Print this page
Monday, 23 September 2019 00:00

የበዓል ክብር፣ የኪነጥበብ ውበት፣ የስፖርት ድምቀት፣ ለሰው የሚመጥኑ የፈጠራ ውጤቶች

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

 እውነተኛ የመንፈስ ምግብ በመሆናቸው፣ ይመሳሰላሉ (ክብረ በዓል፣ የስፖርት ውድድርና ኪነጥበብ)፡፡ ገቢ ማግኛ ስራ አይደሉም፡፡ እንዲያውም ገንዘብ እናወጣባቸዋለን፡፡ ልብ ወለድ መጽሐፍ ለማንበብ፣ የእንቁጣጣሽ በዓል ለማክበር፣ የስፖርት ውድድር ለመመልከት፤ እንከፍላለን:: ለምን? የነፍስ ነዳጅ ለመሙላት ቢከፈል አይበዛበትም፡፡  
እውነተኛ “የመንፈሳዊ አንድነት” ምንጭ በመሆናቸውም፣ ይመሳሰላሉ፡፡ በአዲስ ዓመት የበዓል ሰሞን፣ ሚሊዮን ሰዎች “በአንድነት” የተመካከሩ ይመስል፣ እስከ በዓል ዋዜማ፣ ዝግጅቱ እለት በእለት እየደመቀ፣ ከቤት እስከ አደባባይ፣ እንደ መልካም መዓዛ ደስ የሚያሰኝ መንፈስ ሲናኝ፣ ያስደንቃል፡፡
በእርግጥም ደማቅ ኑሮን መመኘት፣ ለሁሉም ሰው ተገቢ ነው፡፡ የክብረ በዓል ትርጉምም እዚህ ላይ ነው፡፡   
ሕይወትን በምልዐት የማጣጣም ቅዱስ ምኞት፣ ትልቅ ክብር ይገባዋል፡፡ እናም፣ የሩቅ ምኞትን ወደዛሬ አቅርበን፣ ገና ያልተሟላውን ምኞት፣ ለበዓል እለት ለአፍታ  አሟልተን በማጣጣም እናከብረዋለን:: የመሠረት ድንጋይ እንደማስቀመጥ፣ የግንባታ ዲዛይኑን በማየት፣ የወደፊቱን ህንፃ በዓይነ ህሊና አይቶ መንፈስን እንደማነቃቃት   ቁጠሩት፡፡
ታዲያ “መልካም ራዕይንና ምኞትን” በሙሉ ልብ፣ በቅንነትና በተግባር ማክበርን የመሰለ “የአንድነት” ምንጭ ከወዴት ይገኛል? ከክብረ በዓል ብቻ ሳይሆን ከኪነጥበብና ከስፖርትም ይገኛል፡፡
ውብ የኪነጥበብ ስራዎች፣ እጅግ ሃያል ከመሆናቸው የተነሳ፣ ዘመንና ድንበር እንኳ አይገድባቸውም፡፡ ቤቲጂ፣ በአስደናቂ አልበሟ፣ ከአገር አልፋ በአፍሪካ መድረክ፣ ቀዳሚ ተሸላሚ መሆኗን መጥቀስ ይቻላል:: ለዚያውም በተደራራቢ ሽልማት፡፡

        ከ2ሺ ዓመታት በፊት በግሪክ አገር የተፃፈ “አንቲገን” ወይም፣ ከእንግሊዝም 400 ዓመት ያስቆጠረ የሼክስፒር “ኦቴሎ”፣ ከ150 ዓመት በፊት በፈረንሳይ ቪክቶር ሂጉ የፃፈው የዣን ቫልዣ ልብወለድ ታሪክ፣ በየትም አገርና ዘመን፣ እዚህ እና ዛሬ ጭምር፣ ድንቅ የመንፈስ ምግብ ናቸው፡፡
ወይም በጣሊያን አገር፣ ሚካልአንጄሎ የዛሬ 500 ዓመታት ግድም የፈጠራቸው David እና Pieta  እና ሌሎች የኪነቅርጽ ድንቅ ስራዎች እንዲሁም ስዕሎቹ፤ ዘመንና ድንበር አልገደባቸውም፡፡
እንደ ኦሎምፒክ ጀግኖች፣ የኪነጥበብ ማማ ላይ የደረሱ ድንቅ የኪነጥበብ ፈጣሪዎች በአገራችንም ታይተዋል፡፡ ወደር የለሽ የመዝገቡ ተሰማ ስዕሎች፣ በትያትርና በግጥም የፀጋዬ ገብረመድህን ስራዎች፣ የሀዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” ልብወለድ ድርሰት ቀዳሚ ናቸው፡፡
የሃይማኖት ተከታይነትም ሆነ የዘር ተወላጅነት የማያግዳቸው “የአንድነት” ምንጮች ናቸው - ውብ የኪነጥበብ ሥራዎች እንደ ኦሎምፒክ ጀግኖች፡፡
ሃይሌንና ቀነኒሳን የምናደንቃቸው፤ በዝምድና አይደለም፡፡ በዝምድና ቢሆን፣ የወንድምና የእህት፣ የአጐትና የአክስት ልጆች ዝርዝር ይቀድም ነበር:: ገንዘቤን የምናደንቃት የጥሩነሽ እህት ስለሆነች አይደለም፡፡ በአለምና በታሪክ፣ በቀዳሚነት በሚመዘገቡ ውጤቶቿ አማካኝነት፣ የላቀ ብቃቷን ያሳየች ጀግና መሆኗ ነው ክብሯ፡፡ ጀግኖችን ማየት ደግሞ መታደል ነው፡፡ ለምን? እንደዘበት አይገኝማ፡፡
የስፖርት ውድድር ሚስጥር!  
አዎ፤ እያንዳንዱ ሰው፣ ድንቅ ብቃትን የመቀዳጀት እምቅ ተፈጥሯዊ አቅም አለው፡፡ አቅም እና ብቃት ግን ይለያል፡፡ የሰው አቅም፣ የተፈጥሮ ፀጋ (given) ነው፡፡ እንደ መወለድ ነው፡፡ ስኬትም ውድቀትም አይደለም፡፡ ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ ነው:: ነገር ግን፣ በጥረት የሚገኝ ስላልሆነ፤ አልያም በስንፍና የሚቀር ስላልሆነ፣ አያኮራም፤ አያሳፍርም፡፡ አያስከብርም፤ አያዋርድም፡፡
የሰው ክብሩ፤ ከተፈጥሯዊ አቅሙ (ከፀጋው) ውስጥ፤ በጥረት ህያው ብቃትን ማፍራቱ ነው:: በአእምሮ፣ በአካልና በመንፈስ ጥረት አማካኝነት ብቻ የሚቀጁት ነው ብቃት፡፡ የሰው ክብሩ ብቻ ሳይሆን፣ የህልውናው ዋና ቁልፍ ነው ብቃት ማለት:: የህልውናው ዋልታና አለኝታ፡፡
ለራሱ እና ለሰው፤ ለሕይወቱና ለሰው ሕይወት ቅንጣት ክብር ያለው ጤናማ ሰው፤ የትም ቢሆን፣ አንዳች የብቃት ብልጭታ ሲያይ፣ በውስጡ መንፈሳዊ ብርሃን ይለኮሳል፡፡ መንፈሱ ይታደሳል፤ ይነቃቃል፡፡ የዚያኑ ያህልም፣ የብቃት ባለቤትን ለማየት ይጓጓል:: በእውን ለማየት ሲታደልም፤ አድናቆቱን ይገልፃል፡፡ ብቃት ፀጋ አይደለምና፡፡ በአጭሩ…
ብቃት ማለት፣ 1ኛ፣ እጅግ ውድና ድንቅ የህልውና አለኝታ ስለሆነ፤ 2ኛም፣ በጥረት ብቻ የሚገኝ ስለሆነ ነው፤ ብቃትን ለማየት የምንጓጓው፡፡ የብቃት ባለቤት ጀግኖችንም እጅግ ልናደንቃቸው የሚገባን፡፡
ታዲያ፣ “የላቀ ብቃትን የማድነቅ ቀና መንፈስ”፣ እጅግ ውብ፣ እጅግ መንፈሳዊ የአንድነት ማዕድ አይደለምን?
እነ ሃይሌን የምናደንቃቸው እኛ ብቻ አይደለንም::
በአለምም፣ በታሪክም፣  ከፍተኛ ብቃትን የተቀዳጁ ጀግኖች ናቸውና፣ እንደ ዩሴን ቦልት፣ እነ ቀነኒሳም፣ ይደነቃሉ፡፡ ከአሜሪካ እስከ ኔዘርላንድ፣ ከጃፓን እስከ ኢንግላንድ፣ በዓለም ዙሪያ ይከበራሉ:: እዚህ አገርም፣  ወደ አውሮፓ በመንፈስ ተሻግረን እነሊዮን ሜሲን የማድነቃችን ሚስጥርም፤ ብቃትን ማክበር፣ እጅግ ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም እንዳለው ይመሰክራል፡፡ ይህን ትልቅ መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያሟላ ተዓምረኛ የሰው ፈጠራ ነው - የስፖርት ውድድር፡፡
• የስፖርት ውድድር እና ክብረ በዓል - እንደ ትያትር
የስፖርት ውድድር እንደ ትያትር፣ “የፈጠራ ዓለም ተውኔት” ነው ማለት ይቻላል፡፡ “በተውኔትነቱም” የስፖርት ውድድር ከሌላ ውድድር ይለያል፡፡ የስራ ቅጥርና የስኮላርሺፕ ውድድር፣ የግዥ እና የግንባታ ኮንትራት ጨረታ፣… እነዚህም ውድድር ናቸው። ለተሳታፊዎች የሚጠቅሙ፤ ለውሃ ለእንጀራ ተብለው የሚደረጉ ውድድሮች ናቸው እንጂ፣ በራሳቸው ግብ ወይም እንጀራ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ ነገር፣ ውድድሮቹ ለተመልካች ብዙም ትርጉም የላቸውም:: የስፖርት ውድድርስ?
የስፖርት ውድድር ራሱ፣ እንደ ትያትር፣ ለተሳታፊዎች (ለተዋናዮች) እንጀራቸው ነው፡፡ ሁለተኛ ነገር፣ ፣ እንደ ትያትር፤ የስፖርት ውድድር፤ ለተመልካቾች ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም ስላለው ከሌላ አይነት ውድድር ይለያል፡፡
• የክብረ በዓል ሚስጥርስ?
የስፖርት ውድድር፣ “የላቀ ብቃትን ለማክበር” የሚያገለግል የሰው ፈጠራ የመሆኑን የህል፤ ክብረ በዓል ደግሞ፤ “የሰመረ ሕይወትን ለመባረክና ለማክበር” የሚያገለግል ድንቅ የሰው ፈጠራ ነው፡፡
አዎ፤ የበዓል እለት “በተፈጥሮው” ወይም በሌጣው፣ ከሌላው ቀን አይለይም። ልዩ የሚሆነው፣ በሰው ፈጠራ አማካኝነት ነው፡፡ በዓል የሰው ፈጠራ ስለሆነ፤ የበዓል ውሎ፣ ከሌላው ቀን ውሎ ይለያል። ኪነጥበብም፣ ከእውኑ ዓለም፣ ይለያል፡፡ በAyn Rand  አባባል፤ በጥበብ የተካነ ሰው፣ በራሱ የነፍስ ሚዛን እየመረጠ፣ በስርዓት እያቀናበረ “የሚፈጥረው” ምሉዕ ምናባዊ ዓለም ነው - ኪነጥበብ።
ልብወለድ ድርሰት፣ የውሎ ዘገባ (ዜና መዋዕል) ወይም የገጠመኞች ማስታወሻ አይደለም። ትያትር፣ አዳራሽ ውስጥ የሚከናወን ትምህርት ወይም ስብከት፣ የውይይት ወይም የጭቅጭቅ ስብሰባ አይደለም። ፊልም እና  የቴሌቪዥን ድራማም፣ የቀትር ወይም የማታ ዜና አይደሉም። ግጥምና ሙዚቃም፣ ከዘወትር ወሬና ንግግር ይለያሉ። በግጥም አናወራም። በዜማ አንነጋገርም። ስዕልና ኪነቅርፅም እንዲሁ።
በእለት ተእለት ወከባ ስንንከወከው፣ በተለመደ የዘወትር የኑሮ ዑደት ስንጠመድ፣  በቅጡ ልናያቸው ያልቻልናቸውን፣ የአስፈላጊነታቸውና የውድነታቸው ያህል፣ በቅርበት ጎልተውና ገዝፈው፣  ጠርተውና ነጥረው፣ ተዛምደውና ተሰናስለው፣ ተቀናብረውና ምልዓትን ተላብሰው ሊታዩን ያልቻሉ፣ ዋናዋና እውነታዎችን፣ ራዕዮችንና ሕያው የሰብዕና ሚስጥራትን የሚያሳዩ የስዕልና የቅርፅ ኪነጥበባት፣…. ከእለት ተእለት ቁሳቁስና ገጠመኝ ይለያሉ።
የክብረ በዓልና የኪነጥበብ ተመሳሳይነት ይሄ ብቻ አይደለም።
በዘፈቀደ አይከሰቱም። በዘፈቀደ ከምድር አይበቅሉም። ከሰማይ አይዘንቡም። ወፍ ዘራሽ ቁጥቋጦ… የኪነቅርፅ ስራ አይደለም። የወፍ ጩኸትም ኪነድምፅ (ሙዚቃ) አይደለም። በአጋጣሚ የተደፋ ቀለምም፣ የኪነስዕል ሥራ አይደለም። ኪነጥበብ፣ ከሰው ጥልቅ አእምሮና ሃሳብ፣ ጥልቅ ምኞትና ራዕይ፣ ጥልቅ ስሜትና ሰብዕና የሚመነጭ፣ ድንቅ የሰው ፈጠራ ነው። ዓመት በዓልም እንዲሁ፣ ድንቅ የሰው ፈጠራ ነው።
• የእንቁጣጣሽ እና የእዮህ አበባ፤ የቃላት ትርጉም
በተለመደው ውሎና የጊዜ ዑደት ከተሰላ፣ የአዲስ ዓመት መባቻ፣ ከሌሎቹ 364 ቀናት በምንም አይለይም። በአራት ዓመት አንዴ፣ ጳጉሜ ውስጥ የምትገባ ተጨማሪ ቀን እንኳ፣ ከሌሎቹ ቀናት ቅንጣት አትለይም፡፡  “ጳጉሜ 6” የሚል ታፔላ የለጠፈች “ልዩ እለት” አናይም።
በማግስቱ፣ ንጋት ላይም፣ ‹‹የእንቁጣጣሽ በዓል›› የሚል ዘውድ በክብር የጫነች፣ እንደ አበባ የደቀመች የበዓል ቀን ከተፍ ስትል ለማየትና “እንኳን መጣሽ” እያልን በአጀብ ለመቀበል ከጠበቅን፣ ቀኑን እያባከንን መባከን ይሆንብናል፡፡
“የእንቁጣጣሽ በዓል ነኝ” እያለች በ“እዮህ አበባዬ” ዜማና በርችት፣ ክብረ በዓልዋን  የምታውጅ የአዲስ ዓመት ቀን፣ በእውን ብትኖር ኖሮማ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ “እንቁጣጣሽ” የሚለው ቃል ምን ማለት እንደሆነ በነገረችን ነበር።
ንጉሥ ሰለሞን፣ ለንግሥተ ሳባ  ስጦታ ሲያበረክትላት፣ “እንቁ - ለጣጣሽ” ብሏታል በማለት ትርጉሙን ለማስረዳት የሚሞክሩ አሉ። ችግሩ ምንድነው? ንግሥቲቱ፣ ጣጣ የሚነካካት አይነት ሴት እንዳልሆነች ነው፤ ትረካዋ የሚነግረን።
በጣም አስተዋይና አዋቂ፣ ጥበበኛና ስኬታማ፣ በጣም ብልህና ሃብታም፣ የብቃቷ ያህልም በባህርይና በመልክ በጣም የላቀችና የተዋበች ንግስት፣…. ምናለፋችሁ፣…. በአእምሮም፣ በኑሮም፣ በሰብዕናም እጅግ የከበረች ጀግና ሴት፣…. “እንቁ - ለጣጣሽ” የሚል ለጋሽ አያስፈልጋትም። ለስፍር ለቁጥር የሚያስቸግር ስጦታ የምታበረክት ጀግና፣…. ስጦታ ከተቀበለችም፣ ከአድናቂዎቿ ብቻ ነው። “እንቁ - ለጣጣሽ” የሚለው የትርጉም መላምት፣ ለንግስቲቱ አይመጥንም።
የመስከረምን ልምላሜ ወይም የአበቦችን ድምቀት ለመግለፅ፣ “ማቆጥቆጥ” እና “መንቆጥቆጥ” ከሚሉ ቃላት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉም አሉ - የእንቁጣጣሽ ትርጉም። በእርግጥም መስከረም፣ ልምላሜ የሚያምርበት፣ አበባ የሚደምቅበት ወር ነው።
“የአበባ ቀን” ተብሎ ይጠራ የነበረ ጥንታዊ በዓል፣ በመስከረም ወር የሚከበር በዓል አይደል? ከቅርብ አመታት ወዲህ፣ የአበባ በዓልን እንደገና በድምቀት ለማክበር እየተሞከረ ነው፡፡ ለነገሩማ ‹‹እዬህ አበባዬ›› የሚለው የአዲስ ዓመት ዜማም፣ እንቁጣጣሽንና የአበቦች መንቆጥቆጥን የሚያዛምድ ዜማ ነው ቢባል አይገርምም፡፡ በእርግጥ፣ እዚህ ላይም ጥያቄ አለ:: ‹‹እዮህ›› የሚለው ቃል፣ በበዓል እለት የሚነገርና የሚደመጥ እንጂ ዘወትር የምንጠቀምበት ቤተኛ ቃል አይደለም፡፡ ትርጉሙም እንዲሁ፡፡ ‹‹እዮህ›› ምን ማለት ይሆን?
የእንቁጣጣሽን ትርጉም በቅጡ ሳንመልስ፣ ሌላ ጥያቄ ጨመርንበት፡፡ ለማንኛውም፤ እንቁጣጣሽ የሚለው ቃል፣ በበዓሉ እለት ከሚዘጋጀው ‹‹እንቁጣ›› የተሰኘ የዳቦ ዓይነት ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ የሚጠቅሱም አሉ፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች አራምባና ቆቦ ግምቶች መኖራቸው አያከራክርም፡፡
ነገር ግን አንድ መላምት ሳልጨምር ባልፍ ታሪክን ማጉደል ይሆናል፡፡
• የእንቁጣጣሽና የእዮህ ትርጉም፣
ኢትዮጵያና ግብጽ
ኢትዮጵያ፤ የጥንታዊ ስልጣኔ አገር እንደመሆኗ፣ በአገራችን የሚነገሩ ቋንቋዎችና ቃላት፣ ከሌሎች የጥንት ስልጣኔዎች ጋር አብረው ይነሳሉ፤ ጥናት እንደሚካሄድባቸውም ይታወቃል - በተለይ ከጥንት የባቢሎን እና የእብራውያን (የቤተ እስራኤል) ቋንቋ ጋር፡፡
ለምሳሌ የቀናት ስያሜ፣ አሀዱ ብሎ ሳምንቱን በእሁድ የሚጀምር መሆኑ፤ ከዚያም  “ሰንበት” ተብሎ ሰባተኛው ቀን መከበሩ፣ በእብራዊያን  ‹‹Sabbath›› መባሉ ይጠቀሳል፡፡ በባቢሎንም እንዲሁ፣ ሰባት ወይም ሰባ… የሚሉ ቃላትን ይጠቀሙ ነበር - 7 ቁጥርን ለመግለጽ፡፡
የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ግን፣ በአብዛኛው ከጥንታዊው የግብጽ ስልጣኔ ጋር ነው እየተዛመደ የሚነሳው፡፡ ህዳር ወይም ጥር ወርን ከጥንት የግብፅ ‹‹ሀቶር›› ወይም ‹‹አጦር›› ጋር ያይዙታል፡፡
እንቁጣጣሽ እና “አክት ጦጥ”፣ እዮህና “IYOH፡፡
እንደ ጥንታዊ ኢትዮጵያ፣ በጥንታዊ ግብፅም፣ የጳጉሜ ማሟያ ቀናት አሉ። የጳጉሜ ማስተካከያ ቀናት ባይጨመሩ ኖሮ፣ በ10 ዓመታት ውስጥ፣ የአመቱ አቆጣጠር በሁለት ወር  ይዛባል፡፡ ገና የሐምሌው ክረምት ሲጀምር፣ “መስከረም ጠባ” የሚያስብል ዓይነት ስህተት ይፈጠራል ማለት ነው - ያለ ጳጉሜ፡፡
“ጳጉሜን በመፍጠር” ይህንን ስህተት ያስተካከለ የሂሳብና የአስትሮኖሚ አዋቂ፣ እጅግ ቢከበር አይገርምም፡፡
የዚህ ክብር ባለቤት፣ በጥንቱ የግብፅ ቋንቋ ‹‹ጦት››› ወይም ‹‹ጦጥ›› ተብሎ ይጠራል፡፡ በግሪክኛ ‹‹Thoth›› ይሉታል፡፡ ዝናው ብዙ ነው፡፡
ጦጥ፣ የእውቀት ጌታ፣ የሂሳብ ባለቤት፣ የጽሑፍ የበላይ ጠባቂ፣ የሕግና ሥርዓት መዝጋቢ እያሉ ያወድሱታል፡፡ “የዓመት ጌታ” ሲሉም ያሞግሱታል፡፡
የጳጉሜ ቀናትማ፣ የራሱ የጦጥ ንብረት፣ የራሱ የጦጥ ፈጠራ የሆኑ ያህል ነው የሚታመኑለት፡፡ በኢትዮጵያኛ እንቁጣጣሽ የምንለው የአዲስ ዓመት በዓል፣ በጥንታዊ ግብጽ፣ በስሙ ተሰይሞለታል - በዓለ ጦጥ ተብሎ፡፡ በያኔው ግብፅኛ “አክት ጦጥ” የሚል ቃል ይጠቀሳል፡፡ የጦጥ ውድ እቃ፣ የጦጥ እንቁ፣ ቤተ ጦጥ፣ ክብረ ጦጥ እንደማለት ነው የመዝገበ ቃላት ትርጉሙ፡፡ እናም፣ “አክት - ጦጥ”፣ ለእንቁጣጣሽ ትርጉም፣ አንድ ተጨማሪ መላምት ለመሆን ምንም አያንሰውም፡፡
የቀን አቆጣጠር ጌታ ተብሎ የሚከበር እንደመሆኑ መጠን፣ ጦጥ፣ ‹‹የጨረቃ ጌታ››፣  በግብፅኛ የ‹‹Iyoh›› (የ‹‹እዮህ››) ጌታ ነው ይሉታል:: ብዙ ጊዜ ደግሞ፣ ‹‹እዮህ›› ብለው ይጠሩታል - እራሱ ‹‹ጨረቃ›› እንደሆነ በማመን ማለት ነው፡፡ እንደ ጨረቃ ‹‹አበባ›› የሚል ስያሜም ይጠቀማሉ። ‹‹እዮህ አበባዬ›› ለሚለው ዜማ፣ እንደ መላምት ይህንን ብንጨምረውስ?
• ክብረ በዓል - የሩቁን ምኞትና አላማ፣ ወደ ዛሬ አቅርቦ ማጣጣም ነው
ተመራማሪዎች፣ ለእንቁጣጣሽ እና ለእዮህ መነሻ ትርጉም፣ በጥናት ጥንቅቅ ያለ ምላሽ እስኪያገኙና እስኪገልጡልን ደረስ፣ መላምት ብቻ ይዘን መቆየት የግድ ነው፡። ምክንያቱም፤ የአዲስ አመት የመባቻ ቀን፣ ‹‹በራሱ ጊዜ›› … ‹‹እኔ እንቁጣጣሽ እባላለሁ፤ ትርጉሙና መነሻውም…›› ብሎ ራሱን የሚያስታውቅና ታሪኩን ከመነሻው የሚተርክ ቀን አይደለም፡፡ ለምን? የዓመት ክብረ በዓል፣ … ተፈጥሮንና የጊዜ ዑደትን ከማስተዋል የመነጨ፣ ድንቅ የሰው ፈጠራ ነው፡፡ ክብር ይግባቸው - ለጥበበኞቹ አዋቂ ፈጣሪዎች፡፡
ቀንና ማታ፣ ክረምትና በጋ፣…. በቀላሉ የምንገነዘባቸው የተፈጥሮ ክስቶች ናቸው - ግኝት እንጂ ፈጠራ አይደሉም፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ 360 ቀናት ገደማ መኖራቸውም፣ የሰው ፈጠራ አይደለም - ላቅ ባለ የአስተዋይነት ጥረት የሚደረስበት ግኝት ነው።
‹‹ገደማ›› ከማለት ባሻገር፣ (አራት ዓመት ከ1460 ቀናት እንደሚበልጥ ማወቅ ከዚያም አልፎ 1461  ቀናት እንደሆነ መገንዘብ፣) እጅግ የላቀ የአስተዋይነትና የእውቀት ብቃትን የሚጠይቅ፣ ‹‹ተዓምረኛ›› ግኝት ነው፡፡ ተፈጥሮን የመገንዘብ ድንቅ ውጤት!  
ይሄ የትናንት ፍሬ፣ ለዛሬ የሚጠቅም በረከት ነው፡፡ በተጨማሪ፣ ነገና ከነገወዲያ፣ እጅግ ወደላቀ ብቃትና ስኬት እንድንገሰግስ የሚያነሳሳ፣ የመንፈስ ማነቃቂያ ነዳጅ ጭምር ነው፡፡
በእርግጥ፣ የነገን ከፍታ አልሞ፣ ከዓመት ከአስር ዓመት በኋላ ለሚሳካ “ሩቅ አላማ”፣ በየቀኑ በርትቶ በጽናት መትጋት ቀላል አይደለም፡፡ የትናንት ውጤትን መጠቀም ይቀልላል፡፡ የአስር ዓመት ራዕይ ይቅርና፣ አመት ሙሉ የሚፈጅ አላማም፣ እጅግ ሩቅ ሆኖ፣ ውጤቱ አንሶ፣ ስራው ግን ከብዶ ሊታየን ይችላል፡፡
በየእለቱ በሚገጥመን እንቅፋት ሳቢያም፣ ደማቁ ራዕይ ይደበዝዝብናል፡፡ በእለት ተእለት ውክቢያ ብቻ እየተጠመድን፣ የሩቅ አላማችንና ምኞታችን የማይጨበጥ ጉም ይሆንብናል፡፡ መንፈሳችን በየአቅጣጫው እየተበታተነ ይባክንብናል፡፡ ፈተና ነው፡፡
“ደግነቱ”፣ የሰው ድንቅ ተፈጥሮ፣ ለዚህ ፈተና ሁነኛ መፍትሔዎችን የመፍጠር አቅም አለው፡፡
ክብረ በዓል፣ የሩቅ አላማና ምኞትን፣ ወደ ዛሬ አቅርቦ ለአፍታ እንድናጣጥመውና መንፈሳችን እንዲነቃቃ የሚያገለግል ውድ ፈጠራ ነው፡፡ “የላቀ ብቃትን” ለማሳየት ታስበው፣ በጥበብ የተፈጠሩ፣ ምርጥ የስፖርት ውድድሮችንም መመልከት ትችላላችሁ፡፡
በተቃራኒው “ብዝሃነትና አካታች” ወይም (Diversity, Inclusive) በሚል ፈሊጥ፣ ማንኛውም ሰው በእጣ ወደ ኦሎምፒክ ውድድር የሚገባ ቢሆን አስቡት፡፡ ማንኛውም ሰው፣ በወረፋና በየተራ ተጫዋች ሆኖ የሚገባበት የፕሪሚዬር ሊግ ውድድርንም ማሰብ ትችላላችሁ፡፡

Read 8693 times