Print this page
Saturday, 05 October 2019 00:00

70 ተቃዋሚ ፓርቲዎች የረሃብ አድማ እናደርጋለን ብለዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ፓርላማው በመጀመርያ ስብሰባው ጥያቄያቸውን እንዲመልስ ይፈልጋሉ


           በምርጫና በፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ላይ በተደጋጋሚ ተቃውሞ በማሰማት እንዲሻሻል ብንማጸንም ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ያሉ 70 የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ለሁለት ቀናት የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ የገለጹ ሲሆን  የተቃውሞ ድምጽ ፊርማ እንደሚያሰባስቡም ጠቁመዋል፡፡  
በተደጋጋሚ አዋጁ ላይ ያለንን ተቃውሞ  ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ብንገልጽም፣ቀና ምላሽ ሊሰጠን አልቻለም ያሉት ኢህአፓ እና መኢአድ ጨምሮ 70 ያህል የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በፓርላማው የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ አቤቱታቸው የማይታይ ከሆነ፣ ጥቅምት 5 እና 6 ቀን 2012 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የረሃብ አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
በረሃብ አድማው ወቅትም “የኢትዮጵያ ህዝብ ለክብሩ፣ ለነፃነቱ፣ ለእኩልነቱ፣ ለሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ መከበርና ለሠላምና ለፍትህ መስፈን ስንል ለምናደርገው የረሃብ አድማ በመንፈሱ እንዲያስበን፣ በፆም በፀሎትም እንዲያግዙን፣ በሃሳብ እንዲረዳንና ከጐናችን እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን ብለዋል- ፓርቲዎቹ፡፡
ከረሃብ አድማው ማግስት ጀምሮም የተቃውሞ ድምጽ ፊርማ እንደሚያሰባስቡ የገለፁት ድርጅቶቹ፤ ከጥቅምት 7 ቀን 2012 ጀምሮ በሚከናወነው የፊርማ ማሰባሰብ ላይ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ደጋፊዎቻቸውና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለለውጥ ከፍተኛ የደም፣ የአካልና የህይወት መስዋዕትነት ከሚከፍሉ የህዝብ ልጆች እጅ በድንገተኛ ደራሽ ሃይሎችና የድል አጥቢያ አርበኞች በተደጋጋሚ ለውጥ መቀማቱን የጠቀሱት ድርጅቶቹ፤ አሁንም ለውጡ በብልጣ ብልጦች እጅ ተጠልፏል ብለዋል፡፡
መላው የሀገራችን ህዝብ አዲስ ለውጥ መጣልን ብሎ ደስታውን በወጉ አጣጥሞ ሳይጨርስ ግድያው፣ አፈናው፣ የሃብትና ንብረት ዘረፋውና ማፈናቀሉ በመቀጠሉ መላውን ህዝብ አንገት ያስደፋ ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ በለውጡ ተጠቃሚ ሳይሆን ተጐጂ እየሆነ መምጣቱን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡
በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል በንፁሃን ዜጐችና በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እንዲሁም በጋዜጠኞችና በሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ላይ የሚደርሰው አስራትና ጥቃት እንዲቆምና የታሠሩ እንዲፈቱ ሲሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ ጠይቀዋል፡

Read 941 times