Saturday, 21 September 2019 13:01

ጥበብ፤ የሰላም ጠበል

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(2 votes)


                   የሰላም ማዕከል ግንባታ ቢቀርብስ?

      “ተስማምተን በፍቅር ለመኖር አንድ ላይ
       አልረፈደም ዛሬም አልገባችም ፀሐይ
       ይቅር ለመባባል ካለብን በቀና
      ደንገዝገዝ አለ እንጂ አልጨለመም ገና”
              

           ለቅሶም ላይ ሆነን የተደሰትን እንድንመስል ባህል ያስገደድናል፡፡ ባህል ስለሆነ እያከበርነው  እንጂ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አሁን ዘመን መለወጫ አይደለም:: እንደ ሀገር የምንደሰትበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ከአክቲቭስቶችና ፖለቲከኞች ከፍ ባለ፣ ከሕዝብ ባነሰ የሀዘን ድባብ ላይ ነን፡፡
“አበባየሆሽ ለምለም” ሳይሆን ማለት ያለብን “አበባየሆሽ…ለምን?” ነው ማለት ያለብን፡፡ መልስ ሳይሆን ጥያቄ ነው በእጃችንም፣ በልባችንም ያለው፡፡ “ለምለም” የምንለው ምኑ ለምልሞ ነው?
በትግራይና አማራ፣ በሶማሌና ኦሮሚያ፣ በሲዳማና ወላይታ፣ በሌላና ሌላ ብሔር ብሔረሰቦቻችን መሀል የተፈጠሩት አለመግባባቶች፣ ወልደው ባሳደጓቸው፣ ሰይጣኖቻቸው ያመጣባቸውን ልክፍት በጠበልም በዱአም፣ መች ፈውስ አበጁለትና ነው ለምለሙ? ባህል ስለሆነ ግን እንላለን፡፡  
ሰሞኑን የሰላም ሚኒስቴር፣ የሰላም ማዕከል ግንባታ ሊያከናውን  የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል:: ይህ የተደጋገመ ስህተት ይመስለኛል፡፡ የሰላም ማዕከልን በድንጋይና በሲሚንቶ በመገንባት ሀገራችን ላይ ተጨማሪ ሆድና ተቀላቢዎች እንፈጥር ይሆን እንደሆን እንጂ ሰላምን መሬት አውርደን፣ ለዚህ ቀና እንዳይል ለተረፈደበት ሕዝብ፣ ጠብ የሚል ለውጥ አናመጣም፡፡ እስካሁን በሀገራችን የምንፈልገው ሰላም ያልመጠው ስለ ሰላም መነጋገሪያ ህንፃ ጠፍቶ አልነበረም፡፡ የድንጋይና ሲሚንቶው ማዕከልማ “ማዕከላዊ” ተብሎ ሕዝብ ተገርፎበታል፡፡ ቤተ መንግሥት ሆኖ በሕዝቦች ላይ ተዶልቶበታል፡፡ የሞት ፍርድ ተሰጥቶበታል፡፡
አዲስ “የሰላም ማዕከል” ያስፈልገናል
ድንጋይ የማይቆለልበት፣ አሸዋ ከሲሚንቶ የማይቦካበት የሰላም ማዕከል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ያስፈልገናል፡፡ በካድሬዎች ሳይሆን በጥበብ ሰዎች የሚመራ የጥበብ ማዕከል መገንባት ጠቃሚ ነው::  ባለፈው ዕትም ጽሁፌ፣ (በተለይም) በትግራይና አማራ ክልል ለሚኖሩ ሕዝቦች አዲስ መላ ካልዘየድን፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶቹ የሚጓተቱት ገመድ፣ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለሕዝቦችም እንደሚተርፍ ለመግለጽ ሞክሬያለሁ፡፡ የተጋጨ ሕዝብ ኖሮ እርቅ አናወርድም፡፡ አፋፍ ላይ ሆኖ እየተገፋ ያለ ሕዝብ ግን አለ፡፡ አሁንም እሱ ላይ ማተኮር አለብን:: ያንን ቋጠሮ ከመፍታት የተሻለ ዘመን መለወጥ የለም:: አደይ አበባውም እሱ እንጂ ጋራ ተራራውን የሚያደምቀው የእኛ ብቻ አበባ አይደለም፡፡
ለአዲስ አመት እስካሁን ያልታሰበ፣ ቢያንስ እኔ ያልጠበኩት የሀመልማል “ቅምሻ” አልበም ወጥቷል:: በብዙ መልኩ ድምፃዊቷ የተሻለና ከእሷ የሚጠበቅ አልበም ሰርታለች፡፡ ነገሩ ግን ወዲህ ነው፡፡ ገጣሚ ታደሰ ገለታ ለሀመልማል ከሰጣት የሁለት ዘፈን ግጥሞች “እስቲ ስማኝ” የሚለው (ቁ.7) ባለፈው ሳምንት ላነሳሁትና ዛሬም ለምጮህለት የውስጥ ደዌያችን ዱአና ጠበል ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰላም ሚኒስቴር፤ “ከሰላም ማዕከል ይልጥ የጥበብ ማዕከል ቢያስገነባ“ ለማለትም ያበቃኝ ይህ ነው፡፡
ሁሌ እሳት ማጥፋት ላይ እየተጠመድን፣ ሁሌ ዘመቻ ላይ እየሆንን፣ ፕሮፓጋንዳን እንደ ግል አዳኝ አድርገን እየተቀበልን፣ ካለንበት መራመድ አቅቶን እየተደነቃቀፍን እንጂ የጥበብ ጠበል የቱንም በሽታ የመፈወስ አቅም እንዳለው ሳይታወቅ ቀርቶ አይደለም፡፡ ፈውሶ ሳይታይ ቀርቶም አይደለም፡፡ ልክ እንደ ሀገር በቀል መድሃኒቶቻችን ሁሉ፣ መሬት ላይ ሕዝብ እያዳነ፣ አደባባይ ያስወጣ መድሀኒት ነው፤ ጥበብ፡፡
ገጣሚ ታደለ ገለታ “ተው ስማኝ” ይላል፡፡ አሁን እኛ  ያቃተን፣ ሃላፊነት ወስደን “ተው ስማኝ” ማለትና ራሳችንንም የተነገረውንም መስማት ነው፡፡ እውነት ለመናገር ይህን የጥበብ ስራ በአንድ ሌሊት ከ40 ጊዜ ያላነሰ ሰምቼዋለሁ፡፡  እውነት ነው፡፡
“ተው ስማኝ ስማኝማ ዛሬ
በል እንጂ ንገረኝ፣ ሰምተህ ዝም አትበለኝ
ምንድነው ይሄ እንግዳ ፀባይ
ያስሰደብህን ማማረርህ በኔ ላይ
ከመቼ ወዲያ ነው ከመቼ ወዲህ ደግሞ  
በኔና አንተ መሀል አስታራቂ ቆሞ
ከየት የተሰማ ነው ይሄ አዲስ ፀባይ
ኩርፊያ በኔና አንተ ያምርብናል ወይ?...”
ዛሬ በአማራና ትግራይ ሕዝቦች መሀል ይህን ድንበር ጥሶ የሚወጣ ነው የጠፋው፡፡ ፖለቲከኞቹና አክቲቭስቶቹ ይህን ዜማ ሊያዜሙ ፍላጐት የላቸውም፡፡ ወደፊትም የሚኖራቸው አይመስልም:: ምክንያቱም የእነሱ ገበያ ከፍቅርና ከሰላም የሚገኝ አይደለም፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መሀል እንዲህ ያሉ ጥቂት የጥበብ ስራዎች ቢፈልቁም፣ የሰላም መገለጥ በሕዝቦቹ ዘንድ ቢወርድ እነዚህ የማህበራዊ ሚዲያ መርዞች፤ ብዙ ጥፋት ሳያመጡ በረከሱ ነበር፡፡ በግሌ ለሀገሩም ባይሆን እንኳን ለብሔሩ ከልቡ የቆመ አክቲቪስት አላውቅም፡፡ “የእኔ” የሚሉት ሕዝብ ሰላም እንዳይኖረው እየታተሩ ለሕዝብ አሳቢነት የለም፡፡
በሁለቱም ሕዝቦች ይሁን በሀገሪቱ ሰላም መምጣቱ የብዙዎችን ሱቅ ይዘጋል፡፡ የሀገራችን ጥበብ የፕሮፓጋንዳን አጥር እንዳይዘል ስለተፈረደበት ግን እድለኞች ሆነው የፈለጉት ላይ እየተኮሱ ይጥላሉ፡፡
“እንዴት አያሳስብ እንዴት አያስጨንቅ
ተስማምተን በፍቅር ለመኖር አንድ ላይ
አልረፈደም ዛሬም አልገባችም ፀሐይ
ይቅር ለመባባል ካለብን በቀና
ደንገዝገዝ አለ እንጂ አልጨለመም ገና
እንዲህ ነበር እንዴ የኛ ፍቅር ድሮ
የሚያጨካክነን ምን መጣ ዘንድሮ…”
የማታ ማታ፣ ከብልጣብልጥ መንገድ፣ ከዩቲዩብ “ላይክ” ቆጠራ ወጥቶ፣ ሕዝብ አንጀት ላይ ጠብ የሚል ስራ መስራት መጀመሩ በራሱ አደይ አበባ ነው፡፡ እውነት ለመናገር፣ ለእኔ “ተው ስማኝ” ራሱን የቻለ ድንጋይና አሸዋ የማይጠይቅ የሰላም ማዕከል ነው፡፡ ወ/ሮ ሙፈሪያት፤ መሬት ከማስቆፈር፣ አሸዋ ከማስወረድ፣ ብሎኬት ከማስጫን ይልቅ የሃመልማል አባተን “ተው ስማኝ” እያንዳንዱ ሕዝብ ልብ ውስጥ ማስገባት ከቻሉ፣ የራሳቸውን የሕይወት ታሪክ በወርቅ ብዕር ጻፉ ማለት ነው፡፡ የድንጋዩን ማዕከል  ሰላም ሲያገኙ ሕዝቦች ይገነቡታል፡፡ ያ ማዕከል በምንም የማይፈርስ ይሆናል፡፡ በተለይ የአማራና ትግራይ ሕዝቦች የሚከተለውን የታደሰ ገለታን ሃሳብ እየተናገሩ ለጊዜው ለሚያጡ ይመስለኛል፡፡
“ወሬ አራጋቢውን ይቅርብን አንስማ
የሚያባብስ እንጂ የለም የሚያስማማ”
ስለ እኛ በኩራት ስንት የመሰከሩት
ተምሳሌት ፍቅር ሲሉን የነበሩት
ያ ፍቅራችን ዛሬ እንዲህ በመሆኑ
እንኳንስ የሰኑት ያዩትም አመኑ
መጣላታችንን ዞረን ብናወራ
ያስታራቂ ያለህ ብለን ሰው ብንጠራ
ማንም የለምና እውነት ነው የሚለን
እኛው አንስማማ ይቅር ተባብለን፡፡”
እንዲህ ላሉ ኃላፊነት ለሚሰማቸው የጥበብ ሰዎች መድረኩ ምቹ እንዳልሆነ እናውቃለን፡፡ የሰላም ሚኒስቴር ወደ እነዚህ አይነት ፈዋሽ መድሃኒት መዞር ካልቻለ፣ ትክክለኛው የነፍስ ጥበብ ወዳለበት መሄድ ካልቻለ እንደ ብዙዎቹ ተቋማቶቻችን ሁሉ አፈራርቆ መቅረት አይቀርም፡፡ ገጣሚው እንዳለው፤ የደነጋገዘ እንጂ የጨለመ ቀን አልመጣም ገና፡፡
ሙዚቃ የብዙ ጥበባት ጉባዔ እንደመሆኑ የታደሰ ገለታን ግጥም፣ በደስታ ከበደ ዜማና በሀመልማል አባተ እንጉርጉሮ “ተው ስማኝ” የሰላም ሚኒስቴር፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!

Read 9471 times