Monday, 09 September 2019 13:03

መልካም አዲስ ዓመት!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  … እንቁጣጣሽ ነበር መስከረም ሲጠባ
አውቆ የበቀለ ወፍ ዘራሽ አበባ፡፡
ለምለም አረንጓዴ…
ያልተጠበቀ መስክ ከብት የሚግጥበት
የደመና ግላጭ የሚጫወትበት፡፡
ሌላም ብዙ ነበር
   ሌላም… ደግሞ ሌላ
አለብኝ ትዝታ!
   ዘመዶቼ ሳሙኝ
  ጓደኞቼም ጋብዙኝ
  ሊስትሮ ጨብጠኝ
ባለጋሪ ንዳ መንገዴን አሳየኝ
ያገሬ ልጅ ቆንጆ ‹‹ቤት ለእንግዳ›› በይኝ
አለብኝ ትዝታ…
                           ገ/ክርስቶስ ደስታ
                               (እንደገና)
                *  *  *
…በይ ብር በይ ቢራ ቢሮ፣ ክረምት ላንቺ
                        ብቻ አለፈ
ሌላው በጎርፍ ጎረፈ
ሞተ፣ በተኛበት ረጋ…
ፀደይ ላንቺ ብቻ ነጋ
ሽር ብለሽ መንቆጥቆጥ ነው፤ ከዚያም፤
               ከዚያም፤ ከዚያም ሰምሮ
አወቅሁብሽ፤ ነቃሁብሽ፤ አንቺ ሕይወት
                 ቢራ ቢሮ…
ቀናሁ መሰል አንች ወላዋይ?
ነይ ብር በይ እንወያይ
አንቺ የዕፅዋት አዋዋይ
ከፀደይ ጋር ፀደይ መሳይ
ከአበባም አበባ መሳይ…
ምን አለበት ላንዲት ሰሞን
ቢራ ቢሮ እኔ አንቺን ብሆን?
                ፀጋዬ ገ/መድህን
              (ሕይወት ቢራቢሮ)
                *  *  *
… ወፎች ሲዘምሩ ሰማይ ደማስ መስሎ፣
ሐሴት ገባ ልቤ በውበት ተኩሎ፡፡
                      ዮሐንስ አድማሱ
         (ወፎች በተጥለግለግ - 1955 ዓ.ም)
                *  *  *
…ነበረች አበባ፣
በሾህ ተቀንብባ፣
መዓዛዋ ዘምቶ፣
   ተወርዋሪን ኮከብ አቀረበው ጠርቶ፡፡
በውበት ብትልቅ ይህች የዋህ አበባ፣
ረብ የሰው ዘየ በሾህ ተቀንብባ፣
እሾህ አያስደርስ፣ ቆንጥሩ አያስጠጋ፣ የዘመን
               ጋሬጣ አድርጓት ሰለባ፣
በእጦት መቃጠል ነው መዓዛዋ ሲያውድ
                ከልብ እየገባ፡፡
                       ዮሐንስ አድማሱ
                         (ተወርዋሪ ኮከብ)
                *  *  *
የተስፋዬ ዛፉ
ሊከረከም ቅርንጫፉ፣
ሥሩ ሲነቃቀል
ሲበጠስ ሲፈነገል፤
ጭላንጭል ስትዳፈን
ብርሀን ዐይኑ ሲከደን፣
አንጥፌ ደርቤ ማቄን
ዘንግቻት እንቁጣጣሽን
ፀደይ አበባ ዐደዬን፣
በድቅድቅ ተቀመጥሁኝ
ላለማሰብ እያሰብሁኝ፣
የልቤን ልበ ባሻነት ገሰጽኩኝ
ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አረኩኝ፡፡
            ደበበ ሰይፉ
             (የተስፋዬ ዛፉ)               

Read 2195 times