Saturday, 14 September 2019 11:19

የአድማስ ትውሰታ ለአዲሱ ዓመት ጭራ ብናበቅልስ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  [ምናባዊ መጣጥፍ ለአዲስ ዓመት ስጦታ]


              በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሌሊቱን ሁሉም ሰው ጭራ አብቅሎ ቢያድርስ? የፍየልን አይነት አጭር ሳይሆን እንደ ጦጣው በረጅሙ የሚወዛወዝ ጭራ፡፡ ፀጉር የሌለው እንደ ገላችን መላጣ የሆነ ዱልዱም ጭራ፡፡ ወንዱም ሴቱም ትንሹም ትልቁም በቃ ሁሉም ሰው ረጅሙን ጭራ ሌሊቱን አብቅሎ ቢያድርስ?
የእንቁጣጣሽ ዕለት ጧት ማነው ከቤቱ ደፍሮ መጀመሪያ የሚወጣው? እኔ አልወጣም፡፡ ጭራዬን ምን ውስጥ እደብቀዋለሁ? ሰው ሁሉ ጭራ አብቅሎ እንዳደረ አላውቅ፡፡ እንኳን ከቤቴ ልወጣ የመኝታ ቤቴን መስኮትና በርም አልከፍትም፡፡ ምናልባት ድንጋጤዬ ሲበርድልኝ፣ ጭራዬን ብርድ ልብስ ውስጥ ደብቄ ማሰብ እጀምር ይሆናል፡፡ አስቤስ ምን መፍትሔ አገኛለሁ፡፡ ጭራውን ለመንቀል ወይም ለመቁረጥ እሞክር ይሆናል፡፡
ቀኑን ሙሉ ደፍሮ ከቤቱ የሚወጣ ሰው ከተገኘ፣ በሰው ልጅ ታሪክ የደፋሮች ቁንጮ ሆኖ መመዝገቡ አይቀርም፡፡ ለበአሉ የተዘጋጀው ዝግጅት ሁሉስ ምን ያደርጋል? የእነ ዓመት በዓል ዶሮና በግ እድሜ ለመርዘሙ ጥርጥር አይኖርም፡፡ ሌላው ሌላው ነገርስ እንዴት ይሆናል? እኔ እንጃ ማሰቡም ከበደኝ፡፡
ለነገሩ ሁሉም ባለጭራ ከሆነ መቼስ ምን ይደረጋል፡፡ ለጊዜው እርስ በእርሱ እየተፋፈረ፣ ወንዱ በሱሪው ስር አጥፎ እያሾለከና ካልሲው ውስጥ እየሸጎጠ፣ ሴቱም እየጠቀለለ በቀሚሱ ስር ወታትፎ መውጣቱ አይቀርም፡፡ የሚበላውም ከቤት ያልቃል፡፡ ወሬውም ይዛመታል፡፡
አንዱ የአንዱን ጭራ ለማየት የሚኖረው ጉጉት ግን ይታያችሁ፡፡ እኔ የአንቺን፡፡ አንተ የኔን፡፡ አንቺ የእሷን፡፡ እሷ ያንቺን፡፡ አዲስ ነገር ነዋ! እንኳን ተአምሩን የሰው ጭራን የሚያህል ነገር ቀርቶ ጎረቤት የመጣ እንግዳን ፊት ለማየት ብዙ ሰው ታላቅ ጉጉት ያድርበታል፡፡
የዛን ሰሞን ፀገራቸውን ያስረዘሙት ባህታውያን ባለመስቀል ዘንጋቸውን እየነቀነቁ ‹‹ደንቁረህ የኖርክ ዘንድሮ እንኳን አይንህን ክፈት፡፡ ይኸው ስምንተኛው ሺ መጣ፡፡ ፈጣሪ ፍፁም ነው፡፡ የፈጣሪን ረቂቅነት ማንም ተመራምሮ አይደርስበትም፡፡›› ሲሉ፤ የብርጭቆ ቂጥ የመሰለ መነጽር የሰኩ መላጣ ሳይንቲስቶችም ‹‹የሰው ልጅ ከጦጣ ዝርያ መምጣቱ ተረጋገጠ፡፡ ተፈጥሮ ፍፁም ነች፡፡ የተፈጥሮን ረቂቅነት ማንም ተመራምሮ አይደርስበትም፡፡ የሰው ልጅ ጉዞ ወደ ኋላ ነው፡፡›› ማለታቸው አይቀርም፡፡
ሁሉም ያለውን ቢል ለጭራ ደንታም አይሰጠውም፡፡ አንዴ በቅሏላ! ጭራ ያምብርን ይሆን? መቼም ሁሉም  ሰው ላይ ያስጠላል ማለት አይቻልም፡፡ ጭራ የሚያምርበት ሰው አይጠፋም፡፡ ጭራውም እራሱ ልክ እንደ ጣት ወይም ደግሞ እንደ እግርና ባት፣ ቆንጆና ደዘደዝ ሆኖ ነው የሚበቅለው:: አለንጋ ጭራ፣ ቀጥ ያለ ሸንቃጣ  ጭራ፣ ጉንድሽ ወይም ወልጋዳ ጭራ… ወዘተ እየተባለ በውበቱ ሊወደስ፣ በማስቀየሙ ሊጥላላ የግድ ነው፡፡
ልብስ ሰፊ የተባለ ሁሉ በየሱሪውና ቀሚሱ ጀርባ እንደ እጅጌ ክብ ቀዳዳ እየሸነቆረ፣ ረጅም ቱቦ መሳይ ከረጢት ቀዶ መስፋት የተለመደ ተግባሩ ሆኖ ይዋሀደዋል፡፡ ፋሺን ነዳፊዎችም ጉድ ጉድ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ባለ አለንጋና ሸንቃጣ ጭራው እንደ ሚኒስከርትና ቁምጣ፣ ባለ ጉንድሽ ጉንድሹ ደግሞ እንደ ቦላሌ ያለ ልብስ፣ የጭራውን ወርድና ቁመት እያስመተረ፣ እንደ አቅሙ ገበናውን መሸፈን ሊኖርበት ነው፡፡ አንዴ ገላ ሆኖ ከበቀለ መቼስ ምን ይደረጋል፡፡
ቆይ ቆይ ግን ስንቀመጥ እንዴት እናደርገዋለን? በእግራችን መሀል ወደፊት አሾልከን እንይዘዋለን? ወይንስ በስተጀርባችን ሽቅብ ጭስ ማውጫ አስመስለን እናቆመዋለን? በስተጀርባ ወደ ወንበር ስር እንዳንዘረጋው፣ ሰው ሳያይ ሊረግጥብን ይችላል፡፡ የዛሬ ሰው እግሩን ሲሰነዝር እንኳን አዲስ የበቀለውን ጭራ ይቅርና ስንወለድ ጀምሮ ያለውን እግርም አያይ፡፡ በተለይ ሰው በሚበዛበት ስብሰባ፣ ትያትር ቤትና ወጪ ወራጁ አሁንም አሁንም በሆነበት ሚኒባስ ታክሲ ላይ ችግር ነው፡፡ በጀርባችን ሽቅብ እንዳናቆመው ይቆረቁራል፡፡ በዛ ላይ ደግሞ ከኋላ ‹‹ጭራህን ዝቅ አርገው… ከለልከን›› ልንባልም እንችላለን፡፡ ያው እንደወጣብን ጭራችንን በጎንም ይሁን በመሀል ሰብሰብ አርጎ መታቀፉ ነው የሚያዋጣን፡፡
ጭራ መቼስ ያው ጭራ ነውና መንከርፈፉ አይቀርም፡፡ ረስተን ለቀቅ ካደረግነው መሬት ላይ ተጎትቶ ምናምን ሊወጋብን ወይ የጠርሙስ ስባሪ ሊቆርጥብን ይችላል፡፡ ምድጃ ላይ ተኮፍሶ የሚደነፋ ሽሮ ውስጥ ጥልቅ ቢልብንስ? በዚህ ግርግር በበዛበት ከተማ ድንገት ስናወናጭፍ፣ የሰው አይንም ልናጠፋ እንችላለን፡፡ እስክንለምደውና እስክንነግረው ድረስ እንቅስቃሴውን መቆጣጠሩና እንደምንፈልገው ማዘዙ ፈተና መሆኑ አይቀርም፡፡
ታላቁ ጉድ ግን ውስጣዊ ስሜታችንና ማንነታችን እርቃኑን የመቅረቱ ጉዳይ ነው፡፡ የእነ ውሮና የእነ ቡቺ ጭራ የተለያየ ስሜት ሲሰማቸው፣ በየስልቱ እየተንቀሳቀሰ ስሜታቸውንና ፍላጎታቸውን ይገልጻል፡፡ የእኛም ጭራ እንደ እጅ እስኪገራ ድረስ በውስጣዊ ስሜታችንና ፍላጎታችን እየታዘዘ ከኛ ቁጥጥር ውጪ መንቀሳቀሱን አይተውም፡፡ ከእነ ውሮና ቡቺ እንደተማርነው ማለት ነው፡፡ እኛ ደግሞ ፈርዶብን በአብዛኛው እንደ ባህልም እንደ ልምድም ከግልጽነት ይልቅ ድብቅነትን መርህ አድርገን የተቀበልን፣ ከፊት ለፊት በር የጓሮውን የምንመርጥ፣ እንደ ሥነ ምግባር መስፈርት ጮክ ብለን የምናውጃቸውን እሴቶች፣ በሹክሹክታና በስውር የምንሽር ነን፡፡ ጭራችን ደግሞ ይሄንን ገና አላወቀ፡፡ አዲስ በቀል ነው፡፡ አልተገራም፡፡ ‹‹ነውር ነው››፣ ‹‹ያሳፍራል››፣ ‹‹ሚስጥር ነው››፣ ‹‹ይሉኝታ››፣ ‹‹የሆዴን በሆዴ›› … ወዘተ አያውቅም፡፡ ውስጣዊ ስሜታችንንና ፍላጎታችንን እየተከተለ፣ ያለ ሳንሱር ሽንጡን እየሰበቀና እየተወራጨ፣ እኛነታችንን በራሱ መንገድ ያውጃል፡፡ ወይ መከራ!
በየመንገዱ፣ በየቢሮው፣ በየጓዳው ጎድጓዳው በቆዳና ልብሳችን ስር ተሸፍነውና በሹክሹክታ ቅብብሎሽ ደብቀን ያኖርናቸውን ስንትና ስንት ጉዶቻችንን ጭራ እንደሚያጋልጥብን አስቡት እስቲ፡፡
በትንሿ የስራም ሆነ በታላላቅ የሀገር ጉዳዮች ላይ ለመምከር በተሰየሙ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ስንት የጭራ ትዕይንት ይታያል! አድር ባዩ የአለቃን ወይም የበላይን ንግግር በደመ ነፍስ እየሰማ፣ ጭራውን በረጅሙ ሲቆላ፣ አላዋቂውና ነገሩ የተምታታበት በግዴለሽነት ነፍዞ ጭራውን እንደደከመው ጅራፍ አንከርፍፎ አቧራ ሲያስስ፣ ነገሩ ያላማረውና በፍርሀት ዝምታ የተጎለተው ተሰብሳቢ፣ ጭራውን በእግሮቹ መሃል ሸጉጦ በማሳለፍ አፉን በጭራው ጫፍ ሲተመትም፣ አጀንዳው እሱን የሚመለከት ሆኖ በምን ይወሰንብኝ ይሆን ስጋት የተዋጠው ደግሞ ጭራውን በድንጋጤና በጭንቀት እንደ አፈ-ሙዝ ቀስሮ አቁሞ…ወዘተ፡፡ ጭራ ስንት ስንት ትርዒት ያሳየን ይሆን?
በየቢሮው የአገርና የሕዝብ ሀላፊነት ተሸክመን፣ እጀ እርጥቡንና አመዳም ደሀውን የምናስተናግድበትን ስልትም ጭራ አያውቅም፡፡ እጀ እርጥቡ ሲመጣ ጭራችን በራሱ ስልት እየተቆላ፣ አመዳም ደሀው ሲሆን ደግሞ እየተነቀነቀ ሊያሳጣን ነው፡፡ ወይ መከራ! ለነገሩ የጭራን ነገር አታድርስ ማለቱ ይሻላል እንጂ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ‹‹ልጄን ቀጥቼ ተንከባክቤና መክሬ ነው ያሳደግኳት›› እያለ በጠጅ ቤት ጓደኞቹ ፊት ክብር ሞገስን ተላብሶ የኖረ ጋቢ ለባሽ አባወራ፣ ልጅ የልቅሶ ድንኳን ውስጥ ከፊት ለፊቱ ለተቀመጡት ጎረምሶች አጎንብሳ የእራት ሳህን እያደለች ጭራዋን ስትቆላ፣ ድንገት የሱን ሳህን በጭራዋ ነክታ ከእነ እንጀራው መሬት ላይ ስትደፋበት ምን ይላል? ከቀበሌው ባሻገር ከሴት ጋር ጭራውን አቆላልፎ ሲንሸረሸር፣ በቁርባን ያገባት የልጆቹ እናት  ባጋጣሚ ከማህበር መልስ ከእነ ጓደኞቿ ከኋላው የደረሰችበት አባወራስ ምን ብሎ ሊያስተባብል ነው?  
ለመጀመሪያ ልጃቸው የወሲብን በተለይም ከትዳር ውጪ የመሄድን ታላቅ ሀጢያትነት እየሰበኩ ያሳደጉ ግን የጎረቤት ወንደላጤ በወጣ በገባ ቁጥር ጭራቸው የተሰጣ እህል የሚበትንባቸው አሮጊት እናትስ እንዴት ይሆናሉ? ጣጣ ነው፡፡ ጉቦ ሲቀረጥፍ የከረመው የቀበሌ ተመራጭም ሕዝቡን ስብሰባ ጠርቶ ንግግር ሲያደርግ፣ ጭራው በስጋት እየተሸጎጠ ሊያሳጣው ነው፡፡ ከፀሐፊው የተነካካ ሹመኛም እሷን ባየ ቁጥር ጭራው እየተቆላ ሊያሳፍረው ነው፡፡ ምላሱን በጨው አጥቦ ያልተሰራውን ስራ እንደተሰራ ሪፖርት ለበላይና ለሕዝብ የሚያቀርበው ባለ ስልጣንም ጭራው በይነቃብኝ  ይሆን ስጋት እየተሸጎጠ ያሳብቅበታል፡፡ ችግር ነው መቼስ፡፡ የጭራው መዘዝ እንደሆነ መለስ ብለን እራሳችንን እያየን፣ ቢያንስ ለራስ መታመንንና ግልጽነትን  አክብረን፣ የማስመሰል ክንብንባችንን ካላወለቅን… ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ከዚህ ከዚህ ሁሉ አዲስ አመት… አዲስ ራዕይ ይስጠን፡፡   
(አዲስ አድማስ፤ ጳጉሜ 3 ቀን 1993 ዓ.ም)

Read 1228 times