Print this page
Sunday, 15 September 2019 00:00

ኢትዮጵያ በ2011 - በፖለቲካና በኢኮኖሚው ዘርፍ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 (የፖለቲካና ኢኮኖሚ ምሁራን ቅኝት)

              አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት የታየበት ዓመት
                    ሙሼ ሰሙ - (የፖለቲካ ተንታኝ)


            በ2011 ዓ.ም ያለፉትን አመታት ችግሮች ይዘን ነው የተቀበልነው፡፡ በዓመቱ በየቦታው ብልጭ ድርግም የሚሉ ግጭቶችና መፈናቀሎች ቢከሰቱም፣ ባንጻራዊነት የማህበራዊና ፖለቲካዊ መረጋጋት ታይቷል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ እየተከበረ ያለፈበት ጊዜ ነው፡፡ ዜጎች ተደራጅተው ለመታገል የሚያደርጉት ጥረት በአንፃራዊነት የተሻለ ነጻነት ታይቶበታል፡፡ የተፈጠሩ ግጭቶችም ከ2011 አመት በፊት እንደነበሩት ሳይሆን በአፋጣኝ ሲፈቱ አይተናል፡፡ ብዙ ጊዜ ችግሮች ከተባባሱ በኋላ ነበር ወደ መፍትሄ  የሚገባው፡፡ ባለፈው አንድ አመት ችግሮችን ቀድሞ መከላከል ላይ ደካማነት ቢኖርም፣ እግር በእግር ተከታትሎ የመፍታት ጥንካሬ ታይቷል:: በጥቅሉ ልንፈርስ ነው፣ ልንበተን ነው ከሚለው መንፈስ፣ እንደ አገር መቀጠል እንችላለን የሚል ተስፋ ተፈጥሯል፡፡
ለዚህ መንግስትም ትልቅ ስራ ሰርቷል፡፡ ሕዝቡም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል:: ሕዝቡ፤ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ጽንፈኛ ሀይሎችን ሴራ  ቀልብሷል፡፡ ልሂቅ ነን የሚለው አካል፣ አገሩን እስኪያፈርስበት ድረስ አልሰማውም፡፡ ስለዚህም እንደ አገር  መቀጠል ችለናል፡። ብዙ ሙከራዎች ግን ተደርገዋል፡፡ ሕዝቡ ጆሮ አልሰጠውም እንጂ፡፡
ሌላው የምርጫ ጉዳይ ነው። በኔ እምነት ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑና በሂደቱ ላይ ውይይት መጀመሩ፣ ያለፈው አመት አንዱ መልካም ተግባር ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ “አገሪቱ ትቀጥላለች ወይስ አትቀጥልም?” የሚለውን በስጋት ሲከታተለው ነበር፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ እንደ ሀገር ቀጥላለች፡፡ የአገሪቱን ጉዳይ አለቀማፉ ማህበረሰብ እንዲረዳ የተሠራው ዲፕሎማሲያዊ ስራ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህ የዲፕሎማሲ ስራ የውጭ ምንዛሬም ተገኝቷል:: ይሄ የ2011 ትልቅ ስኬት ነው፡፡
ግዙፍ የመንግስት ተቋማትን በሙሉና በከፊል ፕራይቬታይዝ ለማድረግ መወሰኑ፣ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ የ2011 ትልቅ ክንውን ነው፡፡ የኢኮኖሚ አቅጣጫ መቀመጡ ትልቅ ተግባር ነው:: የፀረ ሽብር ህግ፣ የምርጫና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ህግ መሻሻላቸው ገንቢ ተግባራት ነበሩ:: በ2011 በአንፃራዊነት መረጋጋት ነበር ስል፣ ሠላም ነበረ ማለቴ አይደለም፡፡ ሠላም በማስጠበቅ በኩል ድክመት ታይቷል፡፡ ሰዎች ይገደሉ፣ ንብረት ይዘረፍ ነበር፡፡ የዜጐችን የምግብ ዋስትና በማስጠበቅ ረገድም አፈጻጸሙ  ደካማ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ቡድኖችና ግለሰቦች፣ በመንግስት ላይ የሚያሳርፉት ተፅእኖ ገደቡን አልፎ ነበር፡፡ ጉልበትና ሃይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ስለነበር፣ ህዝቡ በመንግስት ላይ የነበረውን እምነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡ ቡድኖችና ግለሰቦች የሚፈልጉትን ነገር በጫና ማስደረግ መቻላቸው ደካማ ጐናችን ነበር፡፡
ሌላው የኢኮኖሚው ጉዳይ ነው፡፡ በነሐሴ ወር እንደሰማነው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ ከፍተኛውን የግሽበት መጠን አስመዝግቧል፡፡ በዚህ አመት ከፍተኛ ግሽበት፣ በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ታይቷል፡፡ ይሄ እጅግ አስፈሪ ነገር ነው፡፡ የዜጐች ገቢ ሳያድግ ግሽበትን መቋቋም ከባድ ነው፡፡ ለዚህ ግሽበት ምክንያቱ ደግሞ የሠላም መታጣት ነው:: ሰዎች ወጥተው እንዲገቡ፣ ገንዘባቸውን ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ የሠላም ዋስትና ያስፈልጋቸዋል:: ሠላም አለመኖሩ ነጋዴውን ስጋት ላይ ጥሎታል:: መንግስት የረጅም ጊዜ እቅድ የማጥናቱን ያህል፣ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ማምጣት ተስኖታል፡፡ የኑሮ ውድነት፣ ለአንድ ሀገር ከባድ ቀውስ ነው፡፡ ይሄን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ከመከተል ይልቅ፣ በኤሌክትሪክ ፍጆታና በነዳጅ ላይ ጭማሪ ማድረጉ የኑሮ ውድነቱን  አባብሶታል፡፡ የመብራት ፍጆታ 300 በመቶ፣ የውሃ ታሪፍ መቶ በመቶ መቶ መጨመሩ፣ በራሱ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ቀንሷል ይባላል እንጂ ተባብሷል፡፡ ኢኮኖሚው ላይ መንግስት ስር ነቀል ስራ መስራት አለበት፡፡
በዚህ ዓመት ሠላምና የህግ የበላይነትን ከማስፈን ባሻገር፣ የእኩልነት ስርአት መስፈን አለበት፡፡ ሂሣብ የማወራረድ ፖለቲካ ሊቆም  ይገባል፡፡ ሁላችንም በህግ የበላይነት ጥላ ስር  መኖር አለብን፡፡ በአዲሱ ዓመት ክልሎች ያሉበት ሁኔታ በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡ መንግስት በቂ መረጃ ይዞ ሊነግረን ይገባል:: በመንግስት ውስጥ ሌላ መንግስት የመሆን ዝንባሌ ይታያል፡፡ ይሄ በአፋጣኝ መሻሻል  አለበት፡፡


_______________________________________________                    የኑሮ ውድነት- የዋጋ ግሽበት-- የውጭ ምንዛሪ እጥረት
                         ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ብሩህ ተስፋ - (የኢኮኖሚ ባለሙያ)


          የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሩ በነበረበት  ነው የቀጠለው፡፡ የውጭ ምንዛሬ ችግሩም እንዲሁ፡፡ የኑሮ ውድነቱም ብሶበታል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ በተለይ ለከተማ ነዋሪዎች ከፍተኛ ጫና ነበር፡፡ የዜጎች የኑሮ ደረጃ ልዩነት አልተሻሻለም፡፡ በተለይ ቋሚ ገቢ አላቸው የሚባሉ የመንግስት ሰራተኞችና ጡረተኞች አሁንም ችግር ላይ ናቸው፡፡ የአገሪቱ የኤክስፖርት ምጣኔም አልጨመረም፡፡ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የኤክስፖርት ምጣኔያችን ሲቀንስ እንጂ ሲጨምር አልታየም፡፡ በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚው መሠረታዊ ችግር አልተፈታም፡፡
በዚህ መሃል ግን የተገኙ ስኬቶችም አሉ:: የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተዋል፣ መሰረተ ልማቶች እየተዘረጉ ነው፡፡ ኢኮኖሚውም ፈጣን አዳጊ የሚባል ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይሄ  መልካም እድል ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ኢኮኖሚውን ክፍት ማድረግ መጀመራቸው ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብዙ አገሮች ውጤታማ የሆኑት በዚህ አይነቱ ውሳኔ ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገቱን  ማስቀጠል መቻልም ትልቅ ስኬት  ነው፡፡ አሁን ያለብንን ዕዳ  መክፈል መቻል ጀምረናል፡፡ ፋብሪካ እየተቃጠለ በአመፅ ላይ የከረመ አገር ኢኮኖሚን አጠናክሮ ማስቀጠል በራሱ ትልቅ ድል ነው፡፡ ይህ የበለጠ መሻሻል አለበት:: ለዚህ  ደግሞ ፖለቲካውን ማቃናት ይጠይቃል:: ኢህአዴግ አንድነቱን አስጠብቆ መምራት መቻል አለበት፡፡ መንግስት ህግና ሥርዓትን ሲያስጠብቅና ሰላምን ሲያሰፍን ብቻ ነው ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ኢንቨስት የሚያደርጉት፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ተግባራት መከናወን አለበት፡፡ የፖለቲካ መረጋጋት እስከሌለ ድረስ ገበያው በትክክል ሊሰራ አይችልም::
በፋይናንስ ዘርፉ አሁንም ውሳኔ የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ መፈቀድ አለበት፡፡ የውጭ ባንኮች ሲመጡ የውጭ ምንዛሬ ይዘው ይመጣሉ፣ አዲስ የማኔጅመንት ስርዓት ያስተዋውቃሉ፡፡ እነዚህ  በእጅጉ ጠቃሚ ናቸው፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት መንግስትንም ሕዝብንም ከፈተኑ ጉዳዮች ዋነኛው  የኑሮ ውድነት ነው፡፡ ዛሬም የምግብ እርዳታ ጠያቂዎች ነን፡፡ ከዚህ ፈቅ አላልንም፡፡ ተፈናቃይነቱ ችግሩን አባብሶታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ማስተካከያ ይፈልጋሉ፡፡ በእርግጥ አሁን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ ይሄ መልካም ነው፡፡
ምርጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቢኖርም አተገባበሩ ላይ ካልተሰራ ዋጋ የለውም፡፡ የመንግስት አስተዳደር ሥርዓት ላይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ ፕሮፌሽናል መሆን ይገባዋል፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ ግልጽ ማስተካከያ ያስፈልጋል፡፡ የመንግስት ወጪ የሚቀነስበትና የግል ዘርፉ የኢኮኖሚው ተዋናይ የሚሆንበት አሰራር መመቻቸት አለበት:: የግብርና ዘርፉን ለማሻሻል ተብሎ ለዓመታት በርካታ ሴሚናሮች ተደርገዋል፡፡ ግን የመጣ ለውጥ የለም፡፡ ግብርናውን ለማሻሻል በቅድሚያ ገበሬውን ማማከር ውጤታማ ያደርጋል፡፡ በዚህ ረገድ በአዲሱ ዓመት ሁነኛ ስራዎችን ማከናወን  ያስፈልገናል፡፡


______________________                         አሁንም መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን
                            ስዩም ተሾመ - (መምህርና ጦማሪ)


              በአገር ላይ ያንዣበበ የህልውና አደጋ ተቀልብሶ፣ ሀገር የቀጠለበት አመት ነው፡፡ ከዚያ በፊት በአጠቃላይ የትርምስ ወቅት ነበር፡፡ ሃገሪቱ በአንድነቷ  ትቀጥል ይሆን? የሚል ስጋት ተጋርጦ ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም ይህን አደጋ የሚቀለብስ ሥራ ተከናውኗል፡፡ በአንድነት መቀጠላችን ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአገራችን የሚነሱ በርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎች፣ ለ100 አመትና ከዚያ በላይ ሲንከባለሉ የመጡ ናቸው፡፡ ለእነዚህ  ጥያቄዎች፣ በአንድ አመት  ውስጥ ምላሽ መስጠት እጅግ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ አዎንታዊ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡
የ100 አመት ችግሮችን ለመቅረፍ ግን የሚያስፈልገው ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን ስር ነቀል ለውጥ ነው፡፡ በኔ አረዳድ፣ አሁንም ለመለወጥ ወይም ላለመለወጥ የምንወስንበት  ጊዜ ላይ ነን፡፡ አማካይ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን፡፡ ያለፉ ስህተቶችን ተነጋግረን ለመለወጥ የምንወስንበት አማካይ ቦታ ላይ ቆመናል፡፡  
አፄ ኃይለስላሴ አምስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎችን አድርገዋል፡፡ እነዚያ ምርጫዎች ግን የራሣቸውን ስልጣን ከማደላደል የዘለለ ያመጡት ለውጥ  የለም፡፡ ደርግም አንድ ጊዜ ምርጫ አድርጓል፡፡ ግን  ስልጣኑን ማጠናከሪያ ነው ያደረገው፡፡ በኢህአዴግ  አምስት ምርጫዎች ተደርገዋል፡፡ እነሱም ተመሳሳይ አላማ ነበራቸው፡፡ አሁን ደግሞ ለ6ኛ ጊዜ ምርጫ ልናካሂድ ነው  ይሄ ምርጫ ለተመሳሳይ አላማ ይውል ይሆን ወይስ የተለየ ይሆናል? ይህን የምንወስንበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ እንደኔ፣ ምርጫ ከማካሄዳችን በፊት አማራጭ ሊኖረን ይገባል፡፡ በ2012 የፖለቲካ አማራጮች የምናገኝበት ጊዜ መሆን አለበት፡፡ አማራጭ ሃሳቦችና የፖለቲካ ቡድኖች በሌሉበት፣ ምርጫ ማድረግ ምን ጥቅም አለው? እንዲሁ ይደረግ ከተባለ፣ ከስህተታችን አልተማርንም ማለት ነው፡፡ 2011 ለመለወጥ ወይም ላለመለወጥ የምንወስንበት ዓመት ነበር፤ ግን ሳንጠቀምበት አልፏል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ አመት  መጥቷል፡፡ ይሄን አመት ለመወሰን እንጠቀምበት ይሆን? ላለፉት 100 አመታት የተሠሩ ስህተቶችን  እንደግመው ይሆን ወይስ አዲስ መንገድ እንከተል ይሆን? ይሄ የሚወሰንበት ጊዜ ከፊታችን አለ፡፡
ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እየዳበረ መምጣቱ፣ የ2011 አንዱ ስኬት ሲሆን፤ ይህ ግን ይበልጥ መዳበር አለበት፡፡ ዜጐች ተቃውሟቸውንና  ሃሳባቸውን በመግለፃቸው፣ ሰበብ እየተፈለገ መታሰር የለባቸውም፡፡
አሁንም የታሠሩ ጋዜጠኞች አሉ፡፡ በ2012  መፈታት አለባቸው፡፡ ይሄ እስካልሆነ ድረስ ለውጡ  በቀላሉ ሊቀለበስ ይችላል፡፡ የዘንድሮን ምርጫ  ማካሄድ፣ ያለፉትን 5 ምርጫዎች መድገም ነው፡፡ መለወጥ የምንሻ ከሆነ፣ ምርጫው ለውጥ የሚያመጣ  መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ አማራጭ ሃሳቦችና የፖለቲካ ቡድኖች ለህዝቡ መቅረብ አለባቸው፡፡ ከዚህ አንጻር  ምርጫው መራዘም አለበት፡፡ 

Read 7019 times
Administrator

Latest from Administrator