Tuesday, 01 October 2019 10:00

የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ወላጆቻቸውና ዩኒቨርስቲው የኃላፊነት ውል ይፈርማሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በዘንድሮ አመት ወደ ከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው የዩኒቨርስቲ ግቢ ደህንነት አጠባበቅ ኃላፊነት መውሰጃ ውል እንደሚፈርሙ የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ ያሠራጨው የተማሪዎችና የግቢ ደህንነት አጠባበቅ ስርአት ኃላፊነት መውሰጃ ውሉ ዋነኛ አላማው የተማሪዎችና የተቋማቱን ሠላምና ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ተማሪዎች ግዴታቸውን እንዲወጡና መብታቸው እንዲጠበቅ ዩኒቨርስቲው፣ ተማሪዎች፣ ወላጆች እና የተማሩበት ወረዳ ት/ፅ/ቤት ኃላፊነት እንዲወስዱ የሚያስገድድ ውል ነው የተዘጋጀው ተብሏል፡፡
ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች ኃላፊነታቸው ሳይወጡ በዩኒቨርስቲ ውስጥ ለሚያደርሱት ችግርም ሆነ ጥፋት ራሳቸው ወይም ወላጆቻቸው (አሳዳጊዎች) ኃላፊነት መውሰድን ውሉ ያስገድዳል፡፡
በዚህ የውል ፎርም ላይ ተማሪዎች የሚገቡት የውል ግዴታ “በተመደብኩበት ተቋም በሠላማዊ መንገድ ትምህርቴን ለመማርና ከሌሎች የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ጋር በጋራና በአንድነት ተግባብቼ ለመኖር፣ በዩኒቨርስቲው ሃብትና ንብረት ላይ ችግር እንዳይፈጠር በምችለው ሁሉ የበኩሌን ለመወጣት፣ ችግሮች ሲከሰቱ ለሚመለከተው አካል መረጃ ለመስጠትና የራሴንና የግቢውን ደህንነት ለመጠበቅ ቃል እየገባሁ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙ ለሚመለከተው አካል በበሰለ አግባብ በማቅረብ መፍትሔ የምሰጥ፣ በምንም ሁከትና አመጽ የማልሳተፍ መሆኑ ሳረጋግጥ፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ለሚፈጠረው ችግር ህጋዊ እርምጃ ዩኒቨርስቲው ሊወስድ የሚችል መሆኑን በመረዳት ለሚጠፋው ሁሉ በኃላፊነት የምጠየቅ መሆኔን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ” ይላል፡፡
ወላጆች ወይም አሳዳጊዎች እንዲሞሉት የተዘጋጀው ውል ደግሞ “ልጄ በዩኒቨርስቲ ቆይታው መልካም ስብዕና ኖሮት ህግና ደንብን በማክበር እንዲማር በዩኒቨርስቲ ውስጥ በማንኛውም መነሻ በሚፈጠሩ ግጭቶችና ጥፋቶች በግልም ይሁን በቡድን እንዳይሳተፍ፣ ተባባሪም እንዳይሆንና በዩኒቨርስቲው የተማሪዎች የዲሲፒሊን መመሪያም ሆነ በሌሎች አካዳሚያዊና አስተዳደራዊ ህጐችና ደንቦች ተገዥ እንዲሆን የመከርኩ ሲሆን፤ ነገር ግን ከዚህ በመውጣት ልጄ በጥፋቶች ተሳታፊና ተባባሪ በመሆን ለሚያደርሰው ጥፋትና ጉዳት ለሚወሰድበት እርምጃ በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ያስገነዘብኩ መሆኑን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ” ይላል፡፡
ይህ የውል ግዴታ ተማሪው የሚገኝበት የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤትም የሚገባ ሲሆን፤ ተማሪውን ስለ መልካም ስነ ምግባር፣ በዩኒቨርስቲ ስለሚኖረው ኃላፊነትና ዲስፒሊን ማስገንዘቢያ ስልጠና መስጠቱን አረጋግጦ፣ በግጭቶችና ጥፋቶች ተሣታፊ ወይም ተባባሪ እንዳይሆን ተማሪውን ማሰልጠኑን፣ ይህን ችግር ከፈጠረም ወላጆቹ/አሳዳጊዎቹና እሱ ተጠያቂ መሆኑን ማስገንዘቡን በማመልከት ውሉን ይፈርማል፡፡
ዩኒቨርስቲው በበኩሉ፤ የተማሪውን ደህንነትና ሠላም ለመጠበቅ እንዲሁም ተማሪዎችን ያለ አድልኦ ለማገልገል በውሉ ግዴታ እንደሚገባ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ተማሪዎች ወደየተመደቡበት ዩኒቨርስቲ ሲጓዙ በእነሱ፣ በወላጆቻቸውና በወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት የተፈረመውን የውል ቅጂ ይዘው መቅረብም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡

Read 1370 times