Print this page
Tuesday, 01 October 2019 11:02

አርአያነት!

Written by  አብይ ተስፋዬ አሳልፍ/አተአ/
Rate this item
(0 votes)

የቀኑ ጸሃይ እጅግ ከመጠንከሩ የተነሳ ውጪ መውጣትና መጓዝ እንዳለብኝ ተረድቼ ቀለል ያለች ነጭ ቲሸርቴን ብቻ አደረግሁ፡፡ በመቀጠል ከዙሪያዬ እንደ ቬሎ የሚከበኝ ኮፍያ ጭንቅላቴ ላይ ከደፋሁ በኋላ ወደ እሳቱ ገባሁ፡፡ ጎዳናው ጭር ያለ ቢመስልም የተወሰኑ ሰዎች በመንገዱ ላይ አይጠፉም፡፡ ሁለት ኩርባዎችን ከታጠፍኩ በኋላ ደግሞ ዋናው መንገድ ላይ ወጣሁ:: ገና ከዚሁ ከናቴራዬ ከገላዬ ላይ መጣበቅ፣ በማጅራቴ ላይ ላቤ መንዠቅዠቅ ጀመረ፡፡
ሩቅ መጓዝ አለብኝና የምሳዬን ነገር አሰብኩት፡፡ አሁን ከቀኑ ስምንት ከሩብ ነው:: ቁርስ አንድ ብርጭቆ ጭማቂ የቀመስኩ ስለሆነ ረሃብ ሞረሞረኝ፡፡ አልሪጋ ነኝ፡፡ ኬኤፍሲ አካባቢ ከሚገኘው ደንበኛዬ ቤት ሄድኩ፡፡ አልጣሂር ሬስቶራንት (የአፍጋኖች ምግብ ቤት!) እንደገባሁ ሽማግሌው አፍጋናዊ አስተናጋጅ ከአንዱ ጥግ ላይ ያንጎላጃሉ፡፡ እጃቸው ላይ ደግሞ አንድ መጽሃፍ ተንጠልጥሎ ይታየኛል::  ባለፈው ተዋውቀን ስለነበር በመጣሁ ቁጥር ጥቂት ያወሩኛል፡፡ ጓደኛ ሆነናል፡፡ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ተስፈንጥረው መጡ፡፡ ሰፊ ቀሚስ መሳይ ግልድም አድርገዋል፡፡
‹‹አሎ አሎ … ሃበሻ!›› ፈገግታቸው ሳይሆን እንደ አያቴ ውድማ አጥር የወላለቁ ጥርሶቻቸው ይታዩኛል፡፡
‹‹አሰላም አለይኩም…›› አልኳቸው፡፡ (እንደዚህ ስንሞክር ደስ ይላቸዋል ሁሉም…)
‹‹ዋአለይኩም አሰላም…››
ወንበር ስበው አስቀመጡኝ፡፡ ልከ እንደልጃቸው ያስተናግዱኛል፡፡ ግንባሬን በሻካራ እጆቻቸው ከዳበሱ በኋላ መዳፋቸውን ሳሙ:: በምንግባባበት እንግሊዝኛ ያወሩኝ ጀመር፡፡ በመቀጠል ከተለመደው አዲስ ነገር እንድቀምስ ከመከሩኝ በኋላ ወደ ምግብ ማዘጋጃው ዞር ብለው ‹‹ለልጄ የሚሆን … መቶን ቲቃ ቃዲ … በጥሩ የተዘጋጀ..›› ብለው አዘዙ፡፡ (ምን አይነት ምግብ እንደሆነ ምን አውቃለሁ!)
‹‹ምን እያነበቡ ነው!›› አልኩ ከግንባሬ ላይ የተንቸራፈፈውን ላብ በጽዳት ወረቀት እየተመተምኩ፡፡ (ባለፈው አንድ መጽሃፍ አውሰውኝ ያነበብኩ ሲሆን እኔም በተራዬ አንድ መጽሃፍ በስጦታ መልክ አበርክቼላቸው ወደውታል፡፡ እንዳጫወቱኝ ሰውየው አገራቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሂሳብ አስተማሪ ነበሩ፡፡ ድሮ፡፡ በስደት እዚህ ከመምጣታቸው በፊት፡፡)
ወደ መጽሃፉ እየጠቆሙ፣ ‹‹ይህ ሰውዬ (ደራሲውን ማለታቸው ነው) ምን ይላል መሰለህ፡፡ ‹ስትሞት በባዶ ሙት!›› ይላል፡፡›› ፈገግታቸው ፊታቸው ላይ ይፈስሳል፡፡
‹‹ስሞትማ ምን ይኖረኛል ብለው ነው…›› አልኩ እየፈገግሁ፡፡
‹‹አይደለም አይደለም … ልትሰራ ያሰብከውን ሁሉ ዛሬ ከውነህ እደር፣ ለነገ አታሳድር ነው ነገሩኮ፡፡ ደግሞ እንዲህ ሲል ይጠይቃል! … በአለም ላይ ካሉ ስፍራዎች ሁሉ የከበረው ምድር የቱ ይመስልሃል!?…›› ጥያቄው ለእኔም ነበር፡፡
ጥቂት አሰብኩና ‹‹ምናልባት በወርቅና በእንቁ የከበረው አፍሪካ ወይም በነዳጅ ዘይት የከበረው ይሔ የአረብ ምድር ይሆናል፡፡ ›› ስል መለስኩ፡፡
በእርጋታ ተነስተው የታዘዘውን ምሳዬን እያቀረቡልኝ በፈገግታ … ‹‹አየህ ብዙ ሰውም እንዲሁ ነው የሚገምተው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ይላል ‹‹የከበረው ምድር የመቃብር ስፍራ ነው፡፡ የመቃብር ስፍራ ውስጥ የተቀበረው ስንት ያልተጻፈ ልብወለድ፤ ያልተዘገበ ታሪክ፣ ያልተወለደ መልካም ሃሳብ፣ እጹብ ድንቅ ነገር ተግባር፤ ይቅር ያላለ ልብ፣ ጽድቅ ሊሰራ ያሰበ መንፈስ፣ አለምን ሊለውጥ የሚችል ሃሳብ …. ይህ ሁሉ እጡብ ድንቅ ሃብት የተቀበረበት ስፍራ ነው በዓለም ላይ የከበረ ምድረ የሚባለው … ሲል ያትታል፡፡›› በአዎንታ ራሴን አወዛወዝኩ:: አጎንብሼ ምሳዬን እየዘመዘምኩ ማዳመጤን ቀጠልኩ፡፡
‹‹እኔ የተማርኩት ነገር ነገሩን ሁሉ ለነገ አለማለትን ብቻ ሳይሆን መልካም ነገሮችን ሁሉ መስራት በህይወትህ ምን ያህል ሊጠቅምህ እንደሚችል ነው፡፡ አባቶች የሚፈፅሙት ተግባር ለልጅ ብቻ ሳይሆን ለትውልድ መቀጠል ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ በውሀ ላይ እንደምትነሳ ትንሽ ማዕበል እስከ ትውልድ ዳር ትደርሳለች:: ምሳ እስክትጨርስ ታሪክ ላጫውትህ ይሆን?›› ጉንጬ ውስጥ እየቀለጠ ያለ ጣፋጭ ምግብ እያጣጣምኩ በአዎንታ ራሴን አነቃነቅሁ:: መቼስ መርፈዱ አይቀርም፡፡ ለጸሃዩም የሚያስቸኩል ነገር የለም፡፡ ቆየት ብዬ ወጥቼ እጣድበታለሁ:: የተጨማደደ ፊታቸውን እያፍታቱ መተረክ ያዙ፡፡
***
ተረክ አንድ
አል ካፖኒን ታውቀዋለህ! መቼም ሰምተሃል ቺካጎን ያንቀጠቀጠ ወመኔ ነበር፡፡ ሁሉንም አይነት ወንጀል የሚሰራ ጋንግ (ማፍያ) መሪ ነው፡፡ የሚገርምህ ሃኪሞች በጉልምስና ዕድሜው የአስራሁለት ዓመት ልጅ አስተሳሰብ እንደነበረው አረጋግጠዋል፡፡ የወሲብ ንግድ፣ ድራግ፣ መሳሪያ፣ ግድያ  … የፈለግኸውን ወንጀል ጥራ ባለቤቱ እርሱ ነበር፡፡
ታዲያ ይህንን ሁሉ እየሰራ ለምን እንደማይታሰር ታውቃለህ? እሳት የላሰ ጠበቃ ነበረው፡፡ ‹ኢዚ ኤዲ!› ሲሉ ይጠሩት ነበር፡፡ ህጉን ከ ሀ እስከ ፐ ከእነ ቀዳዳው ጠንቅቆ የበላ ስለነበር እንደፈለገ ያሾረዋል፡፡ እናም ካፖኒ ያለ ምንም ችግር ይፈነጭ ነበር፡፡ ለዚህም ደግሞ ኢዲ ጠቀም ያለ ክፍያ ይከፈለዋል፡፡ ምርጥ ሃብት አፍርቷል፡፡ ከቺካጎ አብዛኛውን ክፍል ያክል ሃብት አፍርቷል፡፡ ሆኖም የኤዲ ስስ ብልት ደግሞ ምን መሰለህ? የሚወደው ልጁ ነው፡፡ በምንም ዓይነት አሰቃቂ ወንጀል ውስጥ ይሳተፍ እንጂ እጅግ ልጁን ይወድ ነበር፡፡ ስለዚህ ለልጁ ጥሩ ጥሩውን እያስተማረ ለማለፍና ምርጥ አባት ሆኖ ለማለፍ ይሞክራል፡፡
ከእለታት አንድ ዕለት ግን ይወስናል:: ያጎደፈውን ስሙን አስተካክሎ በማለፍ ለልጁ ምሳሌ ለመሆን፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ያው ከፖሊሶች ጋር ቀርቦ መመስከርንም ይጨምራል፣ ያ ደግሞ በራስ ላይ የሞት ፍርድ መፍረድ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ኤዲ ያንን ነው ያደረገው፡፡ መሰከረና ካፖኒን ወደ ወህኒ ሰደደው፡፡
የሚያሳዝነው (ያው የሚፈራው ቢሆንም) ይህ በተካሄደ በትንሽ ጊዜ በቺካጎ ጎዳና ላይ በዘነነበት የጥይት ናዳ ተገደለ፡፡ ፖሊስ ከኪሱ ውስጥ ያገኘው ከጋዜጣ ቆርጦ የያዘውን የግጥም ስንኝ ነበር፡፡
የህይወት ሰከንድ ችሮታ የህይወት ሰዓት
ቆጣሪ
የሚመዘነው አንዴ ነው የሚሰጠን
ያለጭማሪ፤
ዘና ብለህ ስትኖር ነገ አለኝ ብለህ ስትገምት
ጥሩ ነው ብልህ ስታስብ የሚቆም ነው
በድንገት፤
ወይ በጣም ዘግይቶ ወይ ደግሞ በጣም
ማልዶ
በፈቃድ ነው ብንልም ሊቆም ይችላል ተገዶ::
የመጨረሻውን ስንኝ እየሰማሁ ሰሃኑን እየጠራረግሁ ነበር፡፡ ታሪኩ ሲያልቅ እውነትም አልታወቀኝም፡፡ የሚያቃጥል ነገር ስለነበረበት የላብ ምንጬ ጎልብቶ ይንፎለፎላል፡፡
‹‹ምግቡን ወደድከው?›› አሉኝ ሰሃኑን እያነሱ:: ሰሃኑን ጥርግ አድርጌው ነበር፡፡ በአዎንታ ራሴን ነቀነቅሁ፡፡ ‹‹ ታሪኩንም ወድጄዋለሁ!…››
‹‹ቆይማ ሌላ አጭር ነገር ልጨምርልህ:: እስከዚያው ሻሂ ይምጣልህ፡፡ ለሙቀቱ ያግዝሃል፣ የሚያቃጥለውንም ይቀንስልሃል፡፡›› ትኩስና በቅመም ያበደ ሻይ ከፊቴ ሲያስቀምጡልኝ፣ ሽታው አያቴ የምታፈላውን ሻይ ስላስታወሰኝ ሆዴን ባር ባር አለኝ፡፡ አንድ ግዜ በትንሹ ቀመስኩለትና ሃሳቤን ወደ ሽማግሌው መለስኩ:: ከፊቴ ቁጭ ብለው መተረክ ቀጠሉ፡፡
***
ተረክ ሁለት
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ነበር፡፡ በዚያ ወቅት ከነበሩት ጀግኖች አንዱ ኦሃሬ ነበር፡፡ በደቡብ ፓስፊክ ላይ ከነበሩት ጀት አብራሪዎች ውስጥ ነው፡፡ አንድ ቀን ወደ ግዳጅ እየበረሩ እያለ የእርሱ ነዳጅ ልክ አለመሆኑን አስተዋለ:: የሆነ ሰው የእርሱን ጀት ነዳጅ ሳይሞላለት ዘንግቶት ነበር፡፡
ግዳጁን የሚያስጨርሰው ነዳጅ እንደሌለው ሪፖርት ሲያደርግ እንዲመለስ ታዘዘ፡፡ ወደ መነሻው መርከብ የመልስ በረራ እያደረገ እያለ ደግሞ የጃፓን የጦር ጀቶች ወደ መርከባቸው እየመጡ አንደሆነ አስተዋለ፡፡ ሁሉም ጀቶቻቸው ተነስተው ስለነበር የሚመክት አንድም አልነበረም፡፡ ተመልሰውም ሊያድኗት እንደማይችሉ ያውቃል፡፡ እናም ቀጥታ ከጠላት ጀቶች ሰልፍ መሃል ገብቶ ያተራምሳቸው ገባ፡፡  ያለውን የጥይት ስንቅ እስከሚጨርስም ድንገቴ ያወርድባቸው ያዘ፡፡
በድንገተኛው አደጋ የተደናገጡት የጠላት ጀቶች ኢላማቸው ያደረጓትን መርከብ ሳይመቱ ተበታተኑ፡፡ በመጨረሻም ጀግናው ወጣት ከካምፑ በሰላም አረፈ፡፡ ከእርሱ ጀት ላይ የተወሰደው ፊልም ሲታይ ወጣቱ ያደረገው ጀብድ ድንቅ ነበር፡፡ አምስት የጠላት ጀቶች አውድሟል፡፡
ድርጊቱ የተፈፀመው በየካቲት 1942 ነበር:: እናም ኦሃሬ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ከተሰጡት ኒሻኖች የመጀመሪያውን ኤስ ተሸለመ፡፡ በወቅቱ ወጣቱ የመጀመሪያው አብራሪ ነበር - ይህንን ሜዳል ሲወስድ፡፡
ኦሃሬ ከአመት በኋላ በ29 ዓመቱ በጦርነት ላይ የተሰዋ ጀግና ነው፡፡ አሁን ድረስ እናት ምድሩ ቺካጎ ስሙንና ጀግንነቱን ታስበዋለች:: ለመታሰቢያውም አውሮፕላን ማረፊያቸውን ሰይመውለታል፡፡ በሚቀጥለው ጊዜ በቺካጎ ስትገኝና ኦሃሬ አውሮፕላን ማረፊያ ስታርፍ ጀግናውን ማሰብ እንዳትረሳ፡፡ በተርሚናል አንድና ሁለት መካከል ደግሞ የክብር ሽልማቱ ይታያል፡፡ እሱንም እንድትጎበኝ፡፡
‹‹የሚገርም ነው!›› ስል ላቤን እየጠራረግሁ አመስግኜ ተነሳሁ፡፡  ሳይታወቀኝ ግዜው ሄዶ ነበር፡፡ ከኪሴ ሰላሳ ድርሃም አውጥቼ እያስቀመጥኩ ቀበቶዬን አጠባበቅሁ፡፡
‹‹በሁለቱ ታሪኮች መሃል ግንኙነት ያለ ይመስልሃል!?›› ሲሉ ጠየቁኝ፡፡
‹‹ሁለቱም ለሰው ልጆች የተደረጉ መልካም ነገሮችንና መስዋዕትነቶችን ያሳያሉ ይመስለኛል::›› አልኩ ግንባሬን እያኮሳተርኩ፡፡
ፈገግ ብለው ‹‹ ሁለቱ ታሪኮች የሚያሳዩት ለልጅህ የምትሰጠውን ውድ ስጦታ ነው:: በሚቀጥለው ትውልድ የምታገኘው አንተ ያወረስከውን ነው የሚለውን ሀሳብ ነው፡፡ አየህ ኦሃሬ የኤል ካፖኒ ጠበቃ የነበረው ‹ኢዚ ኤዲ› ተወዳጅ ልጅ ነበር፡፡››
‹‹በእውነት!›› አልኩ አሁን በጣም ተገርሜ:: ሰውየው የሚነግሩኝ ነገር ልክ መሆኑን እየተጠራጠርኩ፡፡ በእውነትም አባት ለልጁ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ አልፎ ነበር ማለት ነው፡፡ ሽማግሌው ሊያስገርሙኝ በመቻላቸው እየፈነደቁ በአዎንታ አረጋገጡልኝ፡፡ በመገረም ራሴን እየነቀነቅሁ ተሰናብቻቸው ወደ ጸሃዩ ወጣሁ፡፡ ጥግ ጥጉን እያተዋከብኩ ከምድር ባቡሩ አሳንሳር ገባሁና በደቂቃ ልዩነት ተሳፍሬ መንገዴን ጀመርኩ:: ጥቂት እንደተጓዝኩና ሽማግሌው የነገሩኝን ታሪክ እያሰብኩ፣ የእጅ ስልኬን አወጣሁና ፍለጋ ጀመርኩ፡፡ ከጎግል የመፈለጊያ ሜዳ ላይ አል ካፖኒ ብዬ ፅፌ መረጃውን ማንበልበል ጀመርኩ … እውነትም የነገ ትውልድ የልጆች የሞራል መሰረት የአባቶች አርአያነት ነው፡፡ ታሪኩን በዚያ ተመዝግቦ አገኘሁት፡፡


Read 1168 times