Print this page
Saturday, 21 September 2019 12:54

“እኛ የምናሸንፈው አገራችን ስታሸንፍ ነው “

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)


            ከተመሰረተ አምስት ወራት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ በመቐሌ የመጀመሪያውን ሕዝባዊ ስብሰባ ባለፈው እሁድ (መስከረም 4) አካሄዷል፡፡ ሕዝባዊ ስብሰባው ምን ይመስል ነበር? ምን ዓይነት ጥያቄዎችና ሃሳቦች ተነሱ ? የህዝቡ አቀባበል እንዴት ነበር? የመቀሌውን ስብሰባ የመሩትና የኢዜማ ም/መሪ አቶ አንዷለም አራጌ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡

            የመጀመሪያው እቅዳችሁ የተራዘመው በምን ምክንያት ነበር?
አንደኛው ትንሽ ቢሮክራሲያዊ ጉዳይ ገጥሞን ስለነበር ነው፡፡ እሱ ችግር ከተፈታ በኋላ ደግሞ ባልተጠበቀ መልኩ የጀነራሎቹ ግድያ ማጋጠሙ ጉዳያችንን እንድናራዝም አድርጎናል፡፡ በወቅቱ ሁላችንም ሀዘን ላይ ስለነበርን እኛ ነን ተነጋግረን የሰረዝነው፡፡ በኋላ ግን እነሱም በጣም በጎ ትብብር አድርገውልን፣ ምንም የቢሮክራሲ ችግር ሳያጋጥመን ስብሰባችንን ማከናወን ችለናል፡፡ ለዚህ የክልሉንና የከተማ አስተዳደሩን በእጅጉ እናመሰግናለን፡፡ ሕዝቡም እንደ ሁልጊዜው በጨዋነት፣ በትህትናና በፍቅር ተቀብሎ አስተናግዶናል፡፡ እቤትህ፣ አገር ውስጥ መሆንህ በእጅጉ እንዲሰማህ የሚያደርግ ሕዝብ ነው። በጣም ደስ ብሎን ነው የተመለስነው:: ባለፈው ቅዳሜ (መስከረም 3) በመቀሌ ቀኑን ሙሉ  በፈለግነው ሥፍራ ተዘዋውረን፣ በሞንታርቦ ያለምንም እንቅፋት ነው የቀሰቀስነው፡፡ ሥርዓት አልበኛ የሆኑ ሰዎች ችግር  ይፈጥሩብን ይሆን? የሚል ስጋት ነበረን፤ ነገር ግን ምንም የገጠመን ችግር የለም::  እንደውም አንዳንዶቹ በሙዚቃችን  እየጨፈሩ ድጋፋቸውን ይሰጡን ነበር፡፡ ለሌላ አካባቢዎችም አስተማሪ በሆነ ሁኔታ በጥሩ ጨዋነትና ትህትና ነው የተስተናገድነው፡፡
በጠራችሁት ስብሰባ  ምን ያህል ሰው ተገኘ? አዳራሹን የሞሉት የሕወኃት ካድሬዎች ነበሩ የሚሉ አሉ፡፡ እናንተ ምን ትላላችሁ?
90 በመቶ ታዳሚው ወጣት ነበር። ወደ 300 ያህል ሰው ተገኝቷል፡፡ ከዚያ ውስጥ ምን ያህሉ የህወኃት ካድሬ ነው የሚለውን ማወቅ አንችልም፡፡ ነገር ግን የህወኃት ካድሬዎች ተደራጅተው ገብተው እንደነበር ከሁኔታዎች መገመት ይቻላል፡፡ የአረና አባላትም ነበሩ፡፡ በሞንታርቦ እየዞርን ስንቀሰቅስ ሰው ተገርሞ ነበር የሚያየው፡፡ የትግራይ ሕዝብ ማንም ሳያውቅለት፣ ለአመታት ታፍኖ ነው የኖረው፡፡ የህዝቡ ስጋት ሙሉ ለሙሉ እስኪቀረፍ ድረስ የተወያዩ ቁጥር ሊያንስ ይችላል፤ ወደፊት ግን ሁኔታውን ሲለማመድ በገፍ ወጥቶ እንደሚወያይ ተስፋ አደርጋለሁ:: በእለቱ ወደ አዳራሽ ከመጡት ውስጥ ከ2 መቶ በላይ የሚሆኑት ካድሬዎች አይደሉም፡፡ ከሕዝቡ የመጡ ናቸው የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ለኛ ይሄ የውይይት መድረክ የመጀመሪያችን ነው፤ በዚያ ላይ ዘረኝነት በነገሠበት፣ በጅምላ እነሱና እኛ እየተባባሉ መፈራረጅ በሰፈነበት ጊዜ ላይ ሆነን፣  እንዲህ ያለ ውይይት ማድረጋችን በራሱ ትልቅ ድል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ትልቁ ድል፣ ሕዝቡ አዳራሽ ባይመጣም፣ በመገናኛ ብዙኃን ተከታትሎናል፡፡ በነገራችን ላይ የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ውይይቱን ሙሉ በሙሉ ነው የሸፈነው፡፡ ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋርም ቃለ-መጠይቅ  አድርገናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሚዲያው ለሰጠው ትኩረት እናመሰግናለን፡፡ ስብሰባው በመሳካቱ ህወኃትም እኛም አሸናፊዎች ሆነናል:: ህዝቡም አሸንፏል፡፡ ሁላችንም ያሸነፍንበት ስራ ነው የተሠራው፡፡ ለህዝቡም፣ ለህወኃትም፣ ለመገናኛ ብዙኃኑም ምስጋና ማቅረብ  ተገቢ ነው፡፡
በትግራይ ቆይታዎ ስለ ህዝቡና የክልሉ ፖለቲካ  ምን ተገነዘቡ?
ሕዝቡ በኑሮው የደቀቀ፣ ነገር ግን የሰብዕና ልዕልና ያለው፣ ሰው የሚያከብር ጨዋ ሕዝብ ነው፡፡ የኑሮ መርግ የወደቀበት፣ በዚያው ልክ ሕይወቱን ለማሸነፍ የሚፍጨረጨር ሕዝብ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ በከተማዋ ቤቶች፣ ጥሩ ጥሩ ፎቆች ተሰርተዋል፤ ነገር ግን ልክ እንደ አዲስ አበባ ከፎቆቹ ስር ሰው በድህነት ውስጥ መሆኑን ማስተዋል ይቻላል፡፡ ወጣቶች በብዛት መንገድ ላይ ይታያሉ፡፡ የወጣቱ ቁጥር ከሌላው ይልቃል፡፡ በስራ ሰዓት በሻይ ቤቶችና በየመንገዱ ያለውን የወጣት ብዛት በማየት፣ ወጣቱ ሥራ ፈላጊ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በሌሎቹ የሀገራችን አካባቢዎች የሚታዩ ነገሮች በሙሉ መቀሌ ላይም ይታያሉ፡፡ ድህነቱ፣ የስራ እጦቱ ወዘተ:: ነገር ግን የሕዝቡን ባህሉን፣ ጨዋነቱን ትህትናውን አላሸነፈውም፡፡ ዛሬም ጨዋነቱና ሰው አክባሪነቱን ሕዝቡ ላይ በግልጽ ይታያል፡፡ አንዳንድ ወጣ ወጣ ያሉ ሃሳቦች በሚዲያና በማህበራዊ ሚዲያ እናያለን እንጂ ትግራይ የሄደ ሰው መሬት ላይ የሚያገኘው ጨዋነትን፣ ሀገር ወዳድነትን፣ ሰው አክባሪነትን፣ ትህትናን፣ ሃይማኖተኝነትን ነው፡፡ በቆይታችን ይሄን ተገንዝበናል፡፡
በውይይቱ ምን አይነት ጥያቄዎች  ቀረቡላችሁ?
ብዙ ጥያቄዎች ናቸው የተነሱት፡፡ ነገር ግን በብዛት የተነሱት ጥያቄዎች ከግንቦት 7 እና ከኢሣት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎች ደግሞ የመረጃ እጥረትም ያለባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ እኔ የራሴ ሚዲያ እንደነበረኝ ተደርጐ ጭምር ሲጠየቅ ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ማን እንደተናገረው የማይታወቅ “ያኔ እቃ ወድ ቀበሌ ትግሬ ወደ መቀሌ ሲባል ለምን ዝም አላችሁ?” የሚል ስሜት ኮርኳሪ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ “የትግራይ ህዝብ ሠርቶ እንዳይበላ ከየቦታው ሲሳደድ ሲፈናቀል ለምን ዝም አላችሁ?” የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡ አንዳንድ ካድሬዎች ደግሞ የትግራይን ህዝብ የማይመጥን ጥያቄም ሃሳብም ሲያቀርቡ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚያንቋሽሽ ነገር ሲያነሱ ነበር፡፡ ከሁሉም በእጅጉ ቅር ያሰኘኝ ይሄ ነው፡፡  
ምንድን ነው ጥያቄው?
ለምሣሌ አንድ ደህንነት ነበረ ከተባለ ሰው፤ “ኢትዮጵያውያን የጋራ ታሪክ የለንም፤ ስለ የትኛው የጋራ ታሪክ ነው የምታወራው?” የሚል ጥያቄ  ቀርቦ ነበር፡፡ ይሄ ሰው ለኔ የትግራይ ሕዝብን አይወክልም:: በስነ ልቦናም በአዕምሮም የታወረ አይነት አመለካከት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሃሳቡን እቃወማለሁ እንጂ ተሳትፎውን አከብራለሁ፡፡ አዳራሽ ገብቶ መሞገት መቻል በራሱ የሰለጠነ አካሄድ ነው፡፡ ስብሰባው ጠንካራ ሙግትና ሞቅ ያለ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ይሄ በራሱ አስደሳች ነው፡፡ ምሳ ሰዓት ማለፉን ሳናውቅ 8፡30 ነው ስብሰባው የተጠናቀቀው። ሰው በአሁኑ ወቅት በተለያየ ነገር ቆስሎ ነው ያለው፡። በዘር በጥላቻ የመከፋፈል ስራ ሲሰራ ነው የከረመው፡፡ ቁስሉ እንዲሽር አልተሰራም። ከቀረቡልን ጥያቄዎችና ሀሳቦች የተረዳሁት ቁስሉን የማሻር ሂደት ውስጥ እንደገባን ነው፡፡ እኛም ይበልጥ ለመስማት እንጂ ለመናገር አይደለም የሄድነው፡፡ በቀናነት ሀሳቦች ተሰንዝረውልናል። እነዚያንም ተቀብለናል፡፡
ኢዜማ በቀጣይ ምን ለማከናወን አቅዷል? ስለ ቀጣዩ ምርጫስ ምን ያስባል?
እኛ ከምስረታ ጀምረን ፓርቲያችንን የምርጫ ፓርቲ አድርገን ነው ያደራጀነው፡፡ ስንደራጅም በምርጫ ወረዳ ደረጃ ነው፡፡ ፓርቲያችን ሲጠነሰስ ጀምሮ የምርጫ ፓርቲ ሆኖ ነው፡፡ እኛ የአሁኑን ምርጫ እንደከዚህ ቀደሞቹ ወይም እንደ ተራ ምርጫ አይደለም የምናየው፡፡ በአገራችን ታሪክ ውስጥ  በጣም ብዙ ጊዜ ያማጥንለት ያለቀስንለት፣ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ዘመን እንደደረሰ እናስባለን:: ብዙ ጊዜ እንዲህ ያሉ የለውጥ ጅማሮዎች እየመጡ እየተሰናከሉ ደግሞ እንደገና ለመከራ ስንዳረግ ቆይተናል። የአሁኑ ምርጫ ግን የእውነት ዴሞክራሲን የምናዋልድበት ጊዜ እንዲሆን እንፈልጋለን። ዝም ብሎ ታሪክ ሆኖ እንዲያልፍ አንፈልግም፡፡ እኛ ምርጫው ላይ ያለን ስጋት አገሪቱ ምን ያህል ዝግጁ ናት የሚለው ላይ ነው፡፡ አገሪቱ ምጧን ለመገላገል ምን ያህል ዝግጁ ናት የሚለው ነው የሚያሳስበን። አንዲት እናት ምጧን ለመገላገል ወደ ሆስፒታል ስትገባ በሰላም እንድትገላገል ጉልኮሱ ተሰክቶ ምቹ አልጋ ተነጥፎላት፣ አስፈላጊው መድሃኒት ተሰጥቷት ነው፡፡ ይህ የሚደረገው ጽንሱም እንዳይሞት፣ እናቲቱም እንዳትሞት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም ዴሞክራሲን በምናዋልድበት ምርጫ፣ ጽንሱም ሆነ እናቲቱ የማትሞትበት መሆኑን በሚገባ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ኢዜማ በራሱ በኩል ከበቂ በላይ ምናልባትም መታበይ እንዳይሆንብኝ እንጂ ከሌሎች ፓርቲዎች በተሻለ ለምርጫው ራሱን እያዘጋጀ ነው:: 16 ፖሊሲዎችን አዘጋጅተናል፡፡ ወደ ሕዝቡም መውረድ ጀምረናል። ለኛ ምንም ችግር የለውም፡፡ ጥያቄው አገሪቱ ዝግጁ ነች ወይ የሚለው ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ነው ምርጫው እንዲራዘም ሀሳባችንን ስንገልጽ የነበረው፡፡ ነገር ግን ምርጫው ይካሄድ ከተባለ በኛ በኩል ዝግጁ ነን፡፡ እኛ ብዙ ችግር የለብንም፡፡ ግን አገራችን ስታሸንፍ ነው እኛ የምናሸንፈው የሚል እምነት አለን፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ማሸነፍ አለባት:: ኢትዮጵያ ማሸነፍ የምትችለው ደግሞ ሁላችንም በየዘርፉ ቆመን ዴሞክራሲን አብረን ስናዋልድ ነው:: ዝም ብሎ ፓርላማ ገብቶ ደሞዝ የማስቆረጥ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ አገሪቱ ምን ያህል ዝግጁ ነች የሚለውን ሁላችንም ማሰብ አለብን፡፡
በአገሪቱ የሚታየው የዘር ፖለቲካና  በብሔር  የመቧደን ጉዳይ እንቅስቃሴያችሁን አልፈተነውም?
የብሔር ጉዳይ ዋነኛው የአገሪቱ ተግዳሮት ሆኗል፡፡ ነገር ግን እኛ ሕዝቡ ጋ ገብተን ስናደራጅ ያን ያህል የገጠመን ችግር የለም፡፡ ሕዝቡ አትምጡብኝ አላለንም፡፡ ዘመቻ የሚደረገው ፌስቡክ ላይ ነው።
መሬት ላይ ከሕዝቡ የገጠመን ነገር የለም፡፡ እንደውም በራሳችን ውስንነት ወደ ሕዝቡ ገፍተን አልወረድንም እንጂ ሕዝቡ ጋ ችግር የለም፡፡ እኔ በደሴ፣ ትግራይ፣ ባህርዳር፣ ገጠር ውስጥም ገብቼ አይቻለሁ፤ ሕዝቡ ጋ ችግር የለም፡፡ የፌስቡክ ጩኸት ነው በብዛት ያለው፡፡ በእርግጥ ዘረኝነት አጥንታቸው ድረስ ዘልቆ የጎዳቸው ብዙ ወጣቶች እንዳሉ ተገንዝቤያለሁ፡፡ በአገር ደረጃ እኛን የማያሰራ ሆኖ ግን አላገኘነውም፡፡     

Read 1670 times