Tuesday, 01 October 2019 09:57

ወደ ቀያቸው ለተመለሱ ተፈናቃዮች አለማቀፉ ሕብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀረበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍና ድንገተኛ አደጋዎች አስተባባሪ ጽ/ቤት፤ በግጭት ምክንያት ተፈናቅለው ለነበሩና ወደ ቀዬአቸው ለተመለሱ ኢትዮጵያውያን አለማቀፉ ሕብረተሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረበ፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ የግጭት ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን ቦታዎች የጎበኙት የጽ/ቤቱ ሃላፊ ማርክ ሎውስክ፤ “ወደቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮችን ማቋቋም የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ጉዳይ አይደለም፣ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ከመፈጠሩ በፊት አለማቀፉ ሕብረተሰብ የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ አለበት” ብለዋል፡፡
የጽ/ቤቱ ኃላፊ እንደገለፁት፤ ወደ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮች በክረምቱ ወራት የግብርና ሥራ ባለማከናወናቸው ቀጣዩን አመት ሙሉ እርዳታ ጠባቂ ሆነው ይቆያሉ፡፡
3 ሚሊዮን ከሚጠጉት ተፈናቃዮች በተጨማሪም አገሪቱ 8.5 ሚሊዮን ዜጎቿ በቀጣዩ ዓመት ሙሉ የምግብ፣ መጠለያ፣ ሕክምና፣ አልባሳት እርዳታ ፈላጊ ናቸው ብሏል - ጽ/ቤቱ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ቀውሶችን እየተጋፈጠች ትገኛለች›› ያሉት የጽ/ቤቱ ኃላፊ፤ ከእነዚህም መካከል ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የበሽታ መስፋፋትና የብሄር ግጭቶችን በመጥቀስ  የኢትዮጵያ መንግሥት እየተጋፈጣቸው ያሉትን እነዚህን ተግዳሮቶች አለማቀፉ ማህበረሰብ ተረድቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

Read 900 times