Sunday, 22 September 2019 00:00

መምህር ድንቆ ማርቆስና ቅኔያዊ ፍልስፍናው

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር )
Rate this item
(1 Vote)

  ድንቆማርቆስ በ1699 ዓ.ም ላይ በጎንደር ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ መምህር ነው፡፡ ባሕረ ሐሳብና ቅኔን መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጻሕፍተ ሊቃውንትን የተማረና የተመራመረ ሊቅ ነበር ይላሉ፡፡ የደረሳቸው ቅኔያት በንባብና በምሥጢር የተስማሙ የተከናወኑ፤ እጅግ ደስ የሚያሰኙ ናቸው:: ይህ ሊቅ በጎንደር የደብረ ብርሃን ሥላሴ ሹም ሆኖ ያገለግል ነበር:: በኋላ ጊዜ ግን ተሽሯል፤ በዘመኑ የፀሐይና የጨረቃ ብርሃንን የሚጋርድ አቀድ የሚባል ኮከብ በሚያበራበት ጊዜ ቀኑ ጨልሞ ነበር፡፡
ሊቁ የዚህን ምክንያት አስቀድሞ ያውቀው ነበርና፣ ለሌሎች በማሳወቁ ደግሞ ተሾመ ይላሉ:: ይህ ሊቅ እንደ መምህርነቱ ከላይ የተጠቀሱትን የትምህርት ዓይነቶች አስተምሮዋል፡፡ እንደ ሹምነቱ መግቦዋል ይላሉ፡፡ በዐፀደ ሥጋ የኖረበት ዘመነ መንግሥት፤ የአድያም  ሰገድ ኢያሱ ነው፡፡ ያረፈበት ዘመን፤ የርጉም ተክለ ሃይማኖት ዘመነ መንግሥት ነው ይላሉ፡፡ (ይኵኖ አምላክ ገብረሥላሴ 1959) ይህ ሊቅ በጎንደር ዘመነ መንግሥት ዝነኛው የቅኔ ፈላስፋ ለነበረው የሊቆ ክፍለ ዮሐንስ መምህር እንደነበር ይወሳል፡፡ ክፍለ ዮሐንስ በመምህር ድንቆ ማርቆስ ተኮትኩቶ ስለአደገ፣ ሊቅነቱ እስከ መጨረሻ ድረስ አስተማማኝና አስደናቂ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የመምህር ድንቆ ማርቆስ በርካታ የቅኔ ድርሰቶች ሲኖሩት ከሥራዎቹ ውስጥ ስድስት ያህሉ  እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
ሥላሴ   
በነቢብ፡ወበአርምሞ፡ኵሉ፡ሠናይ፡ግብረ፡ሥላሴ፡
ሠናይትሰ፡እምኵሉ፡ፅንሰ፡ሌዋዊት፡እም፡፡
እስመ፡የብሰ፡ባቲ፡ዘበለስ፡ደም፡፡
ወእምነ፡ይእቲ፡ፅንስ፡ዓረቦነ፡ካልእ፡ዓለም፡፡
ዘከልእዎ፡ፍሬ፡ከመ፡ይቅስም፡፡
በንስቲት፡ሥጋ፡ስቍረተ፡ሰላም፡፡
እደዊሁ፡ለአከ፡አዳም፡፡  
ትርጉም፡- በመናገርና ዝም በማለት የሥላሴ ሥራ ሁሉ ያማረ ነው፡፡ ያማረችስ ከሁሉ ይልቅ   ያማረች የሌዋውያን ሐና እናት ፅንስ  ናት፡፡ የበለስ ደም በእርስዋ ደርቆባታልና፡፡ የሁለተኛ  ዓለም ስጦታ ( ከሆነች) ከዚህች ፅንስስ ፍሬ ይለቅም ዘንድ የከለከሉት በትንሽ የሰላም ቀዳዳ ሥጋ ቀዳዳ (ጭላንጭል፤መስኮት) አዳም እጆቹን ላከ፡፡
ምሥጢር፡- በሔዋን የደማው የበለስ ደም በሐና ልጅ በእመቤታችን መድረቁን ይገልጣል:: ይህም በዘፍጥረት 3 «በከመ አድመውኪያ ለዛቲ በለስ ከማሁ ይረድ ደምኪ እስከነ ሰብዓቱ  ዓመት» የሚለውንና በእመቤታችን ልማደ አንስት እንደሌለባት ያመለክታል፡፡ በአጠቃላይ ሐና ያማረች እመቤታችንን በመፅነስዋ  የበለስ  ደም ፍዳ እንደ ጠፋ፤ ከዚያችም ፅንስ የተነሣ ፍሬ ክብርን ሊሰበስብ አዳም ፍጥረት ጸሎቱንና መሥዋዕቱን እንዳቀረበ፤ያሳያል፡፡ ይህም በሐዋን ምክንያት ከገነት የወጣ አዳም በእመቤታችን ወደ ገነት የመመለሱ ምሳሌ ነው፡፡  የቅኔው ዓይነት ታሪክ ፤ ሐተታ ፤ የምሥጢር ምርምር ቅኔ ሲሆን መንገዱ ሰምና ወርቅ ነው፡፡ በኅሩይ ወልደ ሥላሴ መጽሐፍ (1918፤ ገጽ54)እና በአድማሱ ጀምበሬ ‹‹መጽሐፈ ቅኔ›› 1963 ገጽ 265 ላይም ተጠቅሷል፡፡
2. ሥላሴ  
አርዮስ፡ወመምህሩ፡ላዕለ፡ሐዋርያት፡አመክነዩ፡ብሂለ (በብሂለ ለማለት ነው) ወልድ፡ፍጡር፡በቀዳማዊ፡ልደቱ፡፡
ለአጽድቆ፡ሕልም፡ነገሮሙ፡ዝንቱ፡፡
ዮምኒ፡ይፈጽም፡ (ይትፈጸም ለማለት ነው) ዓመፃ፡በመሥፈርተ፡እሉ፡ክልኤቱ፡፡
እንዘ፡ፍናዊሃ፡በኍልቈ፡ቤቱ፡፡
ሰብእ፡ኵሉ፡ለሃይማኖቱ፡፡
ይቀብዓ፡ስመ፡፻፫፡፡
ትርጉም በመጀመሪያ መወለዱ ወልድ ፍጡር ነው በማለት፣ አርዮስና መምህሩ በሃዋርያት ላይ አመሃኙ፡፡ ይህ የሚሆን ነገራቸው ሕልምን ለማጽደቅ አመሃኙ፡፡ በእነዚህ በሁለቱ መስፈሪያዎች ልክ ዛሬም በደል ይፈጸማል፡፡ በቤቱ ቁጥር ጎዳናዋ ሳለ ሰው ሁሉ በሦስት መቶ  ስም ሃይማኖቱን ይቀባታል፡፡
ምሥጢር አርዮስ ወልድ ፍጡር ነው ማለቱን ያመለክታል፡፡ ቅኔው ሰም አልባ ወርቅ ነው፡፡
ሥላሴ
በፍናው፡፬ይቤ፡መልአክ፡ዓቃቤ፡ርእሱ፡
ላዕለ፡መንኖ፡እክል፡ወማይ፡ î እስመ፡ገብረ፡ሕይወት፡ሐደሰ፡፡
መንኖ፡ዓራዝ፡መንከረ፡ሣልሰ፡፡
ወራብዓይ፡ዕፁብ፡ነገሩ፡ለቀራንብቲሁ፡ድቃሰ፡፡
ከመ፡እለ፡ኪሩቤል፡ኢኃሠሠ፡፡
እመ፡ለብሰ፡ ሥጋ፡ወእመ፡ኢለብሰ፡፡
ክዋኔሁ፡ኢየአመር፡አንሰ፡፡
ትርጉም፡ በዐራቱም መንገዶች ጠባቂው መልአክ አለ ገብረ ሕይወት (ገብረ መንፈስ ቅዱስ ) በሁለቱ በምግብና በውኃ ላይ ቃል ኪዳን አደረገ፡፡ በመኝታ (አልጋ) ላይም  ማለት መኝታ ላይተኛም ሦስተኛውን ቃል ገባ፡፡ በዐራተኛም  ልክ እንደነ ኪሩቤል ለዓይኖቹ እንቅልፍን እንደማይፈልግ ወሰነ፡፡ ሥጋ ለበሰም አልለበሰ  ሁኔታውን እኔ አላውቅም፡፡
ምሥጢር፡-ገብረ መንፈስ ቅዱስ ከተወለዱበት ጊዜ አንሥቶ እኽል  ውኃ እንደ መላእክት ያልቀመሱ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ የቅኔው መንገድ ታሪክ፤ ዓይነቱ ጽድቅ ነው፡፡
ሥላሴ  
መጠንከ፡ገበረ፡ሕይወት፡ዘመደ፡መላእክት፡ተሰምዮትከ፡:
ምስለ፡ ጻድቃነ፡ምድርሰ፡ከመ፡ኢትኩን፡ ዘመደ፡፡
ሕርመተ፡መብልዕ፡ረሰየከ፡ ባዕደ፡፡
ውስተ፡ምኔተ፡ገድል፡ይፈጽም፡አኮኑ፡ቀኖና፡ፍጹማን፡ክቡደ፡፡
በበእልፍ፡እልፈ፡አመ፡ሰገደ፡፡
ለመብልዕ፡ምድራዊ፡ዘኢተዋረደ፡፡
ኢረከብነ፡እምጻድቃን፡አሐደ፡
ትርጉም፡- የመላእክት ወገን የሆንክ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሕዝቡ የመላእክት ወገን ነህ የሚልህ ትክክል ነው፡፡ ከምድር ጻድቃን ጋር ዘመድ እንዳትሆን ምግብ መተውህ ከሰው የተለየህ ባዕድ አድርጎሃል:: የተጋድሎን ሥራ በመፈጸም የበቁ ሰዎችን ከባድ ቀኖና ጾም)ተግዳራዊ ያደርጋልና፡፡ በቀን ውስጥ ሺህ ሺህ ጊዜ ስለሚሰግድ ከምድራዊ ምግብ ጋር አልተወሐደም፡፡ እንደ እርሱ ዓይነት ሰውም ከጻድቃን ውስጥ አንድ እንኳ አላገኘንም፡፡
ምሥጢር፡- አንድ ሰው ምግብ በአግባቡ የማይበላ ከሆነ፣ እገሌኮ የማላእክት ወገን ነው ይባላል፡፡ ቅኔው ሰም አልባ ነው፡፡ ገብረ ሕይወት የተባሉት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ የወርቅ ምሳሌ ናቸው፡፡ በብራና መጻሕፍት ላይ የተጻፈው የሕይወት  ታሪካቸው እንዲያስረዳው  አቡየ ከተወለዱበት ዕለት ጀምረው በሕይወት ዘመናቸው ምግብ አልቀመሱም፡፡ ቅኔው በሦስተኛና በሁለተኛ መደብ አተራረክ የቀረበ ሲሆን መንገዱ ወርቃወርቅ ነው፡፡
5. መወድስ፡
ኵሉ፡ይትኃደግ፡እመ፡ኃደግዎ፡ትእምርተ፡ዝኒ፡ነገር፡እምሐልዮ፡መንበር፡ምጡቅ፡፡
እስመ፡ኢያሱ፡ኃደገ፡መንበረ፡ተድላሁ፡ዘወርቅ፡፡
ወተሰምዮተ፡ነግድ፡በበብሔሩ፡ኢያስተዓፀበ፡ያዕቆብ፡ልሒቅ፡፡
በአንጻረ፡አብርሃም፡ወይስሐቅ፡፡
ትሩፋነ፡እሉሰ፡ንሕነ፡ኃለፍተ፡ፍኖት፡እንበለ፡ስንቅ::
ለጽደቅ፡ኢንትሔዘባ፡ወኢትትሔዘበነ፡ጽድቅ፡፡
እስመ፡ጊዜ፡ብዕልነ፡ንትዔበይ፡ወጊዜ፡ንዴትነ፡ንሰርቅ፡፡
ትካዝነሂ፡ካልእ፡እምትካዘ፡ጳውሎስ፡ሊቅ፡፡
ኀበ፡ዘኢየኃልቅ፡መሰለነ፡ንብረተ፡ዓለምዘየኃልቅ፡፡
ትርጉም፡- ሁሉን ነገር ከተውት ይተዋል፡፡ ለዚህም፡ነገር፡ምልክት፡ሊሆን፡ኢያሱ፡የደስታው፡ምንጭ የሆነውንና በወርቅ፡የተንቆጠቆጠውን፡የወርቅ፡ዙፋኑን፡ትቶታልና፡፡ሽማግሌ፡ያዕቆብ፡በየሀገሩ፡እንግዳ፡መባልን፡በአብርሃም፡እና፡በይስሐቅ፡አንጻር፡አላደነቀም፡፡ መንገድን፡ያለ፡ስንቅ፡የምንሄድ፡የዚህ፡ተረፎች፡እኛ፡ግን፡የእውነትን፡ሥራ፡አንጠራጠርም፡፡ ጽድቅም በእኛ፡ አትጠረጠርም፡፡ የሚያልቅየዓለም፡ንብረትም፡የማያልቅን፡ከመሰለን፡ዘንድ፡ኀዘናችን፡ከሊቅ፡ጳውሎስ፡ኀዘን፡የተለየ፡ነው:: የሚያልቀው፤ የሚያልፈው፡የዓለም፡ሀብትና፡ንብረት፡ የማያልቅ፡ የማያልፍ፡ ይመስለናልና፡፡ (1ኛ.ቆሮ፣7.)
ምሥጢር በማቴዎ ወንጌል ምዕራፍ 5 ቁጥር፡10 ላይ ስለጽድቅ የሚሰደዱ ብፁዓን ናቸው:: መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና ተብሎ እንደ ተጻፈው ታላቁ ንጉሥ አድያም ሰገድ ኢያሱ  እድሜው መጨረሻ ላይ በወርቅ የተንቆጠቆጠውን ዙፋኑን ንቆ ወደ ገዳምበ መግባቱን ያመለክታል፡፡ ይህን መወድስ አድማሱ ጀምበሬ (1963ገጽ563) የአለቃ ናሁዳ ዘጎንደር መሆኑን ከአስረዱን በኋላ መልሰው በገጽ 216 (1963) የድንቆ ማርቆስ ቅኔ እንደሆነ ይነግሩናል::
መወድስ፡
ለዘጐየ፡ሰብእ፡እምገጸ፡አንበሳ፡ኮኖ፡ዕፁበ፡ሶበ፡ተኵላ፡ገዳም፡ረከቦ፡፡
ወአመ፡ውስተ፡ቤት፡ቦአ፣ተረክቦተ፡አርዌ፡ዐፀቦ፡፡
ንብረተ፡ዝንቱሰ፡ይመስል፡ንብረተ፡አዳም፡በሲኦል፡እንዘ፡ቦ፡፡
እስከ፡መንገሌከ፡ትቀጽቦ፡፡
ሥሉጠ፡ልደት፡ክርስቶስ፡ወመሥዋዕተ፡አብ፡ዘዲበ፡ፀልቦ፡፡
እምዝኒ፡እሰምየከ፡ምክንያተ፡ኵሉ፡የብቦ፡፡
ዘመድ፡ጽሩየ፡ፍቅር፡እንበሌከ፡እስመ፡አልቦ፡፡
እመኒ፡ትሁቦ፡ዕረፍተ፡ወሀብተ፡መከራ፡ትሁቦ፡፡
ለርእስየ፡እምርእስየ፡አንተ፡ትቀርቦ፡፡
ትርጉም፡ ከአንበሳ ፊት የሸሸ ሰውን የምድር ተኩላ ቢያገኘው ጭንቅ ሆነበት፡፡ ከቤት በገባ ጊዜም ያውሬው መገኘት አስጨነቀው፡፡ የእርሱ መቀመጥ ግን በሲዖል ሳለ የአዳምን መቀመጥ ይመስላል፡፡ ወደ አንተ ትጠቅሰዋለህና፡፡ የመስቀል የአብ መሥዋዕት የሆንህና በመወለድ የሠለጠንህ ክርስቶስ ወደ አንተ ትጠቅሰዋለሀና፡፡ ከዚህም የሁሉ እልልታ ምክንያት እልሃለሁ፡፡ በፍቅር የጠራ ንጹሕ የሆነ ዘመድ ያላንተ የለምና፡፡ ረፍትንም ብትሰጠው የመከራ ሀብትንም ብትሰጠው  ከራሴ  ለራሴ አንተ ትቀርበዋለህ፡፡
ምሥጢር፡-ክርስቶስ፡ከባሕርይ አባቱ ከአብ እና ከመላእክት ሳይለይ ሰው መሆኑን ያመለክታል:: ቅኔው ረቂቅ ነው፡፡ ይህ መወድስ በኅሩይ ወልደ ሥላሴ መጽሐፍ (1918፤ገጽ፡154) ላይም ይገኛል::  የድንቆ ማርቆስ የቅኔ ፍልስፍና መጽሐፋዊ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስና የታሪክ እውቀቱን በረቀቀ መንገድ ከቅኔ ፈጠራ ጋር እያወሐደ  ያሳየናል፡፡ ቅኔው እንዳሁኑ ዘመን  የሰምና ወርቅ ድርሰት ልባችንን የሚመስጥና በቀላሉ እንድንይዘው የሚያደርገን ሳይሆን በበለጠ ተመስጠን እንድንመራመርና የሐሳብ ጥልቀቱን እንድንረዳው፤ የአስተሳሰብ አድማሱን እንድንፈትሸው ያስገድደናል፡፡

Read 2069 times