Tuesday, 01 October 2019 11:17

“የኪነ ጥበብ ምሽቶች መብዛታቸው ችግር የለውም”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

(ጌታቸው ዓለሙ፤ የ“ሰምና ወርቅ” ምሽት አዘጋጅ)


           “ሰምና ወርቅ” እስካሁን 21 ምሽቶችን አዘጋጅቷል፡፡ እኔ በመመስረት ደረጃ ሶስተኛ ነኝ:: አንደኛ “ጦቢያ ግጥም በጃዝ” ነው:: ሁለተኛ “ሀዋዝ” የኪነጥበብ ምሽት ነው፡፡ ከሁለት ዐመት በላይ ሆኖታል፡፡ ሦስተኛው “ሰምና ወርቅ” ነው፡፡ እንግዲህ ከኔ በኋላ እንኳን 10 የኪነጥበብ ምሽቶች ተፈጥረዋል:: በድምሩ እኔ እንኳን የማውቃቸው 13 የኪነ ጥበብ ምሽቶች አሉ፡፡ መብዛታቸው ምንም ጥያቄ የለውም:: የስነ ጽሑፉን ዘርፍ በማሳደግም ሆነ ሃሳቦችን በማስተናገድ በኩል ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል:: ከኪነ ጥበብ ውጭ አብረው እየተሰሩ ያሉትንም ዘርፎች  ከፍ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ፍልስፍና፣ ባህልና መሰል ዘርፎች ራሳቸውን ችለው ካልሆነ በስተቀር አይነሱም ነበር፡፡ ኪነ-ጥበባዊ ጉዳዮች  ግጥሙን፣ ሙዚቃውን፣ ስዕሉን ብቻ ማዕከል ያደረጉ ነበሩ፡፡ አሁን በተለያየ ሃሳብ ላይ ብዙ ምሁራን ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት፣ እኛም እነሱን የምናገኝበት መድረክ ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል፤ በአንድ ተሰጥኦ ብቻ የምናውቃቸው ባለሙያዎች፣ ሌላ አስደናቂና ወደ መድረክ ሳያወጡት የቆዩትን ችሎታ የምናይበት እድል ፈጥሮልናል፡፡ ለምሳሌ አርቲስት ፍቃዱ ከበደን የምናውቀው በትወናው ብቻ ነበር፡፡ ግን አስገራሚ ወጐችን ይጽፋል፣ መጽሐፍም አሳትሟል:: ስፔሻሊስት ሀኪም ሆነው የበቁ የግጥም ፀሐፊዎች፣ ዲስኩር አቅራቢዎች… እነዚህን መድረኮች እያገኙና እያስተዋወቁን ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምሽቶች፤ ኪነ ጥበብ ከምንለው አጥር ወጥተው በሀገር፣ በታሪክ፣ በአኗኗርና ባህል ላይ ሁሉ  እንድንወያይ… ሃሳብ እንድንጋራ እያደረጉ ስለሆነ፣ መብዛታቸው መጥፎ ጐኑ አይታየኝም፡፡ በርግጥ በየመድረኩ በተደጋጋሚ የሚታዩ ሰዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በተለያዩ መድረኮች ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀርባሉ ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ በተለይ አንባቢዎቹ  ሃሳብ አያልቅባቸውም፤ ባለምናብ ሰዎች፣ አስር ቦታም ቢጋበዙ… አስር የተለያየ ግን ጠቃሚ ርዕሰ ጉዳዮቹን ያነሳሉ፡፡ አያሰለቹም፡፡ በሌላ በኩል፤ በኪነ-ጥበብ አዘጋጆች መካከል ፉክክር የሚመስል ነገር አለ፡፡ እከሌ ምሽት ላይ መጥቶማ እኔ ምሽት ላይ መቅረት የለበትም አይነት ፉክክር ማለቴ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ተመሳሳይ ፊቶች የሚቀርቡት፤ በከተማችንም ሆነ በአገራችን እጅግ የጠለቀ ሃሳብ ያላቸው፣ ተቆጥረው የማያልቁ  ከያኒያን ሞልተዋል፡፡  
እኛ በ2010 ዓ.ም ታህሳስ ወር ላይ ነው “ሰምና ወርቅ”ን ማቅረብ የጀመርነው፡፡ እስካሁን በተለያዩ ሃሳቦች ላይ 21 ምሽቶችን አካሂደናል:: ታዳሚያንን በተመለከተ ትንሹ ታዳሚያችን 300 ሰው ነው፤ ትልቁ ከ1200 ሰው በላይ ነው::
አንዳንዴ አዳራሽ ሞልቶ ሰው የሚመለስበት ሁኔታም አለ፡፡ ለምሳሌ “ያልታመመ አዕምሮን እንዴት ማከም ይቻላል” በሚል ርዕስ ከዶ/ር ወንድሙ ነጋሽ ጋር ባዘጋጀንበት ጊዜ ብሔራዊ ቴአትር ሞልቶ ሰው ተመልሶ ነበር፡፡ 1400 ሰው ገብቶ ነው ቀሪው የተመለሰው፡፡
በአጠቃላይ የኪነጥበብ ምሽት በነዚህ ሁሉ ነገሮች መካከል እየተሽከረከረ ያለ ስራ ሆኗል ለማለት ነው:: ሌላው እኔ ምሽት ላይ ቆንጆ ሃሳብ ያቀረበን ሰው፣ ሌላው አዘጋጅ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዲያቀርብ ቢጋብዘው ችግር የለውም፡፡ ይሄ በቅንነት ቢታይ መልካም ነው፡፡ በፉክክር የሚመስለው ነገርና በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ማዘጋጀቱ ግን  ኪሳራ ነው፡፡ ኪነ-ጥበብ ዋና ዓላማው፤ ማዝናናት፣ ማስተማርና ማሳቅ ነው ባይ ነኝ፡፡  



Read 1383 times