Saturday, 14 September 2019 11:19

ቃለ ምልልስ “እዚህ አገር ባለሥልጣናትን ማሳቅ ከባድ ነው”

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ - የአዲስ ዓመት እንግዳ

         አዲስ አበባ ተወልዶ አዳማ ነው ያደገው፡፡ ከ10 ዓመት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴአትር ጥበባት ትምህርት በማዕረግ መመረቁን ይናገራል፡፡ ከውጭዎቹ እውቅ ኮሜዲያን ኬቨን ኸርትን፣ ከአገራችን ደግሞ ደረጀና ሀብቴን፣ እንግዳ ዘር ነጋን፣ ተስፋዬ ካሳንና ሌሎችን ያደንቅ ነበር፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነትንና ተወዳጅነትን ያተረፈው ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ፤ የስኬቱ ምስጢር ምን ይሆን? የፖለቲካ ቀልዶች ላይ ያተኮረበት ምክንያት ምንድን ነው? የአዲስ ዓመት ዕቅድና የወደፊት ህልሙንም ነግሮናል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከኮሜዲያኑ ጋር ያደረገችው አዝናኝ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡


               ‹‹ፌስቡክ ከእኛ አገር የቡና አፈላል ሥርዓት የተቀዳ ነው›› በሚለው ቀልድህ ብንጀምርስ ---
እሺ! የሕዝብና ቤት ቆጠራ ላይ ነው፡፡ አንዱ ቆጣሪ ሴትየዋን  ይጠይቃል፡-
 ‹‹እድሜዎት ስንት ነው?››
‹‹የኔ እድሜ?››
‹‹አዎ የእርስዎ እድሜ››
‹‹አስካለ ስንት አለችህ?›› ጎረቤታቸው ናት አስካለ፡፡
“ወ/ሮ አስካለ እንግዲህ አርባ አመቴ ነው ብለዋል” አላቸው ቆጣሪው፡፡
‹‹ውይይይይ›› አሉ ሴትየዋ፤ ‹‹እንግዲያውስ የእኔ 20 ዓመት ነው፤ ምክንያቱም እርሷ በእጥፍ እንደምትበልጠኝ አገር ያውቃል›› ይሉታል፡፡
‹‹እሺ መተዳደሪያዎት ምንድነው?›› ሲላቸው
 ‹‹መተዳደሪያዬማ ሕገ መንግስቱ ነዋ››! ይሉታል::
‹‹ኧረ የገቢ ምንጭዎትን ነው ያልኩት” ይጠይቃቸዋል እንደገና፡፡
‹‹ይህቺ ጫፍ ላይ ያለችው አረቄ ቤት ትታይሃለች!››
‹‹አሃ በእሷ ነው የሚተዳደሩት›› ይላል ሕዝብና ቤት ቆጣሪው፡፡
‹‹ኧረ በፍፁም! ባለቤቴ እዛ ይጠጣና ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ መጥቶ ሲተኛ፣ ኪሱን እየፈተሽኩ ብር ካለ በዛ ነው የምተዳደረው›› ይሉታል፡፡
‹‹በትርፍ ጊዜዎት ምንድነው የሚሰሩት?››
‹‹አሂሂሂ… ትርፍ ጊዜ ከየት መጥቶ የኔ ልጅ››
‹‹እንደው አንዳንዴም ቢሆን ትርፍ ጊዜ አይጠፋም ብዬ ነው››
‹‹በትርፍ ጊዜዬ እንግዲህ ፌስቡክ እጠቀማለሁ›› አሉት፡፡
‹‹እንዴት?›› ሲል ጠየቃቸው፤ ገርሞት፡፡  
‹‹ይሄውልህ የኔ ልጅ.. መጀመሪያ ቡናው ሲቀራርብ ‹‹ኦንላይን›› ገባህ ማለት ነው፡፡ ጎረቤት ቡና ጠጡ ብለህ ስትጠራ ‹‹ፍሬንድ ሪኩየስት›› ነው:: ከዚያ ጎረቤት ሲመጣ፣ ቡና ቁርስ ስታድል ‹‹ሼር›› አደረገ ይባላል፡፡ ቡናውን ቀምሶ ሲያደንቅ ‹‹ላይክ›› አደረገ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ቡናው እስኪያልቅ ‹‹ቻት›› እያደረግን፣ ሀሜት ‹‹ፖስት›› እናደርጋለን፡፡ እናም ይሄ የፌስቡክ አካሄድ ከእኛ የቡና አፈላል ስነ ሥርዓት ነው የተቀዳው” አሉት፡፡
የመጀመሪያ ሥራህን የት ነው ያቀረብከው?
ኢዮሃ ሲኒማ ነው የሰራሁት፡፡ እዛ መድረክ ላይ የአንድ ሰዓት ሾው ነበረኝ፡፡
ኮሜዲህ በፖለቲካው ላይ ነው የሚያተኩረው:: ከለውጡ መምጣት ጋር ተያይዞ ነው የደፈርከው?  
በ2006 ዓ.ም ኢዮሃ ሲኒማ ከገባሽ ‹‹ጣዝማ ማር››ን ማለትም ጥቁሯን የፖሊስ ዱላ በተመለከተ የሰራሁትን ቀልድ ታውቂዋለሽ፡፡ ‹‹ለአመታት የአደገኛ ቦዘኔዎችን ጥጋብ ስታበርድ የነበረች ድንቅ የፌደራሎች ዱላ ጣዝማ ማር፤ ከጥቁር ፕላስቲክ የተሰራች፣ ለአያያዝ አመቺ፣ ለመቀጥቀጥ ቀላል፣ በተመሳሳይ ዱላ እንዳይታለሉ፣ አንዴ ቀምሰዋት ሰማይ ምድር ከዞረብዎ አሊያም እግርዎ ላይ ተመትተው ጭንቅላትዎ ካበጠ፣ እሱ ትክክለኛው ጣዝማ ማር ነው፡፡ በ8፣ በ10 እና በ12 ሰዓት በሁሉም ማረሚያ ቤት ያገኙታል፤ ለሰንበርዎ ማማር ምንጊዜም ጣዝማ ማር!›› የሚለውንና የፌደራልን ዱላ በደንብ የተቸሁበትን ሥራ ያኔ ነው ያቀረብኩት:: ለውጡ ሳይመጣ ማለት ነው፤ ስለዚህ ፈሪ አልነበርኩም፡፡
ከዚያ  በመሃል የት ጠፋህ?
እንግዲህ ሕይወትም አይደል… ‹‹የኛ›› የሚባል ድርጅት ቀጠረኝ፡፡ ሲቀጥረኝ ደግሞ ድርጅቱ ውስጥ ብቻ እንድሰራ ነው የተዋዋልነው። በወር የሚከፈለኝ የአንድ የመንግስት ሰራተኛ የ6 ወር ደሞዝ ነበር፡፡
ለመሆኑ ስንት  ቢሆን ነው?
ተይ ትደነግጫለሽ… ደሞዝ ለመቀበል ስንሄድ ጆንያ ይዘን ነው፡፡ ለዚህ ደሞዝ እንኳን በኤክስክሉሲቭ መቀጠር አይደለም… በኤክስኪዩቲቭም ቢሉ በቃ መገጨት ነው፡፡ ደሞዙ ያስገጫል!!
እኮ ስንት ነው? በቁጥር ንገረኝ…
ስንት መሰለሽ!...እኔ እንግዲህ 21 ቁጥርን በማሪያም ነው የማውቀው፡፡ የአንድ ወር ደሞዜ 21 ሺህ ብር ነበር፡፡ እ! ነው ያልኩት፡፡ ‹‹የኛ›› ውስጥ ለአራት ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ ለውጥ ወዳልሽው ስመጣ… መቼ ነው የመጣው? 2010 ማብቂያ ላይ ነው፡፡ 2010 ደግሞ ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነው:: ያኔ እኔ ማናጀር ቀጥሬ፣ ራሴን አደራጅቼ ኮሜዲ ጀምሬ ነበር፡፡ ‹‹ጆሲ ኢን ዘ ሃውስ ሾው›› ላይም እንግዳ ሆኜ ቀርቤ ሁሉ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ፑሽኪን አዳራሽ መጣሁና “የ1 ሰዓት ስታንድ - አፕ ኮሜዲ ሰርቻለሁና ገምግሙልኝ” ብዬ መድረክ አዘጋጀሁ፡፡  ገምጋሚዎቹ ቅጥቅጥ አደረጉኝ፤ በደንብ ነው የተቹኝ፡፡
ምን ብለው ተቹህ…?
ስለ ጠበሳ… ስለ ሴቶች ነው ይዘቱ… ‹‹ከጣዝማ ማርም›› ትንሽ ጨምሬበት ነበር… የ1 ሰዓቱን ሾው ያቀረብኩት፡፡ በሴቶች ጉዳይ ላይ አስተያየት ሰጡኝ:: የሴቶችን ክብር ይነካል፣ የማይባሉ ቃላትን ተጠቅመሃል… ብቻ ብዙ ነገር አሉኝ፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ በጣም የተደነቁም ነበሩ፡፡ ‹‹አንድ ሰዓት ሙሉ ሳናውቀው ነው ያለቀው›› ያሉ ሁሉ አሉ፡፡ ከዚያ በኋላ መድረክ ስጠይቅ ግን ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው›› እያሉ ሁሉም ሊፈቅዱልኝ አልቻሉም:: ስለዚህ ያንን የተገመገመውን አሻሽዬና አስተካክዬ፣ መስከረም 17 ቀን 2011 ዓ.ም ለመስቀል በዓል በጄቲቪ ኢትዮጵያ ቀረበ፡፡ ይሄ ማለት 2010 ላይ የበሰለው ነው፤ በ2011 የቀረበው፡፡ ፈርቼ አይደለም ለማለት ነው፡፡ ብፈራም ደግሞ አይፈረድብኝም:: ጊዜው መፍራት የሚያሳፍርበት ጊዜ አልነበረም፤ ሁሉም ያውቀዋል።
ኮሜዲ ስትጀምርም በፖለቲካ ነው ወይስ ከጊዜ በኋላ ነው የለወጥከው?
በነገራችን ላይ በፖለቲካ አይደለም ኮሜዲ የጀመርኩት፡፡ አሁን ሳላውቀው ሰዎች ፖለቲካል ኮሜዲ ነህ ይሉኛል፡፡ እኔ ግን በስሜት ነው የጀመርኩት፡፡ ስሜቴ የተነካበትን፣ የተናደድኩበትንና የተከፋሁበትን ነገር ነው የምጽፈው፡፡ ለካስ ያ ነገር በአብዛኛው ከፖለቲካ ጋር ይገናኛል፡፡ ይሄ አንዱ ነው፡፡ ፖለቲካ ላይ ስቀልድ ሰው በጣም ይስቃል… በጣም ያራባዋል፡፡ ይሄም ፖለቲካ ላይ ብሰራ የበለጠ ሰው ይወደዋል የሚል ተፅዕኖ አሳድሮብኝ ይሆናል:: እኔ የገባኝን ነገር እየዋሸሁ ማለፍ አልፈልግም:: ፓተርንም አነባለሁ፡፡ ፓተርን ሳነብብ ጎበዝ ነኝ፡፡ ምን አይነት ፓተርን ካልሺኝ… ምን አይነት ቀልድ ስቀልድና በምን መንገድ ሳቀርበው ነው ሰው በጣም የሚስቀው? ምን አይነት ሀሳብ ሳነሳ ነው ሰው ይበልጥ የሚነጋገረው የሚለውን አውጠነጥናለሁ፡፡ ለምሳሌ ስለ ኢትዮጵያዊነት ውስጤን ቆስቁሶኝ ስሰራ ሰው በጣም ይነጋገርበታል፡፡ ‹‹የት ነበርን›› የሚለው ቀልድ በጣም ተወዷል፡፡ ሰው ተነጋግሮበታል፡፡ በተለይ በውጭ አገር፡፡ እሱን ሳይ… እዚህ አገር ሰው ራስ ምታት የሆነበት የዘረኝነት፣ የብሄርና የፖለቲካው ጉዳይ ነው። እነዚህ ነገሮች ላይ አጥንቼ መፍትሄ የሚሰጥ ኮሜዲ መስራት አለብኝ ወደሚል ነገር መጥቻለሁ፡፡ ነገር ግን ፖለቲካ ላይ ብቻ መቀለድ አልፈልግም፡፡ እኔ አጠቃላይ ማህበራዊ ሂስ (Social critics) ላይ መስራት ነው የምፈልገው፡፡ ይህንንም በጥናትና በእውቀት ላይ ተመስርቼ ነው የምሰራው፡፡
ፖለቲካ ላይ እውቀትህ እንዴት ነው? ታነባለህ? የዕለት ተዕለት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ትከታተላለህ?
እውነቱን ነው የምነግርሽ እሺ! ፖለቲካ ላይ በጣም ቀሽም ነኝ፤ የጠለቀ እውቀት፣ ያደገና የዳበረ ግንዛቤ የለኝም፤ ነገር ግን እውነቱ ምንድነው… ከስሜቴ ተነስቼ ነው የምፅፈው ብዬሻለሁ፡፡ አንድ ጉዳይ ስሜቴን ከነካው በዚያ ጉዳይ ዙሪያ እቆፍራለሁ፡፡ ጥልቅ የፖለቲካ እውቀት ላይኖረኝ ይችላል፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ በሆነ ጉዳይ ላይ ስሜቴ ተነክቶ ልሰራ ከፈለግሁኝ በዛ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጽሐፍት፣ የተሰሩ ዜናዎችና መረጃዎች ካሉ፣ ለዚህ ስራ የመደብኩት ባለሙያ (ሪሰርቸር) ስላለኝ የምፈልገውን ሁሉ ቆፍሮ ያመጣል፡፡ ሁሉንም አያለሁ፣ አመዛዝናለሁ፡፡ ከፖለቲከኞች ጋር፣ ከጋዜጠኞች ከስነ ልቦና ባለሙያዎች ጋር ስራዬ ብዬ ቀጠሮ አስይዤ ሄጄ አወራለሁ። የምፈልገው ርዕሰ ጉዳይ ላይ አተኩሬ እውቀት እሰበስባለሁ፡፡  
በመንግስት ባለሥልጣናት፣ በፖለቲከኞች፣ በባለሀብቶች ላይ ትቀልዳለህ? ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብህ ያውቃል?
በመጀመሪያ በእምነት ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ምን ብዬ አምናለሁ መሰለሽ… የመናገር ነፃነት ተጨቁኖ ቆይቷል፤ ሰዎች ሀሳባቸውን በነፃነት መግለጽ አለባቸው ተባለ አይደለ! በቃ  ነፃነት ሰጥተናችኋል ተብለናል አይደለም! በቃ እሱን ቃል ተማምኜ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ይሄን ያለው ግለሰብ አይደለም፤ መንግስት ነው፡፡ ነፃነት በአደባባይ ተሰጥቶናል:: ይሄንን ለምን እጠራጠራለሁ? ደግሞም ነፃነትን ሳይጠቀሙ ማለቃቀስ ተገቢ አይደለም ብዬም አምናለሁ፡፡ ይሄንን የተሰጠንን ነፃነት እጠቀምና የሚመጣውን አያለሁ ከሚል ነው ድፍረቴ የመነጨው፡፡ ግን ከዚያም በላይ የምመካበት የምታመንበት ሀይል አለኝ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፡፡ በተረፈ እኔ አንድን አካል ለመጉዳትና ሌላ አካልን ለመጥቀም አይደለም የምሰራው፡፡ እውነትን ይዤ ነው፡፡ እውነትን በመናገሬ የሚከፋ አካል ካለ ምንም ማድረግ አልችልም፤ አዝናለሁ፡፡
በቀላሉ ማሳቅ የሚቻለው የትኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ነው?
በአጠቃላይ ለመሳቅ ቅርብ የሆነ ሰው፣ መዝናናት የሚፈልግ ሰው ነው። አንዳንድ ሰው ስታንድ አፕ ኮሜዲ ሊያይ መጥቶ፣ አንድ ሰዓት ሙሉ ምንም ሳይስቅ ይወጣል፡፡ አጠገቡ ሰው በሳቅ እንባውን እያፈሰሰ ማለት ነው። እንዲህ አይነት ሰው ይኖራል፡፡ በአንደኛ ደረጃ የሚስቁት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ቀልዱ ገና ግማሽ ላይ እያለ ነው የሚገባቸው፡፡ ምን ለማለት እንደፈለግሁ ቀድመው ያውቁና በጣም ይስቃሉ። ሁለተኛ ደግሞ የኮሜዲ አፍቃሪዎች አሉ፡፡ በነገራችን ላይ የኮሜዲ ሾው ሲዘጋጅ ሁሉም ሰው ነው የሚገባው፡፡ የኮሜዲ አፍቃሪውም ኮሜዲ የማያፈቅረውም ልሳቅ ብሎ ይገባል፡፡ ኮንሰርት ብቻ የሚመቸውም ይገባል:: ነገር ግን የኮሜዲ አፍቃሪዎች አሉ፡፡ ቤት ውስጥ ሆነው ከዩቲዩብ እያወረዱ፣ የውጭውንም የአገር ውስጡንም የሚያዩ፡፡ እነሱ ሲመጡ ገና በአይን ነው የምንተዋወቀው፡፡ በቃ ሊዝናኑ ነው የሚመጡት፤ በጣም ይስቃሉ፡፡ ብዙ ሀላፊነት ስላለባቸው ነው መሰለኝ ባለሥልጣናት እዚህ አገር አይስቁም፡፡ ቀልዱ እየተቀለደ ስለ ፖሊሲ ምናምን የሚያስቡ ይመስለኛል፤ የሚያዳምጡም አይመስለኝም:: ባለሥልጣናት ለማሳቅ ከባድ ከሆኑት ውስጥ ይመደባሉ፡፡ እኔ ግን በዚህ አጋጣሚ የምነግርሽ… አዲስ ተመልካች ከቤቱ ያስወጣሁና ያመጣሁ ይመስለኛል፡፡
እንዴት ማለት?
ኮሜዲ ለማየት ወጥቶ የማያውቀውን ሁሉ አምጥቻለሁ ማለቴ ነው፡፡ አሁን ቪዲዮዎቼን ባሳይሽ መነጽር ያደረጉ ትልልቅ ሰዎች ጡረተኞች፣ ያረጁና ቤት ይቀመጡ የነበሩ፣ ትልልቅ ሥራ ላይ ያሉ ሰዎች ለምሳሌ ዶክተሮች፣ ካፒቴኖችና እንደ አፍሪካ ህብረት ባሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ሰዎች ሁሉ መታደም ጀምረዋል፡፡ አስተያየቶች ይደርሱኛል፡፡
ከኮሜዲያን ማንን ታደንቃለህ?
እኔን የፈጠሩኝ የእኛ አገር ኮሜዲያኖች ናቸው፡፡ ደረጀ ሀይሌና ሀብቴ ምትኩ፣ አስረስ በቀለ፣ እንግዳ ዘር ነጋ… ናቸው፡፡ እነሱ በዚያን ዘመን ይሰሩት የነበረው ኮሜዲ ድንቅ ነበር፡፡ አየሽ ሥራችን ውስጣችን የቀረው የሕዝቡን ስሜት አይተው  ከልባቸው ስለሚሰሩት ነው፡፡ በሕይወት ካሉት ደረጃ ሀይሌንና አስረስ በቀለን በጣም አደንቃቸዋለሁ፡፡ ከሴቶች ቤቲ ዋኖስ፡፡ እስከዛሬ ብቸኛዋ በሴትነቷ በብዙ ሀላፊነት ውስጥ ሳትጠለፍና ሳትወድቅ በስታንዳፕ ኮሜዲ በጽናት የዘለቀች ናት፡፡ አደንቃታለሁ፡፡ ከውጭዎቹ ደግሞ ወደዚህ ዘርፍ እንድገባ በጣም የገፋፋኝ ኬቨን ኸርት ይባላል፡፡ ድምጽ አወጣጡ… የፊት ገፅታው… ሁሉ በጣም አስገራሚ ነው፡፡ የኬቨን ኸርትን ታሪክ አንብቤዋለሁ፡፡ መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ሳነበው ታሪኩ እንደኔ ነው፡፡ የራሱን ሾው ራሱ ሰርቶ፣ መድረክ ፈጥሮ፣ ብር ተበድሮ ነበር የሚሰራው:: የመጀመሪያውን ሾው ሊቀረጽ ሄዶ የአውሮፕላን መመለሻ ብር እንኳን አልነበረውም። እንዴት ፈግቶ ትልቅ ደረጃ ላይ እንደደረሰ አውቃለሁ፡፡ እኔም ከኢዮሃ ሲኒማ በስተቀር ማንም መድረክ ሰጥቶኝ አያውቅም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢዮሃ ሲኒማን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ግን ‹‹ቤላ ቬርዴ›› የሚባል ክለብ ሰርቼ ነበር፡፡ የዛሬ አምስት አመት ገደማ። ከዚያ ውጭ ራሴ መድረክ ፈጥሬ፣ ተጣጥሬ… ራሴ ፕሮዲዩስ አድርጌ ነው የምሰራው:: እግዚአብሄር የፕሮዲዩሰርነትም ፀጋ ሰጥቶኛል:: ኬቨን ኸርት ከዜሮ ተነስቶ እዚህ የደረሰበትን መንገድ ስለምከተል ጥንካሬ አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ትሬቨር ኖህን አደንቃለሁ። ፖለቲከኞችንና ፖለቲካን በቀልዱ የሚተች እውቅ ኮሜዲያን ነው:: ትሬቨር ኖህ ከደቡብ አፍሪካ ወጥቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፈ ኮሜዲያን ለመሆን ችሏል። አገሩንም ለማስጠራት በቅቷል፡፡ እኔም ነገ ከኢትዮጵያ ወጥቼ፣ አገሬን ለማስጠራት እመኛለሁ፡፡
ሰሞኑን በአዶትና በዓለም ሲኒማ ያቀረብከው ስታንዳፕ ኮሜዲ እንዴት ነበር?
እስካሁን እኔ የምሰራው የበዓል ፕሮግራም ነበር:: አሁን ግን አንድ ሙከራ አድርጌያለሁ። አዳራሽ ተከራይቼ ማስታወቂያ ሰርቼ፣ ሰው ከፍሎ ይገባል ወይ የሚለውን ሙከራ ሰርቻለሁ፡፡ በአዶት ሲኒማ በ8 እና በ11 ሰዓት በሰራሁት ‹‹አንድ ዶላር›› የተሰኘ ሾው ላይ ተደንቄም አላበራሁ፡፡ ምክያቱም አዳራሹ 600 ሰው ነው የሚይዘው፤ ተጨማሪ ወንበር ገብቶ ያም ሞልቶ ሰው ተመለሰ፡፡ የ11 ሰዓቱን ነው የምልሽ:: በ8 ሰዓቱ ሰው አልተመለሰም፤ ለመሙላትም ትንሽ ይቀረው ነበር። ቀን ላይ ዝናብ ነበር፤ በዚያ ምክንያት መለሰኝ፡፡ የ11 ሰዓቱ እንደነገርኩሽ ሰው በሰው ላይ ሆኖም፣ የተመለሰው ውስጥ ከነበረው አይተናነስም፡፡ የገቡት ሰዎች  ደግሞ ባለትዳሮች፣ ጥንዶች፣ ከአሜሪካና ከጀርመን እዚህ አገር ቤት ያሉ ቤተሰቦችና ዘመድ ወዳጆችን የጋበዙ ሁሉ አሉ:: ትኬት እንዳያልቅብን በሚል በስልክ የነበረውን ጉትጉታ ልነግርሽ አልችልም። ይሄ ማለት የኮሜዲ ረሃብ አለ ማለት ነው፡፡ ባይገርምሽ የአዶቱ ሾው ሰውን ስላላረካው የተመለሰውም ብዙ ስለሆነ፣ ጳጉሜ 2 እና 3 በዓለም ሲኒማ ደግመነዋል፡፡ ይህ ሙከራዬ እጅግ አበረታቶኛል፡፡ በሌላ በኩል፤ አሁን እየሰራሁት ያለው ፕላትፎርም ነገ አዲስ ለሚመጣ ኮሜዲያንም፤ ኮሜዲ ሰርቼ አዳራሽ ተከራይቼ በራሴ ቆሜ በርካታ ኦዲየንስ በተገኘበት 100 እና 200 ብር እየከፈለ እንዲያይ ማድረግ እችላለሁ… የሚል ልበ ሙሉነት ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ፡፡ እስከ ዛሬ ኮሜዲያኖቻችንን ሰው ጠርቶ ነበር የሚያሰራቸው፡፡
በአንድ መድረክ የተከፈለህ ትልቁ ክፍያ ስንት ነው?
ከኤልቲቪ ጋር በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ባቀረብኩት ሾው ነው ትልቁን ክፍያ ያገኘሁት፡፡ በመድረክ 5 እና 10 ሺህ ብር ለሚቀበል ሰው ከፍተኛ ገንዘብ ነበር፡፡ መጠኑን ይሄን ያህል ነው ባልልሽም፡፡
አንተም እንደ ዘፋኞች… የተከፈለህን ብር አትናገርም ማለት ነው? እስኪ አንተ እንኳን ነገረኝ…
በቃ በቃ… እኔ 100ሺህ ብር ነው የተከፈለኝ፡፡
ግን ለምንድን ነው በዚህ ዙሪያ አንድ ኮሜዲ የማትሰራው? በሌላው ዓለም የአርቲስቶች ስኬት የሚለካው በሚከፈላቸው ከፍተኛ ገንዘብም ጭምር ነው… እኛ አገር ግን አርቲስቱ የተከፈለውን ሲጠየቅ አይወድም?
ትክክል ነሽ፡፡ በዚህ ላይ መስራት ይኖርብኛል:: አስብበታለሁ፡፡ እንደውም በቅርቡ ጠብቂ፡፡ በነገራችን ላይ ኤልቲቪ 100 ሺህ ብር ሙሉውን ነው የከፈለኝ፡፡ አየሽ አጠቃላይ… (ግሮሱ) 130ሺህ ብር ነው፤ እኔ ደረሰኝ ስላለኝ 30ሺህ ብር ታክሱን እነሱ ከፍለው፣ ለኔ 100ሺህ ብር ነው የሰጡኝ፡፡ በሌላ በኩል፤ ቀረፃውን (በነገራችን ላይ እኛ ሾው ስንሰራ በስድስትና ሰባት ካሜራ ነው የምንቀርፀው፡፡) እነሱ የካሜራ የአውሮፕላን ትኬት፣ የቡድኑን ምግብና መኝታ ሙሉውን ወጪ ሸፍነዋል፡፡ ከዚያ ደግሞ ስፖንሰር ካጣሁ 50 በመቶ ሊሰጡኝ ተስማማን፤ ለበዓሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ብቻም አይደለም:: “ዶንኪቲዩብ” የተባለው ዩቲዩብ ቻናሌ ላይም ለመጫን ፈቅደውልኛል፡፡ ይሄን ይሄን ስታስቢው ክፍያው 200 ሺህና ከዚያ በላይ ነው፡፡ ይሄንን ሁሉ ከባድ ውል ሙያውን አክብረው ሲስማሙ፣ ጐንደር ዩኒቨርሲቲ እንድንሰራ ጠየቅኋቸው:: ከዚያ በፊት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለተፈናቃዮች የሰራነውን መድረክና የጐንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ምሳሌ አድርጌ የማሳይበት መድረክ እፈልግ ነበር:: ተማሪው የካፌ ቁርሱን እየለገሰ ይግባ አልኩኝ፡፡ ያለ ክፍያ ማለት ነው፡፡ ጐንደር ዩኒቨርስቲዎች ይህን ሲሰሙ ደስ አላቸው፡፡ ሾው ተሰራ፡፡ ብዙ ተማሪዎች ገቡ፡፡ በዚያ ሾው ብቻ ወደ መቶ ሺህ ብር ተገኝቶ ለተፈናቀሉ ወገኖች ተሰጥቷል፡፡ ፈጣሪ ይመስገን… ስራው ቦምብ ሆነ፡፡ በመፈናቀል ዙሪያ ነበር የሚያጠነጥነው፡፡ ሰው እየነቀሉ ችግኝ መትከል ተገቢ አይደለም… የሚል ይዘት ያለው ነው፡፡ መፈናቀል በጣም የበዛበትና አሰቃቂ የነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ከቡራዩ የተፈናቀሉትን… (አራስ ጭምር) ሲያለቅሱ ሳይ ስሜቴ ይነካ ነበር፡፡ በአካል ሄጄም አግኝቻቸው ነበር፡፡ ስራው ሲወጣ ግማሹ ፖለቲሳይዝ አደረገው:: ከፊሉ እንደኔው ስሜቱ ተነክቶ፣ ሃሳቡን ተጋራኝ፡፡ ብቻ በጣም የገነነ ነበር፡፡ እናም ሳላስበው በደንብ የታወቅሁበት ሥራ ሆነ ፡፡
ትልቁን ክፍያህን ነግረኸናል። ትንሹ ክፍያህስ ?
በ2004 ዓ.ም ክለብ ቤላቬርዴ ስሰራ በመድረክ 600 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡ ያኔ ልጅ ያሬድ እየገነነ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ለእሱ በመድረክ 3 ሺህ ብር ነበር የሚከፈለው፡፡
ለአዲሱ አመት ምን አቅደሃል?
በእቅድ ደረጃ ስታንዳፕ ኮሜዲን በውጭ አገር ደረጃ ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ በውጭ ዩኒቨርስቲ ወይም እዚሁ በኦንላይን ሊሆን ይችላል፡፡ እርግጥ ውጭ መሄዱ ከስራው ስለሚያወጣኝ ብዙ አልፈልገውም፡፡ የሆነ ሆኖ መማር ግን እፈልጋለሁ:: ከተማርኩ በኋላ እዚህ አገር የስታንዳፕ ኮሜዲ ት/ቤት መክፈትና ማስተማር እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው በአዲሱ አመት እጅግ ከማደንቀው ኮሜዲያን ደረጀ ሀይሌ ጋር በመላው ኢትዮጵያ እየዞርን ሥራችንን እናቀርባለን፡፡ አገሪቱን ሰላም ያድርጋት እንጂ በቃ በመላው ኢትዮጵያ እንዞራለን፡፡ በነገራችን ላይ አዲሱ አመት የሳቅና የደስታ ነው የሚሆነው፡፡
ሌላው በአዲሱ አመት ቴአትር ቤቶችን ልዞራቸው ነው፡፡ መስከረም 5 ቀን ብሔራዊ ቴአትር፣ በሳምንቱ ሀገር አቀፍ፣ በሳምንቱ አምባሳደር እንደገና በሳምንቱ ተመልሼ ማክሰኞ ቀን ብሔራዊ ሾው አሳያለሁ፡፡ ለዚህ በጣም እየተዘጋጀሁ ነው ያለሁት፡፡ የምሰራው ደግሞ አዲስ ስራ ነው፤ እስከ ዛሬ ያላቀረብኩት ማለት ነው፡፡ በዚህም ከአድናቂዎቼ ጋር በስፋት እንገናኛለን፡፡ የዛ ሰው ይበለንና፡፡
ዕውቅናና ዝና እንዴት እያደረገህ ነው?
ዝና እንዴት እያደረገህ ነው ከምትይኝ፣ ፍቅር እንዴት እያደረገህ ነው ብትይኝ እመርጣለሁ፡፡ ከፍተኛ ፍቅር እያገኘሁ ነው፡፡ እኔም ከእነ ትህትናዬ ዝቅ ብዬ ነው ፍቅር የምቀበለው፡፡ በነገርሽ ላይ አኗኗሬ አልተቀየረም፤ የድሮው እሸቱ ነኝ፡፡ ውሎዬ፣ ቤቴ፣ አለባበሴ ያው ነው፡፡ መድረክ ሲኖረኝ ብቻ ነው ሱፍ የምለብሰው፡፡ የሕዝቡ አቀባበል፣ ፍቅርና አክብሮት ይበልጥ ዝቅ እንድልና የበለጠ ትሁት እንድሆን ነው ያደረገኝ፡፡ የዝና ሰለባ አልሆንኩም፤ አልሆንምም፡፡ ከፍተኛ የሰው ፍቅር አለ፡፡ በመኪና ሲያልፉ ‹‹ምርጧ›› ባይ በሽ ነው፡፡ ምርጥ ከመባል በላይ ምን ፍቅር ይመጣል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ገና ሳልሰራ እንዲህ የወደደኝና ያከበረኝ፣ አንድ አስር ዓመት ባገለግለው እንዴት ሊያደርገኝ ነው የሚለውን እያሰብኩ በጣም ደስ ይለኛል፡፡
በመጨረሻ አንተ ቀረ የምትለው ካለህ…
እንግዲህ አጋጣሚውን ካገኘሁ ከመንግስት ምን ይጠበቃል የሚለውን እናንሳ፡፡ ኮሜዲው ላይ ከመንግስት የሚጠበቅ ነገር አለ ብዬ ስለማምን ነው፡፡ “ደህና መካሪ የሌለው ንጉስ ያለ አንድ አመት አይነግስ” ይባላል፡፡ መሪዎች የህዝቡን ሀሳብ ማዳመጥና ክፍተታቸውን ማየት አለባቸው፡፡ እኔ መድረክ ላይ ቆሜ የማወራው’ኮ የእሸቱን ሃሳብ አይደለም፡፡ በደንብ አጥንቼ ማህበረሰቡን በግራ በቀኝ አዳምጬ ነው መድረክ ላይ የሕዝብ ድምጽ ሆኜ የምወጣው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ አርቲስትና ኮሜዲ እድልና ነፃነት ተሰጥቶት፣ የሕዝቡን ስሜትና ፍላጐት ማውጣት አለበት፡፡ መንግስት የይስሙላ ሳይሆን የእውነት መድረክና ነፃነት ፈጥሮ ማለቴ ነው:: በአስተዳደር ፣ በስርዓቱ፣ በአካሄዱ ላይ ያለውን ክፍተት እንደ መስታወት እንዲያሳዩት መፍቀድ አለበት፡፡ ይህ ይጠቅመዋል እንጂ አይጐዳውም፡፡
በዙሪያው የሚያጀበጅቡት ካድሬዎችማ የውሸት ሪፖርት ነው የሚያቀብሉት፡፡ እኛ ቀበሌ ካድሬዎች  ‹‹20ሺህ ሰው አደራጅተን ስራ ፈጠርን›› ብለው ሪፖርት አድርገው፣ እኛ ግን ስራ አጥተን እየተንከራተትን ቁንጫ ይበላን ነበር፤ እንደተመረቅን ማለቴ ነው፡፡ አሁንም ውይይቶች ተጀምረዋል፡፡ ግን በአብዛኛው ተመርጠው የሚገቡት ካድሬዎችና አሸርጋጆች ብቻ ናቸው፡፡ መንግስት ለአርቲስቱ ነፃነትም፣ ገንዘብም መስጠት አለበት፡፡ ስራው እንዲያድግ አርቲስቱም በራሱ እንዲተማመንና ከአድርባይነት እንዲወጣ ማለቴ ነው፡፡ የድሮ ንጉሶች ሎሌዎቻቸውን ተወት አድርገው፣ ‹‹እረኛ ምን አለ›› የሚሉት እውነተኛውና ትክክለኛው መረጃ ያለው እዚያ ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል፤ ከአርቲስቱም የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ አርቲስቱ ሁሌ ጭፍን ተቃዋሚ ሆኖ መንግስትን መቀጥቀጥ ወይም ጭፍን ደጋፊ ሆኖ፣ መንግስትን ማወደስ አይደለም ስራው፡፡ በተቻለው መጠን ነፃ ሆኖ፣ እውነት ላይ ተመስርቶ፣ መንግስት ሲያጠፋ መውቀስ፣ መልካም ሲሰራ ሙያውን ተጠቅሞ ለህዝብ ማሳወቅ አለበት:: ያኔ በመንግስትና በህዝብ መካከል፣ በአርቲስትና በህዝብ መካከል መተማመን ይፈጠራል፡፡ መንግስትም እውነተኛ ተከታይ ያገኛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኪነ ጥበብ ነፃነት፣ የአርቲስቱ ብቻ ሳይሆን የመንግስትም ህልውና ነው ብዬ አምናለሁና ይታሰብበት፡፡ ከዚህ በተረፈ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ አዲሱ አመት የሰላምና የፍቅር እንዲሆን እመኛለሁ፡፡ ለመላው አድናቂዎቼ ከመስከረም 5 ቀን ጀምሮ ባሉት ተከታታይ ሳምንታት በብሔራዊ፣ በሀገር ፍቅርና በአምባሳደር ቴአትር ቤቶች በአዲስ ስራ እንገናኝ እላለሁ፡፡

Read 1206 times