Monday, 23 September 2019 00:00

“ኪነ-ሕንጻ በጥልቅ ልባዊ ፍቅር የምተጋለት ሙያ ነው”

Written by  ራሄል ሻውል ዘለቀ፤ የኪነ-ህንጻ ባለሙያ
Rate this item
(1 Vote)

የሕንጻው ውበትና ቅርፅ፣ መጠኑ፣ የቦታ ፅንሰ ሐሳቡና በከተማው ከባቢ ውስጥ የሚይዘው ቦታ፤ የቁሳቁስ፣ የልስላሴና ሻካራነት እንዲሁም የቀለም አጠቃቀም ሁሉ፣ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያ የሥራ ድርሻዎች ናቸው፡፡ አያሌ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች አሻራቸውን በከተሞቻችን ላይ አሳርፈዋል፡፡ እኔም ለትውልድ ከተማዬ ገጽታ መጠነኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት በመቻሌ ራሴን እንደ እድለኛ እቆጥረዋለሁ፡፡
ኪነ-ሕንጻ በጥልቅ ልባዊ ፍቅር የምተጋለት ሙያ ነው፡፡ የተወለድኩት በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን አብዛኛውን የታዳጊነት ዘመኔን ያሳለፍኩት ዛሬም ድረስ እጅግ ማራኪና ንቁ ከሆኑት ሰፈሮች እንዷ በሆነችው በፒያሳ ነው፡፡ ወላጆቼ ካፈሯቸው አምስት ልጆች አንዷ ስሆን፣ ግሩምና ድንቅ በሆኑ አባትና እናቴ እንክብካቤ ነው ያደግሁት፡፡ ወላጆቼ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ አርአያዎቼ ናቸው:: ከልጅነቴ ጀምሮ የተትረፈረፈ ፍቅር ለግሰውኛል:: የትምህርትንና የመማርን ፋይዳም በልቤ ውስጥ አስርፀውብኛል፡፡ በራሴ ላይ እምነት እንዲኖረኝ የሚያስችል ልበ ሙሉነትን አጎናጽፈውኛል፡፡ ስኬታማ የመሆን ጠንካራ ፍላጎት እንዲያድርብኝም አነሳስተውኛል፡፡ ህልሜን ከመከተል ፈጽሞ ወደ ኋላ እንዳልልም አበረታተውኛል። እንደ እኔ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያ የሆነው ባለቤቴ፤ እህቶቼና ጓደኞቼ፣ የዘወትር የጥንካሬዬና መነቃቃቴ ምንጭ እንደሆኑ ቀጥለዋል፡፡  
ከልጅነት የተማሪነት ጊዜዬ ጀምሮ ለጥበብ ልዩ ፍቅር ነበረኝ፡፡ ይሄ የጥበብ ፍቅር ከኪነ-ሕንጻ ጋር ወደ መተዋወቅ ያመራኝ ግን በ1978 ዓ.ም ወደ ኮሌጅ ለመግባት ሳመለክት ነበር፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ሕንጻ ትምህርት ቤት (ያኔ የሕንጻ ኮሌጅ ይባል ነበር) ከተቀበላቸው በጣት የሚቆጠሩ ተማሪዎች አንዷ በመሆኔ እድለኛ ነበርኩ፡፡ የሥነ-ሕንጻ ትምህርት በጀመርኩበት ዓመት፣ ከ24 ተማሪዎች መካከል  እኔን ጨምሮ አራት ሴቶች ብቻ ነበርን:: ከእልህ አስጨራሽ አምስት የትምህርት ዓመታት በኋላ ተመረቅን፡፡ ከሁለት የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ሽርክና በመፍጠር ‹አባ አርኪቴክቶች› የተባለውን ድርጅት በ1984 ዓ.ም አቋቋምን፡፡ እንደ ወጣት የኪነ-ሕንጻ ባለሙያ፣ እነዚህ ጊዜያት ለእኔ የሙያ ጅማሮ ዓመታት ቢሆኑም፣ ቢሯችን በከተማዋና ዙሪያዋ በርካታ ሕንጻዎችን ዲዛይን በማድረግና በመቆጣጠር ሥራ ተጠምዶ ነበር፡፡ አንዳንድ ሥራዎቻችንን፣ ከዓለም አቀፍ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ነው  የሰራናቸው፡፡  
በ1996 ዓ.ም ከሽርክናው ወጥቼ የራሴን ኩባንያ መሰረትኩ፡፡ ‹ራስ አርኪቴክቶች› የተባለው ኩባንያዬ ተወለደ፡፡ አሁን ኩባንያው በአዲስ አበባና በመላ ኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች ጥራታቸውን የጠበቁ ሕንጻዎችን ዲዛይን በማድረግና በመቆጣጠር በስኬት መገስገሱን ቀጥሏል፡፡ እኔ በግሌ በቢሮዬና በፕሮጀክት ስፍራዎች፣ ሃያ የሚሆኑ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎችና የኢንጂነሮችን ቡድን እመራለሁ፡፡ እንደ ፕሮጀክቱ ሁኔታም የኢንጂነሪንግ ሥራዎችን በሌሎች ኩባንያዎች አሰራለሁ፡፡ ቢሯችን በበርካታ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሚሳተፍ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የኤምባሲዎችን፣ የቢሮዎችን፣ የንግድ ሕንጻዎችን፣ የኢንዱስትሪዎችን፣ የት/ቤቶችን፣ የሆስፒታሎችንና የመኖሪያ ሕንጻዎችን ዲዛይን ማድረግ ይገኙበታል፡፡
ብዙ ጊዜ ለዲዛይን ሥራዬ የፈጠራ ሀሳብና ንሸጣ የማገኘው፣ በአገሬ ምድር ሞልቶ ከተትረፈረፈው መልክአ ምድር፣ ቁስና ቀለም ውስጥ ነው፡፡ በአብዛኛው ዘመናዊ ጽንሰ ሃሳቦችን ከባህላዊ የሥነ-ሕንጻ ባህርያትና ቁሶች ጋር በማቀላቀል ቀላል፣ ምቹና ዘና ያለ ስሜት የሚፈጥሩ ሕንጻዎችን ዲዛይን ማድረግ እወዳለሁ፡፡ ማንኛውም የዲዛይን ሥራ ከመጀመሩ በፊት ፕሮጀክቱን ለመረዳትና የደንበኛውን ፍላጎት ለማወቅ ሰፊ ምርምር አካሂዳለሁ፡፡ ሥራው የጽንሰ  ሀሳብ ንድፍ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከደንበኛው ጋር ብዙ ውይይቶችና ግንኙነቶች እናደርጋለን:: ከዚያ በኋላ ሙሉ የሥነ-ሕንጻና ምህንድስና ዲዛይን ለመሥራት  ስድስት ወር ገደማ ይፈጃል:: ዋና ሃላፊው በፕሮጀክቶች ሲጠመድ የዲዛይኑን ቴክኒካዊ ነገሮች የማስተባበርና የመምራት ሙሉ ኃላፊነቱ (ለግንባታ ዝግጁ እስኪሆን ድረስ) በእኔ ላይ ይወድቃል፡፡ ግንባታው እንደ ሕንጻው መጠንና የአሰራር ውስብስብነት እንዲሁም በጀትና ሌሎች መሰል ጉዳዮች፣ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ሊወስድ ይችላል፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ ሁሉንም የሥነ-ሕንጻ ሥራዎች የመቆጣጠርና የምህንድስናውን ክፍል የመምራት እንዲሁም አጠቃላይ ጥራቱንና የፕሮጀክት ወጪ ቁጥጥሩን ሪፖርት የማድረግ  ኃላፊነት አለብኝ፡፡
በኢትዮጵያ ካከናወንኳቸው ከፍተኛ ጥራት ያላቸው በርካታ ፕሮጀክቶች መካከል፤ ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል፣ የኤስኦኤስ አፓርትመንቶች፣ ሾላ ምቹ አፓርትመንቶች፣ የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ሥልጠና ማዕከል፣ ቢንግሃም አካዳሚ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ የአየርላንድ ኤምባሲ፣ አዋሳ ፕሮቲ ሆቴልና ፎር ዩናይትድ አፍሪካ ግሩፕ ይገኙበታል:: ከዓለም አቀፍ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎችና ኢንጂነሮች ጋር በትብብር እየሰራሁ ሲሆን ከሥራዬ ጋር በተያያዘ በመላው ዓለም በስፋት ተጉዣለሁ:: በትብብር ከሰራናቸው ፕሮጀክቶች መካከልም ዓለም አቀፍ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ፣ ብሪቲሽ ካውንስልና ዛሃራ የሕጻናት ማዕከል ይገኙበታል፡፡
በ1999 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለተገነባው የሮያል ኔዘርላንድ ኤምባሲ ፕሮጀክት፤ አርኪቴክት ኦፍ ዘ ሪከርድ እና የደች የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች፣ የአገር ውስጥ አጋር በመሆን እንዲሳተፉ አስተዋጽኦ አድርጌአለሁ፡፡ ሀሳቦቼና ሥራዎቼም ታላቁን ዓለማቀፍ  ‹የአጋክሃንን የኪነ-ሕንጻ ሽልማት› አስገኝተውልኛል፡፡ ለኢትዮጵያ የወደፊት የግንባታ ፕሮጀክቶች  ብዙ ዓላማዎችና ግቦች አሉኝ፡፡ በከተሞቻችንና በሙያችን ላይ አዎንታዊ ለውጥ በሚያመጡ ሥራዎች ላይ የበለጠ ለመሳተፍ  አልማለሁ፡፡
አንዳንዴ ወንዶች  በጣም በገነኑበት ሙያ ውስጥ ሴት የኪነ-ሕንጻ ባለሙያ መሆን ፈታኝ ነው፡፡ ለእኔ ግን ይሄ ስኬታማ ከመሆንና የበለጠ ከመትጋት አላገደኝም፡፡ እንደውም ከወላጆቼ የወረስኩት አዎንታዊ የሕይወት አመለካከት፣ በሥራዬ ላይ የማውለው መልካም ስጦታ ሆኖኛል:: ሠራተኞችን ለማስተዳደርና በውስጣቸው ያለውን ታላቅ ተሰጥኦ ለማውጣት በእጅጉ አግዞኛል:: የሥራ ባልደረቦቼን እወዳቸዋለሁ፤ ከእነሱ ጋር የማሳልፈውም ጊዜ ያስደስተኛል፡፡ ሁሌም ሥራችን አስደሳች እንዲሆንና መልካም ግንኙነታችን ተጠብቆ እንዲዘልቅ ከማድረግ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም:: በማንኛውም ሥራ ስኬታማ ለመሆን እጅግ አስፈላጊው ነገር ይሄ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ከቀጣዩ ትውልድ የኪነ-ሕንጻ ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር እንዲሁም ድጋፍና ሥልጠና መስጠት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ነው በኢትዮጵያ የኪነ-ሕንጻ ተቋምና በሕንጻ ኮሌጅ ለሚገኙ ተማሪዎች ጊዜዬን በበጎ ፈቃደኝነት በመስጠት በውጭ አማካሪነትና በገምጋሚነት የማገለግለው፡፡ በአዲስ አበባ ስኬታማ የኪነ-ሕንጻ ዲዛይን ቢሮ ከሚመሩ በጣት የሚቆጠሩ ሴቶች አንዷ እንደመሆኔ፣ ለሴት ተማሪዎች አርአያ እንደምሆንና በሕይወታቸውና በሙያቸው ብርታት እንደምሆናቸው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ወደፊት ሴቶች በኢትዮጵያ ወሳኝ ሀይል እንደሚሆኑ በጽኑ አምናለሁ፡፡ ውጤታማ የንግድ ሰው እንዲሁም ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት እንደመሆኔ፣ ሴቶች ነገሮችን በአግባቡ ጎን ለጎን መምራት  እስከቻሉ ድረስ የሙያም የቤተሰብም ባለቤት ከመሆን የሚያግዳቸው ምንም ነገር የለም:: ለስኬታማነቴ ያገዙኝ ሦስቱ ቁልፍ ነገሮች፡- ማበረታቻ፣ ማነቃቂያና ድጋፍ ናቸው፡፡ እናም በአንድ ጊዜ አንድ ዲዛይን ብቻ በመሥራት፣ ደረጃ በደረጃ፣ ኢትዮጵያን የበለጠ ውብ ማድረጌን እንደምቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡   
(“ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች”፤2007 ዓ.ም)

Read 812 times