Print this page
Saturday, 14 September 2019 10:55

“ደራሽ የወንዝ ውሀ ‘ተውሳኩን’ ይውሰደው…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


         እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ክረምት አልፎ በጋ፣ መስከረም ሲጠባ
አሮጌው ዓመት አልፎ፣ አዲሱ ሲገባ
ደራሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኩን ይውሰደው
ጤና መሆኑን ነው እኛ የምንወደው፣
ተብሎ ተዚሞ ነበር፡፡ በተለይ ዘንድሮ ፈሳሽ የወንዝ ውሃ እንዲወስድልን የምንፈልጋቸው ብዙ ተውሳኮች አሉ፡፡ በወሬ መልክ፣ በመድረክ ላይ ንግግር መልክ፣ በሬድዮና ቴሌቪዥን ቃለ መጠይቅ መልክ፣ በማህበራዊ ሚዲያ መልክ፣ በ“ጭራቁ መጣብህ!” መልክ እየመጡ ሲያምሱን የከረሙ ተውሳኮች መአት ናቸው…የወንዝ ውሀም ሆን የበረሀ አውሎ ነፋስ እንዲወስድልን የምንፈልጋቸው ተውሳኮች፡፡
አላስቆም አላስቀምጥ፣ አላስበላ አላስጠጣ፣ አላፋቅር አላዋድድ እያለን ያለው ‘የተውሳኮች ሁሉ እናት’ የሆነው የዘረኝነት ተውሳክ፣ ከአሮጌው ዓመት ጋር ተጠራርጎ እንዲሄድልን እንመኛለን፡፡ ለስንትና ስንት ዘመናት ለምንም ሳይበገር ጠንክሮ የኖረውን፣ ተሳስቦና ተቻችሎ አብሮ የመኖር ጠንካራ ስፌትን እየተረተረ ጎረቤት ከጎረቤት፤ ወዳጅ ከወዳጅ እያቆራረጠ ያለ የአክራሪ ዘረኝነት ተውሳክ፣ ይቺ ሀገር ከገጠሟት ደዌዎች ሁሉ የከፋው ነው፡፡
ያለምንም ምክንያት፣ ያለምንም ‘እዚህ ግባ’ የማይባል ሰበብ፣ በባዶ ሜዳ የጎሪጥ እንድንተያይ፣ ከአንድ ማእድ እንዳንቆርስ፣ አንዳችን ሌላኛችንን እንድንጠራጠር፣ አንዳችን የሌላኛችንን ክፉ እንድንመኝ ያደረገን የጥላቻ ተውሳክን፣ የበረሃ አውሎ ነፋስም ይሁን ደራሽ የወንዝ ውሀ፣ ከአሮጌው ዓመት ጋር ይዞልን እንዲሄድ እንመኛለን፡፡
እንቁጣጣሽ፣ አንኳን መጣሽ
በአበቦች መሀል፣ እንምነሽነሽ 
ተብሏልም፡፡ አዎ በአበቦች መሀል መምነሽነሽ እንመኛለን፡፡ በፍቅር አበቦች መሀል መምነሽነሽ እንመኛለን፣ በይቅር ባይነት አበቦች መሀል መምነሽነሽ እንመኛለን፣ በመቻቻል አበቦች መሀል መምነሽነሽ እንመኛለን፡፡
ከምንም በላይ በሰላም አበቦች መሀል መምነሽነሽ እንመኛለን፡፡ ከእያዳንዳችን የግል ጓዳ እስከ የጋራ ሀገራች ድረስ ሰላም፣ ሰላም፣ ሰላም እንላለን፡፡ “ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር አይደለም፣” የሚባል ነገር አለና የሰላምን ትርጉም ሰፋ አድርገን የምናይበትና ከሁሉም በላይ የአእምሮ ሰላም የምናገኝበት አዲስ ዓመት ይሁንልን፡፡
ስሙኝማ…ከዚህ ቀደም ያወራናት ቀልድ ቢጤ አለች፡፡ ሰውየው ጓደኛውን… “ስማ፣ አንተ ቤት እንዲህ ሰላም የሆነው ምን ዘዴ ብትጠቀሙ ነው?” ይለዋል፡፡ እሱዬውም…
“ሁላችንም ሥራ ክፍፍል አለን” ይላል፡፡
“ምን አይነት የሥራ ከፍፍል?”
“ሚስቴ የገንዘብ ሚኒስትር ነች፣ እናቷ የጦር ሚኒስትር ነች፣ ሠራተኛችን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ነች፡፡”
 “አንተ ደግሞ ፕሬዝደንት ነህ?”
“አይደለሁም፣ እኔ ግብር ከፋዩ ሰፊው ህዝብ ነኝ::”
ቢያንስ፣ ቢያንስ ይሄኛው ቤት… አለ አይደል… እንደ ባንኮቻችን ሳይሆን ‘ሲስተም’ አለ፤ (ቂ…ቂ…ቂ…)
ከቤተሰብ ወሬ ሳንወጣ… አውሮፓ ውስጥ እንደ ‘ሱፐርስቲሽን’ የሚነገር ነገር አለ፡፡ ምን ይላል መሰላችሁ… “ማታ፣ ማታ ከመኝታ በፊት የሳሎኑን በር መቆለፍ ያለበት ባልየው ነው፡፡ ምክንያቱም ሚስትየው ከቆለፈችው ሌሊቱ ቅልጥ ያለ ጠብ ይሆናል፡፡” (አሁን ይሄ ነገር እኛ ዘንድ የሚባል ቢሆን ኖሮ…አለ አይደል… “እነኚህ ኋላ ቀሮች…” ምናምን አይነት ነገር ያወርዱብን ነበር፡፡) እናማ…ሌሊት ሌሊት የምትጣሉ ጥንዶች ወገኖቻችን፤ ወደ ‘ራፖር’ ጸሀፊ ከመሄዳችሁ በፊት ማታ የሳሎኑን በር የሚቆልፈው ማን እንደሆነ ለዩማ!
በመስከረም፣ በመስከረም፣ በመስከረም
ስፍራው ሁሉ ለምለም
ተብሎ ተዚሟል፡፡ ስፍራው ሁሉ ለምለም እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡
ስሙኝማ…ሌላ ምን መሰላችሁ፣ አዲሱ ዓመት ከፕሬሚየር ሊግ ተበዳሪነት ወደ አንደኛ ዲቪዚዮን ተበዳሪነት የምንወርድበት ይሁንልንማ! ሀምሳ ምናምን ሀገር! እኛ መቶ ሀምሳ ብር ያበደርነውን ሰው መንገድ ላይ ለሰው እየጠቆምን…“እዛ ማዶ ያለው ሰውዬ መቶ ሀምሳ ብር ተበድሮ ጭጭ አለ እኮ…” እንል የለ! እናማ…ልክ እንደዛው በዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይ የሀምሳ ምናምን ሀገር ተወካዮች፣ አጠገባቸው ላሉት የእኛን ሰዎች እየጠቆሙ…አለ አይደል… “እነኛ ሰዎች እኮ ስንት መቶ ሚሊየን ዶላር አበድረናቸው ጭጭ አሉ…” የሚሉ አይመስላችሁም! 
የምር ግን…ከሀምሳ በላይ ሀገራት ተበደርን የተባለው ገንዘብ ብቻ ነው ወይስ ሌሎች ብድሮች አሉብን? አይ… ከጎረቤት “የቡና ሙቀጫ አውሺኝ…” “በስኒ ትንሽ ሹሮ አበድሪኝ” እንደምንለው የሙቀጫና የስኒ ሹሮ መበዳደር ይኖር እንደሁ ለማጣራት ያህል ነው፡፡ ስሙኝማ…ይህን ያህል ሀገራት ከራሳቸውም አልፈው ማበደር የቻሉት የወዛደሮቹ ቀረና መፈክሩ … “ዓለም የአበዳሪዎች ትሆናለች!” ሆነ እንዴ!
ደግሞላችሁ…የተቀበልነው ዓመት ግራ የምንጋባባቸው ነገሮች የሚቀንሱበት ዓመት ይሁንልንማ! ምን እናድርግ… ግራ የሚያጋቡ ነገሮች እየበዙብን አእምሯችን የአስራ ሁለተኛ ክፍል የጥያቄ ወረቀት ብቻ መሰለብና! (እሱ ነገር እንዴት ሆነ? እንዲያጣራ የተሰየመው ቡድን፣ የአሁኑን ምላሽ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም መፍትሄ ይዞ የሚመጣበት ዓመት ይሁንልን፡፡ በፈተናው አካባቢ የተፈጠረው እሰጥ አገባ እስካሁን እንደገረመን ነው፡፡ በቃ… የተፈጠረውን ስህተት ለይቶ ማስተካከያ መውሰድ፣ የሚጠየቅ ክፍል ካለም በአግባቡ መጠየቅ እያለ፣ ነገሩን  ‘አኒማል ፋርም፣’ ‘ዳስ ካፒታል’ ምናምን ማስመሰል ማንንም አይጠቅምም፡፡
አዎ፣ ችግር በዝቷል፡፡ እለት ተእለት እየከበደ የመጣውንና ጀርባችንን የለመጠውን የኑሮ ጫና እስኪሰለችን ድረስ ስናወራው ከርመናል፡፡ የምግብ ምርቶች ዋጋ እንደተፈለገ፣ ላይ በላይ ሲጨምርና…አለ አይደል… “ዜጋችን እንዲህ መከራውን ሲበላማ፣ በነጻ ገበያ ስም ዝም ብለን አናይም” የሚል  ‘ሀይ’ ባይ ሲያጣ ሆድ እየባሰንም፣ ምስኪንነት እየተሰማንም፣ እየተራገምንም ስንጮህ ከርመናል፡፡ የተቀበልነው አዲስ ዓመት የእኛ የብሶት ጩኸት ብቻ ሳይሆን የሚመለከታቸው አካላት የተጨባጭ መፍትሄ ምላሽን የምንሰማበት እንዲሆን እንመኛለን፡፡
ሰውየው የተከራየውን ቤት ሊለቅ ነው፡፡ ለጓደኛው…
“ቅዳሜ ቤት ልለቅ ስለሆነ አምስት መቶ ያህል በረሮ ፈልግልኝ…” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም ግራ ገብቶት…
“ብር ልትል ፈልገህ ነው?” ሲል ይጠይቃል፡፡
“ብር አይደለም፣ በረሮ ነው ያልኩህ፡፡”
“አንተ ሰውዬ፣ ቆጣሪው ዘለለ እንዴ! አምስት መቶ በረሮ ምን ያደርግልሀል?”
“የፈረምኩት የኪራይ ውል ላይ ስለቅ ቤቱን በተከራየሁበት ጊዜ እንደነበረው እንዳስረክብ ተስማምቻለሁ” ብሎት አረፈ አሉ፡፡ እናማ…እንደ ኤዞፕ ተረቶች ከዚህ የሚገኘው ‘የሞራል ትምህርት’፤ ቤታችሁን ከማከራየታችሁ በፊት በቤት ውስጥ ያለው የአይጦች ‘ዙ’ በኦፊሴል ይዘጋማ! “እንዴት ተደርጎ ይዘጋል!” ካላችሁም፣ ውስጡ ያሉትን ‘አራዊት’ ቆጥራችሁ በፊርማ መረካከብ ነው፡፡ (ቂ…ቂ…ቂ…)
ክረምት አልፎ በጋ፣ መስከረም ሲጠባ
አሮጌው ዓመት አልፎ፣ አዲሱ ሲገባ
ፈሳሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኩን ይውሰደው
ጤና መሆኑን ነው እኛ የምንወደው፣
መልካም የበዓል ሰሞን! መልካም አዲስ ዓመት!
ደራሽ የወንዝ ውሀ ተውሳኩን ደግሞ፣ ደጋግሞ ይውሰደው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3329 times