Monday, 09 September 2019 11:15

ፖለቲካ እና እግር ኳስ

Written by  ከተካ አሰፋው ይልማ (የቀድሞው የቴሌ ስፖርት ክለብ ፀሃፊ)
Rate this item
(0 votes)

 ከአገራችን የእግር ኳስ አንኳር ችግሮች መካከል፤ የእግር ኳስ ዓላማና ግብ ግንዛቤ እጦት፣ የአደረጃጀት ችግር፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት፣ ውጫዊ ጫና እንዲሁም የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የፖለቲካ ዝግመት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡
ግብና ዓላማ
ኳስ መረብ ውስጥ ገብታ መሬት ስታርፍ በመደሰት፣ በመጨፈር ከዚያም የማይሞተውን ጊዜ ገድሎ ተዝናንቶ ወደ ቤት መግባቱን እንደ የእግር ኳስ የመጨረሻ ምዕራፍ የሚቆጥሩ በርካቶች ናቸው። የሚቆጠሩት ግቦች መንፈሳዊ እሴቶች ሲሆኑ የዛሬ ሽንፈት ነገም ሌላ ቀን ነው በሚል እሳቤ፣ በህይወት ውጣ ውረድ ውስጥ ታግሎ  የማሸነፍና ለቀጣይ የማነሳሳት ታላቅ ኃይል አለው፤ እግር ኳስ።
ለዚህም ሊቨርፑል ከኢሲ ሚላንና ከባረሶሎና ጋር በመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች በበርካታ ግቦች በመሸፉ ምክንያት ብዙዎች በቀጣይ ጨዋታዎች ውጤቱን መቀልበስ ይከብደዋል ቢሉም፣ ወጤቶቹን ቀይሮ ሁለቱንም የአውሮፓ ሻምፒዮን ዋንጫዎች በተለያዩ ወቅቶች በእጁ ማስገባቱን እንደ አብነት መውሰድ ይቻላል። ዋንጫውን ማግኘት ሳይሆን ውጤቱ ከተጫዋቾቹና ደጋፊዎቹ አልፎ ለተቀናቃኝ ቡድን ተጫዋቾችና ደጋፊዎች እንዲሁም ለኛም ጭምር የሊቬርፑል ውጤት የተስፋ ትርፍ አስገኝቶልናል ማለት እንችላለን።
ጋዜጠኛ ማርቆስ ኤልያስ ምን ተይዞ ጉዞ በሚል እሳቤ በተለያዩ ወቅቶች፣ “እግር ኳስ ላንተ ምንህ ነው?” በማለት ጥቂት ተጫዋቾችን ጠይቆ ያገኛቸው መልሶች ተመሳሳይና በጣም ውስን ነበሩ። ማንም ሰው ለሚያከናውነው ሥራ ስንቅ የሚሆነውን የጠለቀ እውቀት ይዞ ካልተንቀሳቀሰና እውቀቱ ከተገደበ ብዙ መጓዝ እንደማይችል የአገራችን እግር ኳስ ማሳያ ነው። በአሁኑ ወቅት እግር ኳስ ለአንድነት ለወዳጅነት፣ ለጤንነት እንዲሁም ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ባጠቃላይ ለአገር ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካ እድገት እጀታ አለው ማለት የሚችሉ ውስን ናቸው። የሰው ልጅ አፈጣጠር በምክንያት እንደመሆኑ መጠን የሰው ልጅ ከማህፀን ጀምሮ በእንቅስቃሴ ላይ ነው።
የአደረጃጀት ችግር
የእግር ኳስ በአገር ግንባታ ረገድ የሚኖረውን አዎንታዊ ጠቀሜታ በመረዳት መንግስት እግር ኳስ ራሱን ችሎ እስኪቆም ለተጫዋቾች የደሞዝ ክፍያ በዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደርጋል። ሆኖም ግን ይህ  ከፍተኛ ገንዘብ በምላሹ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚተርፍ ገንዘብ እንኳን ባያስገኝ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ባለመሆኑ፣ የአገሪቱ የክለቦች ኃላፊዎች ገንዘቡን ያለ አግባብና ያለ እውቀት እያባከኑት ስለሆነ፣ መንግስት የክለቦችን አደረጃጀትና አወቃቀር ከፖለቲካ በራቀ መልኩ እንደገና እንዲደራጁ የማድረግ ኃፊነት አለበት፡፡    
አደረጃጀት ከዓላማና ግብ ይነሳል። በቀጣይ ዓላማና ግብ ማሳኪያ የስትራተጂ እውቀት ይጠይቃል። በአገራችን የእግር ኳስ ሲቋቋምና ሲደራጅ በቅድሚያ አዋጭነቱ ተጠንቶና ተፈትሾ ሳይሆን በጨበጣና የህዝብን ገንዘብ ተማምኖ በዘፈቀደ ስለሆነ፣ ፌደሬሽኑ የፊፋና የካፍ የብቃት መለኪያዎች በእጁ ላይ ቢኖርም፣ እናንተም ሃብት የምታመነጩበት ተጨባጭ ”ስትራተጂ” አቅርቡ ተብለው ስለማይጠየቁ፣ ትናንት ተቋቁመው ዛሬ የሚፈርሱ ክለቦች እየተበራከቱ ነው።
በአገራችን አፍራሽ ፖለቲካ፣ የፌደሬሽንና የክለቦች አደረጃጀቶችን ከጅምሩ አንስቶ መቆጣጠር ስለሚጀምር፣ ፖለቲካ እግር ኳስ ውስጥ መግባቱ  የማይቀር መሆኑ የገባቸውና ፖለቲካውን ፍራቻ ሽሽትን የማይመርጡ፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን መክተውና ገርተው፣ እሳቱን ፖለቲካ ውሃ ሆነው የሚያጠፉ፣ በአጠቃላይ በስፖርት ዙሪያ አዲስና የዘመነ  አደረጃጀት ለመፍጠር አቅም ያላቸው ባለሙያዎች በባትሪም ቢሆን መፈለግ አለባቸው።
የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት
የተገራ ፖለቲካ ሌላው ቀርቶ ድንጋይ ውስጥ ገብቶ ድንጋዩን ፎቅ ያደርገዋል፣ ድልድይ ተሠርቶ ህዝብ ይገናኝበታል ወዘተ. ያልተገራውና ተራ ፖለቲካ ደግሞ  እየተወረወረ ሄዶ ሰውና ንብረት ላይ እያረፈ ጉዳት ሲያደርስ የሚታዘቡ፤  “ኦ! ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ነው” በማለት የማይሸሸውን ፖለቲካ ለመሸሽ ይሞክራሉ። ምንም እንኳን ፖለቲካ እግር ኳስ ውስጥ መግባት የለበትም የሚሉ በርካቶች ቢሆኑም፣ ፖለቲካ ሁለገብ ስለሆነ ኳስ ውስጥ አግባብ ባለው ሁኔታ መግባቱ የግድ ነው። ነገር ግን አፋር በተካሄደው ምርጫ፤ ፖለቲካው ጣልቃ ገብቶ፣ አግባብ በሌለው ሁኔታ ለፈደሬሽን የሚመረጡትን ስም ዝርዝር ከምርጫው ቀደም ብሎ ማየቱን አንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በሚዲያ አጋልጧል።
ፖለቲካ እግር ኳስ ውስጥ የመግባቱ ጉዳይ አዲስ አይደለም። ዝናው የናኘው የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግና ሌሎችም ዘንድ  እንደኛ ገንኖ አይውጣ እንጂ ውስጡ በዘረኝነት ፖለቲካ የበሰበሰና ከእነ ጆን ባረነስ ጀምሮ ጥቁር ተጫዋቾችን እያስመረረ የሚገኝ ነው።
የንጉሱ የዘውድ ዋንጫ በኤርትራና በሸዋ ጠቅላይ ግዛቶች ምርጥ ቡድኖች መካከል ሲደረግ የፖለቲካ ውጥረት ነበረው። የኤርትራና የሸዋ ጠቅላይ ግዛቶች ደጋፊዎች ከጥላቻ የመነጩ የሚዘገንኑ የስድብ ቃላትን ይለዋወጡ ነበር። የሸዋና የኤርትራ ምርጥ ተጨዋቾች አዲስ አበባ ስታድዬም ተደባድበዋል። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል በተካሄደ ጦርነት ከሁለቱም ወገን ብዙ ሰው አልቋል። በመጨረሻ ኤርትራ ለመገንጠልዋ የስፖርት ፖለቲካውም አስተዋፅኦ ነበረው። አሁን በባሰ መልኩ በክልሎች መካከል እየታየ እንዳለው መቆራቆዝ፣ በተቀናቃኞቹ በሐማሴንና በአካለጉዛይ ቡድኖች መካከል በአውራጃ  የበላይነት ምክንያት ረብሻና የውጤት ዘረፋ ተካሂዷል።  
በደርግም ቢሆን በአብዮቱ ምክንያት በመለዮ ለባሹ ክፍልና ሲቪሎች  መካከል ከፍተኛ ሽኩቻ ነበር። እነ ትግል ፍሬ  የመለዮ ለባሾች ቡድኖችን  ሲያሸንፉ፣ ሲቭሉ በደስታ ጋዜጣ ሲያበራ እየተቀማ ፊቱ ላይ ሲለኮስ አይተናል። ድብድብ ሲነሳና ሲቪሉ ሲያይል፣ ሲቪል የለበሱ መለዮ ለባሾች ሽጉጥ ሲመዙና ሌሎችም ጉድ የሚያሰኙ ክስተቶችን ታዝበናል።
ያለ ፖለቲካ ህይወት እንደማይኖር የግንዛቤ ችግርና የመደብ ጥቅም እንዳይቀር መሸሽ የማይቻለውን ፖለቲካ እንደ መጋተር ሰንካላ ምክንያቶችን በመፍጠር ለማፈግፈግ መሞከሩ፣ መንግስት በምሬት በጀት አቆማለሁ ወይም እግር ኳሱ ሊቆም ይችላል እንዲል አድርጎታል፡፡ በእርግጥም የ”ሸገር” ስፖርት አዘጋጁ አበበ ግደይ እንዳለው፣ የክለብ አመራሮች፣ “ረግጠው” ስላልሰሩ ችግር ተፈጥሯል።
ፖለቲካ እግር ኳስ ውስጥ ገብቶ እየፈጠረ ያለውን ችግር መፍታት የሚቻለው ”እሾህን በእሾህ ”እንደሚባለው፣ በራሱ በፖለቲካ ስለሆነ፣ ፖለቲካን መሸሽ ሳይሆን ጠንቅቆ በማወቅ፣ በገንቢ ፖለቲካ አፍራሽ ፖለቲካን መገደብ ነው የሚበጀው:: በቆራጥነት በመታገል አፍራሽ ፖለቲካውን በገንቢ ፖለቲካ በመታገል፣ ተቋማትን በተግባር ነፃ ማውጣት የተቻለበት ተሞክሮ አለና፡፡
የውጪ ጫና (DSTV)
እ.ኤ.አ ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ FIFA በሸራተን ባዘጋጀው  የUnity-Come sminar ላይ የወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈደሬሽን ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ፤”የDSTV ስርጭት የአገሪቱን እግር ኳስ እድገት እየተፈታተነ ነው” የሚል ጥያቄ ለፊፋ ሰዎች አቀረበ።  የዶክተር ጥያቄ፣ “ከሞኝ ደጅ አፍ ሞፈር ይቆረጣል” እንደ ማለት ነበር። ጥያቄው የፊፋና የDSTV ሰዎችን ቅር እንዳያሰኝና ወቅቱ የግሎባላይዜሽን ነው የሚል ሰበብ የፊፋ ሰዎች እንደሚደረድሩ ብገምትም፣ ጥያቄው የህዝብና የኔም ስለነበረ፣ ጊዜና ቦታን ጠብቆ መቅረቡ አስደስቶኛል፡፡
የእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ ታላላቆቹ  ቡድኖች ጨዋታ ሲኖራቸውና ጊዮርጊስና ቡናም ግጥሚያ ከሌላቸው ስታድዬሙ ተራቁቶ በበርካታ ጊዜያት አይተነዋል። ፈደሬሽኑና ክለቦች ማግኘት የሚገባቸውን ገቢ አጥተዋል፣ በዚህ ላይ ተጫዋቾች በህዝብ ድጋፍ ታጅበው ከሚጫወቱት ያነሰ ተጫውተዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጨዋታዎች በሥራ ቀን ስለሚደረጉና በተለይም የብሔር እግር ኳስ ጨዋታ እየሆኑ ስለመጡ፣ ለእግር ኳስ ሳይሆን ለፖለቲካ ረብሻ ሲል ተመልካች ተበራክቶ ሊሆን ይችላል።
የውጪው ጨዋታዎች በእግር ኳሳችን ላይ ከፍተኛ የሚባል ተጽእኖ ማሳደራቸው ሀቅ ስለሆነ  DSTV ማካካሻ ለአገራችን እግር ኳስ ድጋፍ  ማድረግ ያለማድረጉን  እርግጠኛ ባይኮንም፣ በቅርቡ ከብስራት ቴሌቪዥንና ሬድዮ ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ ስለተነገረ ይበል ያሰኛል። ሆኖም ግን  በቂ ነው ማለት አይቻልም። በነፃ ገበያና ግሎባላይዜሽን ሰበብ የአገራችን ገበያ ተቀምቷል፤ እግር ኳስችንም ተዳክሟል።
በጎረቤት አገር ህዝቡ በነፃ የሚያይበትና ከቤቱ ወጥቶ ባለማየቱ ምክንያት በወጣቱ መካከል ልዩነት ፈጥሮ የሚጫረስበት ሁኔታ እየተፈጠረ እንዳልሆነ በቅርቡ ከጎረቤት አገር የመጣ ወዳጄ አጫውቶኛል። በአገራችን ግን  DSTV የመደብ (class) ስለሆነ ተደራሽነቱ  ለጭቁኑ ህዝብ አይደለም። የDSTV ኪራይ ውድነት የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቤቱ ተቀምጦ ለማየት ስላላስቻለው፣ ወጣቱ ተሰባስቦ ከቤቱ ርቆ በሚመለከትበት ወቅት ወገን ለይቶ ስለት የተማዘዘበት፣ የተደባደበበትና የተጎዳዳበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ሁለት ወንድ ልጆቼ DSTV ማየት ካቋረጡ ድፍን ሃያ ዓመታት አልፈዋል። ለእግር ኳስ የነበራቸው ፍቅር ተሰልቧል። የተሰማው አዲስና አስገራሚ ዜና፣ በተለይ ያገራችን ወጣቶች፣ የእንግሊዝ ክለቦች ደጋፊዎች ከአገራቸው አልፈው ለውጪው እግር ኳስ ጎራ ለይተው ማህበር መስርተው መደራጀታቸው፣ የአገር ቤት እግር ኳስ ምን ይውጠው ያሰኛል።
የምዕራቡ ዓለም እግር ኳስ እንኳንስ አኛን ሊጠቅም ቀርቶ የፕሪሜር ሊጉ ጨዋታ በድምቀት የሚካሄድባት እንግሊዝ፣ በዓለምና በአውሮፓ ዋንጫ ላይ የምታስመዘግበው ውጤት ይህን ያህልም አስተዋጽኦ አለው ማለት አይቻልም። በሌላ በኩል እግር ኳሱ በዝውውር የተሳከረ ነው። በዝውውር የሰከረው እግር ኳስ እየጠቀመ ያለውም አገሬውን ሳይሆን  የውጪ ባለሀብቶችን ነው።
ግብፃዊው የሰሚናር አሳታፊ የዶክተርን ጥያቄ ወደ እለቱ የሰሚናሩ አምባሳደር ወደ ዛምቢያዊው ካሉሻ መራው፡፡ እንደተባለው ካሉሻ ጊዜው የግሎባላይዜሽን ስለሆነ ፈደሬሽኑ የራሱ የሆነ አካሄድ መከተል እንዳለበት፣ የአገሩን ፈደሬሽን አካሄድ  ልምድ ቢያቀርብም፣ የፊፋን ሰዎች ቅር ላለማሰኘት እንጂ ያቀረበው አማራጭ አዋጪ እንዳልሆነ ከአቀራረቡ ያስታውቅ ነበር።
DSTV የተጫዋቾችና የአሰልጣኞችንም ልፋት ከንቱ አስቀርቷል። የውጪውን ዓለም  ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ኑሮ ምጥቀት ግምት ውስጥ ባላስገባ መልኩ፣ ያገር ቤት ተጫዋቾች “ዝቆሽ ቢከፈላቸውም የDSTV ዓይነት ጨዋታ ማየት ስላልቻልን ክፍያቸው በዛ ይቀነስ፣” የሚል ቅስቀሳ ተካሂዶ የተጨዋቾች ክፍያ ተቀንሷል።
DSTVን አይጠቅምም እርኩስ ከመአሪዮስ ለማለት ሳይሆን ወይም አንዳንድ አገሮች እንደሚያደርጉት ተቀድቶ በሌላ ወቅት ይታይ ማለት ከማይቻልበት ደረጃ ስለተደረሰና ለዛውም ስለሚጠፋ ይገራና፣ በእንግሊዘኛው እንደሚባለው win win ይሁን ለማለት ነው።  ሌላው ቢቀር ኪራዩ ተቀንሶ ተደራሽነቱ ቢሰፋና ወጣቱ በየቤቱ ሆኖ ቢመለከት፣ በወጣቱ ዘንድ በየአውራ ጎዳናው ያለውን ረብሻና ድብድብ ይቀንሳል፤ በለውጡ በወጣቱ ዘንድ ትቶት የሚያልፍ ቁም ነገር ይኖራል፤ DSTVም ከብዛት ይጠቀማል ለማለት ነው።
(ይቀጥላል)

Read 1027 times