Saturday, 31 August 2019 13:20

ስውርስፌት (የአጭር አጭር ልቦለድ)

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(12 votes)

  በተቀመጥኩበት ሁሉ በሀሳብ ጭልጥ የምልበት ሁኔታ  ዘወትር ግራ ያጋባኛል፡፡ ዛሬም የሆነው ይኸው ነው፡፡ የተቀመጥኩበት ወንበር እንደሁ ምቾት የለውም፡፡ ነገር ግን ቦታው እጅግ ሸለቆ የበዛበት በመሆኑ፣ የህይወትን ጠመዝማዛ መንገድ ይወክላል:: ሆኖም ጉዞ ነውና  እያደር ይመሻል፤ ኑሮ:: ለእኔ ግን ከባዱ ነገር ጥቅጥቁ ጨለማ  ሳይሆን  ሸለቆው ነው:: ከተወረወሩ የማይመለሱበት አዘቅት:: ጨለማ በብርሃን መተካቱን ደጋግመን ስለታዘብን ከመጤፍ አንቆጥረውም፡፡ ኸረ እንዲያውም... ተፈጥሮ እራሷን የምታድሰው በጨለማ ይመስለኛል:: ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ኢትዮጵያዊያን ጨለማን ከዝምታ ጋር የሚያመሳስሉት፡፡ አንድም ስውር ሂደት በመሆኑ፣ ሁለትም ፀጥ እረጭ  ያለ በመሆኑ ለቁጥጥር ያስቸግራል፤ ብርቱ ነው፡፡
እኔ ግን ፈላስፋና ጨለማ አንድ ናቸው --- እላለሁ፡፡ ጥልቅ ናቸውና፤ ብርቱ ናቸውና፤ ሁሉንም ውጠው የማይጮሁ በመሆናቸው ይከብዳሉ:: ታዲያ ...ሳስበው፣ ሳስበው በጨለማ ውስጥ ብርሃን እንዳለ ሁሉ በዝምታ ውስጥም ጩኸት አለ፡፡ የጩኸት መጨረሻው ዝምታ ሲሆን የዝምታ መጨረሻው ግን ፀጥታ ነው፡፡ የሰውም ልጅ ለዚህ ተፈጥሯዊ ህግ ተገዥ በመሆኑ  እስረኛ ነው፡፡ ለስጋውም ለነፍሱም ሰላም፣ ፀጥታ ያስፈልገዋል:: የነገሮች ምንጭ ፀጥታ ይመስለኛል፡፡ ህይወት እራሷ ከዝምታ ወደ ዝምታ ዓለም የሚደረግ ሽግግር ሳይሆን ይቀራል? የሚገለጠውም በሞትና በልደት ይመስለኛል፡፡ ከፍፁም ዝምታ ወጥተን ፍፁም ጫጫታ  ውስጥ ኖረን፣ ተመልሰን ፍፁም ዝምታ ውስጥ እናርፋለን:: በርግጥ ዝምታም፣ ጫጫታም ዓለማችን ነው፡፡ የሚጎላው ዝምታ ነው፤ ዘላለማዊ፡፡ በጫጫታ መሃል ዝምታን እንፈልጋለን፤ አግኝተነው ግን አናውቅም:: ለዚህም ነው፤ ጥበብ ውስጥ የምንዘፈቀው፤ ያጣነውን ፍለጋ፡፡ እውቀትም እንዲሁ ነው፡፡ ጭምብል ናቸው፤ ቃሬዛ፡፡ ተፈጥሯችን ዝምታ በመሆኑ ጩኸት ያቅበጠብጠናል፡፡ ያሰክረናል፡፡
በርግጥ ይህ የተፈጥሮ ባህሪ በመሆኑ፣ የህልውናዋ ምንጭ ነው፡፡ ማንም የተፈጥሮ አካል ከዚህ ባህሪ ውጭ መሆን አይችልም፡፡ አይችልም ማለት ደግሞ አገልጋይ ነው፤ ማለት ነው፡፡ ማገልገሉ ለእራሱም ሆነ ለተፈጥሮ ህልው መሆን አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉም የእራሱን ሚና ተጫውቶ ያልፋል እንጂ ሂደቱን ማቆም አይችልም፡፡ ልክ እኔ፤ ይህን ሀሳብ አለማሰብ እንደማልችለው፤ አይነት፡፡ ከማሰብ ውጭ አማራጭ አልነበረኝም፤ ከመፃፍም እንደዚሁ:: ሁሉም ወቅቱን ጠብቆ ይሆን የለ?...እንደዛ፡፡
በርግጥ ይህን ሁሉ ከማሰቤ በፊት ጭንቅላቴን ያሳክከኝ ነበር፡፡ የረገፉ ፀጉሮች ምስክሬ ናቸው፡፡ በጣም... አቅበጥብጦኝ ነበር፡፡ ፀጥታ በሚመስል፤ ግን ...ጩኸት በበዛበት ሂደት ውስጥ እንደነበርኩ አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንዴ ከጎኔ ያለችው ቡችላ ብታናጥበኝም፣ የተሰማኝን እያጣጣምኩ ነበር፡፡
የሚመስለኝ በህይወት እያለን፣ የጩኸቱን ልክ ማጣጣም እንጂ ዝምታን አናውቀውም፡፡ ወዳጄ ...ሰው ዝምታ ውስጥ ነኝ ቢልህ እንዳታምነው ፤ ዝምታ ከጩኸት በኋላ ነችና፡፡ እስኪ አስበው ... የስሜት ህዋሳቶች እያሉን ዝም የምንል ይመስልሃል? ለነገሩ በዝምታ ትርጉም ላይ  መስማማቱ ይቀድማል ለካ...እ...ወይ ጉድ፡፡ ታዲያ ከህይወት ዳገት ይልቅ ጨለማን መሻገር የሚቀል አይመስልህም?
***
ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፦  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3161 times