Saturday, 14 September 2019 11:05

ኃይለ መለኮት አግዘው - የቅርሶቻችን ጠበቃ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ብዙዎቻችሁ ታውቁታላችሁ፤ - ኃይለመለኮት አግዘው ይባላል። የታሪክ፣ የቋንቋ ባለ ሙያና ምሁር ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በከተማ አጠባበቅና የኪነ - ሕንፃ ቅርሶች ዘርፍ (Urban Conservation and Architectural Heritage) የማስትሬት ዲግሪ አግኝቷል።
በአዲስ አበባ ሙዚየም የኤግዚቢሽን አስተባባሪ፣ የትምህርት ኦፊሰር እና ዳይሬክተር፣ በኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ፣ በኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት የ “Ethiopian Herald” ጋዜጣ አዘጋጅ፣ በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ በመሆን አገልግሏል።
በሥራ ዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርሶች እንዲጠኑ፣ ተለይተው እንዲመዘገቡና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከጓደኞቹ ጋር ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። ስለ ከተማችን ቅርሶች መጠበቅ የእርሱን ያህል የጮኸ አላወቅም። በአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም እሰራ በነበረበት ወቅት ለብዙ ጊዜያት ከእርሱ ጋር የመገናኘት፣ የመጨዋወትና የመወያየቱን አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ስለ ከተማችን አዲስ አበባ ታሪክ ያለው እውቀት፣ ስለ እያንዳንዱ ሰፈር፣ ወንዛወንዞች፣ ስለተለያዩ የከተማይቱ ኗሪ ህብረተሰብ ያለው እውቀት ጠሊቅ ነበር።
በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን እየሰራ ሳለም የሀገራችንን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በማጥናት፣ በአጠባበቅና ዓለም አቀፍ ዕቅድ በማዘጋጀት ረገድ የተጫወተው ሚና ይህ ቀረው የማይባል ነበር። እ.ኤ.አ በ2012 እና 2013 ዓ.ም በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን የሀገራችንን የማይዳሰሱ ቅርሶች በተመለከተ የተዘጋጁ ሁለት ባለ 300 ገፅ መፃህፍት በተባባሪ አዘጋጅነት ለህትመት እንዲበቁ አድርጓል። በተጨማሪም ለድሬ ሼኽ ሁሴን፣ ሶፍ ዑመር እና ለጌዴኦ ቅይጥ ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ዓለም አቀፍ የቅርስ አስተዳደር ዕቅድ አዘጋጅቷል።
በተለያዩ የህትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዕውቀቱን በፅሁፍም በአካልም አጋርቷል። ሚዩዚክ ሜይ ዴይ ያዘጋጃቸው በነበሩት የመፅሀፍ ዳሰሳ መድረኮች ላይ ጥናታዊና ሂሳዊ ፅሁፎችን ያቀርብም ነበር። በአሃዱ ሬድዮ ላይ ዘወትር ቅዳሜ ምሽት በሚቀርበው “መናገሻ” ዝግጅት ላይ ከነ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ጋር በመሆን በተለያዩ ርዕሰ - ጉዳዮች ላይ በሳል ሀሳቦችን በመሰንዘርም አክብሮትና ተወዳጅነትን አትርፏል።
ባጠቃላይ ኃይለ መለኮት ሙሉ ሰው ነበር። እንደ ሀገር እርሱን መሰል ሰው በሞት ማጣት ትልቅ ጉድለት ነው - የምር። ታሞ አልጋ ላይ በዋለባቸው ጊዜያት በስልክ ያለበትን ሁኔታ ለመጠየቅ ስደውልልት ህመሙ ምንም እንኳ የከፋ ቢሆንም መዳንንና ወደ ሥራ መመለስን ተስፋ ያደርግ እንደነበር አውቃለሁ። ሆኖም የፈጣሪ መሻት ሆኖ ዛሬ ማረፉን ሰማሁ። አዘንኩም። ነፍስ ይማር !!!
(ከጀሚል ይርጋ ፌስቡክ የተገኘ)

Read 1725 times