Saturday, 16 June 2012 11:48

“ፈጣሪ ያዳላል እንዴ?” - ያልተፈለገ ጥያቄ

Written by  አለሙ ከድር
Rate this item
(0 votes)

ከእግር ኳስ እስከ ኦሎምፒክ፤

ከ”ግራጁዌሽን እስከ “ምርጥ አርቲስት”

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ፤ እዚህም እዚያም ሃይማኖትን አለቦታው ማስገባት፤ አሁን አሁን የተለመደ ፈሊጥ ሆኗል። በእርግጥ የአንዳንዶቹ ሲታይ፤ በቀላሉ የማይሽር አመል ይመስላል። አንዳንዶቹ ግን፤ እንደ አዋቂነት ሳይቆጥሩት አይቀሩም። እንዲያው ስታስቡት፤ በትያትር ጥበብ አሪፍ አርቲስት ነህ ተብሎ በአድናቆት የተጨበጨበለትና ለሽልማት የቀረበ ባለሙያ፤ በምን ምክንያት መድረኩን የሃይማኖት መስበኪያ ያደርገዋል? እግርኳስና አትሌቲክስ ላይስ፤ የሃይማኖት ጉዳይ መነሳቱ አይገርምም? ብዙዎች አይገርማቸውም።

“ከፈጣሪ ጋር እናሸንፋለን”፤ “በፈጣሪ ሃይል አሸንፈናል”፤ “ለሽልማት እንድበቃ የረዳኝ ፈጣሪ ምስጋና ይድረሰው”... እየተባለ ያለ ቦታው የሚነገር ስብከት፤ ለብዙ ሰዎች ጨርሶ አይገርማቸውም። ወይ ለምደውታል፤ ወይ ነገር ያሳመሩ ይመስላቸዋል። ወይ ደግሞ እንደ ትክክለኛ ነገር ይቆጥሩታል። አርቲስቶች ለሽልማት ሲመረጡ፤ ከአፋቸው የሚወጣው የመጀመሪያ ቃል፤ የሃይማኖት ጉዳይ ሆኗል። በትምህርት ወይም በቢዝነስ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች በሚዲያ ሲጠየቁም፤ ሃይማኖትን ጎትተው ያመጣሉ። ብቻ አጋጣሚው ይገኝ እንጂ፤ ተወርውረው ሃይማኖት ላይ ቁጢጥ ነው።

በተለይ በተለይ፤ የስፖርት ውድድርና የትምህርት ውጤት የመሳሰሉ ነገሮች ላይ፤ ሃይማኖት ሲገባ ማየት ያሳዝናል። እንዲያው፤ የስፖርትም ሆነ የትምህርት ውድድሮች ትርጉም የሚኖራቸው፤ ብቃትንና ጥረትን ስለሚያሳዩ አይደለም እንዴ? ምን ዋጋ አለው! የማሸነፍና የመሸለም ጉዳይ፤ የብቃትና የጥረት ጉዳይ መሆኑ ብዙዎች ይረሱታል ይረሳል። እናም፤ የዚያ ወይም የዚህ ሃይማኖት ተከታይ የመሆንና ያለመሆን ጉዳይ ሆኖ ቁጭ ይላል።

ያለ ቦታው ሃይማኖትንና እምነትን እየጎተቱ ማስገባት፤ ለአንዳንድ ሰዎች ጠቃሚና ትልቅ ስራ ሊመስላቸው ይችላል። ነገር ግን፤ ትልቅ ስራ አይደለም። የብቃትንና የጥረትን ክብር የሚያዋርድ ስራ ነው። ጠቃሚም አይደለም። የተለያየ ሃይማኖት በሚከተሉ አማኞች መካከል አላስፈላጊ ቅሬታና ቅራኔ እንዲፈጠር የሚያደርግ ነውና።

አሳዛኙ ነገር፤ የአገሪቱ ድንግዝግዝ ፖለቲካ፤ ሃይማኖት አለቦታው እየጎላና እየገነነ እንዲሄድ ለሚመኙ ሰዎች አመቺ ሆኗል። ያው እንደምታዩት፤ የፖለቲካና የነፃነት፤ የአገርና የመብት፣ የኢኮኖሚና የኑሮ ጉዳዮች ላይ መወያየትና መከራከር ቀስ በቀስ እየጠፋ ነው። በውይይት ምትክ ዝምታ፤ በክርክር ፋንታ ቁዘማ እየነገሰ መጥቷል። ታዲያ ይኸኔ፤ የትም ቦታ (ያለቦታው) ሃይማኖት ለመስበክ አይመችም?

በእርግጥ፤ የፖለቲካ ውይይትና ክርክር ሲጠፋ፤ በሁለት አቅጣጫ ተቃራኒ ጩኸቶች መሰማታቸው አይካድም - በመንግስት በኩል “ፕሮፓጋንዳ” የሚባለው የፖለቲካ ስብከት፤ በሌላው በኩል ደግሞ ባህር ማዶ ተሻግሮ የሚተኮስ ውግዘት። በመሃል፤ የፍርሃትና የአቅመቢስነት መንፈስ የተጫጫነው አብዛኛው ዜጋ በዝምታና በቁዘማ ተውጦ ይደነዝዛል። ያኔ፤ የሃይማኖት ድምፆች እየከረሩና እየገነኑ ይመጣሉ። ይህንን ለማረጋገጥ ከፈለጋችሁ፤ ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በአገራችን እየጎሉ የመጡ ለውጦችን ተመልከቱ።

አላስፈላጊና የትም የማያደርሱ የሃይማኖት ክርክሮች ሲበራከቱ አልታዘባችሁም? ሃይማኖት የእምነት ጉዳይ እንጂ የሳይንስ ጉዳይ እስካልሆነ ድረስ፤ የሃይማኖት ክርክሮች እልባት የላቸውም። የሃይማኖት ክርክሮች፤ ከንቱ ልፋት የሚሆኑትም በዚህ ምክንያት ነው። ይህም ባልከፋ ነበር። ክርክሮቹ፤ አላስፈላጊ  “የእምነት” ፉክክርንና አክራሪነትን ያስፋፋሉ። በዚያ ላይ በሃይማኖት ሰበብ እየተቧደኑ ግጭት መፍጠር በዝቷል።

ባለፉት አመታት በአገራችን የታዩት ለውጦች እነዚህ ብቻ አይደሉም። ያለቦታው የሚደረጉ የሃይማኖት ስብከቶች ተስፋፍተዋል - ከእግር ኳስ እስከ አትሌቲክስ፤ ከቴያትር ፌስቲቫል እስከ ተማሪዎች ምረቃ። ከውድድርና ከሽልማት፤ ከውጤትና ከስኬት ጋር ተያይዞ፤ ወደ መድረክ የሚወጡ እንዲሁም በሚዲያ የሚቀርቡ ሰዎች እንዴት እንደሚናገሩ ሳትሰሙ አትቀሩም። አብዛኞቹ፤ ጥሩ የስብከት አጋጣሚ ያገኙ ሆኖ ይሰማቸዋል።

ለሚከተሉት ሃይማኖት ምስክርነት ስጡ ተብለው የተጠየቁ ይመስል፤ ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት፤ ሱፊ ወይም ዋሃቢያ መሆናቸውን በሚያውጅ መንገድ ይናገራሉ። ለዚህ ያደረሰኝ እግዚአብሄር ይመስገን፤ አላህ ይክበር፤ በወላዲተ አምላክ እርዳታ፤ በጌታ ኢየሱስ ሃይል እናሸንፋለን የሚሉ ንግግሮችን ትሰማላችሁ።

ለነገሩ በደፈናው፤ ያንን ወይም ይሄንን ሃይማኖት በማይገልፅ መንገድ፤ “ከፈጣሪ ጋር እናሸንፋለን፤ በፈጣሪ ሃይል አሸነፍን” ብሎ አለቦታው ሃይማኖትን መስበክና ለሃይማኖት ምስክርነት መስጠትም ተገቢ አይደለም። ለምን? ትርጉሙን እንየዋ። ሶስት ትርጉሞች አሉት።

አንደኛ፤ ፈጣሪ አለምክንያት አድልዎ ይፈፅማል የሚል መልእክት ያስተላልፋል።

ሁለተኛ፤ ሰው በተፈጥሮው አቅመቢስ ሚስኪን ነው የሚል መልእክት ይዟል።

ሶስተኛ፤ ትምህርትን፣ ንግድን፣ ምርትን፤ ኪነጥበብን፣ ስፖርትን ... የመሳሰሉ ነገሮች የአንድ ሃይማኖት ብቻ እንደሆኑ ያስመስላል።

ፈጣሪ ያዳላል?

የእግር ኳስ ወይም የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ በርካታ ስፖርተኞች ሲያማትቡና ጣታቸውን ወደ ሰማይ ሲቀስሩ ማየት የተለመደ ነው። በንግግር “ፈጣሪ”ን ሲጣሩ እንሰማለን። ድል ለማድረግ ፈጣሪ እንዲያግዛቸው ይለምናሉ። በፈጣሪ ሃይል ድል አደረግን ብለው ምስጋና ያቀርባሉ። መብታቸው ነው። ግን፤ ፈጣሪ ያዳላል ማለታቸው አይደለምን?

በእርግጥ፤ ስፖርተኞቹ፤ የሳይንስ ወይም የፍልስፍና አዋቂ እንዲሆኑ መጠበቅ ትክክል ላይሆን ይችላል። ሙያቸው ሌላ ነው። ነገር ግን፤ ከፈጣሪ ጋር አሸንፋለሁ ብሎ መናገር፤ ከዚያም ፈጣሪ ለድል አብቅቶኛል ብሎ መፎከር ትርጉሙ ምን እንደሆነ ለማወቅ ያን ያህል አይከብድም። ከፈጣሪ ጋር አሸንፋለሁ ሲል፤ “ሌሎቹ አትሌቶች ግን ፈጣሪ አይጠጋቸውም” ማለቱ አይሆንም? በፈጣሪ ሃይል ሻምፒዮን ሆኛለሁ ብላ ስትናገር፤ “ሌሎቹ ስፖርተኞች የፈጣሪ ሃይል ተነፍጓቸዋል” ማለቷ አይደለም?

ሃይማኖታቸው፤ “ፈጣሪ ያዳላል” ብሎ የሚያስተምር መሆን አለመሆኑን አላውቅም። ወይስ፤ ፈጣሪ የሚጠጋቸውና ሃይል የሚሰጣቸው ሰዎች፤ ከሌሎች ሁሉ የተለዩ ምርጥ ሰዎች ይሆኑ? ወይስ፤ ፈጣሪ የስፖርተኞችን ሃይማኖት እያየና እየመረጠ ያግዛል?

ለመሆኑ ነገርዬው፤ የእግርኳስና የሩጫ ብቃት ውድድር ነው? ወይስ፤ የሃይማኖትና የእምነት ውድድር? የኦሎምፒክ ውድድርን አስቡት። ፈጣሪ ለየትኛው ሃይማኖት ወይም ለየትኛው አትሌት እንደሚያግዝ ለማወቅ ታስቦ የሚደረግ ፉክክር ነው ኦሎምፒክ?

የአትሌቶችስ እሺ ይቅር። ግን፤ አርቲስቶቹስ ለምን? በቅርቡ በተካሄደ የትያትር ፌስቲቫል ላይ፤ በአገሪቱ የትያትር መድረክ የሚታወቁና “አሉ” የሚባሉ አስር አርቲስቶች ተሸልመዋል። ታዲያ፤ መድረክ ላይ ሲወጡ ምን ምን ተናገሩ? ብቃቴንና ጥረቴን አይታችሁ ለሽልማት ስለመረጣችሁኝ አመሰግናለሁ ብለው የተናገሩ አርቲስቶች ይኖሩ ይሆን? አንድም የለም።

“ለዚህ ላበቃኝ ፈጣሪ...” በሚል መግቢያ ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ የሰጡ አርቲስቶችስ ስንቶቹ ይሆኑ? ከአስሩ ተሸላሚዎች መካከል፤ አስሩም በቅድሚያ ፈጣሪን አመስግነዋል። ማመስገን ብቻ ሳይሆን፤ የትኛውን የሃይማኖት ዘውግ እንደሚከተሉ በሚገልፅ መንገድ ነው በርካታዎቹ ተሸላሚዎች የተናገሩት። “እዚህ ላደረሰኝ፤ እዚህ ላቆመኝ፤ ለዚህ ላበቃኝ፤ ለዚህ ለረዳኝ፤ ሞገስና ክብር ለሰጠኝ፤ ... ፈጣሪ ምስጋና ይገባዋል፤ ፈጣሪ ይክበር ብለዋል አርቲስቶቹ።

አዎ፤ አርቲስቶቹ እንደማንኛውም ሰው፤ የመረጡትን ወይም ከወላጅ “የወረሱትን” ሃይማኖት መከተል መብታቸው ነው። ስለሃይማኖታቸው መናገርም ንክች ሊደረግ የማይግገባ መብታቸው ነው። ግን፤ ፈጣሪ ለሽልማት አበቃኝ ብለው ሲናገሩ፤ ፈጣሪ ያዳላል ማለታቸው አይደለምን? ተሸላሚ ለመሆን የቻሉት በጥረታቸውና በብቃታቸው ከሆነ፤ አድልዎ አይኖርም። ሁሉም የስራውን ያገኛል። በፈጣሪ እርዳታ ከሆነ ግን፤ ተሸላሚ ለመሆን ያልበቁት አርቲስቶችስ ምን አጥፍተው እርዳታ ተነፈጋቸው?

በሚቀጥሉት ወራት፤ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከኮሌጆች ወደ መቶ ሺ የሚጠጉ ተማሪዎች ሲመረቁም፤ ተመሳሳይ የፈጣሪ ምስጋና በብዛት መስማታችን አያጠራጥርም። የምረቃ መፅሄቶችንም ማየት ትችላላችሁ። አንዳንዶቹ፤ የተመራቂዎችን ሃይማኖት በሚያውጁ ጥቅሶችና አባባሎች የተሞሉ ናቸው። በከፍተኛ ውጤት ተሸላሚ የሚሆኑ ተመራቂዎችም በአብዛኛው፤ “በፈጣሪ እርዳታ...” ብለው ይናገራሉ። ሌሎቹ ተመራቂዎች የፈጣሪ እርዳታ አልደረሳቸውም ማለት ነው? ወይስ በቂ እርዳታ አላገኙም?

የሚስኪንነት አምልኮ

አለቦታው ሃይማኖትን የማስገባት ፈሊጥ ተገቢ እንዳልሆነ ግልፅ የሆነ ይመስለኛል - ተናጋሪዎቹ፤ “ፈጣሪ ያዳላል” ለማለት ካልፈለጉ በቀር። ይህም ብቻ አይደለም። ሃይማኖትን አለቦታው የማስገባት ፈሊጥ፤ የኋላቀርነት ዋነኛ ምልክት ነው። ብቃትንና ጥረትን ከሚያዋርድ፤ ሰውን እንደ አቅመቢስ ሚስኪን ከሚቆጥር አስተሳሰብ ጋር የተያያዘ ፈሊጥ ነውና።

“ከፈጣሪ ጋር አሸንፋለሁ፤ በፈጣሪ እርዳታ አሸነፍኩ” ብሎ መናገር፤ “ፈጣሪ ያዳላል” የሚል ትርጉም ብቻ ሳይሆን፤ “ሰው በጥረቱና በብቃቱ ስኬቶችን የመጎናፀፍ አቅም የለውም” የሚል ትርጉምም አለው። “ሰው አቅመቢስ ሚስኪን ነው” የሚለውን እምነት እንደ ቅዱስ አስተሳሰብ መቁጠር ደግሞ ኋላቀርነት ነው።

እዚህ ላይ ሊነሱ ከሚችሉ መከራከሪያዎች መካከል አንዱን ብቻ ላንሳ። “ከፈጣሪ ጋር ይሳካልኛል፤ በፈጣሪ እርዳታ ለሽልማት በቃሁ” የሚል ንግግርኮ፤ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉት አገራት ብቻ ሳይሆን በሰለጠኑት አገራትም በተለይ በአሜሪካ የተለመደ ነው የሚሉ አሉ። ታዲያ እንዴት የኋላቀርነት ምልክት ሊሆን ይችላል?

ሃይማኖትን አለቦታው እዚህም እዚያም ማስገባት፤ እንደኢትዮጵያ በመሳሰሉ ኋላቀር አገራት እንጂ፤ በስልጣኔ ደህና በተራመዱ አገራት (በአሜሪካና በምእራብ አውሮፓ) ብዙም በስፋት የሚታይ ፈሊጥ አይደለም። እንዲያም ሆኖ፤ ከምእራብ አውሮፓ አገራት በተለየ ሁኔታ አሜሪካ ውስጥ የሃይማኖት ጉዳይ ጎላ ብሎ መታየቱ አይካድም። እውነት ነው። PEW Research Center ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ባለ 168 ገፅ ሪፖርት ይህን እውነት ያሳያል። ተቋሙ፤ “Trends in American Values: 1987-2012” በሚል ርእስ ያወጣው የጥናት ሪፖርት፤ የሃይማኖት ጉዳይ በአሜሪካ አሁንም ጠንካራ እንደሆነ ይገልፃል። ቢሆንም ግን፤ ሃይማኖትን አለቦታውና በየቦታው የማስገባት ፈሊጥ፤ በኋላቀር ድሃ አገራት ውስጥ በስፋት የሚታይ መሆኑ የሚያከራክር አይደለም። አሜሪካ ውስጥ የሃይማኖት ጎላ ብሎ ይታያል ቢባልም እንኳ፤ በድሃ አገራት እንደሚታየው ህይወትንና ኑሮን የሚያውክ አይነት አይደለም። ለምሳሌ፤ በአሜሪካ፤ የሃይማኖት አጥባቂ በሚባሉትና ሃይማኖትን ቸል በሚሉ ሰዎች መካከል ያለው የአስተሳሰብ ልዩነት በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ጥናቱ ይገልፃል።

በዚያ ላይ፤ ከአሜሪካውያን መካከል፤ “የፈጣሪን መኖር አልጠራጠርም” የሚሉ ሰዎች፤ ቁጥራቸው ባለፉት አመታት ከ88% ወደ 80% መቀነሱን ሪፖርቱ ያስረዳል (ገፅ 67)። ይህም ብቻ አይደለም። በተለይ በወጣቶች ዘንድ፤ የሃይማኖት ጉዳይ ለዘብ ያለ ሆኗል። ከአስር አመት በፊት ከነበሩት ወጣቶች መካከል የፈጣሪን መኖር የማይጠራጠሩት 80 በመቶ ያህሉ እንደነበሩ ጥናቱ ጠቁሞ፤ ከዛሬው ዘመን ወጣቶች ግን 68 በመቶ ያህሉ በፈጣሪ መኖር እንደማይጠራጠሩ ገልጿል (ገፅ 68)።

እንዲያም ሆኖ፤ ከሌሎች የበለፀጉ አገራት ጋር ሲነፃፀር፤ አሜሪካ ሃይማኖት ጎልቶ የሚታይባት አገር ነች። በአሜሪካና በምእራብ አውሮፓ አገራት መካከል ያለውን ልዩነት በተመለከተ “The American - Western European Values Gap” በሚል ርእስ ባለፈው ህዳር ወር የወጣ የPEW ጥናት ይህንን ያሳያል። ሃምሳ በመቶዎቹ አሜሪካውያን፤ ሃይማኖት በኑሯቸው ውስጥ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ (ገፅ 8)። በአውሮፓ ግን፤ ሃያ በመቶዎቹ ያህል ናቸው፤ ሃይማኖት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚናገሩት። በተለይ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ደግሞ፤ የበለጠ ዝቅ ይላል (13 እና 15 በመቶ)።በስነምግባር የታነፀ ሰው ለመሆን የግድ ሃይማኖት ያስፈልጋል? በሚለው ጥያቄም አሜሪካና ምእራብ አውሮፓ አገራት ይራራቃሉ።  ከአሜሪካውያን መካከል፤ ግማሽ ያህሉ “አዎ ያስፈልጋል” ብለው ያምናሉ። በእንግሊዝና በፈረንሳይ ግን፤ በስነምግባር ለመታነፅ ሃይማኖት የግድ ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት ከ20 በመቶ አይበልጡም (ገፅ 9)። በጥቅሉ፤ ከምእራብ አውሮፓ ይልቅ አሜሪካ ውስጥ ሃይማኖት ጉልህ ቦታ ይዟል። ነገር ግን፤ ብዙዎቹ አሜሪካዊያን፤ “ሃይማኖት በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉ፤ በኋላቀር አገራት ውስጥ ከምናየው መንፈስ ጋር ይለያያል።

አንደኛ ነገር፤ በኋላቀር አገራት በተለይም በአፍሪካ፤ ሃይማኖት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምኑ ሰዎች ቁጥር፤ ከጠቅላላው ህዝብ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ናቸው። በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ደግሞ፤ ቁጥሩ ከ90 በመቶ በላይ ይሆናል። ልዩነቱ ግን ይህ ብቻ አይደለም።

የብዙ አሜሪካዊያን ሃይማኖት በስልጣኔ የተገራ ነው - “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ህይወትና ኑሮ መምራት ይችላል” በሚለው የስልጣኔ አስተሳሰብ። እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ግን፤ እያንዳንዱ ሰው በራሱ ብቃትና ጥረት ህይወቱን መምራትና ማሻሻል ይችላል የሚል እምነት ብዙም የለም። የሰዎች ህይወት በመለኮታዊ ሃይል ወይም በ”እድል” የሚጓዝ መስሎ ይታያቸዋል። ከሁሉም አገራት በተሻለ ሁኔታ፤ በአሜሪካ አብዛኛው ሰው “ህይወቴ በእጄ ውስጥ ናት” ብሎ ያምናል።

ምን ለማለት ፈልጌ ነው? አሜሪካ ውስጥ ሃይማኖት ጎላ ብሎ ቢታይም፤ ያልተገራ ሃይማኖት አይደለም። “ህይወቴ በእጄ ውስጥ ናት” በሚል አስተሳሰብ ተገርቷል። እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ኋላቀር አገራት ውስጥ ግን፤ እጅጉን ጎልቶ የሚታየው የከረረ ሃይማኖት፤ “ህይወቴ ከኔ ቁጥጥር ውጭ ነች” በሚል ኋላቀር አስተሳሰብ የታጀበ ነው። “ከፈጣሪ ጋር አሸንፋለሁ፤ በፈጣሪ እርዳታ አሸነፍኩ” የሚሉ ንግግሮችም፤ ይህንን ኋላቀር አስተሳሰብ የተላበሱ በመሆናቸው፤ በአሜሪካ ከምንሰማቸው ተመሳሳይ ንግግሮች ጋር በመንፈስ ይለያያሉ።

============================================

 

1. “እድል” ይታደላል፤ ፈጣሪ ያዳላል

ማሸነፍና መሸለም፤ ማትረፍና መበልፀግ... በብቃትና በጥረት የሚገኙ መሆን የለባቸውም? ብዙ ሰዎች ግን ፈጣሪን ይለማመናሉ። ፈጣሪ ለነሱ አዳልቶ እያፈሰ እንዲሰጣቸው ነው?

የ”ድል”፣ የ”ሜዳሊያ”፣ የ”ሃብት” ባለቤት የሆኑ ብዙ ሰዎች፤ አርአያነታቸውን በብቃትና በጥረት ከማሳየት ይልቅ፤ ፈጣሪን ያመሰግናሉ -  ፈጣሪ መርጧቸዋል እንድንል ነው?

2. ሚስኪንነትን ማምለክ፤ ስኬትን መመቅኘት

“ለማሸነፍም ሆነ ለመበልፀግ... ሰው ምን አቅም አለው?” የሚል የሚስኪንነት አምልኮ በዝቷል። “እኔማ በምን አቅሜ? አንድዬ ይድረስልኝ እንጂ፤ አንድዬ ደረሰልኝ እንጂ”

በጥረቴ ተሳካልኝ፤ በብቃቴ ተሸለምኩ፤ በታታሪነቴ በለፀግኩ የሚሉ ሰዎች ይወደዳሉ እንዴ? ጉረኛ ትእቢተኛ ተብለው ይወገዛሉ - “እንደናንተው ሚስኪን ነኝ” እስኪሉ ድረስ።

3. ብቃቴን አይደለም ሃይማኖቴን አወድሱ

በአድናቂዎች ደማቅ አቀባበል የተደረገለት አትሌት፤ በተመልካቾች ምርጫ የተሸለመ አርቲስት፤ በስኬቱ ዝነኛ የሆነ ባለሃብት ወይም ምሁር ... መድረክ ሲያገኝ ሰባኪ ይሆናል።

ብቃቱን አይተው የሚያሞግሱት አድናቂዎቹኮ፤ በሃይማኖት እንደሚለያዩ ያውቃል። ግን “የስኬቴ ሚስጥር፤ ሃይማኖቴ ነው” ይላቸዋል - ብቃቱን ሳይሆን ሃይማኖቱን እንዲያሞግሱ።

 

 

Read 3254 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 12:00