Print this page
Saturday, 07 September 2019 00:00

የደቡብ አፍሪካ መንግስት የመጤ ጠልነት ጥቃትን እንዲያስቆም የኢትዮጵያ መንግስት አሳስቧል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   ሁለት ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ተጠቁሟል

            በደቡብ አፍሪካ ከመጤ ጠልነት ጋር በተገናኘ ከሚፈጸመው ጥቃትና ዘረፋ ንብረታቸውን ለመታደግ ሲሯሯጡ የነበሩ ሁለት ኢትዮጵያውያን በመኪና አደጋ መሞታቸው የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እንዲሁም የአገሬው መንግስት ጥቃቱን እንዲያስቆም አሳስቧል፡፡
ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በንብረታቸው ላይ ጥቃት እየተፈፀመ መሆኑን በሰሙበት አጋጣሚ ተሽከርካሪያቸውን አስነስተው ወደ ሌላ ቦታ በመሸሽ  ላይ ሳሉ፣ መኪናቸው ተገልብጣ መሞታቸው የተጠቆመ ሲሆን ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ንብረት መዘረፉና መውደሙም ታውቋል፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን ከጥቃቱ ለመዳን ንብረታቸውን ሜዳ ላይ ጥለው በየቤታቸው ተደብቀው እንደሚገኙ ነዋሪነታቸውን በደቡብ አፍሪካ ያደረጉ ግለሰቦች ለአዲስ አድማስ የተናገሩ ሲሆን መንግስት ሕይወታቸውንና ንብረታቸውን ከጥቃት እንዲታደጋቸው ተማጽነዋል፡፡  
በአለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ባለፈው ረቡዕ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀኑት  ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፤ ከትናንት በስቲያ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን መንግስታቸው ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ባለሥልጣናት ጋር በጉዳዩ ላይ እየተወያየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  
በዚህ ጥቃት የበርካታ ኢትዮጵያውያን የንግድ መጋዘኖችና መደብሮች መዘረፋቸውንና መቃጠላቸውን ኢትዮጵያውያኑ ለፕሬዚዳንቷ ያስረዱ ሲሆን የዘንድሮው ጥቃት ከዚህ በፊት ከነበረው ይልቅ ኢትዮጵያውያን ላይ ያነጣጠረ  መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የዘንድሮው ጥቃት በእጅጉ አደገኛና አስጊ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለጹት ኢትዮጵያውያኑ፤ የኢትዮጵውያን ቤተ እምነቶችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል  ብለዋል፡፡
በዚህ የደቡብ አፍሪካውያን መጤ ጠል ጥቃት በርካታ ዜጎቿ የተጎዱባት ናይጄሪያ፣ ከሐሙስ ጀምሮ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ያቋረጠች ሲሆን  የማላዊ፣ ዚምባቡዌ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ መንግስታት በበኩላቸው፤ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ጥቃቱን በመቃወም  ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡

Read 5215 times