Saturday, 21 September 2019 12:51

በ2 ዓመት ውስጥ 3 መቶ ሺህ ኢትዮጵያውያን ከሣውዲ ተባረዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

 - በአማካይ በየወሩ 9453 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል
      - ከተመላሾቹ 84500 ያህሉ ከአማራ ክልል የተጓዙ ስደተኞች ናቸው

            ባለፉት ሁለት አመታት 3 መቶ ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ህገወጥ ናችሁ በሚል ከሣኡዲ አረቢያ ወደ ኢትዮጵያ በሃይል መባረራቸውን አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (IOM) አስታውቋል፡፡
በሚያዚያ 2009 የሣኡዲ መንግስት ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሀገሩ የሚኖሩ ህገወጥ ያላቸውን የተለያዩ ሀገራት ዜጐች በ90 ቀን ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ማስቀመጡንና በኋላም ቀነ ገደቡን ማራዘሙን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ በዚህ ግፊት ወደ ሀገር ቤት ለመመለስ ከተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን 90 በመቶ (3መቶ ሺህ) ያህሉ መመለሳቸውን አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ ከግንቦት 2017 እስከ ነሐሴ 2019 ድረስ በየወሩ በአማካይ 9,453 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ውስጥ እንደተመለሱ ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ከተመላሾቹ ውስጥ 78 በመቶ የሚሆኑት ወንዶች፣ 22 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ከተመለሱት 89ሺህ 222 ያህሉ ወንዶች እንዲሁም 8ሺህ 861 ያህሉ ሴቶች ኢትዮጵያውያን ሣውዲ ያለምንም ስራ የተቀመጡ እንደነበር ያስገነዘበው ሪፖርቱ 22ሺህ 306 ያህሉ ደግሞ እድሜያቸው ከ18 አመት በታች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብሏል - ሪፖርቱ፡፡
ከተመለሱት መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የአማራ ክልል ተወላጆች ሲሆኑ 84 ሺህ 495፣ ከኦሮሚያ ክልል 81ሺህ 784 እንዲሁም ከትግራይ 77ሺህ 779 መሆናቸውን ቀሪዎቹም ከደቡብ፣ አዲስ አበባ፣ አፋር፣ ድሬደዋ፣ ሶማሌ፣ ሀረሪ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልል መሆናቸውን ሪፖርቱ በዝርዝር አትቷል፡፡
ከሳውዲ ከተመለሱት 71 በመቶ የሚሆኑት በአገሪቱ ከ6 ወር እስከ 2 አመት የቆዩ ሲሆን፣ 13 በመቶ የሚሆኑት ከ2 እስከ 5 አመት፣ ከ5 እስከ 10 አመት የቆዩት ደግሞ 6 በመቶ ሲሆኑ እስከ 6 ወር ብቻ በሳውዲ የቆዩት 1 በመቶ ናቸው ብሏል ሪፖርቱ::
ከተመላሾቹ መካከል 2ሺ 77 ያህሉ ወደ ሳውዲ ተመልሰው የመሄድ እቅድ እንዳላቸው፣ 113ሺህ 316 ያህሉ የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ለመወሰን ግራ እንደተጋቡ እንዲሁም 149ሺሕ 299 ያህሉ ደግሞ ወደ ሳውዲ መመለስ እንደማይፈልጉ በጥናት መለየቱን አይኦኤም አስገንዝቧል፡፡
ከተመላሾቹ 69 በመቶ የሚሆኑት ወንዶችና 62 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች የትምህርት ደረጃቸው የመጀመሪያ ደረጃ (1-8ኛ ክፍል) መሆኑን፣ 24 በመቶ ወንዶች እና 24 በመቶ ሴቶች ደግሞ የ1ኛ ደረጃ ትምህርትም ያልተማሩ መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ 7 በመቶ ወንዶችና 14 በመቶ ሴቶች ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተከታተሉ ናቸው ብሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲ የገቡ ከ1 በመቶ በታች ናቸው ብሏል - ሪፖርቱ፡፡

Read 9238 times