Saturday, 31 August 2019 13:46

“Á ዶላር” ስታንድ አፕ ኮሜዲ ሾው ዛሬ ይካሄዳል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

 “Á ዶላር” የሚል ስያሜ የተሰጠው የወጣቱ ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ ልዩ የስታንድ አፕ ኮሜዲ ሾው፣ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓትና 11 ሰዓት ላይ ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በሚገኘው አዶት ሲኒማ ይካሄዳል::
ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ “Á ዶላር” የስታንድ አፕ ኮሜዲ ሾው በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑና ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ የኮሜዲ ስራዎች የሚቀርቡበት ሲሆን፣ አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ያህል እርዝማኔ ይኖረዋል፡፡
የ“Á ዶላር” ስታንድ አፕ ኮሜዲ ሾው የመግቢያ ዋጋ 100 ብር ሲሆን፣ ትኬቱ በጌቱ ኮሜርሻል 1ኛ ፎቅ ብራይት ካፌ እና ሬስቶራንት፣ በደምበል ሲቲ ሴንተር ግራውንድ ፍሎር ዩቱ ካፌ፣ በአቻሬ ጫማ፣ በጎተራና ሳሪስ አዲስ ሰፈር አጎና አቤል ሲኒማ እየተሸጠ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጥናት ላይ የተመሰረቱ፣ በቂ ዝግጅት የተደረገባቸውና በይዘት የዳበሩ የኮሜዲ ስራዎችን በአዲስ አይነት አቀራረብ ይዞ በመምጣት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውቅናን ለማትረፍ የበቃው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ፣ ከዚህ ቀደምም “ዘመነ ፍሰሃ” እና “ነግ በኔ” የተሰኙ ሁለት አነጋጋሪና ተወዳጅ የስታንድ አፕ ኮሜዲ ሾዎችን ለተመልካች ማብቃቱ ይታወሳል፡፡
በ2003 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትያትር ጥበባት በማዕረግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘውና በ2006 ዓ.ም “ጣዝማ ማር” በሚል ርዕስ ባቀረበው የስታንድ አፕ ኮሜዲ ከህዝብ ጋር የተዋወቀው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ፣ በዛሬው ፕሮግራሙ ተመልካቾችን ለማርካት ወራትን የፈጀ ዝግጅት ማድረጉን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጧል፡፡

Read 829 times