳቸው፣ ይህ ዕቃ ከወዴት መጣ? እንዴት ያምራል፣ እንግዛው ብለው ሲገዙት ይታያሉ::
እነኝህ ሰዎች የልዩ ልዩ ሕዝቦች የሥልጣኔ ሥራ (ብልሃት) ምን እንደሆነ ሄደው ዓይተው መርምረው፣ ለገበያ የተሠራውን የንግድ ዕቃ አብልጠው ሲሰሩ፣ ለሀገራቸው ብቻ መሆኑ ቀርቶ ወደ ውጭ አገር ልከው፣ ትርፍ ገንዘብ አግኝተው ተቀምጠዋል፡፡
ይህን ሁሉ ማድረጋቸው ምን ይሆን?
ባንዳንድ አገር ያሉት ሰዎች ከውጭ አገር የንግድ ዕቃ አስመጥተው፣ ለሀገሩ ሰው በውድ ሸጠው፣ እነሱም አትርፈው በልተው ጠጥተው በደስታ ያድራሉ፡፡ ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ የራሳቸውን ትርፍ ብቻ ነው እንጂ የሀገራቸው ሀብት ወደ ውጭ መሄዱን አያስታውሱም፡፡ ስለዚሁም ነገር ቢጠይቁዋቸው፣ እኔ የምፈልገው ለጥቅሜ ነው እንጂ ሌላ አልፈልግም ብለው ሲመልሱ ይገኛሉ፡፡
እነኝህም ሰዎች እንደ እንስሳ ያገራቸውን ገንዘብ ወደ ውጭ ወጥቶ መቅረቱን ሳያስቡ እኛ ብቻ እንጠቀም ብለው ማለታቸው በጣም ያስገርማል፡፡
ወንድ ልጅ ለቤቱ ዳኛ፡፡ ውሻ ለመንደሩ ዘበኛ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ ደህና ሰው ከቤቱ አትርፎ ለጐረቤቱ ይሰጣል፡፡ ውሻም በመንደሩ አውሬ ሲከላከል የሩቁን መንደር ከብት ያድናል:: የሰማይና የምድር ንጉሥ ቸሩ ፈጣሪ አምላካችን፣ እኛን ፍጡሮቹን ከሞት ወደ ሕይወት ለመመለስ ሲል ብዙ መከራና ስቃይ ተቀብሎ እስከ መሰቀል ደረሰ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ መድኃኒት እንዲሆን እስከ መሰቀል በመድረሱ የመላው ዓለም ሕዝብ በደሙ ዳነ፡፡ የካደው ይሁዳ አስቆሮታዊ አፍቃሪ ተብሎ የነበረው ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ቡቃያ እንደዘሩት ነውና ተከትለውት ብዙዎች ወደ ጥፋት ጐዳና ሲመሩ ይገኛሉ፡፡
የጀርመን መንግሥት ፕረሲዳንና ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሴ ሂትለር፣ በሀገራቸው ውስጥ የነበሩትን አታላይ ሰዎች ማስወጣታቸው ሃገራቸው ታፍራ፣ ሕዝባቸው ተከብሮ እንዲኖር ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ የሀገር ፍቅር ምን እንደሆነ ልክና ሚዛን እንደሌለው ለማስረዳት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በመካከላቸው እበላ ባይ ገብቶ እንዳያጣላቸው የጀርመን ዘር ከሌላ ዘር እንዳይደባለቅ በጣም የተስማማ ደምብ አወጡ፡፡ ይህም ደምብ የፍቅር ሰዋሰው ምን እንደሆነ የሚገልጽ ነው፡፡
የጀርመን መንግሥት ፕረሲዳንና ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሴ ሂትለር፣ ሀገራቸው በገንዘቡዋና በኢኮኖሚክ ጉዳይዋ በኩል ባእድ ገብቶ እንዳያበላሻት ብለው በየጊዜው በሚሰሩት ሥራቸውና በንግግራቸው እንዳሳዩ ናቸው፡፡ አሁን በቅርቡም ሃገሬን ሰው አይንካት፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋራ በማናቸውም በኩል እኩልነት እንድታገኝ እፈልጋለሁ ብለው ለመላው ዓለም መንግሥታት አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ሁሉ መሥራታቸው ያገራቸውና የሕዝባቸው ፍቅር በልባቸው ስላደረባቸው ነው እንጂ በተለይ ለራሳቸው ጥቅም ብለው አይደለም፡፡
ጀርመን የሚባሉ ሕዝቦች በአሥራ ስድስት ወገን ይከፈላሉ፡፡ እነኝህ አሥራ ስድስት ወገኖች ዘራቸው ጀርመን ስለሆነ በአንድ ገዢ ተገዝተው ይኖራሉ:: በየወገናቸውም በተለይ አገረ ገዢ ያላቸው ናቸው እንጂ የኔ ወገኔ ይህ ነውና ከእገሌ ወገን ሆኜ አልሠራም ወይም ጠላት መጥቶበታልና አልረዳውም ብሎ አይልም፡፡ ጠላት በመጣባቸው ጊዜ ባንድ ልብና ባንድ ሐሳብ ሆነው የመንግሥታቸውን ጥሪ ሰምተው ካሉበት ይመጣሉ፡፡ ይህን ሁሉ ማድረጋቸው ያገራቸውን ፍቅር የራሳቸውን ነጻነት የወገናቸውን ክብረት አጥብቀው ስለሚፈልጉ ነው፡፡
ዛሬ ኢጣልያ፣ ኢትዮጵያ ተብላ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኘችውን ክብር ለማጥፋት መጣች፣ መጥታም ያንድ አባትና ያንድ እናት የሆኑትን ሕዝቦች ለማለያየት አጉል ስብከቱዋን ስትሰብክ ትገኛለች፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደምም አሁንም ዛሬ ከውጭ አገር የሚመጡትን ሰዎች አክብራ አስተናግዳ በሰላም ወደ ሀገራቸው ከመመለስ በተቀር እንግዳ አዋርዳ አታውቅም፡፡   
(ምንጭ፡- አዕምሮ ጋዜጣ፤ መጋቢት 13 ቀን 1928 ዓ.ም)


Read 639 times