Tuesday, 17 September 2019 00:00

የ10ኛው ‹‹አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ›› ምርጥ አምስት እጩዎች ይፋ ተደረጉ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

‹‹አዲስ ሚዩዚክ አዋርድ›› ለዘንድሮ የ10ው ዙር ሽልማት ምርጥ አምስት ውስጥ የገቡ እጩዎችን ይፋ አደረገ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል ይፋ በሆነው በዚህ ዝርዝር መሰረት፤ በ “የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ አልበም” ዘርፍ፡- የጐሳዬ ተስፋዬ “ሲያምሽ ያመኛል”፣ የጃኪ ጐሲ “ባላምባራስ”፣ የዚጋዛጋ “ኮርማ”፣ የዮሐና “ዮሐና” እና የዳጊ ዳንኤል “ስሜቶቼ” ወደ ምርጥ አምስት እጬዎች ሲያልፉ፤ በ‹‹የዓመቱ ምርጥ ነጠላ ዜማ የአብርሃም በላይነህ “እቴ አባይ”፣ የኤፍሬም አማረ “አሰይ አሰዬ”፣ የራሄል ጌቱ “ጥሎብኝ”፣ የያሬድ ነጉ “አዲመራ” የኪራ ቢጋሮ “አያሌ ሞኙ” እና የአሊ ቢራና የሄለን በርሄ “ሲያዴ” ተመርጠዋል፡፡
በ“የአመቱ ምርጥ ቪዲዮ” ዘርፍ፤ የዮሴፍ ገብሬና ሚለን “ኮከበይ”፣ የያሬድ ነጉ “አዲመራ”፣ የአብሌክስና ሔዋን “ቀብራራዬ”፣ የአብርሃም በላይነህ “እኔ አባይ”፣ የኤፍሬም አማረ “አሰይ አሰዬ” እና የቶማስ ሀይሉ “ዘና ላርጋት” ወደ ምርጥ አምስት ሲገቡ፤ በ “የዓመቱ ምርጥ ድምፃዊ” ዘርፍ ልኡል ሀይሉ (እሳቱ ሰዓት)፣ ቸሊና (ቸሊና)፣ ጃኪ ጐሲ (ባላምባራስ)፣ ዮሃና (ዮሐና)፣ ዳጊ ዳንኤል (ስሜቶቼ) ተመርጠዋል፡፡ በ‹‹የአመቱ ምርጥ የሙዚቃ አቀናባሪ›› ምድብ፡- በ”እሳቱ ሰዓት” ኤልያስ መልካ፣ (“በጃሉድ በጎሳዬና በስሚዝ”) ሙዚቃዎች ካሙዙ ካሳ፣ በ “ስሜቶቼ” ታምሩ አማረ፣ በበርካታ ነጠላ ዜማዎች ጊልዶ ካሳ ታጭተዋል፡፡
በ‹‹የአመቱ ምርጥ ፊልም››፣ ‹‹ወደፊት፣ 3ኛው ዓይን፣ ቁራኛዬ፣ ወጣት በ97፣ ሲመት እና ተፈጣሪ›› ሲመረጡ፣ በ “የዓመቱ ምርጥ ተዋናይት” ዘርፍ፡- በ “ወጣት በ97” ዘሪቱ ከበደ፣ በ “ወደፊት” ዕድለወርቅ ጣሰው፣ በ “ቁራኛዬ” የምስራች ግርማ፣ በ“ባለ ቀሚስ” ሰላም ተስፋዬ፣ በ “ሲመት” መስከረም አበራ እና በ “ሞኙ ያራዳ ልጅ” ሄለን በድሉ ወደ ምርጥ አምስት ውስጥ በተፎካካሪነት ተካትተዋል፡፡ በ “የዓመቱ ምርጥ ተዋናይ” ዘርፍ፡- አማኑኤል ሀብታሙ በ “3ኛው አይን”፣ ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ) በ “ሞኙ ያራዳ ልጅ”፣ ሔኖክ ወንድሙ፣  በ “ሱማሌው ቫንዳም”፣ ዘሪሁን ሙላት በ “ቁራኛዬ”፣ አለምሰገድ ተስፋዬ “በአስታራቂ 2” እና ግሩም ኤርሚያስ በ “ተፈጣሪ” ወደ ምርጥ አምስት አልፈዋል፡፡
እጩዎቹ የፊታችን አርብ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በሚደረግ ደማቅ ስነ ሥርዓት አሸናፊዎቹ የሚሸለሙ ሲሆን እስከ መስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም ለእጩዎቹ ድምጽ መስጠት እንደሚቻል የሽልማቱ አዘጋጅ ይገረም ስንታየሁ (ዲጄ ቤቢ) አስታውቋል፡፡

Read 1819 times