Tuesday, 01 October 2019 09:54

በቁጥጥር ስር የዋሉት አሸባሪዎች ማንነት ይፋ ተደረገ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(2 votes)

 ህዝብ የሚሰበስብባቸው በዓላት የአሸባሪዎቹ ኢላማዎች ነበሩ ተብሏል
                    
           የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት በመፈፀም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ በዝግጅት ላይ እያሉ በቁጥጥር ስር አዋልኳቸው ያለውን አሸባሪዎች ማንነት ይፋ አደረገ፡፡ አሸባሪዎቹ ህዝብ የሚሰበስብባቸውን ሃይማኖታዊ በዓላት ለጥቃቱ ኢላማ አድርገው ነበር ተብሏል፡፡
የጽንፈኛው ኢስላማዊ አሸባሪ ቡድን አይ ኤስ አይ ኤስና የአልሸባብ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉት እነዚሁ አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ አበባ፣ እና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የኢትዮጵያ፣ የሱማሊያ የየመን እና የሶሪያ ዜግነት ያላቸው ሲሆን ሁሉም አማርኛ ቋንቋን በደንብ ተምረው የተላኩ መሆኑን ደርሼበታለሁ ብሏል ኤጀንሲው፡፡
አሸባሪዎች በአገሪቱ ለሚፈፀሙት የሽብር ተግባር በዝግጅት ላይ የነበሩ ሲሆን፤ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ የሚሰበስብባቸውን ቦታዎች፣ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት የሚከናወንባቸውን አካባቢዎች፣ ሆቴሎች፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና የመንግስት ተቋማትን የመለየትና የፎቶግራፍ መረጃዎችን የማሰባሰብ ተግባር ላይ እንደነበሩ ተደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
ከአሸባሪ ቡድን አባላቱ መካከልም የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን አባል የሆነውና ጥቃት ለመፈፀም በጅቡቲ በኩል ወደ አዲስ አበባ እንደገባ የተነገረው የሽብር ቡድኑ መሪ ነው መሐመድ አብዱላሂ በቅጽል ስሙ ዱለት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቦሌ አካባቢ መያዙን ኤጀንሲው ገልጿል፡፡
ኤጀንሲው ሌሎች አሸባሪዎችን ቦባሶሳ እና ሱማሌላንድ ሃርጌሳ በኩል ወደ አዲስ አበባ በመግባት የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸውም ይፋ አድርጓል፡፡ ከአሸባሪ ቡድን አባላቱ በተጨማሪ ለሽብር ተግባሩ የሚጠቀሙባቸውን የተለያዩ የግንኙነት መሣሪያዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችንም በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል፡፡
ከደቡባዊ ሱማሊያ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ ለመጓዝ በዝግጅት ላይ ነበሩ የተባሉት ይስአቅ አሊ አደም እና አደም መሐመድ ሱማሌ ላንድ ውስጥ ተይዘዋል፡፡ ይሳቅ አሊ አደም ከሱማሌ ክልል ቦሀ ወረዳ ጨርቃን ቀበሌ የተሰጠ የነዋሪነት መታወቂያ ይዞ የተገኘ ሲሆን፤ አደም መሐመድ መሐመድ የተባለው ተጠርጣሪ ደግሞ በስሙ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2.5 ሚሊዮን ብር ተቀማጭ ተገኝቶበታል ተብሏል፡፡
ኤጀንሲው ተጠርጣሪ አሸባሪዎቹን በሱማሌ ክልል ጨርጨር ዞን አራርሶ ወረዳ፣ በአፍዴራ ዞን ምዕራብ ኢሚ ወረዳና ፈቄ አካባቢ እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደዋላቸው ተናግሯል፡፡
በዚሁ ተጠርጣሪ የሽብር ቡድን አባላቱን በቁጥጥር ስር የማዋል ኦፕሬሽን የአሜሪካ የጣሊያን፣ የፈረንሳይ፣ የስፔን፣ የጅቡቲ የሱማሌ ላንድና የፑንትላንድ የመረጃ ተቋማት እገዛ ያደረጉለት መሆኑን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ በመግለጫው ይፋ አድርጓል፡፡
ጽንፈኛው ኢስላማዊ አሸባሪ ቡድን አይ ኤስ አይ ኤስ በአማርኛ ቋንቋ የተፃፉ መልዕክቶችን በቴሌግራም ማስተላለፍ እንሚጀምሩ ማስታወቂያ ማሰራጨታቸው ይታወሳል፡፡  

Read 1473 times