Print this page
Saturday, 21 September 2019 12:49

ኢዜማ ከ70 በላይ በሚሆኑ የአለም ሀገራት የደጋፊ ማህበር እያደራጀ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ኢዜማ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባቸው ከ70 በላይ የአለም ሀገራት የአለማቀፍ የድጋፍ ማህበር እያደራጀ መሆኑን ትናንት በሰጠው መግለጫ አስታወቀ፡፡
ከተመሠረተ 5 ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜጐች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በሀገር ውስጥ በ400  የምርጫ ወረዳዎች አባላትንና ደጋፊዎችን አደራጅቶ ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጁ ማድረጉን በዚሁ መግለጫው ያስታወቀ ሲሆን፤ የአለማቀፍ ድጋፍ ማህበሩንም የሚያደራጀው በሀገር ቤት የተጠቀመውን የማደራጃ ስልት ተጠቅሞ መሆኑን አስገንዝቧል::  ኢትዮጵያውያን ይኖሩባቸዋል ተብለው በተለዩ ከ70 በላይ ሀገራት በየከተሞቹ የደጋፊ ማህበር ም/ቤት የሚቋቋም ሲሆን፤ የእነዚያ ም/ቤቶች አባላት የሆኑ ግለሰቦች አመራርነት ተመርጠው የክፍለ አለም ደጋፊ ማስተባበሪያ የሚኖረው አደረጃጀት ነው ተብሏል፡፡
ይህን አደረጃጀት ለመፍጠርም በየከተሞቹ የሚገኙ ደጋፊዎች መሠረታዊ ማህበራትን እንዲመሠርቱ ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ እንደሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ይመለከታቸዋል” ሲል ፓርቲው በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ባዘጋጀው ፖሊሲው ላይ ያስቀመጠ ሲሆን፤ እስካሁንም በሀገሪቱ እየታየ ላለው የለውጥ ተስፋ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግዙፍ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ብዬ አምናለሁ ብሏል፡፡
በቀጣይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ የማይተካ ሚና እንደሚጫወቱ ፓርቲው በመግለጫው አመልክቷል፡፡  


Read 9093 times