Monday, 09 September 2019 11:53

ቃለ ምልልስ የሀመልማል የአውዳመት ስጦታ - ፍቅርና ይቅርታ!

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(3 votes)

አንጋፋዋ ድምፃዊ ሀመልማል አባተ፣ ለዛ ባለውና ጣዕም በሚፈጥር አዘፋፈኗ፣ በቅጽበት የሚስቡና ከአእምሮ የማይጠፉ ማራኪና ተናፋቂ ዜማዎችን በማበርከት የምትታወቅ ድንቅ የጥበብ ሰው ናት:: በርካታ ተወዳጅ አልበሞቿ፣ የጥበብ በረከትን ይመሰክራሉ፡፡ አሁን ደግሞ፤ “ከላይ ነው ትዕዛዙ” የተሰኘ አዲስ አልበም ሠርታም ለ2012 አዲስ ዓመት ለሙዚቃ አፍቃሪዎቿ እነሆ ብላለች፡፡ በእርግጥ የሀመልማል ዝና፣ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ እውነትንና የምታምንበትን ሃሳብ የመናገር ግልጽነትን ጨዋነት ከማይለየው ፀባይ ጋር ያዋሃደች፣ ቅንነትን ከጥንካሬ ጋር፣ በራስ መተማመንን ከሰው አክባሪነት ጋር በማሳየትም እንደ አርአያ የምትጠቀስ ስመጥር አርቲስት ናት፡፡ ድምፃዊቷ በአዲሱ አልበሟ ዙሪያ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው እንደሚከተለው አጫውታታለች፡፡


           እስቲ ስለ አዲሱ አልበምሽ…ስለ ሙዚቃ ስራዎችስ ትንሽ ንገሪን…
ከልብ በፍቅር የተሰራ አልበም ነው፡፡ የእኛ ድምፅ የፍቅርም የአገርም ድምጽ ነው፡፡ የልብም የህዝብም ድምፅ ነው፡፡ የፍቅር ዘፈን ሆኖ የልብን የሚገልጽ፣ በውስጡም አገርን ያቀፈ የፍቅር ቅኔ ነው፡፡ የፍቅርና የይቅርታ ልብ ይዞ የመጣ ነው፡፡ ብዙ ፍቅርና ይቅርታ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ብዙ ይቅርታ፣ ብዙ ቁምነገር ውስጡ አሉ፡፡ ካሁን በፊት እንደሰራሁትም በአማርኛና በኦሮምኛ የተሰሩ  ናቸው፡፡
በአልበሙ ሥራ ላይ እነማን ተሳትፈዋል?
የተለያዩ አቀናባሪዎች ፣ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተሳትፈውበታል፡፡ አንጋፋዎችም፣  አዳዲስ ልጆችም የተሳተፉበት ነው፡፡ እነ አበጋዝ ክብረወርቅ እንዳሉ ሆነው በማቀነባበሩ ሌሎች አዳዲሶችም አሉበት::  ከቀድሞ ግጥምና ዜማ ደራሲዎችም ሙሉጌታ አባተ፣ አበበ ብርሃኔና አዳዲስ ወጣት ድምፃውያንን ጨምሮ ተሳትፈውበታል፡፡ የአልበሙ መጠሪያ “ከላይ ነው ትዕዛዙ” ይላል፡፡ በውስጡ ከዚህ ቀደም በመልእክትም በዜማም ከሰራኋቸው የተለዩ ብዙ ስራዎች አሉት፡፡
የዘፈኖቹ መልዕክት ሃይለኛ ነው ብለሻል…
“ሀገሩ ሲለካ” የሚል በምንጃር ዘይቤ የተሰራ፣ ጥልቅ መልእክት የያዘ ዘፈን አለ፡፡ ከፍተኛ መልዕክት ያላቸውና በይቅርታ መንፈስ የተሰሩም አሉ፡፡  ለምሳሌ “ራሴን” የሚለው ሙዚቃ ውስጥ በስማ በለው ሳይሆን እራሴን የሆንኩትን ነገር በሚል የተሰራ ነው:: “ሰው ምን አገባው” የሚል ዘፈንም አለ:: አንዳንዱ ሰው በዘፈቀደ ዘልሎ በህይወታችን ጣልቃ ይገባል፡፡ አንቺ ይቅር ባልሽበት ጉዳይ፣ “ለምን ይቅር አልሽ” ብሎ የሚናገርሽ ሰው አለ፡፡ ምክንያትሽን ሳያውቅና ሳይጠይቅ በህይወትሽ ጣልቃ የሚገባ ማለት ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች የፍቅርም፣ የቁምነገርም ናቸው፡፡ በጎጃምኛ ቢት የተሰራው “ተው ስማኝ” የተሰኘው ሙዚቃ እንዲህ ይላል፡-
“ይቅር ለመባባል ካሰብን በቀና
ደንገዝገዝ አለ እንጂ አልጨለመም ገና”
የአልበም ሽያጭ ከድሮ ጋር ሲነፃፀር ምን ይመስላል?
እርግጥ የአርቱን ልፋትና ዋጋ የሚያውቁ ሰዎች አሉ፡፡ የጥበብ ወዳጆች አሉ፡፡ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆነው እንኳን ኦሪጅናል ይገዛሉ፡፡ በተረፈ ግን ሁሉም ነገር በፍላሽ ኮፒ እየተደረገ የአልበም ሽያጭ እየተሞተ ነው፡፡ ኮንሰርት ካልሰራን ወይም በሌላ መንገድ ገቢ ካላገኘን፣ ሲዲውን ሸጬ ያወጣሁትን እተካለሁ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ጥበብ ግን አይቆምም፡፡ ካለን የሙያ ፍቅር የተነሳ መስራታችንን አናቆምም፡፡ አሁን የሰራሁትንም ስራ ከማሳተም ጀምሮ እስከ ማከፋፈል እራሴ ነኝ የሰራሁት - ልፋቱና ወጪው ብዙ ነው፡፡
የአልበምሽ ወጪ ምን ያህል ነው?
ገና ሒሳብ አልተሠራም፡፡ ማሰብም አልፈልግም:: ክሊፕም መስራት ጀምረናል፡፡
በዩቲዩብ ከሚለቀቁ ሙዚቃዎች የምታገኙት ጥቅም አለ?
እስካሁን አልተጠቀምንም፡፡ በዓለም ላይ ያለ እልፍ ሰው ሁሉ፤ እንዳሰኘው  ጭኖ እየተጠቀመበት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን እየዞሩ መጠየቅ ይከብዳል:: አሁን ግን መቆጣጠሪያ ሲስተሙ ስላለ እንጠቀምበታለን የሚል ተስፋ አለን፡፡ መንግስትም ሊያግዝ ይገባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ኮፒው ላይ መቆጣጠሪያ ባይኖረንም፣ የባለቤትነት መብታችንን ያስከብርልናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ልጆቻችን የእናታችን ቅርስ ነው ብለው እንዲያስታውሱት ያደርጋል ብዬ አስባለሁ፡፡
አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቋሚነት በሚሰሩት ፕሮግራም ላይ አስመስለው የሚዘፍኑ ሙዚቀኞች አሉ፡፡ ስለእነሱ ምን ትያለሽ?
በእርግጠኝነት ሙዚቀኛውን አስፈቅደው ነው የሚሰሩት፡፡  አርቲስቱ ወይ መጠየቅ አለበት አለበለዚያ ከጥቅሙ መካፈል አለበት፡፡ በልምድ ዝም ብለው የሚያደርጉት አሉ፡፡ ያ ስራ እኮ ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም፤ ብዙ ተለፍቶበት፣ ብዙ ተደክሞበት ነው እዛ ላይ የደረሰው፡፡ እራሱ ቻናሉ ያንን ስራ ሲሰራ ስፖንሰር አለው፡፡ ከስፖንሰር ገቢ ካገኘ፣ ለአርቲስቱ ደግሞ መክፈል አለበት፡፡ እዚህች አጠገባችን ያለችው ሱዳን፣ ለኢንተርቪው ይከፈልሻል፡፡ ኢንተርቪው ሲደረግ በነፃ የለም:: በተለይ ቲቪ ላይ፡፡ ምክንያቱም ወጪዎች አሉ፡፡ ቲቪ ላይ ለመቅረብ ፀጉር መሰራት፣ ልብስ፣ ሜካፕ… ወጪዎች ናቸው፡፡ ድሮ በደርግ ጊዜ፣ ቲቪ ላይ ስትቀርቢ እኮ፣ የፀጉር መሰሪያ ተብሎ ገንዘብ ይሰጥ ነበር፡፡
ብዙ ጊዜ ሀመልማል ፊት ለፊት ነው የምትናገረው ይባላል፡፡ የተቃወመሽ ወይም የተቀየመሽ አጋጥሞሽ ያውቃል?
ቢገጥመኝም ምንም ቅር የሚለኝ ነገር የለም:: እኔ በመንግስትም ደረጃ እንኳን፤ የማየውን ስህተት ቀጥ ብዬ ቢሮ ድረስ ሄጄ እናገራለሁ፡፡ “ይሄ ችግር አለ፤ ታውቁታላችሁ ወይ?” ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ “ይሄ ነገር እንደዚህ መሆን አለበት” በማለት የምችለውን  ያህል የአቅሜን እናገራለሁ፡፡ አንዳንዴ፣ “በሰዓቱ ቢነገር፣ ቢደመጥ ቢስተካከል ኖሮ” የሚባሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሌላ ሰው አያደምጥም፣ አያስተካክልም ብዬ ዝም አልልም፡፡ ትክክል ነው ብዬ ባሰብኩትና ወይም የተቀየመሽ ባመንኩበት ነገር ከመናገር ወደ ኋላ አልልም፡፡ እኔም ሰው ነኝ፡፡ አልሳሳትም ብዬ አልልም፡፡ አስተካክላለሁ፡፡ የጥበብ ድምጽ… የእኛ ድምፅ የህዝብም ጭምር እንጂ   የእኛ ብቻ አይደለም፡፡ እኔ ላይ ደግሞ… ሀረርነቱም አለ፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ሳይ ዝም አልልም፡፡ እናገራለሁ:: ይጠቅማል፡፡ አድማጭ ሰው ይኖራል፡፡ እኔም፣ የሚነግረኝን ሰው መስማት አለብኝ፡፡ ጓደኛሽ ላይ ችግር አይተሽ ነግረሽው ይጥላሽ፡፡ ካልነገርሽው ግን ሌላው ይስቅበታል፡፡
ስለ ሃገራችን ምን ታስቢያለሽ? መከፋፈሉ…..
ይሄን ያመጣው ያለ ማስተዋል ነው፡፡ የአገራችን ጉዳይ የሁላችንም ነው፡፡ ሰው በዘር ካሰበ ልክ አይደለም፡፡ ሰው ማሰብ ያለበት በሰውነቱ ነው፡፡ እንዴት ነው ስለ ዘር የምናስበው? በአለም በሙሉ  ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩት,ኮ፣ ሀይማኖታቸውን ብሄራቸውን ሳይጠየቁ ነው፡፡ ያ ለእኛ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ በተለይ እኔ ያደኩበት አካባቢ፣ ዘሬ ምን ይሁን ምን፣ እንደዚህ አይነት ነገር በፍፁም ሰምቼም አላውቅ:: ያንቺ ዘር እንደዚያ ነው፤ ያንተ ዘር እንደዚህ ነው ብሎ የሚያስተምረንም የሚነግረንም የለም፡፡ በዘር እየመነዘሩ አገርን ማመስ በፍፁም ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ ለሰላም ፌስቲቫል ጅጅጋ ሔጄ ነበር፡፡ እንዴት ደስ ይላል መሰለሽ! ያ በፊት የነበረው ፍቅር አሁንም አለ፤ አልተቀየረም:: ይሄ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ጎንደር የተወለደ ሰው ጅጅጋ ሄዶ ተዋዶ ሰርቶ መኖር፣ አብሮ
 መዝናናት መቻል አለበት እንጂ፤ “አይ ይሄ የእኔ ክልል ብቻ ነው” ተገቢ አይደለም፡፡ ለሁላችንም ሀገራችን ነው፡፡ ፖለቲከኞችም ደግሞ እዚህ ላይ መስራት አለባቸው፡፡ ሚዲያው አሁን በርክቷል፡፡ ሚዲያ ለአርት ጥሩ ነው፡፡ ቁም ነገር ለማስተማርና ግንዛቤ ለመፍጠርም መስራት አለባቸው፡፡ ትልቁ ነገር ይሄ ነው፡፡ እኔ የሰራሁት አዲሱ ስራዬ ላይ ለምሳሌ፣ “ዋሽቶ የሚያጣላ በበዛበት ዘመን” ይላል፡፡ ስለዚህ ማስተዋል አለብን፡፡ ሁላችንም የምንሰማውን ነገር፣ “እውነት ነው ወይ?” ብለን እውነትን መናገር አለብን:: መናገር የአንድ ፓርቲ ሃላፊነት ብቻ አይደለም፡፡ የእኛም ነው፡፡ የአገር ጉዳይ የሁላችንም ነው፡፡ ለአገሩ ሁሉም ዘብ መቆም አለበት፡፡ ለምሳሌ በውጪ አገር ሁሉም ለአገሩ ዘብ ነው፡፡ አንድ ነገር ካየ ይናገራል፡፡ የሚመለከተውም አካል፣ የተነገረውን ነገር በቁም ነገር ነው የሚወስደው፡፡ አይ ብሎ አይተወውም፡፡ እያንዳንዱ ሰው የአገሩ ዘብ መሆን አለበት፡፡ አንዳንድ ሰው የራሱን አጀንዳ ያራምድ ይሆናል፡፡ እሱ የራሱ ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ሌላው ሊጎተትለት አይገባም፡፡ በአሁን ጊዜ ሰዓት እራሱ ቢፈተሽ ከድሮው እየፈጠነ ይመስለኛል፡፡
ይሄን ጊዜ ሰርተን ካላሳለፍን፣ ነገ አይኖረንም፤ ዛሬ የምንኖረው ትናንት በሰራነው ነው፡፡ ለነገ ደግሞ ዛሬ መስራት አለብን፡፡ ህይወት እንደሆነ ይደርሳል የሚባል ነገር የለውም፡፡ አመለካከታችን፣ አስተሳሰባችንን መስተካከል መሻሻል አለበት:: አመቱ ሲቀየር እኛም መሻሻል አለብን፡፡ “ከላይ ነው ትዕዛዙ” የሚለውን በደንብ አዳምጡት፡፡ ብዙ ትምህርት አለው፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይወጣል፡፡ አሸሼ ገዳሜ ብቻ አይደለም፡፡ ቁም ነገር አለው፡፡
እስቲ ስለ ቤተሰብ ልጆች አስተዳደግሽ አጫውቺን…
በጣም ቅርበት አለኝ - ከልጆቼ ጋር፡፡ ከእነሱ ጋር ለመግባባት ስል፣ ኮሌጅ ገብቻለሁ፡፡ እኔ ብቻዬን ነው ልጆቼን ያሳደግኩት፡፡ Single Mom ነኝ ባልልም ግን ብዙ ሰዎችን እጠይቃለሁ፡፡ እንዴት ነው ልጆቻችሁን የምታሳድጉት ብዬ፡፡ እኔ ልጆቼ ጓደኞቼም ናቸው፡፡ ይሄንን ያመጣው ምናልባት አስተዳደጌም ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ እኔ ወግ አጥባቂ እናት ነኝ፡፡ ከልክ ሲያልፍ ግን አይጠቅምም፡፡ ብዙ ጊዜ ስለ ፍቅር ጓደኛ ምንም እንዳያወሩ፣ ዝም ብዬ አልፋቸው ነበር፡፡ ይሄ ጥሩ አይደለም፡፡
ቤተሰብ ጓደኛ ነው መሆን ያለበት፡፡ ካንቺ ጋር ካወሩ፣ የሚያደርጉትን የሚውሉበትን ታውቂያለሽ:: ግልጽ መሆን ይጠቅማል፡፡ ምን ሄደ? ምን መጣ? መቼ የት ምን እንደሚያደርጉ ታውቂያለሽ፡፡ ችግር ካለ በጊዜ ማረም ትችያለሽ፡፡ ልጆቻችንን ጓደኛ ማድረግ ነው የሚጠቅመው፡፡ አለበለዚያ ከሌላ ሰው ጋር ነው የሚያወሩት፡፡ ሚስጥር ያበዛሉ፡፡ ሳታውቂና በጊዜ ሳይታረም፤ ጥፋት ይመጣል፡፡ ይሄ መሆን የለበትም፡፡ በፍፁም፡፡
እኔም እንደዚህ ነበር የማደርገው፡፡ ልክ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ አሁን እንግዲህ እንደፈለጋችሁ መሆን ትችላላችሁ፤ ያኔ እኮ ድንገት ከትምህርታችሁ አንዳንድ ነገር ሊያፈናቅላችሁ ይችላል በሚል ነው ብላቸው “ማም ለምን ነበር የማታወሪን” አሉኝ፡፡ ከትምህርታችሁ እንዳትስተጓጐሉ ብዬ ነው፤ አሁን ጨርሳችኋል እንደፈለጋችሁ ስላቸው “ውይ ማማዬ አደገች” አሉኝ፡፡ የተማርኩት ነገር፤ በጣም ግልጽ መሆን እንዳለብኝ ነው፡፡ አንዴ የትልቋ ልጄ የፍቅር ጓደኛ እናትና አባቷ ቤት መጥቷል፡፡ እንዴት እዚህ ይመጣል ስላት፣ “ይህ ደህንነቱ የተጠበቀ ቦታ ነው” አለችኝ:: “እዚህ ሲመጣ ቤተሰብ ያውቃል” ብላ ከኔ ልጄ ተሽላ አስረዳችኝ፡፡ ይሄ በእድሜያቸው የሚመጣ ነው፡፡ ተደብቀውም ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ነው፡፡ እኛ ውጡ እየተባልን በጫና ነው ያደግነው:: አለመነጋገር መጥፎ ነው፡፡ ለዚህ ነው ብዙ ትዳሮች ለፍቺ የሚዳረጉት፡፡ ሚስቱ ላይ ያየውን ችግር ለሚስቱ አይነግርም፡፡ ለጓደኛው ወይም ለሌላ ሰው ግን ይነግራል፡፡ ሚስትም እንደዛው፡፡ ይሄ የመጣው ከአስተዳደጋችን ነው፡፡ ባህላችን ጥሩ ሆኖ አንዳንድ ጐጂ ልምዶች አሉ፡፡ ልጆቼን የምችለውን ሁሉ አድርጌ አሳድጌያለሁ፡፡ እነሱም አላሳፈሩኝም:: ተመርቀው ያገኙትን ስራ እየሰሩ ነው፡፡ ወደ አገራቸው ሲመጡም በጐ አድራጐት ድርጅቶችን በሚችሉት መጠን ያግዛሉ፡፡ እኔም የህፃናት መርጃ ማዕከል አምባሳደር የሆንኩት ልጆቼ በጀመሩት የድጋፍ ተግባር ነው፡፡  
የአዲስ ዓመት መልዕክት እንድታስተላልፊ፣ ልጠይቅሽ…
እንግዲህ በአዲስ አመት፣ አዲስ ዘፈን አዲስ ሲዲ ገዝታችሁ ተዝናኑ፡፡ በጣም ጥሩ ጥሩ ስራዎች ናቸው:: መልካም አዲስ አመት ይሁንልን፡፡ በተለይ የሰላም እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ሠላም ሲኖር ነው ሁላችንም ወጥተን የምንገባው፡፡ የሠላም፣ የደስታ፣ የፍቅር፣ የብልጽግና፣ የኦሪጅናል ካሴት ግዢ ይሁንልን እላለሁ፡፡ ሁሉም በያሉበት ለልጆቼ፣ ለቤተሰቦቼ፣ ለጓደኞቼ፣ ለወዳጆቼ ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም አመት በዓል እላለሁ፡፡


Read 2191 times