Tuesday, 01 October 2019 11:03

የ‹‹ሆሄ ሽልማት›› የሦስት ዓመት ጉዞ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

                          - የዘንድሮ የሽልማት ሥነስርዓት ጥቅምት 11 ይካሄዳል
                           - የትምህርትና የምርምር መጻሕፍት በሽልማቱ ውስጥ ተካትተዋል

          በልጆች መጻሕፍት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የንባብ ባህልን ለማዳበርና ሥነ ጽሑፍን ለማበረታታት ታልሞ የተቋቋመው ‹‹ሆሄ›› የሽልማት ድርጅት፤ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን አወዳድሮ ይሸልማል። በዚህ ዓመት በኦሮምኛና ትግርኛ ቋንቋ የተጻፉ የህፃናት መጻሕፍትን
እንዲሁም የትምህርትና የምርምር ሥራዎችን በሽልማቱ ውስጥ መካተታቸውን ከ‹‹ሆሄ ሽልማት” ዋና አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ ለመሆኑ የ‹‹ሆሄ›› የሦስት ዓመት ጉዞ ምን ይመስላል? ስኬቶቹና ተግዳሮቶቹ ምንድን ናቸው? የአዲስ አድማሱ ደረጀ በላይነህ ከ“ሆሄ ሽልማት” ዋና
አስተባባሪ ጋር በሽልማት ድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ዙሪያ እንደሚከተለው አውግተዋል፡፡ ፡-

         የሽልማ-ት መርሀ ግብሩ እንዴትና በምን ሁኔታ ተጀመረ?
የ“ሆሄ ሽልማት” የተጀመረው በ2009 ዓ.ም ነው:: ዋና ዓላማው ሥነ ጽሑፍን ማበረታታትና የንባብ ባህልን ማዳበር ነው፡፡ በተለይ የልጆች የንባብ ልማድ እንዲዳብር ለማድረግ በሚል የተጀመረ ነው፡፡ ይህንን የሽልማት ድርጅት ስንመሰርት፣ ከዚህ በፊት በአገራችን የነበሩ የሽልማት ፕሮግራሞችን ለመቃኘት ሞክረናል:: የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት፤ ከዚያም በ1990ዎቹ የነበረ የኪነ ጥበብ ሽልማት ድርጅት አሰራርን አይተናል፡፡ የዳኞቹን ሁኔታ፣ መስፈርቶቹንና የሽልማቱን ዓይነት በመቃኘት ራሳችንን ለማዘጋጀት ብዙ ተጠቅመንበታል፡፡
እንግዲህ እነዚህንና የመሳሰሉትን ልምዶች ገምግመንና ቀስመን ነው የሆሄ ሽልማት ፕሮግራምን ለማዘጋጀት እየጣርን ያለነው:: ለጊዜው ይህንን ሽልማት ሀላፊነቱን ወስዶ የሚያካሂደው ‹‹ኖርዝ ኢስት ማርኬቲንግ››  የተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቢሆንም ያንድ ድርጅት ፍላጎት ማንፀባረቂያ እንዳይሆን አስራ አምስት አባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ የሽልማት ዝግጅቱን የሚመራው፣ ዘርፎቹን የሚመርጠው፣ ዳኞቹን የሚሰይመውና አጠቃላይ የፕሮግራሙን ይዘት የሚያቀናጀው ይኼ  ኮሚቴ ነው፡፡ ይህም  የሽልማት ፕሮግራሙ ነፃነቱን ጠብቆ በተዓማኒነት እንዲሰራ አድርጎታል:: ከዚህም ባሻገር የመጻሕፍቱ ዘርፍ ሦስት ሦስት ዳኞች እንዲኖሩት፣ ዳኞቹ ደግሞ በተሰማሩበት ዘርፍ ትልቅ አበርክቶ፣ ልምድና ዕውቀት ያላቸው እንዲሆኑ ተመርጠው፤ ምክንያታዊና አሳማኝ በሆነ መንገድ እንዲሰራ አድርገናል፡፡ ሥራው ከመጀመሪያው ዙር ጀምሮ ባሰብነው አይነት እየሄደ ነው፡፡ በሥነ ጽሑፍ ቤተሰቡ ዘንድ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ‹‹ለምን የኔ መጽሐፍ ከአምስቱ ምርጥ ውስጥ አልተካተተም?... ዳኞቹ እነማን ናቸው? መጻሕፍቱ በምን መንገድ ተመረጡ? መመዘኛው ምንድነው?›› ከሚለው ማጉተምተም ባለፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ ተቀባይነትና ተዓማኒነት እያገኘ መጥቷል:: በዚህ መሰረት ይኸው ዘንድሮ ሦስተኛውን ዙር የሽልማት ፕሮግራም እያዘጋጀን ነው፡፡
በዚህ የሽልማት ፕሮግራም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያላችሁ ግንኙነት በምን ላይ የተመሰረተ ነው?
የሽልማቱ ፕሮግራም በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና ፍሬያማ ይሆን ዘንድ፣ ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው ለማድረግ፣ ከትምህርትና ተዛማጅነት ካላቸው ተቋማት ጋር መስራት የተሻለ ውጤት ይኖረዋል የሚል ሀሳብ ስላለን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና መጽሐፍት ኤጀንሲ ጋር በጋራ እንሰራለን፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያሉ የሥነ ጽሑፍ ምሁራንም ባቋቋምነው አስተባባሪ ኮሚቴ ውስጥ ታቅፈው ብዙ እገዛ ያደርጉልናል:: ከዚህም ባለፈ የተቋማቱ አብሮነት የሽልማቱን ከበሬታ ከፍ ያደርገዋል የሚል እምነት አለን፡፡
ከእነርሱ ሌላ የተለያዩ ትብብር የሚያደርጉልን ተቋማትም አሉ፡፡ ትምህርት ላይ ከሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል ‹‹ጄኔቫ ግሎባል›› የተሰኘው የአሜሪካ ድርጅትና የጀርመን የባህል ተቋም ይጠቀሳሉ:: በሚዲያም ተባባሪዎች አሉን፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ ነው፡፡ ይህን ፕሮግራም በማስተዋወቅ በያመቱ የተመረጡትን መጻሕፍት ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፤ እያገዘን ነው፡፡ “ሪፖርተር” ጋዜጣና ኢቢኤስም ትብብር ያደርጉልናል፡፡ ሁሉንም እናመሰግናለን፡፡
ውድድሩን አዘጋጅታችሁ ሽልማት ከሰጣችሁ በኋላ መርሃግብሩ በደራሲውም ሆነ በሕብረተሰቡ ዘንድ  የሚፈጥረውን ስሜትና ተፅዕኖ ትገመግማላችሁ?
የሽልማቱ መርሀ ግብሩ ምን ለውጥ አምጥቷል? የሚለውን ለማየት እንሞክራለን፡፡ ብዙም የማይታወቁ መጻሕፍት ወደ አደባባይ ወጥተው እንዲተዋወቁና እንዲነበቡ በማድረግ ረገድ ሽልማቱ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው:: ወጣት ፀሐፍት በመጀመሪያው ሥራቸው ከትላልቅ ደራስያን ጋር ተወዳድረው ያሸነፉበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ “የአመቱ ምርጥ አምስት መጻሕፍት” ዝርዝር ውስጥ የገቡ ጀማሪ ደራስያንም አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ‹‹ወሰብሳቤ›› የሚል መጽሐፍ ደራሲ ሲሆን ሁለተኛ መጽሐፉን ሲያሳትም፣ መግቢያው ላይ ስለ ሽልማት ፕሮግራማችን በዝርዝር ጽፏል፡፡
እንደዚህ አይነት ነገሮች እኛንም ያበረታቱናል:: በመጀመሪያው ዙር ተሸላሚ ከሆኑት ደራሲያን መካከል አንዱ አዳም ረታ ነው፡፡ አዳም ረታ የአገራችን ትልቅ ደራሲ ነው፡፡ እኛም ለርሱ ትልቅ ከበሬታ አለን፡፡ በመጽሐፍት ሽያጭ አካባቢ የሚሰሩ ሰዎች፣ ከሽልማቱ መርሀ ግብር በኋላ የመጽሐፉ ሽያጭ በተወሰነ ደረጃ መጨመሩን ገልፀውልናል፡፡ እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች ውጤታችንን ለመገምገም ይረዱናል፡፡
የሽልማት መርሃ ግብሩን በማዘጋጀት ሂደት የሚገጥሟችሁ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው?
ይህን መርሀ ግብር ስናዘጋጅ ብዙ ተግዳሮቶች ያጋጥሙናል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ  ከሥነ ጽሑፍና ከንባብ ጋር ያለው ልምምድ በጣም አናሳ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና አንድ መጽሐፍ ደራሲው ረቂቁን ካዘጋጀበት ጊዜ ጀምሮ መጽሐፍ ሆኖ ለገፀ ንባብ እስኪበቃ ድረስ የሚያልፍበት ብዙ ሂደት አለ፡፡ ከዚህም አልፎ ሥርጭቱ ሳይቀር የደራሲው ሸክም ነው:: በሌላው አለም የተደራጁ አሳታሚዎች ስላሉ ብዙውን ሥራ ያቃልሉለታል፡፡ እኛ አገር ግን ሁሉም እዳ በደራሲው ጫንቃ ላይ የወደቀ መሆኑ ነገሩን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መጻሕፍት ወደ ተደራሲው እንዳይደርስ ያደርጋል፡፡
እኛም በዚህ የሽልማት ሂደት ውስጥ በርካታ ሰዎች መጻሕፍት ጽፈው በእጃቸው እንዳለ ተገንዝበናል፡፡ የመጀመሪያው ዙር የልጆች መጻሕፍት አሸናፊ የነበረው አስረስ በቀለም ጥቂት የማይባሉ የልጆች መጻሕፍት ጽፎ እንዳስቀመጠና የሕትመቱ ጉዳይ አስቸጋሪ እንደሆነበት ነግሮናል፡፡ እነዚህ ነገሮች የተሻሉና የተጠናከሩ ቢሆን የሽልማቱም ድርጅት የተጠናከረ እንዲሆን ያግዘው ነበር፡፡
ይህ ሁሉ ችግር እያለም ቢሆን በየአመቱ በሚካሄደው የሽልማት መርሀ ግብር ውስጥ አንደኛ የሚወጡት፣ ምናልባትም ምርጥ አምስቱ ዝርዝር ውስጥ የሚገቡትም ሳይቀር አሳታሚ የማግኘት ዕድላቸውን ይጨምራል የሚል እምነት አለን:: በዚህ ጉዳይም ላይ የተሻለ ነገር ለመስራት ጥረት እያደረግን ነው:: በተለይ ከአሳታሚ ጋር ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል ብዙ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የእኛም ዓላማ ንባብን ማበረታታት ስለሆነ በያመቱ ከመጻሕፍቱ ባሻገር ‹‹ለንባብ መዳበር አስተዋጽኦ ያደረጉ›› ግለሰቦችንና ተቋማትን እንሸልማለን፡፡ በዚህ ረገድ በየጋዜጦች ላይ መጻሕፍትን የሚገመግሙና ሂሳዊ ዳሰሳ የሚሰሩ፣ አዳዲስ መጻሕፍትን የሚያስተዋውቁ ግለሰቦችና ተቋማት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለን እናምናለን፡፡ አዳዲስ መጻሕፍት ላይ ውይይት የሚያካሂዱ ክበባት፣ የሬዲዮ ትረካና ፕሮግራም የሚያቀርቡ ተቋማትን እየመረጥን ሽልማት እንሰጣለን፡፡ ለአይነ ስውራን መጽሐፍትን ወደ ብሬል የሚቀይሩና በድምጽ የሚያዘጋጁትንም እንሸልማለን፡፡ የአሳታሚነት ሥራ እንዲበረታታና የሕትመት ዋጋ በጣም እንዳይወደድ በማድረግ የራሱ ድርሻ ይኖረዋል የሚል እምነት አለን፡፡
የሽልማት ዝግጅቱን ወጪ እንዴት ነው የምትሸፍኑት?
ይህን ሥራ ለመሥራት አንዱና ከባዱ ችግር የስፖንሰርሺፕ ጉዳይ ነው፡፡ ከስራው ጋር የተያያዙ ለማስቀረትና ለመቀነስ የማይቻሉ ብዙ ወጪዎች አሉ፡፡ ሥራውን የምንጀምረው የአመቱ መግቢያ ላይ ነው፡፡ በዚያ ላይ መጻሕፍቱን መሰብሰብ፣ ለየዘርፉ ዳኞች ማድረስ፣ የተመረጡት መጻሕፍት ድምፅ እንዲሰጥባቸው ማድረግ እንዲሁም፤ የራሳችንን የማህበራዊ ሚዲያ ማስተዳደር የመሳሰሉት ሥራዎች በጣም ከባድ ናቸው፡፡ እነዚህን ወጪዎች  የሚሸፍኑልን ስፖንሰሮች ለማግኘት በያመቱ ብዙ ጥረት ብናደርግም ብዙም የተሳካ አይደለም፡፡ ከመጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ እያገዘን ያለው ‹‹ሄንከን ቢራ›› ሲሆን፤ ዘንድሮም በ“ሶፊ ቡና›› ምርቱ ድጋፍ እያደረገልን ነው፡፡ የሽልማት ድርጅቱ እንዳይቋረጥ ባለው ቀናነት የተነሳ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ያለ ተቋም ነው፡፡ ሌሎችም አነስተኛ ድጋፍ የሚያደርጉልን አሉ፡፡ አንዱ ‹‹ጄኔቫ ግሎባል›› የሚባል በልጆችና ጎልማሶች ንባብና ትምህርት ላይ የሚሰራ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው:: ‹‹ስቱዲዮ ኔት›› የተባለ ድርጅት የምናዘጋጃቸውን ፕሮግራሞችና ማቴሪያል ዲዛይን በማድረግ ያግዘናል:: በርካታ ግለሰቦችም ለዚህ ሥራ የራሳቸውን ጊዜ መስዋዕት አድርገው እየደገፉን ነው፤ ያለ እነርሱ ድጋፍ እዚህ ደረጃ መድረስም አንችልም ነበር፡፡
በሚቀጥሉት አመታት ይህንን ሁኔታ ለማሻሻል ሌሎች መንገዶችን ለመሞከር እያሰብን ነው፡፡ ከሚቀጥለው አመት ጀምሮ ድርጅቱ እንደ አካዳሚ ሆኖ እንዲዋቀር ለማድረግ ከሥነ ጽሑፍ ዘርፍ፣ ከአካዳሚክ ማህበረሰቡ፣ ከጋዜጠኞችና ደራስያን እንዲሁም ከንግዱ ሴክተር አባላትን በመመልመል የተወሰኑት የአባልነት መዋጮ የሚያደርጉበትን፣ ከዚያም ባሻገር ገንቢ ሀሳብ የሚያዋጡበትን ዕድል ለመፍጠር እንሰራለን፡፡ የአባላቱ ቁጥር በጨመረ መጠን ሽልማቱ ይበልጥ ተአማኒና ተቋሙም ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል ብለን እናምናለን፡፡ ከአባላት በሚገኙ መዋጮዎች አንዳንድ የሥራ ወጪዎችን መሸፈን የምንችልበትን መንገድ እያጠናን ነው፡፡
የመንግሥት ተቋማትስ አያግዟችሁም?
ከአዲስ አበባ የባህልና የኪነ ጥበብ ቢሮ ጋር አብረን እየሰራን ነው፡፡ በዚህ አመት አንዳንድ ድጋፍ እናደርግላችኋለን ብለውናል፡፡ ‹‹አብረን ብንሰራ ጥሩ ነው፤ ልትደግፉን ይገባል” እያልናቸው ነው:: የመንግስት ተቋማት ይህንን አገራዊ ፕሮግራም የማገዝ ኃላፊነት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁልጊዜ ከተለያዩ ግለሰቦችና የንግድ ድርጅቶች እየተለመነ መዝለቅ አይቻልም፡፡ መጻሕፍት ትውልድን ይቀርፃሉ:: ስለዚህ የደራስያን ገቢ የሚሻሻልበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ይህን የማሻሻል ኃላፊነት መንግሥትንም ይመለከታል፡፡
በዚህ አመት አዲስ የሸልማት ዘርፎች መጀመራችሁን ሰምቼአለሁ…
ትክክል ነው፡፡ ዘንድሮ በኦሮምኛና በትግርኛ የተጻፉ የልጆች መጻሕፍት አወዳድረን እንሸልማለን:: በሚቀጥሉት አመታትም በሌሎች ተጨማሪ ቋንቋዎች ላይ በተለይ በሕጻናት መጻሕፍት አካባቢ የተሻለ መነሳሳት እንዲፈጠር እንፈልጋለን:: በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስና የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬስ የትምህርትና የጥናት ውጤቶችን ስለሚያሳትሙ፣ ይህንንም ዘርፍ በሽልማቱ መርሀ ግብር ለማካተት ሞክረናል። መስከረም የመጨረሻው ሳምንት ላይ ለፍጻሜ ውድድር የደረሱትን መጻሕፍት እናስተዋውቃለን:: ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም የሽልማት ሥነስርዓቱ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡ የዚህ አመቱ ፕሮግራም በተሻለና በተሳካ ሁኔታ ይካሄዳል ብለን እናምናለን፡፡


Read 1137 times