Tuesday, 01 October 2019 11:00

ኢንዶኔዢያውያን ከትዳር በፊት ወሲብ የሚከለክለውን ህግ ተቃወሙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


               የኢንዶኔዢያ ፓርላማ ከትዳር በፊት ወሲባዊ ግንኙነት ባደረጉና የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ባዋረዱ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ቅጣት በሚያስጥለው አዲስ ረቂቅ ህግ ላይ ውይይት መጀመሩን ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢንዶኔዢያውያን አደባባይ ወጥተው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
ትዳር ሳይመሰርቱ ወሲባዊ ግንኙነት ሲያደርጉ የተገኙ የአገሪቱ ዜጎችን በአንድ አመት እስራት ያስቀጣል በተባለው ረቂቅ ህግ ላይ ባለፈው ማክሰኞ ውይይት ያደረገው ፓርላማው ምንም እንኳን በዕለቱ ረቂቅ ህጉን ሳያጸድቀው ቢቀርም በርካታ ቁጥር ያላቸው የአገሪቱ ዜጎች ግን  በፓርላማው ደጃፍ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አዲሱ ህግ ከዚህ በተጨማሪም ትዳር ሳይመሰርቱ አብረው የሚኖሩ ጥንዶችን በስድስት ወራት እስር፤ የጤና ችግር ወይም አስገድዶ መድፈር ካላጋጠመ በስተቀር የጽንስ ማቋረጥ የፈጸመን ደግሞ አራት አመት በሚደርስ እስር እንደሚያስቀጣ የጠቆመው ዘገባው፣ የአገሪቱን ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የመንግስት ተቋማትን፣ ሃይማኖትን፣ ሰንደቅ አላማንና ብሄራዊ መዝሙርን አለማክበርና ማዋረድም ህገወጥ ተግባር እንደሆነ የሚያትት ነው ብሏል፡፡
ፓርላማው ረቂቅ ህጉን የሚያጸድቅበትን ቀን ቢያራዝምም ኢንዶኔዢያኑ ግን መጽደቁ አይቀርም በሚል በመዲናዋ ጃካርታ አደባባይ ወጥተው ከፖሊስ ጋር እየተጋጩ መሆናቸውንና ተቃውሞው ወደሌሎች ከተሞች መስፋፋቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 1941 times