Print this page
Tuesday, 01 October 2019 11:13

“የኛ ዓላማ ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ ነው”

Written by  (ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ፤ የ”ጦቢያ ግጥም በጃዝ” አዘጋጅ)
Rate this item
(1 Vote)

“ጦቢያ ግጥም በጃዝ” ከተመሰረተ ቢቆይም፣ ሳይቋረጥ ለ8 ዓመታት እንደተወደደ ዘልቋል:: ዋናው የ“ጦቢያ ግጥም በጃዝ” አላማ ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ ነው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ብዙ ኢትዮጵያዊ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተዋል:: በጐ የሆኑም በጐ ያልሆኑም ጉዳዮች ተነቅሰው እየወጡ በግጥም፣ በተውኔት በዲስኩር እየቀረቡ፤ ሰው እንዲያይበት፣ መንግስትም ደግሞ ከነዚህ ሃሳቦችና ትችቶች ማስተካከል ያለበትን እንዲያስተካክል በማመላከት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡ በዚህ መድረክ ላይ ብዙ የህዝብ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡ በዚያ በአስቸጋሪው ጊዜ ብቻችንንም ስለነበርን፣ ለመፈተሽም እንጠቀምበት ነበር፡፡ ብዙ ምሁራን እየመጡ በወቅታዊ ሁኔታዎች፣ በህዝቡ ጥያቄ ላይ ሃሳብ እያነሱ ውይይት ይደረግ ስለነበር፣ ለመንግሥትም እንደ አንድ ክፍተት መመልከቻ መስተዋት አገልግሏል ብለን እናምናለን:: በሌላ በኩል፤ በእኛ መድረክ ላይ ትልልቅ ሰዎችን የማመስገን፣ ታሪክን የማወደስ፣ የሰውን ልዕልና የማክበር ባህል አለን፡፡ ለህዝቡም ሆነ ለአገር ትልቅ ፋይዳ እንዳበረከትን እንገነዘባለን፡፡
በስምንት አመት ውስጥ ከ200 ሺህ በላይ ታዳሚያን፤ ኢትዮጵያዊነትን፣ አብሮነትን፣ አንድነትን በግጥም፣ በዲስኩር፣ በተውኔት እየሰማ ተደምሟል ተደስቷል፡፡ በአዳራሽ ጥበት የሚመለሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ብዙ ሰዎች  ከበረከቱ ተቋድሰዋል ማለት ነው። እኛ ፈር ቀዳጅ ብንሆንም፣ ዘግይተውም ቢሆን ሌሎችም ተመስርተዋል፡፡ መብዛታችን ፋይዳውን ያሰፋዋል፤ግን  ጉዳትም አለው፡፡ እንዴት ከተባለ… በየመድረኩ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ኪነ ጥበብ የምናወራና የምንወያይ ከሆነ፣ መሰረትና ዓላማውን ሳይለቅ መሰራት አለበት:: ያለበለዚያ እንደ ንግድ ካየነው፣ ከፋይዳው ይልቅ በተቃራኒው ችግሩ ያመዝናል። አንድ ሰው በየኪነ ጥበብ ምሽቱ ሲጋበዝና ሀሳብ ሲያቀርብ፣ አጥንቶ አንብቦ፣ በደንብ ተዘጋጅቶ ነው መሆን ያለበት፡፡ ነገር ግን ያንን ሰው ሁሉም የኪነ ጥበብ ምሽት አዘጋጅ አቅርብ ሲለው፤ ያንን የመዘጋጀት፣ የማንበብና የነጠረ ሀሳብ የማቅረብ እድልና ጥሞና አያገኘውም፡፡ ስለዚህ ያንን ሰው ማስቸገርና ሳያነብና ሳይዘጋጅ እንዲመጣ መጋበዝ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከፍሎ ለሚገባ ታዳሚ የማይመጥን መድረክ ማዘጋጀትና ማሰልቸት ነው፡፡ ሁለትም ያንንም ሰው ሃይል ማስጨረስ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች እኛም ያየናቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም በተቻለን መጠን አዳዲስ ሰዎችን ለማምጣት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ጀማሪ እንደመሆናችን መጠን ስንኮረጅም እንዳለ ነው የተኮረጅነው፤ የተለየና የተጨመረ ነገር የለውም፡፡

Read 1156 times