Saturday, 07 September 2019 00:00

በቀጣዩ አመት ኢትዮጵያን የምግብ እጥረት ሊፈታተናት ይችላል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

• ከ8 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ለድርቅ አደጋ ይጋለጣሉ
                   - የነሐሴ ወር የዋጋ ግሽበት የዓመቱ ከፍተኛው ነው ተብሏል

         የበልል ዝናብ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ በሶማሌ፣ ምስራቅ ኦሮሚያና ሰሜን አፋር አካባቢዎች እስከ ቀጣዩ ጥር ወር 2012 ድረስ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚጋለጡ የአለም የምግብ ፕሮግራም አስታወቀ፡።
የአለም የምግብ ፕሮግራም ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህ የበልግ ዝናብ ካጠራቸው አካባቢዎች በተጨማሪ በአንዳንድ የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ኦሞ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ የጣለ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ፣ የሰብል መውደምና የእንስሳት ሞትን ማስከተሉን በመጠቆም አካባቢዎቹ በቀጣይ አመት በሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ይቆያሉ ብሏል፡፡ የአርብቶ አደሮች አካባቢ በሆኑ የደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና ደቡብ ክልል ከሚፈለገው በታች የሆነ ዝናብ መመዝገቡን በመጠቆም አካባቢዎቹ በቀጣይ አመት ለከፋ ድርቅ ሊጋለጡ ይችላሉ ብሏል፡፡
በአጠቃላይ በ2012 ዓ.ም 8.1 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን ለድርቅ አደጋ እንደሚጋለጡና ቀጥተኛ ድጋፍም እንሚፈልጉ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በከተሞች አካባቢ የምግብና ምግብ ነክ ግብአቶች ዋጋ በየጊዜው ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ በቀጣይ የኢትዮጵያ ፈተና የምግብ እጥረት ሊሆን ይችላል ብሏል፡፡  
መንግስት በበኩሉ፤ የምግብ እጥረቱን ለመቋቋም ከወዲሁ ከውጭ አገር ስንዴ ገዝቶ በማስገባት ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ የነሐሴ 2011 የኑሮ ውድነት መጠን የአመቱ ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል፡፡ የነሐሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት መጠንም 17.9 በመቶ መሆኑን ማዕከላዊ እስታትስቲክስ የጠቆመ ሲሆን ይህ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲመሳከር በ23 በመቶ ማሻቀቡ ተመልክቷል፡፡ ካለፈው የሐምሌ ወር አንጻር ደግሞ የ2.4 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ጤፍ፣ ገብስ፣ ማሽላና በቆሎ በየወሩ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገባቸው ሲሆን ቀይ ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርትም በነሐሴ ወር የተጋነነ ዋጋ ያስመዘገቡ ሆነዋል፡፡


Read 870 times Last modified on Monday, 09 September 2019 10:18