Saturday, 31 August 2019 13:48

ምርቃት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

(… አይነቱ ብዙ ነው)
ለማኙ ይመርቅሃል፡፡ አሮጊቷ ይመርቁሃል፡፡ ሆቴል ተከፍቶ ይመረቃል፡፡ ከኮሌጅ ትመረቃለህ፡፡ የደሞዝ ቦነስ ይመረቅልሃል፡፡ ቅቅል በልተህ የመረቅ ጭማሪ ታስመርቃለህ፡፡
በገጠር ሰዎች ስም የሚሸቅል አንድ ጩሉሌ የዕርዳታ ድርጅት ደግሞ የደከመ የቦኖ ውሃ ያሰራል:: ከዛም የወረዳው አስተዳዳሪ በክብር እንግድነት ተጋብዞ፣ ከፊት ተቀምጦ፣ ወደ መድረክ ቀርቦ፣ ስለ ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ ስለ መልካም አስተዳደር ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ ሰላማዊ ምርጫ፣ ስለ ጸረ ሰላም ኃይሎች፣ ስለ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ስለ በጥልቀት መታደሰ አልተገናኝቶ ነገር ለፍልፎ፣ በአጀብና በጭብጨባ ቦኖው ወዳለበት ቦታ ሄዶ፣ የባህል ቀሚስ ከለበሰች ጩጬ ልጅ መቀስ ተቀብሎ፣ የጩጬዋን ጉንጭ አገላብጦ ስሞ፣ ሪባኑን ሁለት ቦታ ቆርጦ፣ ቧንቧውን ከፍቶ ውሃውን ቀምሶና ሕዝቡን አስጨብጭቦ ቦኖውን ይመርቀዋል፡፡
ደሞዝ የማይበቃቸው፣ ኑሮ ያካለባቸው አራት የኢቲቪና አዲስ ዘመን ጋዜጠኞች ዳጎስ ያለ ውሎ አበል ተከፍሏቸው ይመጡና፣ ነገርየውን እንደ ትልቅ ልማታዊ ዜና አካብደው ይዘግቡታል:: መጨረሻ ላይ 47 ገጽ የሚሞላው Evaluation Report በExternal Consultant  ተረቅቆ ‹‹በዚህ ቦኖ መሰረት ሳቢያ ሆዱን የሚያመው አበሻ በ16% ቀነሰ፣ ሴቶች ታጥበው ቀሉ ወደ ጅረት ወርደው ውሃ የሚቀዱበት ሰዓት ስላጠረላቸው ጤና ጣቢያ ሄደው መውለድ ጀመሩ፤ ሕጻናት ወፈሩ፣ Climate Changeን ለመከላከል በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ፈጠረ…›› ምናምን የሚል ጆካ ሪፖርት ተጽፎ፣ ሴቶችና ሕጻናት ውሃ ጠጥተው ፈገግ ሲሉ የተነሱት ፎቶ ተጨምሮበት ለፈረንጅ ይላካል፡፡
(ይሄኛው ምርቃት ግን የተለየ ነው)
***
ልጅቷ አንድ የግል ኮሌጅ ውስጥ ሰቃይ የነርሲንግ ተማሪ ነበረች፡፡ Bird Chick ያስባሏት 3 ነገሮች አሏት፡፡ ቀይ ነች፡፡ ከኋላ ነፍፍ ነገር ነች፡፡ ቦርጭ የላትም፡፡ ሌላው ውብቷ የቦዲ፣ የቃርያ ጅንስ፣ Victoria’s Secret ሊፕ ግሎስ፣ ከፓኪስታን ወይዘሮ ጭንቅላት ላይ ተቆርጦ የመጣ Human Hairና ፊቷ ላይ የለደፈችው የFair and Lovely ክሬም ድምር ውጤት ነው፡፡
(…እንደ ዱሮ ደራሲ ልብን የሚያርደው፣ ብርሃን የሚረጨው፣ አሎሎ መሳይ ኩሩው ዓይኗ፣ ሰልካካው አፍንጫዋ፣ የሮማን ፍሬ የሚመስለው ዲምፕላሙ ጉንጯ፣ እንደ ሲዳማ በቆሎ እሸት መጠንና ቅርጹን ሳይስት የተደረደረው ሃጫ በረዶ የመሰለው ነጭ ጥርሷ፣ እንደ ብስል እንጆሪ ብሉኝ፣ ብሉኝ ግመጡኝ ግመጡኝ የሚለው ከንፈሯ፣ ጥቁረቱ ሃርን የሚያስንቅ፣ ጀርባዋ ላይ ተዘናፍሎ እንደ ዘንዶ የተጠመለለው ጸጉሯ እንደ ታንክ አፈ ሙዝ ቀጥ ብለው የተሰደሩት ጡቶቿ… ምናምን ብለን እንዘግባት እንዴ?)
የማታ እየተማረች የቀን አንድ የግል ሆስፒታል ውስጥ በተለማማጅነት ገብታ መስራት ጀመረች:: በሥራም፣ በቅልጥፍናም፣ በተግባቢነትም እሳት የላሰች ስለነበረች እንደተመረቀች እዛው አስቀሯት፡፡ የማታ የዲግሪ ትምህርቷ ቀጠለች፡፡ ታማሚውም፣ አስታማሚውም፣ አካዳሚውም ሁሉም የሚወዷት ጎበዝ ነርስ ሆነች፡፡ ‹‹ካይን ያውጣሽ›› ተባለች፡፡
ለሶስት ዓመታት ከሰራች በኋላ ‹‹በቃኝ›› ብላ ሥራ አቆመች፡፡ የሥራ ልምድም ሳትጠይቅ፣ ቻውም ሳትል ጥላ ጠፋች!
***
ሥራዋን ለቅቃ ከጠፋች በኋላ በስድስተኛው ወር ወደ ሆስፒታሉ ሄደች፡፡ ሃኪሞቹን በምሳ ሰዓት ላይ የሚበሉበት ካፌ ውስጥ አገኘቻቸው፡፡
‹‹አንቺ አለሽ እንዴ?››
‹‹ስልክ አታነሺም?››
‹‹ትገርሚያለሽ!››
‹‹እንዴት ነሽ ግን?››
‹‹ጠፋሽ››
‹‹ተስማማሽ››
ምናምን ተባባሉና ለምን ሥራ እንደለቀቀች፣ አሁን ምን እየሰራች እንደሆነ ጠየቋት፡፡ ‹‹አሁን በግሌ እየሰራሁ ነው - አሪፍ ነገር ጀምሬያለሁ፡፡››
‹‹ምን?››
‹‹አትላስ አካባቢ ጫት ቤት ከፍቻለሁ:: በጣም ቢዝነስ አለው፡፡ አሁን ለምዷል፡፡ ግን ገና አልተመረቀም፡፡ እናም ቅዳሜ ከሰዓት ጀምሮ መጥታችሁ እንድትመርቁልኝ ልንገራችሁ ብዬ ነው የመጣሁት›› አለችና ለያንዳንዳቸው የምረቃ ጥሪ ካርድ አደለቻቸው፡፡
(ደርቀው ቀሩ!)
አንዱ የገባው ዶክተር ‹‹ያዋጣል ብለሽ ነው?››
‹‹ቀላል! ፀዳ ያለ ሰው ነው እሚመጣበት፡፡ በክላስ የሚቅሙ ነጋዴዎችና ኮንትራክተሮች አሉ፤ በጣም ቢዝነስ አለው፡፡ ኪራዩ ትንሽ ውድ ነው፤ በወር ሰላሳ ሺ ብር ነው የተከራየነው፡፡ አንድ እዚህ ሲታከም ከተዋወቅኩት ሰውዬ ጋራ ነው በሼር አብረን የከፈትነው፡፡ ግን ገበያ አለው፤ ሺሻው ብቻ ኪራዩንና የሰራተኞችን ወጪ ይችላል፡፡”
‹‹እና ህክምናውን ተውሽው!›› ጠየቋት - ሽማግሌው ሀኪም፡፡
‹‹ውይይይ ዶክተርዬ፤ ሁሌ በሽተኛ ማየት አይደብርም? ኑሮ ራሱኮ በሽታ ነው! በዛ ላይ የሰው አመል እንኳንስ ታሞ እንዲሁም አልተቻለም፡፡… እኔ ድሮም ፈታ ያለ ነገር ነው እሚመቸኝ፡፡ ጭንቀታም ፊት አልወድም፡፡ … ደሞ ደሞዙስ? ደሞዝ ነው እንዴ? አንተ እራስህ መች አለፈልህ? ያንን ሁሉ አመት ተምረህ ተምረህ፣ ስንቱን በሽተኛ ፈውሰህ አድነህ ምን ተረፈህ? ስም ብቻ እኮ ነው የተረፈህ::… ሰው ቁጭ ብሎ ስልክ ብቻ ተደዋውሎ፣ አየር ባየር  ከብሮ ያድራል፡፡ አንተ የሰው ሆድ ቀድድህ እየሰፋህ፣ ‹ዳነልኝ ወይንስ ሞተብኝ?› የሚል ጭንቅ ነው የተረፈህ፡፡››  
የሥራ ሰዓት ደረሰ፤ ተለያዩ፡፡… ሃኪሞቹ ከራሳቸው ጋር መሟገት ጀመሩ፡፡
(ከኢዮብ ምህረትአብ ዮሐንስ
 “ቼ በለው!” መጽሐፍ የተቀነጨበ)

Read 3223 times