Print this page
Tuesday, 01 October 2019 10:11

በፀረ ሽብር አዋጁ ክስ እንዳይመሰረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

በ2011 ዓ.ም በወጣውና በርካታ ውግዘትና ተቃውሞ በገጠመው የፀረ ሽብር ሕግ ክሶች እንዳይመሰረቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጠየቀ፡፡
የፀረ ሽብር ሕጉን መልሶ የመጠቀም አካሄድ እየታየ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፁት የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ ከሰኔ 15ቱ የባለሥልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አካላት ላይ በፀረ ሽብር ሕጉ መሰረት የምርመራ ጊዜ መጠየቁም አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ፖሊስና አቃቤ ሕግ ለምርመራ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቂያነት የፀረ ሽብር ሕጉን መጠቀማቸው አሳሳቢ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በዚህ ሕግ ክስ የሚመሰረት ከሆነም ትክክል አይደለም፤ አዲስ ከተከፈተው የፖለቲካ ምዕራፍና ከተነደፈው የኢትዮጵያ ራዕይ ጋር ፈጽሞ አብሮ የማይሄድ ነው ሲሉ ተቃውመዋል፡፡
ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ ከታሰሩት ውስጥ ጋዜጠኞችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መኖራቸውም ኮሚሽኑን ያሳስበዋል ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ የተፈፀመ ወንጀል ካለም በመደበኛው የወንጀል ሕግና ሥርዓት መሰረት መታየት ይችላል ሲሉ፣ በፀረ ሽብር ሕጉ የተካተቱ ድንጋጌዎች በመደበኛ የወንጀል ሕጉ ሊሸፈኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
የተወገዘውንና የተነቀፈውን የፀረ ሽብር ሕግ መልሶ መጠቀም መጀመሩ አዲስ ከተከፈተው የፖለቲካ ምዕራፍ ጋር አብሮ የማይሄድ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡
በእስረኞች አያያዝ ረገድ ግን መሻሻል መኖሩን፣ እንደ ከዚህ ቀደም በምርመራ ወቅት የማሰቃየት ተግባር እየተፈጸመ አለመሆኑን መገንዘባቸውንና እንዲህ ያለ ድርጊት ተፈጽሞ ከሆነም ሕብረተሰቡ ጥቆማ እንዲያቀርብ ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል፡፡  

Read 6501 times