Tuesday, 01 October 2019 11:12

2011 - በመጻሕፍትና በኪነ ጥበብ ምሽቶች

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  ‹‹ንባብ የተነቃቃበት ዓመት ነው››
                             (ሰይፈዲን ሙሳ፤ በጃፋር መፃሕፍት መደብር የማርኬቲንግ ባለሙያ)

             በዓመቱ በርካታ መጻህፍት ለገበያ ቀርበዋል:: ከሌሎቹ አንፃር የግጥም መጽሐፍት በርከት ብለው ይወጡ ነበር፡፡ በአሁኑ አመት ግን በተለየ መልኩ የታሪክና የፖለቲካ መጽሐፍት ገበያውን በደንብ ተቆጣጥረውታል፡፡ ተነባቢም ነበሩ፡፡ የአንዳርጋቸው ጽጌ “እኛም እንናገር ትውልድ አይደናገር”ን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሌላው የመምህር ታዬ ቦጋለ ‹‹መራራ እውነት›› ሲሆን በኢትዮጵያ ታሪክና ፖለቲካ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ነው፡፡ በልቦለድ ዘርፍ በተለየ አቀራረብ የመጣው የደራሲ አለማየሁ ገላጋይ “ውልብታ“ በደንብ የተሸጠና የተነበበ መጽሐፍ ነው፡፡ ሌላው በኤርሚያስ አመልጋ የህይወትና የሥራ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው “የማይሰበረው- ኤርሚያስ አመልጋ”፤ ተነባቢ ነበር፡፡ የዶ/ር ኤርሲዶ ለንዶቦ “ኑሮ ማፕ” እንዲሁ  በደንብ ተሸጧል፡፡
በቅጂ በኩል የአንዳርጋቸው ጽጌ መጽሐፍን ስንወስድ፣ 30 ሺ ኮፒ ታትሞ ነበር፤ በሙሉ ተሸጦ አልቋል፡፡ የታዬ ቦጋለ “መራራ እውነትም” 30ሺ ኮፒ ታትሞ፣ ተሸጦ እየተጠናቀቀ ነው:: “ኑሮ ማፕ” ህይወትን እንዴት መምራትና መለወጥ እንደሚቻል መንገድ የሚያሳይ አነቃቂ መጽሐፍ ነው፡፡ 10 ሺህ ኮፒ ታትሞ በአንድ ሳምንት ውስጥ አልቋል፡፡ የአለማየሁ ገላጋይ “ውልብታ”ም በአንድ ሳምንት 10 ሺህ ኮፒ አልቋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከቀድሞው በተለየ መልኩ የህትመት ቁጥር እንዴት ጨመረ ከተባለ፣ ከዚህ ቀደም ያለው ልምድ፣ አንድ መጽሐፍ ሲታተም ፍራቻ ስለሚኖር፣ በተለይ ታዋቂ ፀሐፊ ካልሆነ፣ 3ሺህ፣ ቢበዛ 5ሺህ ኮፒ ነበር፡፡ አሁን ግን አሳታሚም ፀሐፊም እየደፈረ፣ እስከ 30ሺ ኮፒ እያሳተመ ነው:: ያ ማለት የንባብ መነቃቃት ተፈጥሯል፡፡ የንባብ መነቃቃቱ ከምን የመጣ ነው ከተባለ፣ የአገሪቱ ፖለቲካ ሲለዋወጥ፣ አዲስ መሪ ሲመጣ፣ አይዲዮሎጂ ሲቀየር፣ አዳዲስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሲመጡ፣ አዳዲስ አመራሮች ሲለወጡ…በአጠቃላይ የፖለቲካ ትኩሳቱ ከፍና ዝቅ ሲል፣ የህብረተሰቡን መረጃ የማግኘትና የማወቅ ጉጉት ስለሚጨምሩት ወደ ንባብ ያዘነብላል፡፡
ፖለቲከኞችም ስለ አገር ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ ጉዳይ ይጽፋሉ፡፡ የህይወት ታሪካቸውን  ጭምር ሲጽፉ ሰው ያነባል:: ለዚህ ነው ዘንድሮ የንባብ መነቃቃትም፣ የመጽሐፍት ህትመት ቅጂም መጨመር የታየው፡፡ ከላይ የጠቀስኩልሽ ፀሐፊዎችም፣ የታሪክ ባለቤቶችም ተጽእኖ በመፍጠር ረገድ ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ ዘመኑም እንድታነቢ ያስገድድሻል፡፡ ምክንያቱም ካላነበብሽ ከመረጃ ወደ ኋላ እንደምትቀሪ፤ ከሌላው እኩል በእውቀት እንደማትራመጂ ታውቂያለሽ፡፡ ስለዚህ የግድ ማንበብ አለብሽ፡፡ በማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቀውን የሃሳብ ውሽንፍር ለመለየት፣ የግድ መጽሐፍትን ወደ ማጣቀስ ትመጫለሽ፡፡ ይሄ ሁሉ ንባቡን አነቃቅቶታል:: ግን በቂ አይደለም፡፡ በአገራችን ላይ ያለው የህዝብ ብዛትና የሚታተመው የመጽሐፍት ቁጥር ምንም አይቀራረቡም፡፡ አሁን የልጆች መጽሐፍት የሉም በሚያስብል ደረጃ ያለ ነው፤ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በልቦለድ በኩል፤ የዓለማየሁ ገላጋይ “ውልብታ” እና የሀብታሙ አለባቸው “አንፋሮ” ጐላ ብለው ወጥተዋል፡፡ የገነነ መኩሪያ (ሊብሮ)፣“ኢህአፓና ስፖርት” ከታተመ ቆይቶ ነበር፡፡ ግን በዚህ ዓመት በድጋሚ ታትሞ  በደንብ ተሸጧል፡፡ የወጐች ስብስብ ነው፡፡ የግጥም መጽሐፍት በብዛት ቢታተሙም አንባቢ ፊት ይነሳቸዋል፡፡ ዘንድሮ ግን አንባቢያን የግጥም መጽሐፍ ርዕስ ጠርተው መግዛት መጀመራቸው አስደምሞናል፡፡ ለምሳሌ የመዘክር ግርማ “ወደ መንገድ” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ በደንብ ተሸጧል፡፡ በቅርብ ከወጡት ውስጥ የዮናስ ኪዳኔ “የነፋስ መሰላል”ም ተሸጧል፡፡ “የሽልንግ ተሳፋሪዎች” የተሰኘውም እንዲሁ በደንብ ተሸጧል:: ከበፊቱ አንፃር ያስደንቀናል፡፡
የንባብ ባሕል እንዳይዳብር ማነቆ ሆኗል ብዬ የማምነው የወረቀት ዋጋ መወደድ ነው:: የወረቀት ዋጋ መወደዱም ብቻ ሳይሆን ወረቀት የሚያስመጡትም ነጋዴዎች በቁጥር ማነስም ምክንያት ነው፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ከፈለጉ ያስወድዱታል፡፡ ከፈለጉ ደግሞ እጥረት እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡ የቀረጡ ከፍተኛ መሆንም ተደማምሮና እነዛ ጥቂት አስመጪዎች ገበያውን በግል መቆጣጠራቸው ተጨማምሮበት፣ የመጽሐፍን ዋጋ አንረውታል፡፡ የንባብ ባህል እንዲዳብር በጥብቅ አለመሰራቱም፣ ሌላው የንባብ ማነቆ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይሄ ከመንግሥት፣ ከግለሰቦችና ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቅ ስራ ይመስለኛል፡፡ ንባብ በመሰረታዊነት እንደ ልብስ መጠለያና ምግብ አስፈላጊ ሆኖ እንዲወሰድ መደረግ አለበት፡፡
ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ 5 ሚሊዮን ህዝብ ይኖራል እንበል፡፡ አንድ ሚሊዮን ያህሉ የተማረ፣ የሚያነብ፣ የሚመራመር ነው ብለን ብንወስድ፣ አንድ መጽሐፍ ለአንድ ሚሊዮን ህዝብ 3ሺ ኮፒ ብቻ ነው የሚታተመው፡፡ በአማካይ ስናስበው ከኔጌቲቭ በታች ነው፡፡ ለ1 ሚሊዮን ህዝብ ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን መጽሐፍ መታተም አለበት:: መጽሐፍም በብዛት ሲታተም ዋጋው ይቀንሳል፡፡ 3ሺ ኮፒ ሲታተምና 40ሺ ኮፒ ሲታተም፣ የመጽሐፍ ዋጋ እኩል አይደለም፤ 40ሺ ሲሆን ዋጋው ይቀንሳል፡፡
የንባብ ባህል እንዲዳብር፣ አዳዲስ ፀሐፍት እንዲበረታቱ፣ ውይይቶች እንዲዳብሩ ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት፡፡ የአንድ ተቋም ወይም ግለሰብ ብቻ ሀላፊነት አይደለም ባይ ነኝ:: በእናት ማስታወቂያና በሚዩዚክ ሜይዴይ የሚሰናዱ ውይይቶች መበረታታት አለባቸው:: የሽልማት ድርጅቶችም መስፋፋት አለባቸው እላለሁ፡፡ በንባብ ለውጥ ያመጡ ሰዎችን ወደ አደባባይ እያመጡ መሸለምና ማወደስም ሌሎች አንባቢዎችን ያፈራል:: ይህም መጠናከር አለበት፡፡ በዚህ አጋጣሚ እናንብ እላለሁ፡፡ መልካም አዲስ አመት እመኛለሁ!!  


Read 972 times