Monday, 09 September 2019 11:55

የሚያተኩሱ ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

ግጥም በስሜት እየናጠ፣ ሀሳብ ሰብስቦ፣ በዜማ ጥፍጥና ወደ ጆሮና ነፍስ የሚደርስ ጥበብ ነው:: ይሁን እንጂ ስሜት ብቻውን ግጥም አይሆንም፡፡ ኢ. ኤ. ግሪኒንግ ላምቦርን የሚሉትም እንደዚያ ነው፡፡ እኔም በዚያ እስማማለሁ፡፡ ማዕበል ያናወጠው ባህር ሁሉ አሳ ይዞ ብቅ አይልምና።
ሀሳብ በስሜት ውስጥ ሊሳሳና ሊደድር እንደሚችል ግን መናገር ይቻላል። አንዳንዴ በሰከነ ስሜት ከፍ ያለ አተያይ፣ የረቀቀ ስልት፣ የሚኮረኩር ቋንቋ፣ የጠነነ ምናብ ሊነጠብ ይችላል፤ አንዳንዴ ደግሞ ተቃራኒው፡፡
የዘላለም ገበየሁ ‹‹በገሃነም ሥር መፅደቅ›› የሚለውን የግጥም መጽሐፍ ሳነበው፤ የስሜት ሃያልነት የከባቢ ጠረን፣ የዘመን ሀሳቦች ጠረን አይቼበታለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ‹‹ዳሞትራ›› የሚል የግጥም መጽሐፍ ያሳተመው ይህ ወጣት ገጣሚ፤ ጥሩ ጥሩ ሀሳቦች መንቀስ፣ ዜማው ባልተናጋ ስልትና በልከኛ/አጫጭር አርኬዎች ማስቀመጥ እንደሚችል ታዝቤአለሁ፡፡ በሚያዝናና ስሜት፣ የቆረፈዱ ሀሳቦችንና ምሬቶችን ለአንባቢ በማድረሱ ተደስቼ ነበር፡፡ ብዙ የግጥም ሊቃውንት እንደሚስማሙበት፤ የግጥም ግቡ መፈላሰፍ ወይም መስበክ ሳይሆን ነፍስን ወደ ፈንጠዝያ ማሳፈር ነውና ‹‹ዳሞትራ›› እንዲያ ነበር፡፡
አዲሱ መጽሐፉ ግን እንደ ‹‹ዳሞትራ›› አይደለም፤ አንዳንዴ በቁጣና ምሬት ትካዜው አፍጥጦ ይታያል:: አጥንቱ ላይ ያለበሰው ሥጋ የአደይ አበባ ያህል ቀለሙ አልደመቀም፣ የህጻን ልብ ያህል ጣፋጭ ሳቅ አልሳቀም፡፡ ግን ደግሞ ለዛ ቢስና አስቀያሚ አይደለም፤ ኮርካሪ ስሜቶች ያንጠለጠሉት ወዛም ጥበብ አለው፡፡ እስቲ የተወሰኑትን እንይ፡-
‹‹አማራነት ዛሬ››
የሚዘርፉት አልማዝ የሚያፈርሱት አድባር
የሚሸጡት ርስት የሚያደርቁት ባህር፡፡
***  
ጠባቂ ያጣ ዛፍ የሚቆርጡት ዋርካ
የሚያረግፉት ቅጠል የሚያሄዱት ጫካ፡፡
***
በገነባት አገር ጧት ማታ ’ሚገደል
የተረሳ ታሪክ የተናቀ ገድል፡፡
(አማራነት ዛሬ)
ገጣሚው ሀዘን ውስጥ ነው፡፡ ‹‹አማራ››ን በለዋጭ ዘይቤ ውስጥ እየሳለ፣ ብሶቱን ቁጭቱንና ክሱን በስንኝ ዜማ ይዘምራል፡፡ ወይም ግራና ቀኙን ይወቅሳል፡፡ ይህ የገጣሚው የራሱ ሀቅ፣ የግሉ ሚዛን ነው። ምናልባትም ገጠመኞች ሊጠቅስ፣ ታሪክ ከወደ ኋላ ሊተነትን ይችላል፡፡ ብቻ ሀሳቡን እየተነፈሰ ነው:: የጋለ ልቡን ወላፈን በስንኝ ቋጥሮ ለአንባቢው በዜማና በውበት ማዕድ እየፈተፈተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከቅርብ ጊዜው የፖለቲካ አየር፣ የአገሪቱ የለውጥ ማዕበልና የብሔር ግጭቶች ቀለም የሰጠው ሀሳብ ነው፡፡
ግጥም እንዲህ ነው፤ ከስሜት ይነሳና በስሜት ንፋስ ውስጥ የጊዜውን ቀለም ያሳያል፤ የትርታውን ከበሮ ይደልቃል፡፡ የዘላለም ግጥሞች ባብዛኛው የፖለቲካ ደጅ የሚያንኳኩ፣ ብሶት የሞላባቸው ናቸው፡፡ ቢሆንም ማስጠሎና ምንቅርቅር አይደሉም:: አስተዋይ ሀሳቦችም አሉት፡፡
‹‹ሀገሬ መልሽ?!››
ጥቁር አፈር ይዘሽ ሳይቸግር ማዕድኑ
ልጅሽ ለምን ከሳ? ለምንስ ሳሳ ጎኑ?
ድህነት ’ሚባል ትልቅ ባላጋራ
ምነው አብሮ ኖረ ከልጆችሽ ጋራ
በአጉል ወሬ ናዳ በጭምብል ተጋርደን
በጥላቻ ናውዘን ፍቅር ገድለን ሄደን
ምንድነው ትርፋችን
በባዶ ቤታችን??
በማለት… ለምን ባዶ ሆንን እያለ ነው፡፡ የዳዊት ልጅ አምኖንን አፍቅሮ በየዕለቱ ሲከሳ ‹‹የንጉሥ ልጅ ሆይ ለምን ከሳህ?›› እንዳለው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ፤ ምንም ሳናጣ ለምን ከሳን? ለምን ሳሳን? ድህነት ለምን በቆርፋዳ እጆቹ አቅፎ ያንገላታናል?... ለምን በገጠጠ ጥርሱ ይነጨናል?... እያለ አገሩን ይጠይቃታል። በወሬ ናዳ እየፈረሰች፣ በፍቅር ረሀብ የምንሳቀቀው ልጆችዋ፤ የጥፋቱ ሁሉ መነሾ ራሳችን ነን፤ የምናገኘው ትርፍ ግን ምንድነው? የሚል አንደምታ አለው፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ቤታችን ባዶ ነው፤ በባዶ ቤት ምን ያናጨናል? በሚል ቁጭት ከንፈሩን የሚነክስ ይመስላል፡፡ ግጥሙ ሊሪክ ስለሆነ ስሜቱ ላቅ ያለ፣ ቁጭቱ የመረረ ነው፡።
‹‹ሞት ወይም ሕይወት››
ህዝቤ ሲያሳድዱት ለምን ይሰደዳል
ንብረትና አድባሩን ለምን ጥሎ ይሄዳል?
ንገሩት ወገኔን
እንደያዙት አሳ ባህር እንደከበደው
በሞቱ ብቻ ነው የሚድን ከፍዳው፡፡
ይህም ግጥም ባሳለፍነው አንድ አመት ውስጥ ያለውን አታካች ስደትና መፈናቀል የሚያሳይ ነው፡፡ ‹‹ከዚህ ኑሮ ሞት ይሻላል!›› የሚል ይመስላል፡፡ ሰው የኖረባትን ቀዬ፣ ንብረቱንና ደብሩን ለቅቆ ከሚሄድ፤ ከዚህ ፍዳ ይልቅ ሞት መቅመስ ከሰቀቀን መዳን ነው አይነት ነው፡፡ ግጥሙ አሁንም በሬት የተነከረ፣ እንባ ያነቀው ነው፡፡ ግን ደግሞ የምንኖርበት በአይናችን ያየነው፣ በጆሯችን የሰማነው ሀቅ ነው። አንድ የስነ ግጥም ፕሮፌሰር፤ ‹‹ምሬትን ሀዘንንና ልቅሶን ወደ ዘና አርጌ ለውጦ ሞቱን በተስፋ ቀለም ለብጦ ማቅረብ የጥሩ ገጣሚ ሚና ነው›› ይላሉ፡፡ ቀጥታ እየጎፈነነ እየቧጠጠ ባይሆን ይመረጣል፡። ዘላለም፤ እንደ ‹‹ዳሞትራው›› ዘመን ሁን ባይባልም፣ የተስፋ ጥርሶቻችንን፣ የፈገግታችንንና የነገአችንን ቀለም፣ ፅልመት ጥርስ ላይ አትሰካቸው መባል አለበት፡፡
የደረቁ የሀሳብ ገፆችን በሌላ የሕይወት መልክ የገለጠበት በቀጣዩ ግጥም አይነት ለዛ ጠምቋቸዋል:: (ግን ጥቂት ሆኑ)
ከከንፈሮችሽ ዳር እድሜ ይወለዳል
ከእቅፍሽ ሲያነጉ መሞት ይሰደዳል
በጭኖችሽ መሀል ገነት ተገንብቷል
የፀደቀው ብቻ የኔ ገላ ላልቷል
ሀጣን ተዳፍረውሽ ሰብረው እንዳይገቡ የገነትሽን በር
የኔ ውድ ቅጠሪኝ ስጠብቅሸ ውዬ  ስጠብቅሽ ልደር፡፡
ይህ የፍቅር ፍካሬ፣ የፍቅር አለም ውበት ነው:: የአለምን ኮተት አስጥሎ በገነት ወንዞች ዋና የሚያስተምር ሊቅ! ሞትን እየገረፈ የሚያባርር የሕይወት ንጉስ! ሀጢአን የማይደፍሩት፣ በቅድስና የተጠበቀ የድድቅ ቅጥር! ከከንፈሮችዋ ማህጸን ውስጥ እድሜ የሚያረዝም መድሃኒት የሀሴት ነበልባል ብቅ ይላል፡፡ አለም መአዛዋን ትቀይራለች፡፡ ታዲያ ይህቺ የሕይወት ቅመም እድል ትስጠኝና ቀጠሮ ብታረፍድ እንኳ ሳልመረር ልጠብቃት፤ አንድ ቀን አይደለም፤ ደግሜ ደጋግሜ ሌትና ቀን ልጠብቃት ይላል፡፡ ይህ የሕይወት ሌላኛው የውበትና የተስፋ ክንፍ ነው፡፡ በዚህ መብረር እድሜ ያረዝማል!...
‹‹ሀገሬ አርጅታለች››
ሀገሬ አርጅታለች ጃርቶች በቀሉባት
እሾህ እያፀደቁ ወይን ነቀሉባት
ሀገሬ አርጅታለች
ከመታመን ክፍሏ
ከፍቅር ወለሏ
   ጥላቻ ከተተ
እምነትና አንድነት በምድሯ ከሰሙ
    ሰው መሆን ሻገተ፡፡
ወይን ተነቅሎ እሾህ ሲተከል መኖሩ ሀቅ ነው። ጃርቶች በቅለው ቀስት ማስወንጨፋችንን ባለፉት አመታት አይተናል፡፡ ዛሬም እሳቱ እየላሰን፣ ክፋቱ እያፈረሰን ነው፡፡ መታመን ጠፍቶ የጎሪጥ መተያየት ውስጥ ነን፡፡ አይናችንን ጨፍነን ካልካድን በቀር ጥላቻ አንቆ ይዞናል፡። ታንኳችን በማዕበል እየተናጠች ነው፡፡ እምነትና አንድነት ከስሞ፣ መለያየትና መናቆር ሰማይ ጥግ ደርሷል፡፡ ይሁንና ሌላም ተስፋ አለ - እሸት ያንጠለጠሉ፣ ብሩህ ቀን ያረገዙ ዜጎችም አሉን፡፡ ነፍሳቸውን ስለ ጎዶላችን ቤዛ ለማድረግ የተዘጋጁ ሕሩያን አልታጡም፡፡ በረሀብ እያዛጋን በጥላቻ እየነፈርን እንዳንኖር፣ የታሪካችን ምዕራፍ በሀዘን እንዳይዘጋ፤ አደባባያችን ላይ አበባ የሚነሰንሱ ከታሪክ ገጽ አልተፋቁም፡፡
‹‹ንጉሳችንና ያንቺ መዘናጋት›› የሚለው ግጥሙም ይህንኑ የሀገር ነገር ያዜማል፡፡
እንኳንስ አንድ ሰው
እንባሽን ሊያብሰው
መቶ ሚሊየን ሕዝብ ሊያድንሽ ቢተጋ
ሕመሙ ጽኑ ነው የቆሰለ ጉበት በጦር የተወጋ
እናልሽ እናቴ…
ጋብቻ ማፍረስ ነው የመዳንሽ ውሉ
አንቺን በልቶ መግደል
አንቺን መጥባት ብቻ
ችጋራም ማድረግ ነው የባልሽ አመሉ፡፡
       ***
እንዲያው ቢሆን እንኳ…
ንጉሱን ብናምነው
የበዙ እባቦችን እንደምን አድርጎ አንድ ርግብ ይመራል
አንድ ሻማ ብቻ የጨለመ ሀገርን እንደምን ያበራል
ቤተ እምነቶች ዱዳ ሽማግሌው ዱጋ ጋዜጠኛው ዱዳ
እንዳልተወለደ እንዳልኖረ ሁሉ ሕዝብሽም እንግዳ፡፡
…ግጥሙ ይቀጥላል፡፡ የዚህ ግጥም ወቀሳ ብዙ እውነት አለው። ፍርሃትና ጥርጣሬው፣ ነባራዊው እውነትም አሳማኝ ነው፡፡ በተለይ ሁለተኛው አንጓ ላይ ያለው ሀሳብ በእምነት ተቋማቶቻችን፣ በጋዜጠኞቻችን… በአጠቃላይ በሽንቁሮቻችን ላይ አተኩሯል፡፡
መጽሐፉ አሁን ባለንበት አገራዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ መረር ያለና የሚያሳዝንም ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ሚዛን የሳተ ይመስላል፡፡ ወደ አንድ ጥግ የሄዱ ግጥሞች አሉ፡፡ ገጣሚ የአገር ወገን፣ የሕዝቦች ተገን መሆኑን ግን መርሳት የለበትም፡፡ እንደ መጽሐፍ ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ጭብጦቹ ከአንድ ድንኳን የተመዘዙ፣ ባለ ተመሳሳይ ጭብጥና ድምጽ መሆን የለባቸውም፡፡ ስሜት የጥበቡን ዋልታዎች እንዳይበትን መጠንቀቅና ምሰሶውን ሁለንታዊ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ በተረፈ ገጣሚው ክፍተቶቹን ሞልቶ፣ በግሩም ሥራዎች እንደሚመለስ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

Read 1199 times