Saturday, 21 September 2019 07:52

የመስከረም ግጥሞች ቀለም!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

በአዲስ ዓመት የችቦ ልኮሳው፣ የአደይ አበባው፣ የመስቀሉ ደመራ፣ የቢራቢሮው ውርውርታ ሁሉ ቀልብን ይስባል፡፡ ችቦው በራሱ “ብርሃን መጣ፣ የምስራች፣ ወንዞች ሞልተው የተለያዩ ወዳጅ ዘመድን ልናገናኝ ቀኑ ደረሰ”፤ የማለትም ምልክት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ተባብሮ የሚያሰማው አዋጅ ደስ ይላል። ሰማዩና ወንዙም በፈገግታ መሳሳቃቸው አይቀርም:: የደፈረሰ ጅረት፣ የጠገገ ሰማይ ይሰናበቱና ብሩህና ንጹህ ይሆናሉ፡፡  
ታዲያ ይህን ያስተዋሉ ከያንያን በተለይ ደግሞ ገጣሚያን ብዕራቸውን ስለው በቀለም ያፏጫሉ ወይም ይናጫሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ውበት ያደንቃሉ፡፡ ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ…ም ይባላል፡፡
የቀደሙት ገጣሚያን እነ ሎሬት ጸጋዬ፣ መንግስቱ ለማና ሌሎቹም ስለ አዲስ አመት፣ ስለ መስቀል ደመራ ብዙ ብለዋል። በተደጋጋሚም ለአዲስ አመት ማድመቂያ ተጠቅመንባቸዋል፡፡ ይሁንና ወጣት  ገጣሚያን ስለ አዲስ ዓመት፣ ስለ እንቁጣጣሽ ምን እንዳሉ፣ የስሜታቸው መጦዝና መርገብ ወደ የት ጎራ እንደሚያደርጋቸው አላየንም፡፡ የዛሬ ቅኝቴ  ከነዚህ ገጣሚያን የተወሰኑትን ይመለከታል፡፡
ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም ‹‹የማለዳ ድባብ›› በሚለው ስብስቡ፣ ስለ እንቁጣጣሽ የጻፈው ዘና የሚያደርግና የሚቆረቁር ነገር አለው፡፡ የጨበጠው ችቦ ወደፊት ሳይሆን ወደ ኋላ እያበራ፣ በልቡ ያቀጣጠለው ስሜት ያለ ይመስላል፡፡ ምናልባትም በኑሮ ሲዳክር እንቁጣጣሽን እንደ ዋዛ ዘንግቶታል:: ዝንጋዔው ግን በስልጣኔ መስመር ገብቶ “በአል አያስፈልግም›› በሚል ፍልስፍና ይሁን፣ በኑሮ ምጣድ ቅዝቃዜ አይታወቅም፡፡ አንባቢው ራሱ ይፈትሸው፡፡
‹‹አዲስ አመት ገባ›› ይላል ርዕሱ፡፡
አዲስ አመት ገባ
ያለ መስቀል ወፎች፣ ያለ አደይ አበባ
በግዜር ሰራሽ ማማ
ቁራ ብቻ ሰፍሯል
የመስቀል ወፍማ
ወይ አገር ለውጧል
ወይ ልብሱን ቀይሯል፤
በዕውቀቱ ከመስቀል ወፍ ይልቅ ቁራ ይታየኛል እያለ ነው፡፡ የመስቀል ወፍ  ወይ ባገሩ የለም፤ ወይ ልብስ ቀይሯል ሲል ምናልባት ተምሳሌታዊ አገላለጽ ይመስላል፡። አደይ አበባም በምድሩ የለም፤ ምክንያት ግን አልሰጠንም። ገጸ ሰቡ አይኑን ይጨፍን ወይም ምድር ውበቷን ትደብቅ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ግን አንድ ነገር እናደምጣለን፤ አንድ ነገር በልባችን ይቀራል፡፡ እንቁጣጣሽ እንቁጣጣሽ አይመስልም፣ ውበት የለም፣ ዝማሬው ነጥፏል፡። የቸከከ የለዘዘ ነው፡፡
በቀጣዩ አንጓ ደግሞ እንዲህ ይላል፡-
አዲስ አመት ገባ
በቄጠማ ምትክ፣ ብሎኬት ጎዝጉዞ
በ’ቅፍ አደይ ምትክ፣ ጉንጉን ሽቦ ይዞ
በሉባንጃ ምትክ፣ አቧራ እያጤሰ
በፈንዲሻ ምትክ፣ ጠጠር እያፈሰ
አዲስ አመት ገባ
አዲስ እንዲህ ዋዛ
ተፈጥሮ በውበት፣ መንፈሴን ሳይገዛ
በመዐዛው ሳይዋጅ
መስከረም መግባቱን በሬዲዮ ልስማው
እንደ መንግስት አዋጅ፡፡
በሁለተኛው አንጓ ያለው የስሜት መዛባት፣ የጣዕም መጥፋት፣ የማስታወሻ ዕጦትም እንቁጣጣሽን ከልቡ እንዳጠፋው ያሳያል፡፡ የሚዘምር ጅረት የለም፣ ለምለም ቄጠማ ጎንበስ ቀና አይልም፣ የሉባንጃ ሽታ የለም፣ ፈንዲሻ አልፈካም:: ይልቅስ ደረቅ ብሎኬት፣ በድን ሽቦ፣ የሚያስነጥስ አቧራ፣ የሚቆረቁር ጠጠር ከብቦታል፡፡ የተፈጥሮ መልክ የለም፤ አዲስ አመትን የሚያሳዩ ምልክቶች ጠፍተዋል፡፡ ደረቅ አፈር፣ ደረቅ ነገር ብቻ!  ገጣሚው እነዚህ ሁሉ ከሌሉ እንቁጣጣሽ የታለች ወደሚል ክህደት ገብቶ፣ በሬዲዮ እንደ መንግስት አዋጅ ሰማሁ በማለት በግነት ሀሳቡን ይቋጨዋል፡፡ እንግዲህ ያንዱ ገጣሚያችን እንቁጣጣሽ እንዲህ ተገልጣለች:: ይሁንና ግጥሙ በራሱ ያነፀረበት መንገድና ያየበት ጥልቀት ሸጋ የሚባል ነው፡፡
ሌላው የምቃኘው ግጥም የ “ሆሄ” ሽልማት የመጀመሪያው ዙር ተሸላሚ የነበረው ገጣሚ አበረ አያሌው የከተበውን ነው፡፡ ስለ አዲስ አመት ‹‹መልካም አዲስ ሀገር›› በሚል ርዕስ እንዲህ ይላል፡-
ይሄ ያ’ገሬ ሰው
ሁለት በሬ ኋላ እየተከተለ በረሃ የሚያርሰው
አደባባይ ቆሞ ተመስገን እያለ ጓዳ የሚያለቅሰው
ካሳለፈው መዓት ከሌሎችም አልፎ
      ራሱን ጠርጥሮ
ያገሩን አለቃ ሆድ እሞላ ብሎ ሺህ ፍዳውን ቆጥሮ
‹‹ቀን ያልፋል›› እያለ
የወጣውን ሁሉ ተግቶ እያዘለ
ኑሮው የሚስ’ለው…
እያለ የሌለው…
ይሄ ያገሬ ሰው
አምቡላውን እንጂ ጠጁን ያልቀመሰው
‹‹ሀገር አለህ›› ሲባል ሆዱን የሚብሰው
‹‹አዲስ አመት መጣ›› ያላችሁት ገርሞት
          እስኪያመው የሳቀ
(የማሽላ ነበር)
አዲስ ሀገር እንጂ አዲስ አመትማ ድሮስ መች ናፈቀ!
የአበረ ግጥም፣ የጊዜ መለዋወጥ፣ የነገን ሕይወት ብሩህ ተስፋ ካልጠነሰሰ፣ ምን ፋይዳ አለው የሚል አንድምታ አለው። በተለይ ደግሞ አገርን የተሸከመ ልብ፣ በልቅሶ ቤት ውስጥ ዳንኪራ አይሆንለትም:: በሙሾ መሀል በሳቅ አይንከተከትም፡፡ የገጣሚው ነፍስ በደሀው የአገሩ ገበሬ ሕይወት ላይ እንደ ሀረግ ተጠምጥማለች፡፡ አደባባይ ‹‹ተመስገን›› ማለቱ የጓዳውን ልቅሶ አላስቀረለትም፡፡ ዛሬም በበሬ ያርሳል፣ ዛሬም ጎተራው ተርቧል፡፡ ይልቅስ ሰርቶ ለአለቆቹ፣ ዘርቶ ለሌሎች ነው። ቀፎ ሰቅሎ ጠጅ አይጠጣም፣ አምቡላ ይደርሰዋል፡፡ በሀገሩ ላይ ነፃ አይደለም፡፡ ጫንቃው በጭቆና ቀንበር ሰልሏል፡፡ ‹‹ሀገር አለህ›› ሲባል ያስቀዋል። ምንም አዲስ ነገር በሌለበት አዲስ አመት ምን ያደርጋል? ባይሆን አዲስ ሀገር መጥታ የቤቱን ጥቀርሻ ብትጠርግ፣ የልቡን ስብራት ብትጠግን የመመኘት ድምፀት አለው፡፡
የአዲስ አመት ግጥሞች በኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌሎች የሰለጠኑ አገራትም ለዛ ያላቸውና  አዲስ ስሜትን የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ይሄኛው ግን አደይ አበባም፣ የመስቀል ወፍም አልታዩት፡፡ የጠራው ሰማይ፣ በአይኑ አልገባም፡፡ ምክንያቱም ትኩረቱ ከቤቱ አልወጣም፡፡ ከእልፍኙ አላለፈም:: የሚያንጎራጉር ልብ፣ ደረት የሚደቃ የቁጭት መንፈስ ታጥቋል፡፡
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለት ገጣሚያን ምናልባት ዘመኑን፣ የትውልዱን ጠባብ መንገድ መማሰን፣ የተስፋ መነጠቅና የቀጣዩን አድማስ ጨፍጋጋነት የሚያሳዩ ይመስላል፡፡ ወደ ኋላ ሄደን የሰዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታን ግጥም ስናይ ደግሞ ምናልባት በሰዓሊነቱ አይን፣ የመስከረምን ወር ቀለም ነክሮ፣ በደማቅ ምሰላ ያሳየናል፡፡ ‹‹አንተ ነህ መስከረም›› ይላል፡፡
ማለቂያ በሌለው ደማቅ ሰማያዊ፣
ከሩቅ ያለው ጋራ ተነክሮ ሀምራዊ
በዚያ ላይ ደመናው እንደ ጥጥ ተነድፎ
እየተራራቀ ሲያንጃብብ ተቃቅፎ
አንተ ነህ መስከረም
የሀምሌን ጨለማ የነሐሴን ዝናም
የሻርከው አንተ ነህ
በብርሃን መዛትህ
በክረምቱ ወራት ሰማዩን ያስጌጠው
የማርያም መቀነት በቀለም ያበደው፡፡
ጤዛው አርሶታል መሬቱ ላይ ለቆ
በቀይና ቢጫ መስኩ ተለቅልቆ
ወንዝና ጅረቱ ድንጋይና አፈሩ
አገሩ ውብ ሆኗል ሜዳ ሸንተረሩ፡፡
ገብረ ክርስቶስ ውበቱ ላይ ተመስጧል፡፡ እያንዳንዱ ስንኝ የሚጋልበው ወደ ቀለም ነው፡፡ ቀለም ደግሞ ውበት ነው፡፡ ወደ ጓዳ፣ ወደ ኑሮ፣ ወደ ሕይወት ውጥንቅጥ አልገባም። ልቡ ያለው በሰማዩ ላይ፣ በተራራው፣ በቀስተ-ደመናው ውስጥ ነው፡፡ ሜዳና ሸንተረሩ ፊቱ ላይ ተነጥፏል፡፡ ወንዙ፣ ጅረቱ፣ ድንጋዩ፣ አፈሩ -- ፡፡ ወደ ዝማሬው፣ ወደ ችቦው ሰፈርም አልሄደም፡፡ ስለ ውበት ብቻ ይቀኛል፡፡  
ሌላው ገጣሚ ደግሞ ተፈሪ አለሙ ነው፡፡ ተፈሪ አለሙ እንደ ሰዓሊው ስለ ቀለማቱ ውበት፣ ስለ አድማሱ የብርሃን ፍንጭት አላወጋም፡፡ ይልቅስ የአዲስ አመትን ዥንጉርጉር ልብ፣ ባተሌ ሀሳብ  ስንኝ ቋጥሯል፡፡
‹‹መስከረም በሆነ›› ነው ርዕሱ፡፡
ክረምት አልፎ በጋ መስከረም ሲጠባ
አሮጌ አመት ሄዶ አዲሱ ሲገባ
አደይ ተከናንባ እንቁጣጣሽ ስትደምቅ
ምድር በልምላሜ ፀሐይ በሳቅ ስትሞቅ
አዲስ አመት ሁሌም አዲስ ይታሰባል
ምኞት ይታቀዳል ተስፋ ይታለማል
ሁሉም በየቤቱ እንደ አዲስ ይነቃል
ሁሉም በየሞያው በአጭር ይታጠቃል፡፡
ሙሉ ግጥሙ የሚለው፤ አዲስ አመት ሲባል ሁሉም ይታትራል፣ ሁሉም ያቅዳል፣ ሁሉም ይታጠቃል፡፡ ስለዚህ ምነው አመቱን ሙሉ መስከረም በሆነና ከስንፍና ጥርስ ውስጥ ነቅሎ ባወጣን ማለቱ ነው፡፡ እንግዲህ መስከረምና እንቁጣጣሽ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተጋግዘው በሚስብ ውበት፣ በሚጥም ቃና፣ በአበቦች ታጅበው፣ በችቦ ተከብበው ስለሚመጡ፣ ብርሃን ብርሃን ይሸታሉ:: ከዚህም ባሻገር  ሰው ባሰመረው የጊዜ ድንበርም አዳዲስ ሕልሞች ተረግዘው በመጪው አመት ይወለዳሉ፡፡ “እግዚአብሄር መልካም ጽንስ፣ ብሩህ ሕይወት የምንገላገልበት ዘመን ያድርግልን” ብንል “ባዶ ምኞት” ይሆን? - በፍፁም!!
መልካም አዲስ ዓመት!!      

Read 3111 times