Tuesday, 01 October 2019 11:05

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)

ሰውየው “ጐበዝ ነኝ” ባይ ነው፡፡ በአጋጣሚ ሊዘርፉት የመጡትን ሶስት ወንበዴዎች ማረከ፡፡ ማን ሃሳቡን እንዳፈለቀ፣ ማን እንደጠቆመበትና ማንኛው ኦፕሬሽኑን እንደመራ አጣራ፤ እንደየደረጃቸውም ሊቀጣቸው ተዘጋጀ፡፡
የመጀመሪያውን ሰው ጠራና በጠረጴዛው ላይ ካስቀመጣቸው ሦስት ፍራፍሬዎች፡-
“አንዱን ምረጥና ሳታኝክ ከእነ ገለባው ዋጠው” አለ፡፡ የታዘዘውን ከመፈፀም ሌላ አማራጭ እንደሌለው የተረዳው ወንበዴ እያለቀሰ ሙዙን አንስቶ ዋጠ፡፡
ሁለተኛውን ጠርቶ እንደ መጀመሪያው ሰው እንዲያደርግ አዘዘው፡፡ እሱም ኮኩን አነሳና ለመዋጥ እየታገለ እያለ አላስችል ያለው ሳቅ ገነፈለበት፡፡ ባለቤቱም፤
“ምን ያስቅሃል?” ሲለው
“የኋለኛውን እያሰብኩ” አለ፡፡ የኋለኛው ምን ይሆን ?
***
ከእናታችን ሆድ ስንወጣ፣ ዓይናችን ሳይገለጥ፣ ለመተንፈስ ወይም ለመጥባት ክፉኛ እንፈራገጣለን:: ቀናችን ደርሶ ወደ መጣንበት ስንመለስም ሳንወራጭ እጅ አንሰጥም፡፡ ከውልደት እስከ ሞት ስጋና ነፍሳችንን የሚነዳ (Driving force) ሃይል አብሮን አለ፡፡ ይኸ ተፈጥሯዊ ሃይል ደመናን ሰብሮ እንደሚወጣ የፀሐይ ብርሃን ሊገደብ አይችልም፡፡ የአዲሱን ዓለም መጋረጃ ገልጦ የመኖር ምጣድ ላይ እያንከባለለ ያበስለናል፡፡
ከማያቋርጠው የሰው ልጅ የመፈለግና የማሸነፍ ጉጉት የተሰራው ወይም የመነጨው ይህ ሃይል ወደ ዕውቀትነት ሲቀየር፣ ሌሎች የሃይል ምንጮችን እያስገበረ ጥቅም እንዲሰጡት ያደርጋል:: እርሻ ማረስ፣ ሮኬት ማስወንጨፍ ለመሳሰሉት፡፡ ለክፋት ካዋለውም በደቂቃዎች ውስጥ ስልጣኔን እንዲያፈራርስ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ወዳጄ፡- ዕድሜን ጥቅም በሚሰጥና በማይሰጥ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ በያንዳንዱ ሰው “የማሰብ ብቃት” ይወሰናል፡፡ መውደቅና መነሳት እንዳለ ሆኖ መኖር፣ መፍጠር፣ ማወቅና የስልጣኔ አሻራ ማሳረፍ የምንችላቸው ነገሮች ሁሉ የታጨቁት እዚሁ “ብቃት” የምንለው ቋት ውስጥ ነው፡፡
የ“ቋት”ና የ“ብቃት” ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ የድሮ ቀልድ ነበረች፡- አንድ ባለጌ ሰውየውን እያከታተለ ይሳደባል፡፡ ሰውየው ታገሰ ታገሰና “አንተ የስድብ ቋት ነህ” አለው፡፡
ባለጌውም እንደ ጀመረው ስሜት የሚፈታተን ስድብ ሲያስከትል፡-
“እሱም እዛ ቋት ውስጥ አለ” አለው ሰውየው::
ሌላ ስድብ ቢሞክርም ተመሳሳይ መልስ ሰጠው:: “ስድብ ሁሉ ያለው አንተ ውስጥ ነው፣ አንተ ራስህ ስድብ ነህ” ማለቱ ነበር፡፡ በአንድ ዓ.ነገር ባለጌው ቆመ፡፡ ያለ “ክፉ” ቃል፣ ድንቁርና ወለድ ስሜቶችን ማረቅ በራሱ ለሰውየው ብቃት ነው፡፡
ወዳጄ፡- ሳይንስ፣ ፍልስፍናና ጥበብ የመሳሰሉት የዕውቀት ዘርፎች ቀኖናዊ ትክል ካላቸው አመለካከቶችና አተረጓጐሞች ይለያሉ:: ምክንያቱም በራቸው ለአዳዲስ አስተሳሰቦች፣ ሙከራዎችና ግኝቶች ክፍት በመሆኑ ነው፡፡ እንደ “ፍካሬ ኢየሱስና ስምንተኛው ሺ” አበቃ፣ ተደመደመ ወይም ሊረጋገጥ የማይችል ነገር ይሆናል አይሉም፡፡ ዕውቀት የሚዳብረው ከሰው ልጅ አእምሮ እድገትና ልማት ጋር መሆኑን ይቀበላሉ፡፡ ገደቡ የግለሰብ አእምሮ “ብቃት” ነው፡፡ ግለሰቡ ቀኖናዊ ከሆነ፣ አእምሮው ከታመመ ወይም የሌሎች አስተሳሰብ ጥገኛ ከሆነ ችግር አለው፡፡
የሂዩስተን ዩኒቨርስቲው ሮበርት ሲ. ሶለሞን እ.ኤ.አ በ1997 ባሳተመው የፍስልፍና መጽሐፉ ዕውቀት “ተቸካይ” አለመሆኑን ሲያስረዳ፤ “ከአስር ዓመት በፊት “ስኬፕቲኮች” ኮምፕዩተር ቼስ መጫወት እንደማይችል እርግጠኞች ነበሩ:: ዛሬ ግን መጫወት ብቻ ሳይሆን ታላላቆቹን ጥበበኞች (Great masters) እያሸነፈ ነው” በማለት ጽፏል፡፡
ወዳጄ፡- ከመቶ ዓመት በፊት ስልክ፣ ሬዲዮ፣ የውሃ ቧንቧና የመሳሰሉት የስልጣኔ በረከቶች አገራችን ሲገቡ “የሰይጣን ስራዎች” ተብለው ተወግዘዋል፡ ዛሬ የደረሱበትን ደረጃ ስንመለከት ዕውቀት በቅብብሎሽ ለመዳበሩ ሌላ ማረጋገጫ አያስፈልገንም፡፡ ቀኖናዊነት ግን በስልጣኔ በር ላይ ተደንቁሮ የአእምሮ ዕድገትን ይፈታተናል፡፡
ወዳጄ፡- የሰው ልጅ ግብርና ከመጀመሩ፣ ጦር፣ ቀስትና ወጥመድ አበጅቶ አደን ከመቻሉ በፊት አንዱ ሌላኛውን ይበላ ነበር፡፡ ያኔ በግለሰቦች አእምሮ ሰሌዳ ላይ ተጽፎ የነበረው ጥያቄ መኖር ወይ አለመኖር የሚለው ሲሆን ብቃትና ውድድሩም ሆድን አሸንፎ ለማደር ነበር፡፡ አሁን ግን ዘመኑ ተቀይሮ የስልጣኔያችን መርሆ ኑር እንኑር - “Live and let Live” የሚል ሆኗል፡፡ እናም ሰው ነፃ የወጣው በልምድና በዕውቀት ድግግሞሽና ዕድገት ነው ቢባል እውነት ነው፡፡ እዚህ ጋ በልጅነት ከሰማናቸው መዝሙሮች አንዷ በከፊል ትዝ አለችኝ፡፡
ከሙሉ የህይወት ዘመናት
ከመኖር ትርጉም ፀባያት
ሁሉን ማየት ጠቃሚ ነው
የህይወት ምዕራፍ አንዱ ሂደት ነው፡፡
    ብቃትና ጥራት የሚገኘው
ከመኖር ቅይጥ ልምድ ተምሮ ነው
ተፈጥሮን እንዲያርቅ ያረገዋል
ከዛሬ ነገ እያወቀ ይሄዳል፡፡
አዝማች   
ሳይንስ እንዳለው ከፀሐይ በታች
በዚች ግዙፍ ዓለም ምድራችን
ውጣ ውረዱና ትርምሱ
አድራጊው ፈጣሪው
ሰው ነው ራሱ ---
ወዳጄ፡- ተፈጥሮ ሚስጢሯን ለሰው ልጅ አልደበቀችም፡፡ አእምሮውን ተጠቅሞ ሊገልጣት፣ ሊያውቃትና ሊገለገልባት ፍቃደኛ ናት፡፡ ሌላው ቀርቶ በላይዋ ላይ እየኖረ በሆዷ ውስጥ ያለውን አያውቅም፡፡ ከተፈጠረ ቢሊየን ዓመታት ቢቆጠርም እስከዛሬ ድረስ ባካበተው ልምድና ዕውቀት መጠቀም የቻለው “የአእምሮውን አንድ አስረኛ ያህል ነው” ይባላል:: በዚህ ዘመን እንኳ ከአውሬነት ባህሪያቸው ያልተላቀቁ ወንድሞች እንዳሉን ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ክፉና ደጉን መለየት ያልቻሉ፣ ነገን ማየት የተሳናቸው፡፡ በነገራችን ላይ “ሚዛናዊ” ነን ከምንለው “እኛ” በአንዳንድ ነገሮች የሚሻሉ፣ በደመነፍሳቸው የሚንቀሳቀሱ እንስሳት፣ አእዋፍና አራዊት አያሌ ናቸው፡፡
“እደጅ የተኮለኮሉት ፍጥረታት አሳማውን ከሰው፣ ሰውየውን ከአሳማ እያቀያየሩ ቢመለከቱም አንደኛውን ከሌላኛው መለየት አቃታቸው” (--Impossible to say which was which) እንዳለው ጆርጅ ኦርዌል፡፡
***
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- ሰውየው ሁለተኛውን ወንበዴ፤ “ምን ያስቅሃል?” ሲለው
“የኋለኛውን እያሰብኩ” ብሎት ነበር፤ ጠረጴዛው ላይ የተረፈውን  ፓፓዬ እየተመለከተ፡፡ ተሳስቷል:: ባለቤቱ፤ ዋነኞቹ ጥፋተኞች ሃሳብ አቅራቢውና ጠቋሚው ናቸው፤ ይኸ ያለቦታው የገባ “ጐበዝ” ነው ብሎ በማሰቡ ነፃ አድርጐታል፡፡ ወዳጄ፤ ኋለኛውን ማን ያውቃል? ባለመስቀሉ ካልሆነ!
መልካም የመስቀል በዓል!!
ሠላም!!

Read 1035 times