Print this page
Monday, 09 September 2019 11:28

የአዲስ ዓመት ማስታወሻ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(7 votes)

 የዓለም ሕዝብ በየዓመቱ በታላቅ ደስታ ከሚያከብራቸውና ከሚዘክራቸው በዓላት መኻከል አንዱ የዘመን መለወጫ በዓል ነው፡፡ ዕለታት እየበረሩ፣ ወራት እየተቀመሩ አልፈው አዲስ ዘመን በባተ ቍጥር ሕዝብ ዅሉ ፍሥሐ ያደርጋል፡፡ ሰላምን፣ ብልጽግናን፣ ጤንነትን፣ ፍቅርን፣ … ለወዳጅ ዘመድ ይመኛል፡፡ አዲሱ ዓመት ዘመነ ሰላም፣ ዘመነ ጥጋብ … እንዲኾን መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡ አዲስ የሥራ ዕቅድና ምኞትን በስሜቱ ያሠርፃል፡፡ ወደ ተግባርም ለመተርጐም ሌት ተቀን ይፋጠናል:: በአገራችን ኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ በዓል መስከረም ፩ ቀን ይከበራል፡፡ ‹‹ለመኾኑ በኢትዮጵያ መስከረም የአዲስ ዓመት መባቻ ኾኖ የተመረጠው ለምንድን ነው? በአራቱ ወንጌላውያንና በአራቱ እንስሳ (ኪሩቤል) መካከል ያለው የስያሜ ትሥሥርስ ምሥጢሩ ምንድን ነው?›› የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአእምሯችን ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ለነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ በአንድ ወቅት እነዚህን ጥያቄዎች አቅርቤላቸው  እንደመለሱልኝ፤ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በመስከረም የሚያከብሩት ከኖኅ በፊትና በኋላ በተዘረጋው ስሌተ ዘመን እንደ ኾነ በማስረዳት የሚከተለውን ትምህርት ሰጥተዋል፡-
የኢትዮጵያ ይዞታ መሠረተ ባሕርይ ከጥንት ጀምሮ ሃይማኖት ሲኾን፣ በጽሑፍም በአፈ ታሪክም እየተወራረሰ የመጣ ነገር ነው፡፡ በሰው ፍልስፍና ወይም በመንግሥት ለውጥ ምክንያት የተናወጠ ነገር የለም፡፡ ለውጦች ጦርነቶችና ግጭቶች፣ በተለያዩ የመንግሥት መሪዎች ቢፈራረቁም መሠረተ እምነትን አልነኩም፡፡ የአገሪቱን ባህልና ታሪክ የሚነካ ለውጥ አልደረሰም፡፡ ነገር ግን ባለ ሥልጣናት በሹም ሽር ሲቀያየሩ በምርጫ የመንበረ መንግሥት መቀመጫ ቦታ ልውውጥም ሲደረግ መጥቷል፡፡ አዲስ ዓመት ከጥንት ከአዳም ጀምሮ የነበረ በዓል ነው፡፡ ከአዳም ጀምሮ የመጣውን የቍጥር ዘመን በጽሑፍ ያስተላለፈው ሄኖክ ነው፡፡ ይኸውም ሳምንታት በፍጥረት ከእሑድ እስከ ቅዳሜ ሰባት፣ የዕለት ሰዓት ሃያ አራት፣ የወር ቀናት ሠላሳ፣ የዓመት ቀናት ሦስት መቶ ስልሳ አራት ሲኾኑ፣ ስልሳ አምስተኛዋ መዛወሪያ ቀን ናት፡፡ ጳጕሜን አምስት ቀን ስትኾን የሚዘለው ስድስተኛው ቀን ሠግር (የወር መባቻ) ይኾናል፡፡
የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር ከጥፋት ውኃ በፊት ሦስት ትውልዶችን አሳልፏል፡፡ እነርሱም ሄኖክ፣ ላሜህና ኖኅ ናቸው፡፡ ኖኅ የሰው ልጆች ዅሉ አባት እንደ ኾነው እንደ አዳም የሚቈጠር ከጥፋት ውኃ በመጨረሻ የተረፈ አባት ነው፡፡ ኖኅ ከአባቶቹ የተቀበለውን ጥበብ ዅሉ ለልጆቹ አስተላለፈ:: ለአብነትም ዛሬ የምንጠቀምበት የኮሶ መድኃኒት የኖኅ ተረፈ ጥበብ ነው፡፡ ኖኅ በሰኔ ወር ከመርከብ በወጣ ጊዜ የበግ መሥዋዕት ሠውቶ፣ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀ፡፡ እግዚአብሔርም ያን ጊዜ ከኖኅ ጋር አዲስ ቃል ኪዳን መሠረተ፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ልቡ ምንም ክፉ ቢኾንና ቅጣትም የማይቀርለት ቢኾን፣ ጨርሶ እንደማያጠፋው ለኖኅ ቃል ገባለት፡፡ ምልክቱንም የቀስቱን ደጋን ወደራሱ፣ ገመዱን ደግሞ ወደ ሰው ልጆች አድርጐ በደመና ላይ ቀስት ስሎ አሳይቶታል፡፡
ጌታ ‹‹መዓልትና ሌሊት፣ በጋና ክረምት፣ ብርድና ሙቀት፣ ዘርና መከር ጊዜያቸውን ጠብቀው ሲፈራረቁ ይኖራሉ፡፡ በምድር ላይ ይህ አይቀርም›› በማለት እንደ ተናገረው፣ በቃሉ መሠረት ክረምት ገባ፡፡ ክረምቱ ካለፈ በኋላ የዓመት መሥፈሪያ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በመኾናቸው፣ መስከረም አንድ ቀን የአዲስ ዓመት መባቻ ኾነ፡፡ አዲስ ዓመት ሥራውን ጨርሶ በሔደ ቍጥር፣ ዕለት ግን በየጊዜው እየታደሰ ይሔዳል፡፡ እስከ አዲስ ኪዳን መጀመሪያ ድረስ አበው በልዩ ልዩ ጊዜያት የተገለጹላቸውን ምልክቶች በመያዝ የየዘመናትን ብተት (መግቢያ) የእግዚአብሔርን ዙፋን ተሸካሚ በኾኑ በኪሩቤል መላእክት እያመሳሰሉ ገጸ ሰብእ፣ ገጸ ላህም (ላም) ገጸ ንሥር (አሞራ)፣ ገጸ አንበሳ እያሉ ዓመታትን ይመድቡ ነበር፡፡ ከስብከተ ሐዲስ በኋላ ግን ይህ ተሽሮ ወንጌልን በጻፉት አርድእት ስም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ ስም ተሰየመ፡፡ ወንጌላውያኑ ወንጌልን ሲጽፉ፤ ዕለት ተቀደም (በቅደም ተከተል) ነውና ተራቸውን ጠብቀው በየዓመቱ ይመላለሳሉ:: ይህም ማለት ዘመኑ ዘመነ ምሕረት መኾኑን ለማብሠርና ድኅነት (መዳን) የሚሰበክበት ዘመን መምጣቱን ለመግለጽ ነው፡፡
በገጸ ሰብእ የተተካው ማቴዎስ ነው፡፡ ምሥጢሩም ‹‹ጌታ ከሰማይ ወረደ፤ ሰው ኾነ›› ብሎ ማስተማሩን የሚያመለክት ነው፡፡ በገጸ አንበሳ የተተካው ማርቆስ ነው፡፡ ይኸውም አሕዛብ በግብጽ (ምሥር) በላህም (በላም)፣ በጣዕዋ (ጥጃ) አምሳል ጣዖት አሠርተው ያመልኩ ስለ ነበር ያንን አምልኮ አጥፍቶ፣ ሽሮ በክርስቶስ እንዲያምኑ ስላደረገ ነው፡፡ በገጸ እንስሳ (ላህም) የተተካው ሉቃስ ነው፡፡ ምሳሌነቱም የጌታን መሥዋዕትነት ስለሚያስተምር ነው፡፡ በገጸ ንሥር የተተካው ዮሐንስ ነው፡፡ ንሥር ከአዕዋፍ ዅሉ መጥቆ ይሔዳል፡፡ መሬትም ላይ ምንም ኢ ምንት ነገር ብትወድቅ አትሠወረውም፡፡ ዓይኑ ጽሩይ (ብሩህ) ነው፡፡ ይህም ማለት ቅዱስ ዮሐንስ ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቈጠር ወደ ነበረው ኹኔታ በሕሊናው ርቆ በመሔድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቀዳማዊ ቃል መኾኑን፤ እግዚአብሔርም ዓለሙን የፈጠረው በእርሱ ቃል እምነት መኾኑን፤ ያም ቃል ሰው መኾኑን ስለሚያስተምር ነው ገጸ ንሥር የተባለው፡፡ የሦስቱ ወንጌላውያን ትምህርት ታሪክ ጠቀስ ኾኖ፣ ለሰሚዎችና አንባቢዎች ዅሉ በቶሎ ሲረዳ፣ የዮሐንስ አስተምህሮ ግን ጥልቅ የአእምሮ ብስለትና ምርምርን ይጠይቃል፡፡
ዘመን በተለወጠ ቍጥር ከሰው ልጆች ስሜት ጋር አብሮ የሚንቀሳቀስ ተስፋ አለ፡፡ በጥፋት ዘመን ሰማይ በደመና ተሸፍኖ፣ ከላይ ዝናም፣ ከታች የሚፈልቀው ጎርፍ የኖኅ ሰዎችን አስጨንቋቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ምድር ላይ ለውጥ ታየ፡፡ ነፋስ ነፈሰ፡፡ ብርሃን ፈነጠቀ:: አበባ አበበ፡፡ የኖኅ መልእክተኛ የኾነችው ርግብም ‹‹ማየ አይህ ነትገ፤ የጥፋት ውኃ ጐደለ›› እያለች ርጥብ ቄጠማ በአፏ ይዛ መጥታ ስታበሥረው፣ የኖኅ ሰዎች ከመርከቧ ወደ መሬት ሲወርዱ በመጀመሪያ አበባ፣ እንግጫ፣ ቄጠማ፣ የለመለመ ሣር … አገኙ፡፡ እግዚአብሔርንም በአንቃዕድዎ ልቡና አመሰገኑና በዓላቸውን አከበሩ፡፡ በዚህም አምሳል ክረምት አልፎ መሬት በምታሸበርቅበት በምታብበት ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ አዲስ ዓመታችንን እናከብራለን፡፡ ሰውም ከመሬት የተገኘ በመኾኑ እንደ ዕፀዋትና እንደ አበቦች ዅሉ በመስከረም ወር በተስፋ ስሜት ይለመልማል፡፡ ያጣው አገኛለሁ፣ የታመመው እድናለሁ ብሎ በቁርጥኝነት ይነሣሣል፡፡ በዘልማድም እምነቶች ይገለጻሉ፤ ‹‹በዮሐንስ እረስ፣ በማቴዎስ እፈስ … ጳጕሜ ሲወልስ ጎታህን አብስ … ጳጕሜ ሲበራ ስንዴህን ዝራ›› እያሉ ገበሬዎች ይናገራሉ፤ ይተነብያሉ፡፡ ገበሬዎች ገና በግንቦት ወር የክረምቱን አገባብ ለይተው የሚዘሩትን ዘር ደንብተው የሚያውቁ ሜትሮሎጂስቶች (የአየር ጠባይዕ ትንበያ ባለሙያዎች) ናቸው፡፡
አለቃ አያሌው እንዳስተማሩት፤ ዐውደ ዓመት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ መሠረት የሚከበርና መንፈሳዊ ምሥጢር ያለው ሃይማኖታዊም አገራዊም በዓል ነው፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ በዓል በቤተ ክርስቲያን ከሚፈጸመው መንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር በአዲሱ ዓመት ዋይዜማ በየቤቱ ጨፌና ቄጠማ ይጎዘጎዛል፡፡ አበባ በሥርዓቱ እየተዘጋጀ በየቦታው ይቀመጣል:: ልጆችና አረጋውያን አዳዲስ ልብሳቸውን ለብሰው በደስታ ይፈነድቃሉ፡፡ አመሻሽ ላይ ችቦ አቀጣጥለው ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ … ኢዮሃ የበርበሬ ውኃ … በሸዋ በጎንደር፣ በትግራይ በወሎ፣ በሐረርጌ፣ በሲዳሞ … ያላችሁ እንዴት ከረማችሁ? እንኳን ከዘመን ዘመን ከጨለማ (ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ) ወደ ብርሃን (መስከረም) በሰላም አሸጋገራችሁ! … እንጉሮ ገባሽ በያመቱ ያምጣሽ …›› እያሉ ያቀጣጠሉትን ችቦ በአየር ላይ እየወረወሩ ደስታቸውን ሲገልጹ፣ የምሽቱም የችቦ እሳት ርቀት እስከሚወስነው አድማስ ድረስ ከቀዬ ቀዬ፣ ከአድባር እስከ አድባር፣ ከመንደር እስከ መንደር … ሲንቀለቀልና ሲንቦገቦግ መሬት የእሳት ላንቃዋ ተከፍቶ ነበልባል የምትተፋ ትመስላለች፡፡ የአየር ላይ ወጋገኑን ሲመለከቱት ደግሞ እግዚአብሔር ከመንበረ ጸባዖቱ ወርዶ፣ የብርሃን አክሊል ደፍቶ፣ ቀይ መጐናጸፊያ ተጎናጽፎ፣ ጨለማውን እየገፈፈ፣ በጠፈር (በአየር) ላይ እየተንሳፈፈ ወደ መሬት የሚወርድባት የመጨረሻዋን የምጽአትን ቀን ታስታውሳለች – የዕንቍ ጣጣሽ ሌሊት፡፡
አባቶች የችቦ ብርሃን ላሰባሰበው ሕዝብ ቡራኬና ምርቃት ያደርጋሉ፡፡ ‹‹የተዘራውን እኽል እኽለ በረከት፣ የዘነመውን ዝናም ዝናመ ምሕረት፣ ዘመኑን የሰላም ዓመት ያድርግልን፡፡ እኽል ይታፈስ፤ ይርከስ:: ሳቢ በሬው፣ አራሽ ገበሬው ይባረክ፤ ቁንጫ፣ ተባይ ተምች፣ አንበጣ … ፀረ ሰብል ዅሉ እንደ ችቦው ተቀጣጥለው ይንደዱ…›› እያሉ ይመርቃሉ:: እናት አባት በልጆቻቸው፣ በወዳጅ ዘመዶቻቸው የተበረከተላቸውን የእንግጫ ጉንጉን በራሳቸው፣ በእንጀራ ማቡኪያና መሶቡ፣ ከቤቱ ምሰሶ ላይ … ያሥራሉ፡፡ ይህ በአበባ የተዘጋጀ የእንግጫ ጉንጉን፣ የመስቀል ደመራ ዕለት ከእሳቱም ከዐመዱም ላይ ይጣላል፡፡ ተምሳሌቱም እንደ ቁንጫ ዅሉ ቁርጥማቱ ራስ ምታቱ፣ ምችጎንፍ ቁርጠቱ፣ ምቀኛ፣ ሸረኛ፣ ሰላቢው፣ ሌባ፣ ቀማኛ ቀጣፊው … እንዲቃጠልና እንዲጠፋ ነው፡፡ በቤቱም (በአባወራው ቤት) በረከትና ሞገስ (አግሟስ) እንዲቀርብም ነው፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!

Read 4076 times