Saturday, 21 September 2019 12:53

በ2 ወራት ውስጥ 276 ግጭቶች ተከስተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(12 votes)


               የሀገሪቱ የደቡብ ምዕራብ ክፍል፡-  ወለጋ፣ ምዕራብ ጉጂና ጋምቤላ አካባቢዎች ክረምቱን በግጭትና አለመረጋጋት ማሳለፋቸውን ተከትሎ፣ የረድኤት ተቋማት የሰብአዊ ድጋፍ ማከናወን ተስኗቸው እንደከረሙ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ አስታውቋል፡፡ በመላ ሀገሪቱ በ2 ወራት ውስጥ 276 ግጭቶች የተመዘገቡ ሲሆን፤ በምዕራብ ወለጋ በአንድ ሳምንት ብቻ አራት ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውንና ገዳዮቹም አለመያዛቸው ታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው ወቅታዊ ሪፖርቱ፤ በሰኔና ሐምሌ ወር ብቻ 197 ያህል ግጭቶች በመከላከያ ሠራዊትና ማንነታቸው በውል ባልታወቁ ታጣቂ ቡድኖች መካከል መከሰታቸውን ጠቁሟል፡፡
በአካባቢው ከተፈጠሩ 197 የግጭት ክስተቶች 110 ያህሉ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ በወለጋና ምዕራብ ጉጂ ሲሆኑ ቀሪዎቹ በጋምቤላ አካባቢ መከሰታቸውን ተቋሙ አስታውቋል::
በሰኔ ወር በወለጋ የተፈጠሩ ግጭቶች ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውንና የአካባቢውን ማህበራዊ ህይወት መረበሻቸውን የገለፀው ሪፖርቱ፤ ጥቂቶቹም ለሠላማዊ ዜጐች መገደል ምክንያት ነበሩ ብሏል፡፡ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ግን ሪፖርቱ ያለው ነገር የለም፡፡
በሐምሌ ወር ደግሞ ግጭቱ በስፋት ወደ ደቡብ ኦሮሚያ በተለይ ከሱማሌ ክልል ጋር አዋሳኝ በሆኑ አካባቢዎችና በጋምቤላ ማየሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም 36 ግጭቶች መከሰታቸውን አመልክቶ፤ ከእነዚህም መካከል 19 ያህሉ በጋምቤላ መከሰታቸውን አትቷል፡፡
በአጠቃላይ በመላ ኢትዮጵያ በክረምቱ ወራት (ከሰኔ እስከ ሐምሌ) ድረስ 276 የግጭት  መፈጠራቸውን ያስገነዘበው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ከእነዚህ መካከልም በአማራ ክልል ባለስልጣናት ላይ የተፈፀመው ግድያ፣ ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ ግጭቶችን በዋነኝነት ጠቅሷል፡፡
በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በወለጋ በጉጂ የተፈጠረው ግጭት አሁንም ድረስ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ተፈናቃዮችና እርዳታ ፈላጊዎች ድጋፍ ለማድረግ አዳጋች ሆኖ  መዝለቁን የጽ/ቤቱ ሪፖርት አስገንዝቧል፡፡
በተያያዘ ዜናም በምዕራብ ወለጋ ውስጥ በአንድ ሳምንት ብቻ የጉሊሶ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ አራት ሰዎች ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች መገደላቸው ታውቋል፡፡ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ አበበ ተካልኝ በመኖሪያ ቤታቸው በራፍ ላይ በታጣቂዎች በጥይት ተደብድበው የተገደሉ ሲሆን ገዳዮቹ ወደ ቤት በመግባት ለስብሰባ የተዘጋጀ ጹሑፍና የአካባቢውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝር የያዘ ላፕቶፕ ይዘው ተሰውረዋል ተብሏል፡፡ የከንቲባውን መገደል ተከትሎ የከተማው የመንግስት ሰራተኞች በሁኔታው ተደናግጠው ወደ ስራ ባለመግባታቸው የመንግስት ተቋማት ዝግ ሆነው መሰንበታቸውን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ከከንቲባው መገደል አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሁለት የጊዳሜ ከተማ ነዋሪዎች በጥይት ተመተው መገደላቸውን እንዲሁም ከከንቲባው መገደል በኋላ መስከረም 5 ቀን 2012 በመንዲ ከተማ በሚገኝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ በተፈፀመ የቦንብ ጥቃት የአንድ ሰው ሕይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆስለዋል:: በሳምንቱ ውስጥ እነዚህን አራት ግድያዎች የፈፀሙት ታጣቂዎች እንዳልተያዙም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡    


Read 10336 times