Print this page
Monday, 09 September 2019 11:56

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

“ፀሐፊው እንደሚለው፤ ዛፎቹ የሮማን ኢምፓየርን፣ የክርስቶስ ልደትን አይተዋል፡፡ ታላላቅ ጦርነቶችን ታዝበዋል፡፡ ኮለምበስ አሜሪካንን ሲያገኝ እዛው ነበሩ፡፡ የጆርጅ ዋሽንግተንን ንግግሮች አዳምጠዋል፣ ኬኔዲና ኪንግ ላይ የተተኮሱትን ጥይቶች ድምጽ ሰምተዋል፡፡--”
              

               አንድ አባት አንድ ቀን ልጃቸውን፤
“ዛሬ ምን ተማራችሁ?” ብለው ጠየቁት፡፡
“ጂኦግራፊ”
“ምንድነው እሱ?”
“የመልክዓ ምድር ሳይንስ…”
“ምድር መልክ አላት?”
“አዎ፡፡ መሬት ስትዞር ወቅቶች ስለሚፈራረቁ…”
“ቆይ ቆይ መሬት ትዞራለች ያለው ማነው?”
“ቲቸር ናቸዋ!”
“መሬት ትዞራለች ብሎ አስተማረ?”
“አዎና!”
አባት ቢያስቡ፣ ቢያስቡ ሊገባቸው አልቻለም:: ይህን ከሰሙ ከጥቂት ወራት በኋላ በቤታቸው ዙሪያ የተከሉትን የበቆሎ እሸት ማሳ እያረሙ ሳለ፣ በአጋጣሚ የልጃቸው አስተማሪ በዛ በኩል ያልፍ ነበረና እንዳያቸው፡-
“ጤና ይስጥልኝ አባት እንዴት ዋሉ?”
“አሃም ድልላሂ! እንዴት ዋልክ መምህር?”
“ክብሩ ይስፋ! ደህና ነኝ፡፡ እሸት እየደረሰ ነው መሰለኝ?”
“አዎ ደርሷል”
“እንግዲህ እንዳይረሱኝ፡፡” አለ፤ መምህሩ እየቀለደ፡፡ አባት የመለሱት መልስ መምህሩን እስከ ዛሬ ድረስ እያስታወሰ እንዲስቅ አድርጐታል፡፡ ምን ብለውት ይሆን?
***
ወዳጄ፡- አዲስ ቀን፣ አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ሰው የሚወለዱት ወይም ከአንድ ቅርጽ ወደ ሌላው የሚሸጋገሩት በዚች “የሌለች” በምትመስል፣ ነገር ግን ከሷ በቀር “ምንም” አለመኖሩ በተረጋገጠባት ቅጽበት ነው፡፡ ለውጥና ቅጽበት አንድ ናቸው፡፡ ህይወት ደግሞ ብዙ ገፆች ያሏት የነሱ አንድ ፊት ናት---እንደ ሂንዱ ብራህማን ----እንደ ምድር እንደ ራሷ:: ወዳጄ፡- ቀን በብርሃን ቦርቀን፣ ሌት የምንጋደመው መሬት ፊቷን ስለምታዞር እንጂ ፀሐይ ስለጠለቀች ወይም ጀንበር ስለፈነጠቀች አይደለም፡፡ መሬት ፊቷን የምታየው በፀሃይ መስታወት ነው፤ ፊቷን ባዞረችበት ቅጽበት ሁሉ ወቅቶች፣ ሴንቸሪዎች፣ ሚሊኒየሞች ይፈራረቃሉ፡፡ ግግር በረዶ፣ ነዲድ በረሃ ይፈጠራል፡፡ ጊዜውን ጠብቆ ደግሞ በረዶው ቀልጦ ምድረበዳ፣ ምድረበዳው ውሃ ይሆናል፡፡ ገጣሚው፤
ምድረበዳ ውቅያኖስ እንዳልነበር
አንዲት ጠብታ ውሃ ተነፍጐ
ይጨሳል ይቃጠላል
ለሀሩር ንዳድ ተዳርጐ
እንደነበር “ያለ” ወይም “እንዳለ” ‘ሚኖር
ምን አለ ‘ማይለወጥ ቋሚ ነገር በዚች ምድር?
ሁሉም ነገር ይቀየራል - የበፊት መልኩን ትቶ
የተፈጥሮ ህግ ነውና - ማን ይሽረዋል ከቶ?
የሰውም ልጅ በበሃሪው - አንዳንዴ ሰው
አንዳንዴ አውሬ - የሚሆነው
የግዜርን ፊት ከዲያቢሎስ
ዲያቢሎስን ከፈጣሪው
ለመለየት ሲያቅተው ነው፡፡
 በማለት ጽፎ ነበር፡፡ እርግጥ ነው፡፡ ውበት ከለውጥ ይወለዳል፡፡ ተራው ደርሶ እስኪቀየር ድረስ---እንደ ፋሽን፡፡
All changed, changed utterly
A terrible beauty is born
(W.B. Yeats)
ወዳጄ፡- ዘመንን በጨረቃ ጉዞ (lunar calendar) የሚያሰሉ እንዳሉ ሆነው በራሳቸው ወይም በተለየ መንገድ የሚቆጥሩ አገራትና ማህበረሰቦች ብዙ ናቸው፡፡ የዘመን መለወጫ በዓል አከባበራቸው “መንፈሱ” ከሞላ ጐደል ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ስነስርዓቱ የሚከናወንበት ዕለት ግን ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ የልዩነቱ ምክንያት ሲጠና ምድራችንን ጨምሮ ሁሉም ሰማያዊ አካላት ከሚያደርጉት ያላሰለሰ፣ የተቀናጀ ግን ተፈጥሯዊ ከሆነው እንቅስቃሴ (harmony) ጋር የተሳለጠ ነው፡፡
የኖህ መርከብ አራራት ሳይሆን ራስ ዳሸን፣ ኪሊማንጀሮ፣ ፉሪ ወይም የጅሬን ተራሮችን ተደግፋ ቆማ ቢሆን ኖሮ፣ አሁን ያለው ዕምነታዊ ትርክት ወይም አስተሳሰብ ሌላ ይሆን ነበር፡፡ ነጭ፣ ቢጫ፣ ጥቁር የምንለው የሰው ልጆች የቆዳ ቀለምም አሁን ካለው የተለየ እንደሚሆን ሳይንሳዊ ግምት አለ:: አፍሪካውያን ነጮች፣ አውሮፓውያን ጥቁሮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የዘመን ስሌትና ከበዓላት ጋር የሚዛመዱት ወግና ልማዶችም ሊቀያየሩ ወይም ቦታቸው ሊለዋወጥ ይችል ነበር፡፡
የዘመን መለወጫ በዓል ከሰብል ምርት፣ ከልምላሜ፣ ከጥጋብና ከ“አዲስ” ፀሐይ መውጣት ጋር ተያያዥነት አለው፡፡ ብዙ ማህበረሰቦች እኛንም ጨምሮ፣ ይህንን ፀጋ ለሰጡት አማልክት “እንኳን ለዚህ አደረሳችሁን” በማለት ወቅቱን ያስታውሳል:: አበባ በመለዋወጥ፣ ቄጠማ በመያዝ፣ በወገብ ላይ በመታጠቅ ወይም ጭንቅላት ላይ በማሰር በዕልልታ፣ በሆያሆዬና በጭፈራ ምስጋናውን ያቀርባል:: ወንዞቹን፣ ተራሮቹን፣ ሃይቆቹን ይመርቃል:: ዛፎቹን ቅቤ ይቀባል፣ ንፍሮ ይበትናል፡፡ እሳት እያነደደ፣ ጪሱን ወደ ሰማይ እያንቦለቦለ ለጨረቃና ለክዋክብቱ ደስታውን ይገልፃል፡፡
ይሁን እንጂ ሰው ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥብቅ ዝምድና በተገቢው መጠን ባለመንከባከቡ በወቅቶች መፈራረቅ ላይ መዛባት እየታየ ከባቢው አየር እየሳሳ፣ ሥነ ምህዳሩ እየተናጋ በሰው ልጆች አኗኗር ላይ ስጋት ፈጥሯል፡፡
ወዳጄ፡- የሰው ልጅ ሌሎች በሰጡት እየኖረ እሱ ለሌሎች መስጠትን በመንፈጉ ለመጪው ትውልድ ዕዳ እያኖረ መሆኑን የገባው አሁን ነው፡፡ ዛፍ መትከል ለትውልድ ትንፋሽ መስጠት ውበት፣ ጤናና ምቾትን ማውረስ እንደሆነ የነቃው አሁን ነው፡፡ አለበለዚያ የዘጠኝ ዓመቷ ኬኒያዊት ህፃን ኤሊያን ዋንቺጉ እንዳለችው፤ ድርቅ ረሃብ፣ በሽታና የመሳሰሉት ጥቃቶች የመጪው ዘመናት ሳንካ ይሆኑበታል:: ኤሊያን 1500 ችግኞችን ተክላ እየተንከባከበች በመሆኗ ዓለም አጨብጭቦላታል፡፡ “ገና ምን ታይቶ” ባይ ናት እሷ!!
ወዳጄ፡- የዓለም ህዝብ የሚተነፍሰውን ስልሳ በመቶ ያህል ኦክስጂን የሚያገኘው አሁን በከፍተኛ ቃጠሎ ላይ ከሚገኘው አማዞን አካባቢ ወይም ትሮፒካል ሬይን ፎረስት ከሚባለው የአረንጓዴ ዱር ሰንሰለት ነው፡፡ ዓለማችን በአየር ብክለት ክፉኛ በተመታችበት በዚህ ዘመን አደጋው መባባሱ ያሳዝናል፡፡
አማዞንን ካነሳን አይቀር፣ ዩኤስ ካሊፎርኒያ ስለሚገኘው የሳንፍራንሲስኮ አካባቢ ደን አለማውራት ንፉግነት ነው፡፡ በረዣዥሞቹ የሴኮያ ዛፎች የታጨቀው የሳንፍራሲስኮው ጫካ ከፍተኛ እንክብካቤ የሚደረግለት ውብ የቱሪስት መዳረሻ ነው፡፡ ደራሲ ጌቮርግ ኤሚን ስለተመለከተው ዛፎች ሲገልጽ፡- “ሰማዩን በስተው ወደ ከዋክብቱ የሚምዝገዘጉ ሮኬቶች ይመስላሉ” ብሏል፡፡ ዛፎቹ ከሁለት እስከ ሶስት ሺህ ዓመት ዕድሜ ባለፀጐች ናቸው፡፡ ከ30-40 ሜትር ወይም ከ10-15 ፎቅ እንዳለው ህንፃ የሚረዝሙ ሲሆን የአንዱን ዛፍ ወገብ ለማቀፍ እጃቸውን ወደ ጐን የዘረጉ ቢያንስ አስር ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ አጃሂብ አያሰኝም!?
ፀሐፊው እንደሚለው፤ ዛፎቹ የሮማን ኢምፓየርን፣ የክርስቶስ ልደትን አይተዋል፡፡ ታላላቅ ጦርነቶችን ታዝበዋል፡፡ ኮለምበስ አሜሪካንን ሲያገኝ እዛው ነበሩ፡፡ የጆርጅ ዋሽንግተንን ንግግሮች አዳምጠዋል፣ ኬኔዲና ኪንግ ላይ የተተኮሱትን ጥይቶች ድምጽ ሰምተዋል፡፡ አሁንም እንደ አስተዋይ ሰው አስተሳሰብ፣ ወደ ላይ ከፍ ከፍ ማለታቸውን አላቆሙም፡፡
ወዳጄ፡- መጪው እንቁጣጣሽ የአዲስ አስተሳሰብና የአዲስ ቀን ጋብቻ ይሁንልን፡፡ እነሆ የብርሃን አበባ መሬት ተሽከርክራ አንተ ባለህበት ቦታ ስታልፍ ተቀበላት፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፣ መምህሩ ለተማሪው አባት፡- “እባክዎ እሸቱ ሲደርስ እንዳይረሱኝ” ሲላቸው፤ “ችግር የለም፣ መሬት ትዞራለች እያልክ አይደል የምታስተምረው? ጓሮዬ ባንተ ቤት በኩል ሲመጣ የፈለግኸውን ያህል ውሰድ” ነበር ያሉት፡፡
We and the laboring world are passing by
 Amid men’s souls, that waver and give place,
Like the pale waters in their wintry race
ይልሃል የቅድሙ ገጣሚ፡፡
ሰላም!!
መልካም በዓል!!


Read 1533 times