Monday, 09 September 2019 10:36

“የኢኮኖሚ ማሻሻያ” 4 እቅዶች፣ አገርና ኑሮ እንዲያንሰራራ ይረዳሉ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)


         ብዙ ቢሊዮን ብሮች፣ በከንቱ የባከነባቸው ናቸው- ግዙፎቹ የመንግስት የቢዝነስ ፕሮጀክቶች:: እነዚህን በሽያጭ ለግል ኩባንያዎች ማዛወር፣ ትክክለኛ የማሻሻያ እቅድ ነው፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ከብክነት ይገላግላል፡፡ በአረም ተውጠው፣ በዝገት ተበልተው ከሚቀሩ፣ በግል ኩባንያ ስር፣ ውጤት እንዲያፈሩና ትርፋማ እንዲሆኑም እድል ይከፍታል - እቅዱ በስርዓትና በጥንቃቄ ከተከናወነ፡፡
ይሄ ቁጥር 1 ማሻሻያ እቅድ ነው፡፡
“ፕራይቬታይዜሽን” ልትሉት ትችላላችሁ፡፡ ወይም ደግሞ፣ “ልማታዊ” በሚል ስያሜ “አጥፊነት”ን ከማስፋፋት የመቆጠብ እቅድ ነው ቢባልም ያስኬዳል፡፡
ነገር ግን አባካኝና አክሳሪ የመንግስት ቢዝነሶችን (በተለይ የስኳር ፋብሪካዎችና እርሻዎችን) ለግል የመሸጥ እቅድ፣ የተገቢነቱ ያህል ከባድ ስራ ቢሆንም፤ ይሄ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ከአጥፊነት መቆጠብ በቂ አይደለም፡፡
መንግስት፣ ለግል ኩባንያ የሸጣቸውን እርሻዎችና ፋብሪካዎችን፣ ዞሮ ለማሰናከል ቀን ከሌት የሚያሴር ከሆነ፤ ድካሙ ሁሉ ከንቱ ይቀራል፡፡ ለምሳሌ፣ ከስኳር በተጨማሪ ኢታኖል ማምረት የማያዋጣ ከሆነ፣ በኪሳራ እንዲሰሩ ከማስገደድ ወይም አካክሳለሁ ብሎ በድጐማ የዜጐችን ሃብት ከማባከን ካልተቆጠበ፤ ነገሩ አዙሪት ይሆናል፡፡ ወደ ሸሸው ነገር ተመልሶ እንደ መሮጥ ነው፡፡
እንደተለመደው “ዋጋ ልቆጣጠር” የሚል ከሆነም፣ ከኢኮኖሚ ቀውስ አያመልጥም፡፡ ኢኮኖሚን ለማሰናከል እንደመዝመት ቁጠሩት፡፡ የኢንዱስትሪ ምርትንና የፋብሪካ ስራን በእንጭጩ ያስቀራልና፡፡
እናም ቁጥር 2 የማሻሻያ እቅድ፣ ከአሰናካይነትና ከአድናቂነት መታቀብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ “ease of doing business” በሚል ስያሜ ከሚካሄዱ ማስተካከያዎች ጋር ይዛመዳል፡፡
ቁጥር 3 የማሻሻያ እቅድ ደግሞ፣ መረን ካጣ የገንዘብ ህትመትና አለመጠን ከሚያብጠው የመንግስት በጀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡  
በየትኛውም የምርት ዓይነት ላይ፣ የገበያ ዋጋ የሚወደደው በሁለት ምክንያቶች ብቻ ነው:: ከገበያ ተፈላጊነት ጋር የሚመጣጠን ምርት ወደ ገበያ ካልደረሰ (ለምሳሌ፤ መንግስት መሬትን በሞኖፖል… ማለትም በጉልበት ጠቅልሎ በመያዙና በእልፍ አሰናካይ ህጐች ስለተበተበው የመኖሪያ ቤት እጥረት ሲፈጠር፣ ዋጋና ኪራይ ይወደዳል፡፡ የዓመቱ አጋማሽ ላይ እንዳየነው የኤሌክትሪክ ሃይል በማጣት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርት በግማሽ ሲቀንስ፣ ወይም  ከውጭ የተገዛው ስንዴ በትራንስፖርት ችግር ለወራት ሲዘገይ) የእነዚሁ ምርቶችና የተዛማጅ ምርቶች ዋጋ ይጨምራል፡፡
ይሄኔ፣ ፍቱን መድሃኒቱ፣ የመንግስትን ሞኖፖል ማስወገድ፣ “የነፋስ ተርባይን፣ የፀሐይ ሃይል፣ ጂኦተርማል” እያሉ በድሃ አገር ሃብት ላይ ከመቀለድ ይልቅ፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ሃይል በአነስተኛ ዋጋ የሚያቀርብ ኢንቨስትመንት ላይ ማተኮር፤ የስንዴ እጥረትንም ሆነ የትራንስፖርት ችግርን ማቃለል ነው፡፡
ይሄ፣ እውቀትን፣ ጥረትንና ቅንነትን ይጠይቃል:: በተቃራኒው የምርቶቹን ዋጋ በመንግስት ቁጥጥር አማካኝነት ወደታች ጨፍልቆ ለማቆየት መሞከር፣ የሰነፍ፣ የሞኝ ወይም የክፋት ተግባር ከመሆን አያልፍም፡፡
በሌላኛው ሁለተኛ ምክንያት ሳቢያ የሚፈጠረው የዋጋ ችግር፣ በአንድ ወይም በሁለት አይነት ምርቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛውን ገበያ የሚያናጋና “የዋጋ ንረት” (inflation) የሚባለው ችግር ነው:: መንስኤውም፣ መረን የወጣ የገንዘብ ህትመት ነው፡፡ መንግስት በገፍ ገንዘብ እያተመ፣ የብር ኖትን እያረከሰ፣ በዋጋ ንረት ኢኮኖሚውን ማናጋቱ ያነሰ ይመስል፣ ሌላ ተጨማሪ ቀውስ ይፈጥራል:: ራሱ የፈጠረውን ችግር በነጋዴዎች ላይ በማላከክ፣ የዋጋ ቁጥጥርን በማወጅ፣ ገበያውን በግርግር ያተራምሰዋል፡፡
ቅጥ ባጣ የብር ህትመት ሳቢያ የሚመጡት መዘዞች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ ብር እየረከሰ የዶላር ምንዛሬ ካልተስተካከለ፤ ዋጋው እየተዛባ፤ ይህም ኤክስፖርትን እያዳከመ የኢኮኖሚ ቀውሱን ያባብሰዋል፡፡ የወርቅ ኤክስፖርትን በምሳሌነት ማየት ይቻላል፡፡
በ2002 የዶላር ምንዛሬ ሲስተካከል፣ የወርቅ ኤክስፖርት በፍጥነት ስላደገ፣ በ2003 ከግማሽ ቢሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር አደገ፡፡
ከዚያ ወዲህ በገንዘብ ህትመት ሳቢያ ብር እየረከሰ፣ የዶላር ምንዛሬ እየተዛባ ሲመጣ ግን፣ የወርቅ ኤክስፖርት በፍጥነት መውረድ ጀመረ:: ስርዓት አልበኝነትም ተደርቦበትም አሽቆለቆለ:: ካቻምና ወደ 200 ሚሊዮን ዶላር ገደማ፣ አምና ወደ 100 ሚሊዮን ዶላር፤ ዘንድሮ ደግሞ 30ሚ ዶላር ብቻ ሆኗል - የወርቅ ኤክስፖርት፡፡
ይሄ ሁሉ መዘዝ የሚመጣው…በዋጋ ንረት የዜጐች ኑሮ የሚናጋው፣ በዋጋ ቁጥጥር ዘመቻዎች ኢኮኖሚው የሚታመሰው፣ በተዛባ የዶላር ምንዛሬ ሳቢያ የኤክስፖርት ገቢ የሚደነዝዘውና የሚያሽቆለቁለው፤ በገንዘብ ህትመት፣ በበጀት እብጠትና በውጭ እዳ ክምር ምክንያት ነው፡፡ እናስ ምን ተሻለ?
መንግስት፤ ወጪዎቹን ከማሳበጥ፣ የውጭ ብድርን ከመቆለልና ከመረን የገንዘብ ህትመት እቆጠባለሁ ብሏል - የተረጋጋ፣ ቁጥብ እና ጥብቅ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ አንድ የማሻሻያ እቅድ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይሄ ነው፤ ቁጥር 3 የማሻሻያ እቅድ፡፡  
በገፍ ገንዘብ ከማሳተም የመቆጠብ እቅድ ነው ልንለው እንችላለን፡፡
ከላይ እንዳየነው፣ መንግስት፣ “አለማለሁ”፣ እያለ ነው የሚያጠፋው፡፡ “ዋጋ እተምናለሁ፤ እቆጣጠራለሁ”፤ ወይም “ስራ እፈጥራለሁ” በሚል ሰበብም ነው ስራን ማደናቀፍና ስራ ፈጣሪዎችን ማሰናከል የሚችለው፡፡ ከዚህ መቆጠብ፤ ጥሩ ማሻሻያ ለውጥ ነው ብያለሁ፡፡ በአጥፊና በአላስፈላጊ ቁጥጥር አማካኝነት የስራ ነፃነትን ከመጣስ መታቀብ፣ በዋጋ ቁጥጥርም ሆነ በታክስ ጫና ሳቢያ የንብረት ባለቤትነት መብትን ከመሸርሸር መቆጠብ፣ በጣም ተገቢና ከባድ ጥረትን የሚጠይቅ መልካም እቅድ ነው፡፡ ነገር ግን፤ የመንግስት ስራ፣ አደናቃፊና አሰናካይ ከመሆን መቆጠብ ብቻ አይደለም፡፡ ነፃነትና መብትን ማክበር ብቻ ሳይሆን ማስከበርም ይኖርበታል፡፡  
የግል ኢንቨስትመንትና የግል ቢዝነስ ያለ እንቅፋትና ያለ ማሰናከያ እንዲሰሩ መፍቀድ ብቻ ሳይሆን፣ ከስጋትና ከጥቃት፣ ከዝርፊያና ከቃጠሎ ውድመት፣ ከተዘጋ መንገድና ከአመጽ ነፃ ሆነው የሚሰሩበት፣ የንብረት ባለቤትነት መብትና የህግ የበላይነት የተከበረበት ስርዓትን ማጠናከር፤ ትልቁ ቁምነገርና እጅግ ከባዱ የማሻሻያ እቅድ ነው፡፡ ሌሎቹን እቅዶች ሁሉ የሚያስተሳስርና የሚደምር ዋነኛው እቅድ ይሄ ነው፡፡
ቁጥር 4 እቅድ ልንለው እንችላለን፡፡
“የነፃ ገበያ ስርዓትን ማስፋፋት” ወይም “Liberalization” የሚል ስያሜ ሊሰጡትም ይችሉ ነበር:: ግን የፈለጉ አይመስሉም፡፡ ትክክለኛ ስያሜ ይሆን ነበር፡፡ ከዚያ ይልቅ “አገር በቀል” የሚል ቅጽል ነው የተጠቀሙት::
አንዳች የማሻሻያ ሃሳብ ሲቀርብ፣ “ይሄ የምዕራባዊያን አስተሳሰብ ነው”፣ “ይሄ የባዕዳን ሃሳብ ነው” እያሉ ማጣጣል እንደ ክፉ ዓመል በተለመደበትና ጭፍንነት በሰፈነበት ዘመን ውስጥ በመሆናችን ፣ “አገር በቀል” የሚል ቅጽል በመለጠፍ ድጋፍ ለማግኘት መመኘት ቢበራከት አይገርምም፡፡ የማያዛልቅ እርባና ቢስ ምኞት መሆኑ ነው - ችግሩ፡፡
በእርግጥ የማሻሻያው እቅድ፣ “አገር በቀል” እንደሆነ የተገለፀው፤ ለሃሳቡ አመንጪዎችና አዘጋጆች ተገቢውን እውቅና ለመስጠት ታስቦ ከሆነ መልካም ጅምር ነው፡፡ አንድ ሰው ያፈለቀው ሃሳብ ወይም ሁለት ሰዎች ያመነጩት ሃሳብ ሲሆንማ፣ የማሻሻያ እቅዱ በስማቸውም ጭምር ቢሰየም አይበዛባቸውም፡፡ የአላዋቂነትና የኋላቀርነት ነገር ይዞን እንጂ፤ ለእያንዳንዱ ሰው፤ የብቃቱና የስራው ያህል፣ እውቅና መስጠት፣ የፍትህ ስነምግባር መሰረታዊ ኃላፊነታችን ነው፡፡
“የኢኮኖሚ ማሻሻያ” የሚለው ስያሜ ላይ፣ “አገር በቀል” የሚል ቅጽል የተጨመረበት፣ ለአዘጋጆቹ እውቅና ለመስጠት ከሆነ መልካም ጅምር ነው ያልኩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ነገር ግን፣ “አገር በቀል” የሚል ታፔላ ዘወትር ሲለጠፍ የሚታየውና ሲራገብ የሚደመጠው፣ በአቋራጭ ተሰሚነትን፣ በደበስባሳው ድጋፍና ጭብጨባን ያስገኛል በሚል ምኞት ነው፡፡ አራት ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ውጤታማነትን በእውን የሚያሳይ አለ፡፡ “አገር በቀል ችግኞችን ትከሉ” ብሎ የሚደሰኩር ደግሞ አለ፡፡
“አገር በቀል” ማለት፣ ትክክለኛና ጠቃሚ ማለት አይደለም (አድራሻን ይጠቁማል እንጂ) በእርግጥ፤ “አገር በቀል” የሆነ፣ አገር ውስጥ ከሚገኝ ሰው የፈለቀ፣ ትክክለኛ ቀና ሃሳብ አለ፡፡
አገር በቀል የሆነና የተሳሳተ ጠማማ ሃሳብም አለ (ለዚያው ክምር ክምር)፡፡ የማንኛውም ሃሳብ እውነተኛነትና ትክክለኛነት፤ ቀናነትና ጠቃሚነት፣ በመነጨበት አድራሻ አይመዘንም፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ “ከውጭ የመጣ”፣ “የምዕራባዊያን ሃሳብ” ብለው ሃሳብን በአቋራጭ ለማንቋሸሽ፣ በጭፍን ለማውገዝ የሚሞክሩ ጥቂት አይደሉም፡፡ ከመሞከርም አልፈው  አብዝተው ሲያዘወትሩት፣ ቀስ በቀስ ሱስ የሆነባቸው አሉ፡፡
“የመሬት ስበት” ቲዎሪና ቀመር፣ በእንግሊዝ አገር፣ አይዛክ ኒውተን የተሰኘ ሰው ባካሄደው ምርምር የተገኘ እውቀት ስለሆነ፤ “መጤ ሃሳብ”፣ “የምዕራባዊያን እውቀት” ብሎ ከማጣጣል ጋር የሚስተካከል ጭፍንነት አለ? (አዎ ሞልቷል)፡፡ ግን፣ ይሄም ቀላል ጭፍንነት አይደለም፡፡ ነፃ ገበያን ለማስፋፋት የሚዘጋጁ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ለማንቋሸሽ የሚያገለግል፣ የወረደ መሳሪያም፤ ከዚህ ጋር ይመሳሰላል፡፡
የኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ አዘጋጆችን፤ ይሄ ቢያሳስባቸው አይገርምም፡፡ ነገር ግን የወረደ ጭፍንነትን ለመከላከል፤ አብሮ መውረድ ብዙም የሚያዛልቅ መፍትሔ አይደለም፡፡ ይልቅስ፣ ሰሞኑን እንዳየነው፣ የማሻሻያ እቅዱ ይዘቶችን ለመግለጽ፣ ለማብራራትና ለማስረዳት መጣር፣  ደግሞ ደጋግሞ መጣር ነው የሚሻለው፡፡
የማሻሻያ እቅድ ትልቁ ፈተና - የተጣመመ አስተሳሰብ፡፡
አደናቃፊ ህጐችን በትክክለኛ ህግ መቀየር፤ አሰናካይ አሰራሮችንም የህግ የበላይነትን በሚያስፋፋ መንገድ መለወጥ ድርብ ስራ ነው፡፡
ከአሰናካይነት መቆጠብ፣ ከዝርፊያ እንደመቆጠብ ቁጠሩት፡፡ ቀላል ያለ ስራ ነው፡፡ ከዚህ የሚከብድ ሌላ ዋና ስራ አለ፡፡ ዝርፊያን መከላከል ደግሞ የህግ የበላይነት ስርዓትን እንደማስፋፋት ቁጠሩት:: እነዚህ ስራዎች፣ ደረጃ በደረጃ ያለማቋረጥ በትጋት እየተከናወኑ፣ የዚያኑ ያህልም ውጤት እያስገኙ በርካታ አመታትን የሚፈጁ ስራዎች ናቸው፡፡
ነገር ግን፣ ሌላ በጣም ከባድ ስራ ደግሞ አለ:: አዎ፤ ህጐችንና አሰራሮችን የማስተካከል እቅድ፤ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በትጋት፣ በጥበብና በጽናት ከተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር፣ በአጠቃላይ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን ማስተካከል ካልተጀመረ ግን፤ የማሻሻያ ለውጥ ብዙም አይዘልቅም፡፡ ፈተና ይበዛበታል፡፡
አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስ፡፡
መንግስት ብዙ ድጋፍ የሚያገኘው፤ “የቤት ኪራይ፣ የዳቦና የሙዝ ዋጋ እተምናለሁ፤ እቆጣጠራለሁ” ቢል ነው? ወይስ፣ “ያለ ስጋት ህግን ተማምናችሁ ስሩ፤ በምርታችሁ ላይ አዛዥ ናዛዥ አልሆንም፤ እንዳሻኝ ጣልቃ አልገባም፤ የገበያ ዋጋ ላይ ድርሽ አልልም” ብሎ ቃል ቢገባ ነው ብዙ ድጋፍ የሚያኘገው?
“ዋጋ እተምናለሁ፤ ዋጋ እቆጣጠራለሁ” በማለት ብዙ ድጋፍ የሚያገኝ ከሆነ፤ እጅግ ጥልቅ የሆነ፤ የጭፍን አስተሳሰብ ጨለማ ገደል ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ ይሄንን ጭፍን አስተሳሰብ ለማስተካከል የማንተጋ ከሆነ፣ የማሻሻያ ለውጦች፣ በፈተና ብዛት ተሸርሽረው፤ ተበጣጥሰው፣ ተንገራግጨው ድራሻቸው ይጠፋሉ፡፡ እንዴት?
ከንግድ ፈቃድ ምዝገባ ጀምሮ፣ ምርትን ወደ ውጭ እስከ መላክ ድረስ፣ በየቦታው፣ በየጊዜው የሚያጋጥሙ የተንዛዙ ውጣውረዶችን የማቃለል፤ እንቅፋቶችና ማሰናከያዎችን የማስወገድ እቅድ… በቀላሉ የሚሳካ የማሻሻያ ለውጥ ይመስላል፡፡ በእርግጥም፤ እንዲሁ ስታስቡት፤ መንግስት አንዳች ትልቅ ስራ እንዲያከናውን ሳይሆን፣ የሚሰሩ ሰዎችን ከማንገላታት፣ ከማደናቀፍና ከማሰናከል እንዲቆጠብ ማድረግ እንዴት ይከብዳል? ግን ከባድ ነው፡፡
ከማሻሻያው ጐን ለጐን፣ በየቦታው ከፌደራል እስከ ወረዳ፣ በየፊናቸው ማሰናከያ እንቅፋት ከመፈብረክ ውጭ ሌላ ስራ የማያውቁ የመንግስት ተቋማት ሞልተዋል፡፡
መኖሪያ ቤቶችን እገነባለሁ አስገነባለሁ ብሎ ሳይካላት የቀረ የመንግስት ተቋም፤ ከመኖሪያ ቤት እጥረት በተጨማሪ ሌላ ብዙ ችግር ለመፍጠር፤ “የቤት ኪራይ” እቆጣጠራለሁ ብሎ አዋጅ ያዘጋጃል::
እንኳን የቤት ኪራይ ቁጥጥር ይቅርና፤ የዳቦ የዋጋ ቁጥጥር እንኳ አላዋጥም፡፡ “ይሄን ያህል ግራም ዳቦ በምናምን ብር እና ሳንቲም” ብሎ የዋጋ ተመን ማወጅ፣ ለዚያውም አንድ ሺ ሁለት ሺ ዳቦ ቤቶችን ብቻ መቆጣጠር ቀላልና የሚያዋጣ መስሎ ለጊዜው ቢታይ አይገርምም፡፡ ነገር ግን፣ መዘዝ ነው የተረፈን:: አንዳንዶቹን አክስሮ፣ የዳቦ እጥረትን ፈጥሮ፣ የስንዴ ምርትን ደፍጥጦ፣ ከባህር ማዶ ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ ከመገፍገፍ ያለፈ ምን ውጤት አስገኘ?
የቤት ኪራይ ቁጥጥርማ የባሰ ውስብስብ ነው፡፡
የኪራይ ተመን በካሬ ሜትር ሊተምን ነው? ወይስ በጣሪያ ቁመትና በኮርኒሱ አይነት? በመስኮቱ ስፋት ወይስ በበሩ ቁልፍ ዝገት፣ በመፀዳጃ ቤቱ አሰራር ወይስ በንጽህናው? በግንቡ ውፍረት ወይስ አይነት፣ የአፈር ወይስ የብሎኬት፣ የተቃና ወይም የተንጋደደ ግድግዳ አይቶ ነው ኪራይ የሚተምነው? በግቢው ሰላማዊነት ወይስ በሰፈሩ ጨለማነት፣ ለአስፋልት መንገድ ባለው ቅርበትና  ርቀት፣ ወይስ በጉራንጉሩ አይነት፣ የኮብልስቶን ወይስ ጭቃ የውስጥ ለውስጥ ቅያሶችን በማነፃፀር ነው? ወይስ፣ በትራንስፖርት ወጪውና አመቺነት? ወይስ…
ወይስ፣ ዋናው ቁምነገር፣ በዘፈቀደ እንዳሰኛቸው፣ ዋጋ የመተመን ስልጣን ማግኘታቸው ነው?
በካሬ ሜትር የኪራይ ዋጋ ከተተመነ በኋላ፣ ቤቱን ማደስ ይቅርና ቀለም ለመቀባት ፈቃደኛ የሚሆን ስንቱ ነው? ከዚያ ደግሞ በየመንደሩ እየዞሩ፣ በግቢው እየገቡ የቤት ስፋትና ይዞታ የሚመረምሩ፣ ትዕዛዝ የሚሰጡና ዋጋ የሚቆጣጠሩ፣ ሌላ እርባና ያለው ነገር ሳይሰሩ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሰዎችን ለመቅጠር፣ ስንት ገንዘብ ወጪ ይደረጋል? ቅንጣት ታህል ፋይዳ የሌለው፣ ከመነሻው “ለስኬት ያልተፈጠረ” የውድቀት ግርግር ነው የሚሆነው፡፡ “እልፍ ጥቃቅን የሙስና እድሎችን ለመክፈት ይሳካለታል” ካልተባለ በቀር ማለቴ ነው፡፡
ለማለት የፈለግኩት፤ የቤት ግንባታን በሚያደናቅፉ እልፍ መሰናክሎች ላይ፣ ሌላ ተራራ የሚያክል አዲስ ማሰናከያ መፍጠር እንደ ትክክለኛ ስራ የሚቆጠርበትና የሚፎከርበት የተበላሸ አስተሳሰብ ውስጥ ነው የምንኖረው:: ታዲያ ከአደናቂፊነትና ከአሰናካይነት መቆጠብ ቀላል ነው? ቀላሉ ስራ እጅግ ከባድ መሆኑም፤ የአገራችን ችግር ምንኛ ሥር የሰደደ እንደሆነ ያሳያል፡፡

Read 5503 times