Saturday, 07 September 2019 00:00

መንግስት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንድነትን የሚፈታተን አካሄድ እንደማይቀበል አስታወቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተን አካሄድን መንግስት እንደማይቀበል ትናንት ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር በጽ/ቤታቸው የተወያዩት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ 40 ያህል የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ችግሮች ላይ ከጠ/ሚኒስትሩና ምክትላቸው ጋር መወያየታቸው የታወቀ ሲሆን ውይይቱም በመግባባት መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች ለጠ/ሚኒስሩና ምክትላቸው ከቀረቡላቸው አቤቱታዎች መካከል  በየቦታው የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠልና የምዕመናን መሳደድ አሳሳቢ መሆኑ፣ በዚሁ ቃጠሎ ለተጎዱ አብያተ ክርስቲያናትና ለተፈናቀሉ ምዕመናን ተገቢውን ካሳ መንግስት እንዲከፍል፣ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ለተፈፀመው ጥፋትና በደል መንግስት ተገቢውን እውቅና ሰጥቶ ይቅርታ እንዲጠይቅ እንዲሁም በቀጣይ መንግስት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተናዊ ደህንነት እንዲያስጠብቅ የሚሉት ዋነኞቹ መሆናቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት በሚፈታተን መልኩ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እናቋቁማለን የሚለውን አካሄድ መንግስት እንዲያስቆም አቤቱታ ቢቀርብለትም በቸልታ መመልከቱን በመጥቀስም፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጠንካራ ጥያቄ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለእነዚህ አቤቱታዎች ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትሩ “ቤተ ክርስቲያንን መንግስት አላቃጠለም፤ ምዕመኗም እንዲሰደዱ አላደረገም፡፡ ነገር ግን በቀጣይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን ይወጣል” ማለታቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት የሚፈታተን ነገርም እንዲፈጠር መንግስታቸው እንደማይፈቅድና ቤተ ክህነትም ጉዳዩን በውስጥ አሰራሯ እንድትፈታው ጠ/ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ ‹‹ኦርቶዶክስ ተዋህዶ በምንም መንገድ አትከፈልም፣ በአንድነቷ ላይ የሚመጣ ሁሉ ድፍረት ነው፣ ተቀባይነት የለውም›› ማለታቸውን ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
የእሳቸውም ሆነ የመንግስታቸው ፍላጎት የተጠናከረች፣ ለአገር ግንባታ የሚቻላትን ሁሉ የምታደርግና አንድነቷ የተጠበቀ ቤተ ክርስቲያን ማየት መሆኑን የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ የኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት መጠናከርና አንድነት ጥቅሙ ለአገርም ጭምር ነው፤› ብለዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችም በለውጥ ሂደት እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች አካል መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ ገልፀው፤ በቀጣይም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መንግስት ከቤተ ክህነት ጋር በመተባበር መፍትሄ እንደሚያበጅ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከትናንት በስቲያ ሀሙስ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ላይ በመገኘት መንግስታቸው የቤተ ክርስቲያንን መከፋፈል እንደማይፈቅድ መግለፃቸውም ታውቋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ እያጋጠሟት ባሉ ወቅታዊ ችግሮችና ትናንት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገውን ውይይት አስመልክቶ በዛሬው እለት ቅዱስ ሲኖዶሱ ለጋዜጠኞች መግለጫ እንደሚሰጥም ለማወቅ ተችሏል፡፡     
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት መቋቋምን ለመቃወም ለመስከረም 4 ቀን 2012 ሰላማዊ ሰልፍ እያዘጋጁ ከነበሩ የአዲስ አበባ መንፈሳዊ ማህበራት ጋር የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በተመሳሳይ ሐሙስ እለት ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡ ማህበራቱ በቤተክርስቲያኗ ላይ ከተለያዩ ወገኖች እየደረሰ ያለው ጫና እንዳሳሰባቸው አስረድተው መንግስት በአፋጣኝ እልባት እንዲያበጅ ጠይቀዋል፡፡ ም/ከንቲባውም መንግስት አስፈላጊውን የእርምጃ  እርምጃዎች እንደሚወስድ አስገንዝበዋል፡፡
የኦሮሚያ ቤተ ክርስቲያን የማቋቋምን አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ቀሲስ በላይ መኮንን እና ባልደረቦቻቸው በበኩላቸው የቤተክርስቲያኒቱን ቅዱስ ሲኖዶስ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንዲቋቋም ለቀረበው ጥያቄ እስከ መስከረም 30 ቀን ምላሸ እንዲሰጥ በጋዜጣዊ መግለጫ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡

Read 7081 times