Print this page
Sunday, 08 September 2019 00:00

በአዲሱ ዓመት የአስተሳሰብ አብዮት

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(0 votes)

  ቀደም ሲል ካቀረብኳቸው ጽሁፎቼ በአንዱ ውስጥ “የአስተሳሰብ አብዮት ባልተደረገበት ሁኔታ የልማት፣ የዴሞክራሲና የፖለቲካ አብዮታችን የተሳካ ሊሆን አይችልም፡፡ ምን ዓይነት አብዮት ያስፈልገናል በሚለው ላይ ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ” የሚል ሃሳብ ማስፈሬን አስታውሳለሁ፡፡ ቃሌን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ለዚህ ላለንበት ወቅት ከሚያስፈልጉን አንገብጋቢ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ የአዲስ ዓመት መልእክት ማስተላለፍ ፈለግሁና  ይቺን ማስታወሻ ከተብኩ፡፡
መቼም በአብዮት ካልሆነ በተረጋጋ መንፈስ ስራ መስራት አልቻልንም አይደል… ለማንኛውም፣ መግባባትን ለመፍጠር ይቻል ዘንድ ከቃሉ ትርጓሜ እንነሳ፡፡ “የባህል አብዮት” ማለት “መንግስት የሀገሩን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ እሴቶች በፈጣንና ስር-ነቀል በሆነ ሁኔታ ለመለወጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነው” የሚል በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው ትርጉም እንዳለው የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡
በዓለም የታሪክ ሰሌዳ ላይ “በአብዮተኛነት” የተመዘገቡና “ቀንደኛ አብዮተኛ” ተብለው የሚታወቁ ግለሰቦች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፤ ቼ ጉቬራ፣ ፊደል ካስትሮ፣ ካርል ማርክስ፣ ቭላድሚር ሌኒን፣… ተጠቃሽ መሆናቸውን አንዳንድ ሰነዶች ይነግሩናል፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ሶሻሊስት አብዮተኞች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በማኦ ዜዱንግ የሚመራው የቻይና አብዮት በሶሻሊስት ርዕዮተ-ዓለም ማዕቀፍ ውስጥ የሚጠቀስ ቢሆንም በሌሎች ሀገራት ከተካሄዱት ለየት ያለ ባህሪ እንዳለው ይነገራል፡፡
የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት፤ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ ሁለት ዋነኛ የባህል አብዮቶች ተካሂደዋል፡፡ እነዚህም አብዮቶች እ.ኤ.አ በ1923 የተጀመረውና እስከ 1938 የዘለቀው በቱርክ በሙስጠፋ ሀሰን አታቱርክ መሪነት የተካሄደውና በ1960ዎቹ አጋማሽ በማኦ ዜዱንግ አማካይነት በቻይና የተካሄደው አብዮት ናቸው፡፡ እነዚህ አብዮቶች ከላይ ወደ ታች የተካሄዱ መሆናቸው ተመሳሳይ ያደርጋቸዋል፡፡ ልዩነታቸው ግን ሰፊ ነው፡፡ ወደ አዲስ ዓመት መልእክት ከመሄዴ በፊት ለመንደርደሪያ ይሆነኝ ዘንድ ስለ ቻይና፣ ስለ ቱርክና በሀገራችን ስለተካሄዱ አብዮቶች የመንደርደሪያ እውነታዎችን ልጠቃቅስ፡፡
ከአንዳንድ ሰነዶች ላይ እንዳገኘሁት መረጃ ከሆነ፤ የቻይና አብዮት መነሻ የሆነው በዚያ ወቅት አዝመራቸውን የሚያወድም የወፍ መንጋ መከሰቱ ነበር ይባላል፡፡ ቻይናዎች ያንን የወፍ መንጋ ድራሽ አባቱን አጠፉት፡፡ ይሁን እንጂ ይህ እርምጃ መዘዝ አመጣባቸው፡፡ በሰው ልጅ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ተፈጥሮ ተዛባ! ወፎቹ ሲጠፉ አዝመራው ጥሩ ይሆናል ብለው ሲጠብቁ፣ ተምች መጣና አዝመራውን ገና በቡቃያው አመድ አደረገው፡፡ ወፎቹ ቢኖሩ ኖሮ (አዝመራው ሲደርስ የድርሻቸውን መውሰዳቸው እንደተጠበቀ ሆኖ) ተምቹን ይለቅሙት ነበር፡፡ ወፎቹ የተምቹን ያህልም አያወድሙም፡፡ የተምች ሰራዊት ባደረሰው ጉዳት አዝመራ ጠፋ፡፡ በቻይና የከፋ ርሃብ ተከሰተ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አለቀ፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድ በቻይና የባህል አብዮት ተካሄደ፡፡
በቻይና የባህል አብዮት የተካሄደው እ.ኤ.አ ከ1966 እስከ 1976 ባለው ጊዜ ነበር፡፡ የቻይና የባህል አብዮት “ቀዩ ጦር” በሚባሉ የቻይና ቄሮና ፋኖዎች ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተከናወነ እንቅስቃሴ ነው:: እንቅስቃሴው የተጠነሰሰው በማኦ ዜዱንግ ሲሆን፤ በወቅቱ የነበረውን የመንግስት ቢሮክራሲ በማፈራረስ የህዝቡን አመለካከትና ባህሪ አብዮታዊ ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግ ነበር የታለመው:: የቻይና የባህል አብዮት በኪነ-ጥበብ ስራዎች በተለይም በቴአትሮች ታጅቦ የተካሄደ እንደነበር ይነገራል፡፡ በመጽሐፍ ረገድ የማኦን ጥቅሶች የያዘው “ቀዩ መጽሐፍ” በ350 ሚሊዮን ቅጂዎች ታትሞ በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭቷል፡፡
የቻይና አብዮት ዓላማ ያደረገው አራቱን “አሮጌዎች” ማፈራረስ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አራቱ “አሮጌዎች” ተብለው የተሰየሙት ጉዳዮች፡- አሮጌ ባህል (old culture)፣ አሮጌ ወግ (old custom)፣ አሮጌ ልማድ (old habit) እና አሮጌ አስተሳሰብ (old ideas) ናቸው፡፡ በእነዚህ “አሮጌዎች” ምትክ ደግሞ አራት “አዳዲስ” ነገሮች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ እነሱም፡- “አዳዲስ ከተማዎች፣ አዳዲስ ጎዳናዎች፣ አዳዲስ መንደሮችና አዳዲስ ሰዎችን” መፍጠር የሚል ግብ ነበረው አብዮቱ፡፡
የሚያሳዝነው ነገር የዚህ አብዮት ሂደት ነባሩን የቻይናውያንን ባህልና ሃይማኖት አጥፍቷል፡፡ ታሪካዊ ስፍራዎችን አውድሟል፡፡ ቤተ መጽሐፍትን ከታሪካዊ ሰነዶቻቸው ጋር እንዲቃጠሉ አድርጓል፡፡ ቤተ ክርስቲያናት፣ መስጂዶች፣ ገዳሞች፣ የመቃብር ሥፍራዎች፣… ተዘርፈዋል፤ ወይም ተዘግተው ወደ ሌላ ተቋምነት እንዲቀየሩ ተደርገዋል፡፡ የቻይና አብዮት በአውዳሚነቱ የታወቀ ሲሆን በዚሁ መሀል ግን “ያንግትዝ ለተባለው ትልቅ ወንዝ ድልድይ ለመስራት፣ የሩዝን ዘር ለማሻሻልና የህዝቡን ንቃተ ህሊና ለማዳበር ረድቷል” የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ያ አብዮት የዛሬዋን ቻይና የቀረጸ ነው፡፡ ዛሬ ቻይናውያን በኢኮኖሚ አድገዋል፡፡ በቴክኖሎጂ መጥቀዋል፡፡
ወደ ቱርክ እናምራ፡፡ የቱርክ የባህል አብዮት እስከ አሁን ድረስ የዘለቁ ሁለት ውጤቶችን እንዳስገኘ ይናገራሉ፤ የታሪክ ምሁራን፡፡ እነሱም በሴቶችና በትምህርት ላይ የተደረጉ የአስተሳሰብ ለውጦች ናቸው፡፡ ኦቶማን ቱርክ ሲፈርስ “ቱርክ” የምትባል ሀገርን የመሰረቱት ሙስጠፋ ሀሰን አታቱርክ የተከተሉት ዓለማዊ (ሴኩላር) የመንግስት አስተዳደርን ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሴቶች በቱርክ ፖለቲካ የመምረጥም የመመረጥም መብት እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ሃይማኖት ከመንግስት እንዲለይ አድርገዋል፡፡ 99.6 በመቶ ሙስሊም ማህበረሰብ ባላት ቱርክ፤ ሴቶች እንደዚያ ዓይነት መብት እንዲኖራቸው ማድረግ ትልቅ የአስተሳሰብ ለውጥ ተደርጎ የሚታይ ነው ይላሉ፤ ምሁራን፡፡
በትምህርት ረገድ እነ አታቱርክ የተከተሉትና እስከ አሁን ድረስ በዘለቀው ፖሊሲ፤ ተማሪዎች የሃይማኖቶችን አንድነትና ልዩነት (comparative religion) እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ሀገር ወዳድነትን በዜጎች አእምሮ ውስጥ ለማስረጽ ተማሪዎች ከአንደኛ ደረጃ ጀምረው የዜግነት ትምህርት ይማራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ የደህንነት ትምህርትም ይሰጣል፡፡ እነዚህም ሁኔታዎች ሀገሩን የሚወድና በመቻቻል የሚያምን ዜጋ እንዲፈጠር አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ ቱርክ ውስጥ ጽንፍ የረገጠ አስተሳሰብ የሚያራምድ ዜጋ እምብዛም ነው፡፡
ከዓመታት በፊት ቱርክ በኢኮኖሚዋ ያላደገች ሀገር ነበረች፡፡ ቱርክ የፖለቲካ መረጋጋት የፈጠረቺው፣ የኢኮኖሚ ግስጋሴዋን ያቀላጠፈቺው እነ ሙስጠፋ ሀሰን አታቱርክ በጀመሩት የባህል አብዮት አቅጣጫ በመመራት፣ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት በመቻላቸው ነው፡፡ ይህንንም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማቀላጠፍና ውጤታማ ለማድረግ ቱርክ ከዓመታዊ ሀገራዊ በጀቷ የበለጠውን ገንዘብ የምትመድበው ለባህል ሚኒስቴር ነው፡፡ የባህል ሚኒስቴር ደግሞ ለቱርክ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ማስፋፊያና ማበልጸጊያ ያውለዋል፡፡ ለዚህም ነው ዛሬ የቱርክ የፊልም ኢንደስትሪ ያደገውና በዓረቡ ዓለም ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በአውሮፓ ጭምር ተመራጭና ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን የቻለው፡፡ የቱርክ ፊልሞችና የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የቱርክን ባህል፣ ወግና ልማድ ያስተዋውቃሉ፡፡ ህዝባቸውን ለስራ ይቀሰቅሳሉ:: ፍቅርና ሰላምን ይሰብካሉ፤ የቱሪስት መስህቦችን ያስተዋውቃሉ፡፡
ወደ ሀገራችን እንምጣ፡፡ በ1920ዎቹ መጀመሪያ ላይ አፄ ኃ/ስላሴ ስልጣን ላይ በወጡበት ወቅት ከቱርክና ከጃፓን ጋር ተመሳሳይነት ያለው የአስተሳሰብ ለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ነበሩ፡፡ የአፄ ኃ/ስላሴ እንቅስቃሴ በጣሊያን ወረራ ምክንያት ተደናቅፎ ሲቀር፣ ጃፓንና ቱርክ የአስተሳሰብ ለውጥ እንቅስቃሴያቸውን ለውጤት አብቅተዋል፡፡ ከጣሊያን ወረራ በኋላ በርካታ ተራማጅ አመለካከት የነበራቸው ኢትዮጵያውያን፣ ሀገራቸው በየትኛው የእድገት ሞዴል መመራት እንዳለባት ሀሳባቸውን ይሰነዝሩ ነበር፡፡ እንደ ደራሲ ከበደ ሚካኤል ያሉት “ጃፓን እንዴት ሰለጠነች” የሚል መጽሐፍ እስከ መጻፍ ደርሰዋል፡፡ በ1966 የደርግ አብዮት እስከፈነዳበት ጊዜ ድረስ ተራማጅ ምሁራኑን የሚሰማቸው አላገኙም፡፡
የደርግ አብዮት የፊውዳሉን ስርዓተ ማህበር ከገረሰሰ በኋላ ከወሰዳቸው እርምጃዎች አንዱ የባህል አብዮት ማካሄድ ነበር፡፡ ደርግ የባህል አብዮቱን ያራመደው በቀበሌ፣ በከፍተኛ፣ በወረዳ፣ በአውራጃና በክፍለ ሀገር ደረጃ የኪነት ቡድኖችን በማቋቋም አዳዲስ አስተሳሰቦችን ወደ ህዝቡ በማቅረብ ነበር:: የያኔዎቹ የኪነት ቡድኖች አሮጌውን ስርዓት በማውገዝ፤ አዲሱን የሶሻሊስት ስርዓት በማሞገስና በማወደስ አዲስ አስተሳሰብ እንዲያቆጠቁጥ የላቀ ሚና ነበራቸው፡፡
በሦስቱ ሀገሮች የተካሄዱትን አብዮቶች ስንመለከት፤ ዋነኛው ልዩነታቸው የቀጣይነት ጉዳይ መሆኑን ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ሙስጠፋ ሀሰን አታቱርክ በ1938 ቢሞትም የቱርክ አብዮት እስከ አሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው፡፡ የቻይናው አብዮት ግን ማኦ ሲሞት አብሮ ሞቷል፡፡ የእኛውም የሶሻሊስት አብዮት ከደርግ ጋር ከስሟል፡፡ በምትኩ የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር ባለመደረጉ ባለፉት 27 ዓመታት ሌላ ምንነቱ በውል ያለየ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የተሰኘ በድቅድቅ ጨለማ የተሞላ ዋሻ ውስጥ ስንዳክር ቆይተናል፡፡ አሁን ከጨለማው ወጥተን የዋሻው በር ላይ ቆመን፣ ደፋር መሪ አጥተን፣ ወደ የት እንደምንሄድ ግራ ገብቶን እየቆዘምን እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ወደተሻለ አቅጣጫ ይዞን የሚሄድ “አብዮታዊ የለውጥ ኃይል” ያስፈልገናል ብዬ አስባለሁ፡፡
ይህንን ሃሳብ እያውጠነጠንኩ ባለሁበት ወቅት አንድ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር፣ አጉስቲነስ ዳንኤል (Agustinus Daniel) የተባለ ኢንዶኔዥያዊ ጸሐፊ “MENTAL REVOLUTION - A Small Change For A Better Civilization” የሚል መጽሐፍ መጻፉን በመጥቀስ፣ “ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውን የሚያስፈልጋቸው አዲስ አስተሳሰብና አዲስ መንፈስ ነው” ከሚል መልእክት ጋር በፌስቡክ ገጻቸው ለጥፈውት አየሁ፡፡ መጽሐፉን ለማግኘት ጥረት ባደርግም ለጊዜው አልተሳካልኝም:: የዚህ መጽሀፍ ዋነኛ መልእክት ምን እንደሆነ ግን ከኢንተርኔት ያገኘኋቸው መረጃዎች አሉ፡፡
በዚህ ወቅት የሰው ልጅ ስልጣኔ አስቸጋሪ ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ በዓለም ላይ በርካታ ቀውሶች ተከስተዋል፡፡ እነዚህ ቀውሶች “የተለዩ” ቀውሶች አይደሉም፡፡ ከሰዎች የሚመነጩ ትልልቅ ቀውሶች አካል ናቸው፡፡ የአስተሳሰብ አብዮት በማካሄድ የመፍትሄው አካል መሆን እንችላለን፡፡ የጠፋውን ሰብአዊነት በመመለስ ራሳችንን የለውጡ አካል ማድረግ እንችላለን፡፡ ስልጣኔ የፈጠረውን ቀውስ በማስወገድ መጪውን ዘመን ብሩህ ማድረግ እንችላለን፡፡
ከላይ የጠቀስኩት የአጉስቲነስ ዳንኤል መጽሐፍ በሦስት ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል ችግራችንን የሚያመለክተው “የበሰበሰው ስልጣኔ” ነው ይለዋል፡፡ የበሰበሰው ስልጣኔ በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተያይዞ የመጣ ቀውስ መሆኑን ያመለክታል፤ ደራሲው፡፡ ይህ ስልጣኔ ከኢኮኖሚ እድገት ጋር ተቀናጅቶ በመምጣት ሰብአዊነትን በማጥፋት፣ ባህልን በመግደል፣… የራሳችን የሆነውን (አገር በቀሉን) ስልጣኔ መፈታተኑን ያብራራል፡፡ በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ኢኮኖሚን በማሳደግ የመጣ፣ በ“እኔነት” የታጠረ የቀውስ ስልጣኔ ነው፡፡ ይህ ስልጣኔ “ለእኛ” የሚለውን የኛን ስልጣኔ በእጅጉ ተፈታትኖታል ይላል፤ ደራሲው፡፡
ሁለተኛው ክፍል መፍትሄውን የሚያመላክት ሲሆን መፍትሄው “የአስተሳሰብ አብዮት” ማካሄድ መሆኑን ይነግረናል፡፡ መፍትሄው (እንደየ ሃይማኖታችን) “ወደ ፈጣሪ መመለስና ሰብአዊ አስተሳሰብን መመለስ ነው” ይለናል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ አብዮት እንዴት ወደ ነበርንበት ቀደምት ስልጣኔ መመለስ እንደምንችል ያብራራል:: ለዚህ ደግሞ ወደ ፈጣሪ ፊታችንን መመለስ፣ ወደ እውነተኛው ሰብአዊነት መመለስ ነው፤ መንገዱ:: ይህንን ለማድረግ የበሰበሰውን አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ በመጣል፣ በአዲስ ሰብአዊ አስተሳሰብ መተካት መሆኑን ያሳስባል፤ ደራሲ አጉስቲነስ ዳንኤል፡፡
ሦስተኛው ክፍል ከአስተሳሰብ ለውጡ የሚጠበቀው “አዲስ ስልጣኔ” መሆኑን ያስረዳል፡፡ አዲሱ የስልጣኔ መንገድ ከኢኮኖሚ ጋር ያልተያያዘ የስልጣኔ ጎዳና ነው ይለናል፤ ደራሲው፡፡ በቂ፣ ሞልቶ የተትረፈረፈ፣ ተዝቆ የማያልቅ የበጎነት ሀብት መሆኑንም ይነግረናል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ ብዙ ጉልበት፣ ብዙ ሀብት፣ ብዙ ጊዜ… የማይጠይቅ፤ አጋዥ ሳያስፈልገን እያንዳንዳችን ልንፈጽመው የምንችለው፣ ራሳችንን ቅን አሳቢ፣ ሩህሩህ፣ አዛኝ፣ ጥሩ ሰው፣ በማድረግ ከራሳችን የምንጀምረው አብዮት ነው ይለናል፡፡ ይህንን ለውጥ ለማምጣት የስርዓት ለውጥ አያስፈልግም፣ የመንግስት ለውጥ አያስፈልግም፡፡ የሞራል ልዕልና በመጎናጸፍ፣ የመልካም ስነ-ምግባር ካባ በመደረብ ራሳችንን መለወጥ ብቻ ነው የሚያስፈልገው ይለናል፤ ደራሲ አጉስቲነስ ዳንኤል፡፡
የእኔም የአዲስ ዓመት የመልካም ምኞት መልእክት፣ ከደራሲ አጉስቲነስ ሃሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት በራሳችን ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት ለራሳችን ቃል እንግባ፡፡ ለአዲሱ ዓመት የመልካም ምኞት መግለጫ በመለዋወጥ በጎነትን “ሀ” ብለን እንጀምር፡፡ ለወላጆቻችን፣ ለትዳር አጋሮቻችን፣ ለልጆቻችን፣ ለጎረቤቶቻችን፣ ለአካባቢያችን፣ ለሀገራችን፣ ለስራ ባልደረቦቻችን… መልካም ምኞታችንን እንግለጽላቸው፡፡ የሞቱትን በጸሎት እናስታውሳቸው፡፡ በአልጋ ቁራኛ፣ በደዌ ዳኛ የተያዙትን ሄደን እንጠይቃቸው፡፡ የተራቡትን ካለን ላይ ቆርሰን እናካፍላቸው፡፡ የታረዙትን እናልብሳቸው፡፡ በጎነት ማለት ይኸው ነው፡፡ ሰብአዊነት ማለት ይሄ ነው፡፡
በመጨረሻ፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ለአንድ ዓመት በነበረኝ ቆይታ ጽሁፎቼን ላነበባችሁም ላላነበባችሁም፣ አስተያየት ለሰጣችሁኝም ላልሰጣችሁኝም አንባብያንና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡-ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡
“MENTAL REVOLUTION - A Small Change For A Better Civilization” የሚለው መጽሐፍ ጭብጥ

Read 767 times